ከዓባይ ግድብ የተገኘው ተሞክሮ የተፈጥሮ ሀብቶቻችንን ለማልማት የተሻለ መነቃቃትን የፈጠረ ነው

ሀገራት ተፈጥሮ የቸረቻቸውን ሀብቶቻቸውን በመጠቀም የሕዝቦቻቸውን መሠረታዊ ፍላጎቶች የማሟላት፤ አለፍ ሲልም የመልማት የመበልጸግ ተስፋቸውን እውን የማድረግ ያልተገደበ መብት አላቸው። ምክንያቱም ሀገራት እንደ ሀገር የሚኖራቸው ሕልውና በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ በዚሁ ሀብታቸውን በአግባቡ አልምቶ በመጠቀም እና አለመጠቀም ላይ የተመሠረተ ነው፡፡

እናም ተፈጥሮ የቸረቻቸውን ሀብቶች አልምቶ የሕዝቦቻቸውን መሠረታዊ ጥያቄዎች የመመለስም ሆነ የልማትና የብልጽግና ፍላጎቶቻቸውን የማሟላት ጉዳይ ለጥያቄ የሚቀርብ አይሆንም። ይህንን ሀብት አልምቶ የመበልጸግ እውነት ታሳቢ በማድረግም፣ ሀገራት በሚያዋጣቸው መንገድ ሀብቶቻቸውን በማልማት ለዜጎቻቸው የተሻለ ሕይወት መፍጠር ችለዋል።

በዚህ መልኩ ሀብቶቻቸውን ለይተው በማልማትም በዓለም አቀፍ ደረጃ አንቱ የሚያስብላቸውን ማንነት መገንባት የቻሉ ሀገራት ጥቂት አይደሉም፡፡ ይሄንን የታዘቡና ዘግይተውም ቢሆን የበለጸጉትን መንገድ መከተል የጀመሩ፤ በዚህም አሁን ላይ ያላቸውን ሀብት በማልማት የሕዝባቸውን ሕይወት ለመለወጥ የሚተጉ ሀገራትም ብዙ ናቸው።

ጉዳዩ የህልውና ጉዳይ ከመሆኑ አንጻር በተለይም በድህነትና ኋላ ቀርነት ብዙ ዋጋ እየከፈሉ ያሉ ሀገራት መንግሥታት የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር፤ የሕዝቦቻቸውን ሕይወት ለመታደግ ያላቸውን የተፈጥሮ ሀብት መጠቀም ወደሚያስችል አስገዳጅ ሁኔታ መግባታቸው የማይቀር ነው። የሕዝቦቻቸውን የመልማት ተስፋም ሊመልሱ የሚችሉት በዚህ መንገድ መሄድ ሲችሉ ብቻ ነው።

በተለይም ለዓመታት በግጭት አዙሪት ውስጥ የሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት፤ ዘላቂ ሰላም ለማግኘትና ሕዝቦቻቸው አብዝተው የሚሹትን ልማት እውን ለማድረግ፤ የግጭት ምንጭ የሆኑ የተፈጥሮ ሀብቶቻቸውን ፍትሐዊ በሆነ መንገድ በማልማት የሕዝቦቻቸውን ነገዎች ብሩህ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለዚህ የሚሆንም ሁለንተናዊ ዝግጁነትም መፍጠር ይኖርባቸዋል።

ፍትሐዊነት በጎደለው እራስ ወዳድነት ገዝፎ በሚታይበት የዓለም የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ ብሄራዊ ጥቅምን ሆነ ክብርን ማስጠበቅ የሚቻለው እንደ ሀገር ጸንቶ መቆም፣ ቀና ብሎ መሄድ የሚያስችል ማህበራዊ ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቁመና መገንባት ሲቻል ነው። ይህን ደግሞ በቀደመው የጠባቂነት የፖለቲካ እሳቤ እውን ማድረግ የሚቻል አይደለም።

ከዚህ ይልቅ ሀገራት ያላቸውን የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ አውቀው/ አጥንተው ማልማት የሚችሉበትን ስትራቴጂክ መንገድ መርጠው መጓዝ ፤ ለዚህ የሚሆን ሀገራዊ/ሕዝባዊ መነቃቃት መፍጠር ይጠበቅባቸዋል። ነገዎቻቸውን ብሩህ አድርገው ለማየት ሆነ ለመጪዎቹ ትውልዶች የተሻለ ሀገር ፈጥረው ለማለፍ ያላቸው ብቸኛ አማራጭም ይሄው ነው።

ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያውያን እንደ ሀገር ጸንተን ለመቆምና ቀና ብለን ለመሄድ ከዚህም በላይ ብሄራዊ ክብራችንን ሙሉ አድርጎ ለማስቀጠል የሚያስችለንን ልማት እውን ለማድረግ ሀገራዊ መነቃቃት ፈጥረን መንቀሳቀስ ከጀመርን ዓመታት ተቆጥረዋል ፤ይህ መሻታችን ከውስጥም ከውጪም በብዙ ፈተናዎች ውስጥ እንድናልፍ፤ብዙ ዋጋ እንድንከፍል አድርጎናል።

በተለይም ያለንን የተፈጥሮ ሀብት /የውሃ ሀብት ፍትሐዊ በሆነ ሁኔታ ለሀገር ሁለንተናዊ ልማት ለመጠቀም የጀመርነው መንገድ ይዞብን የመጣው ተግዳሮት የተፈጥሮ ሀብታችንን የመጠቀም የሕግና የሞራል መብታችንን በብዙ የፈተነ ነው። ባልተገባ ሁኔታ ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ጭምር እንዳመጣብን የአደባባይ ምስጢር ነው።

ይህንን ፈተና ለመሻገር እንደ ሀገር የቆምንበት ጽናት አሁን ላይ ፍሬ አፍርቶ ለልማታችን ሁለንተናዊ አቅም ሊሆን የሚችለውን የዓባይ ግድብ ግንባታ ወደ ፍጻሜ አድርሰናል። በዚህም ከሁሉም በላይ ድህነትና ኋላ ቀርነት አሸንፎ ለመውጣት የሚደረግ ትግል የቱን ያህል ፈታኝ እንደሆነ በተጨባጭ መረዳት ችለናል።

ባሉን ብዙ የተፈጥሮ ሀብቶች መሀል ተኝተን ፣ ያለንበትን ድህነት እና ኋላ ቀርነት ተቀብለን ፣ እጃችንን አጣምረን እንድንኖር የሚፈልጉ ኃይሎች ፍላጎትን እና የሴራ መንገድ የቱን ያህል እንደ ሀገር ያለንን ህልውና ሳይቀር የሚፈታተን ስለመሆኑም በፈተናዎች ውስጥ በተግባር ብዙ ዋጋ ከፍለን አይተናል።

ይህ ተሞክሯችን በቀጣይ ያሉንን የተፈጥሮ ሀብቶች በአግባቡ አውቀን ከራሳችን ሆነ ከሌሎች አፍሪካውያን ወንድሞቻችን ጋር ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንድንጠቀም የሚያስችል ተጨማሪ መነቃቃት የፈጠረ ነው ። በዚህ ሂደት ሊያጋጥሙን የሚችሉ ተግዳሮቶችን በአግባቡ አውቀን በተሻለ ዝግጁነት እና ቁርጠኝነት እንድንቆም የሚያስችለን ጭምር ነው።

አዲስ ዘመን  መጋቢት 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You