“በዓባይ ግድብ የግንባታ ሂደት የገጠመውን ፈተና በማረም ሕዝቡ የሚጠብቀው ውጤት ተገኝቷል” አቶ ተመስገን ጥሩነህ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር

አዲስ አበባ፡– በዓባይ ግድብ የግንባታ ሂደት የገጠመውን ፈተና በለውጡ መንግሥት አማካኝነት በማረም ሕዝቡ የሚጠብቀው ውጤት ተገኝቷል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ።

የዓባይ ግድብ ግንባታ የተጀመረበትን 13ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀ የፓናል ውይይት መድረክ ትናንት ተካሂዷል።

በመድረኩ ንግግር ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ እንደገለጹት፤ በግንባታ ሂደቱ የገጠመውን ፈተና በለውጡ መንግሥት በማረም ሕዝቡ የሚጠብቀው ውጤት ተገኝቷል።

በግድቡ ግንባታ ሂደት ለተወሰዱ የማስተካከያ ርምጃዎችና ፈጣን ውሳኔዎች የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሚና መቼም እንደማይዘነጋ ተናግረዋል።

የዓባይ ግድብ ውሃ ሙሌቱ በታቀደው መሠረት የተከናወነ መሆኑን ጠቁመው፤ ከ42 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ ውሃ የያዘ ትልቅ ሰው ሰራሽ ሀይቅ መፍጠር መቻሉን አመላክተዋል። ግድቡ ሙሉ ለሙሉ ሳይጠናቀቅ የአሳ ምርት እንዲሁም ታዳሽ የኤሌክትሪክ ኃይል መጠቀም ተችሏል ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን የግድቡን ግንባታ በዲፕሎማሲው ሂደት ያሸነፍነው እንደ ዓድዋ ዘመቻ በህብረብሔራዊ አንድነት በመነሳታችን ነው ያሉት አቶ ተመስገን፤ አሁንም የገጠሙንን የሰላም ፈተናዎችና ከድህነት የመውጣት ጥረት በድል በመወጣት የኢትዮጵያን ብልጽግና የምናረጋግጥበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም ሲሉ ተናግረዋል።

ልማታችንን የማይፈልጉ ኃይሎች ግድቡን በራሳችን አቅም ለመገንባት በተነሳንበት ጊዜ የማያስፈልጉ ምክንያቶችን በማቅረብ መታገላቸውንና በዓለም መድረኮች ኢትዮጵያን መክሰሳቸውን አስታውሰው፤ የግድቡን ግንባታ ማንም ሳያቆመን ዓለም አቀፍ ደረጃውን እንደጠበቀ ወደ መጠናቀቁ መቃረቡ እንደሀገር ስኬት ነው ብለዋል።

ግድቡ አሁን ላለበት የማጠናቀቂያ ምዕራፍ እንዲደርስ አስተዋጾ ላደረጉና በጽናት ለተፋለሙ የተደራዳሪ ኮሚቴ አባላት፣ ያላቸውን ለሰጡ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ለኢትዮጵያ ወዳጆች እንዲሁም በግንባታ ሥራው እየተሳተፉ ለሚገኙ ሁሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በመድረኩ የተገኙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ አሁን ላይ የዓባይ ግድብ ግንባታ በአማካኝ 95 ነጥብ ስምንት በመቶ ደርሷል፤ የግድቡ ዋና አካል ግንባታ ደግሞ ከ99 በመቶ በላይ ሆኗል።

የዓባይ ግድብ በኢትዮጵውያን የተባበረ ክንድ ብቻ ያለምንም የውጪ ድጋፍና ርዳታ መገንባቱ ኢትዮጵያውያን ለጋራ ዓላማ በጋራ መቆም እንደሚችሉ ያሳዩበት እንዲሁም በወንዞቻቸው ላይ የፍትሐዊ ተጠቃሚነት መብት እንዳላቸው ለዓለም ያሳዩበት ነው ብለዋል።

በዓባይ ግድብ ግንባታ ካሳካነው ትልቁ ዓላማ ጎን ለጎን ትላልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶችን የመምራትና የመገንባት ልምድ ያዳበርንበትና አንድነታችንን ለዓለም ማህበረሰብ ያሳየንበት ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ በድምሩ 750 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያላቸው ሁለት ተርባይኖች ሥራ መጀመራቸውንም ተናግረዋል።

በመድረኩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ፣ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)፣ የተለያዩ ምሁራንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል። በዕለቱ የዓባይ ግድብ የግንባታ ሂደቶችን የሚያሳዩ ምስሎች ለዕይታ ቀርበው ተጎብኝተዋል።

በመድረኩ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት የግድቡን 13ኛ ዓመት በማስመልከት ያዘጋጀው የአባይ ግድብ የመታሰቢያ ቴምብርም ይፋ ተደርጓል።

መዓዛ ማሞ

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You