የኦቲዝምና ተዛማጅ የአእምሮ እድገት እክሎች ያሉባቸው ዜጎችን ለመደገፍ መዋቅር ተደራጅቷል

አዲስ አበባ፡- የኦቲዝምና ተዛማጅ የአእምሮ እድገት እክሎች ያሉባቸው ዜጎች በሀገር አቀፍ ደረጃ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲደገፉ ለማስቻል እራሱን የቻለ መዋቅር በማደራጀት የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ዓለም አቀፍ የኦቲዝም ቀንን ምክንያት በማድረግ የኒያ ፋውንዴሽንና አይፓስ ኢትዮጵያ በመተባበር ያዘጋጁት የስነ ተዋልዶ ጤና መብት፣ ጥንቃቄ የተሞላበት ፅንስ ማቋረጥ፣ ፆታዊ ጥቃት መከላከልንና ኦቲዝም ላይ ያተኮረ ሀገር አቀፍ ወርክሾፕ ትናንት ተካሂዷል።

በመርሀ ግብሩ ላይ በጤና ሚኒስቴር የስፔሻሊቲና ሪሀብልቴሽን ዴስክ ተወካይ ዶክተር ጎበና ጎዳና እንደተናገሩት፤ የኦቲዝምና ተዛማጅ የአእምሮ እድገት እክሎች ያሉባቸው ዜጎች በሀገር አቀፍ ደረጃ ትኩረት ተሰጥቷቸው እንዲደገፉ ለማስቻል እራሱን የቻለ መዋቅር በማደራጀት የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ሲሆን፤ እክል ያለባቸውን ዜጎች ችግር ለመፍታት የጤና ሚኒስቴር የሚጠበቅበትን ለማበርከት ዝግጁ ነው።

የዓለም አቀፍ የኦቲዝም ቀን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እ.አ.አ በ2007 እንዲከበር የተወሰነ ሲሆን፤ ይህም ግንዛቤ በመፍጠር የኦቲዝምና ተዛማጅ ችግሮች ያለባቸው ግለሰቦች መሰረታዊ መብታቸው እንዲጠበቅና አጽንኦት እንዲያገኙ ባለድርሻ አካላት ትኩረት እንዲሰጡ ለማድረግ መሆኑን ተናግረዋል።

ዘንድሮ “ድምፅ አልባ የኦቲዝም ልጆችን ማብቃት” በሚል መርህ እንደሚከበር ያነሱት ዶክተር ጎበና፤ ይህም ኦቲዝም ያለባቸውን ዜጎች በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በሌሎች መስኮች ላይ መሳተፍ እንዲችሉ ለማስቻል ነው ብለዋል።

እንደ ዶክተር ጎበና ገለፃ፤ ያደጉ ሀገራት ኦቲዝም ያለባቸውን ዜጎች መሠረታዊ መብታቸውና ነጻነታቸውን ከማረጋገጥ ባሻገር የማገገሚያ፣ የትምህርትና የስልጠና አገልግሎቶችን በዘመናዊ መልኩ እንዲያገኙ በማድረግ አመርቂ ውጤቶች እያስመዘገቡ ነው።
የኒያ ፋውንዴሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢሌኒ ዳምጠው በበኩላቸው፤ የሚያዚያ ወር የዓለም አቀፍ የኦቲዝም ግንዛቤ ወር እንደሆነ በመግለፅ፤ የኦቲዝም ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ16ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ቀደም ብሎ የተጀመረ በመሆኑ ለ22ኛ ጊዜ እንደሚከበር ተናግረዋል።

የዘንድሮው የኦቲዝም ግንዛቤ ወር የኦቲዝም ወጣቶችና የስነ ተዋልዶ ጤና ላይ ትኩረት የሚሰጥበት ሲሆን፤ በጉዳዩ ላይ ግልፅ ውይይት በማድረግ መፍትሔ መስጠት ያስፈልጋል ያሉት ወይዘሮ ኢሌኒ፤ መንግሥትና በዘርፉ ላይ ያሉ ባለሙያዎች የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳት መፍትሔ እንዲሰጡም ጠይቀዋል።
የኒያ ፋውንዴሽን ከሚያዝያ 5 እስከ 19 ባሉት ቀናት በመቀሌ፣ በጅማ፣ በወላይታ ሶዶና በድሬዳዋ ከተሞች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን እንደሚያከናውን አመላክቷል።

እንዲሁም የፊታችን መጋቢት 28 በ4 ሺህ 622 ካሬ ሜትር ላይ የኒያ ፋውንዴሽን በማስገንባት ላይ የሚገኘው የጆይ ኦቲዝም ማዕከል በከፊል እንደሚመርቅ ጠቁመው፤ ግንባታው ከ16 ዓመታት በፊት የተጀመረ እንደመሆኑ ተጠናቆ በሙሉ አቅሙ አገልግሎት መስጠት እንዲችል ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የማዕከሉ ግንባታ ሲጠናቀቅ 500 ኦቲዝም ላለባቸው ዜጎች አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል።

ቃልኪዳን አሳዬ
አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You