“በለውጡ ችግሮችን ወደ ዕድል የቀየረና ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚያስችል መሠረት ተጥሏል” ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) የሸገር ከተማ ከንቲባ

አዲስ አበባ፡– ከለውጡ ወዲህ የውስጥና የውጪ ችግሮችን ወደ ዕድል በመቀየር ብልጽግናን ማረጋገጥ የሚያስችል መሠረት ተጥሏል ሲሉ የሸገር ከተማ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) ገለጹ።

በኦሮሚያ ክልል በሸገር ከተማ አስተዳደር “ለሰላማችን ዘብ እንቆማለን ለውጡን እናጸናለን” በሚል መሪ ሃሳብ ከለውጡ በኋላ የተገኙ ውጤቶችን ለማስቀጠል ያለመ የድጋፍ ሰልፍ ትናንት ተካሂዷል።

የሸገር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፤ ከለውጡ ወዲህ የውስጥና የውጪ ችግሮችን ወደ ድል በመቀየር ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚያስችል መሠረት ተጥሏል።

በሀገሪቱ የወል አቅምን በማሳደግ የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ የሁሉም ዜጋ የነቃ ተሳትፎ ያስፈልጋል ያሉት ዶክተር ተሾመ፤ ከለውጡ ወዲህ ከውስጥና ከውጪ የገጠሙ ችግሮችን በማሸነፍና ወደ ዕድል በመቀየር ሀገርን ከመፍረስ መታደግ ተችሏል ብለዋል።

ባለፉት ስድስት ዓመታት የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ የሚያስችል መሠረት መጣሉን ጠቅሰው፤ የሸገር ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች ከሀገራዊ ልማት ተጠቃሚ እየሆኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

የለውጡ መጀመሪያ የሆነው መጋቢት 24 ቀን ለሀገሪቱ ሕዝቦች አሮጌውን ትርክት በወል ትርክት በመተካት አዲስ እረፍትን አምጥቷል ያሉት ከንቲባው፤ የሸገር ከተማ መመስረት ለውጡ ያመጣው ውጤት ነው ብለዋል።

በሕዝቦች ትግልና መስዋዕትነት የተገኘውን ታሪካዊ ድል መጠበቅና ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ በየደረጃው የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ግዴታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ኢትዮጵያ ለብሔር ብሔረሰቦች ምቹ እንድትሆን እውነተኛ እኩልነትና ዴሞክራሲን ወደ መሬት ማውረድ  መቻሉን ጠቅሰው፤ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት በመጠበቅ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ መሠረት የጣለ ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል።

ከለውጡ ወዲህ ለዘመናት ተሻግረው የቆዩ ችግሮች በብልሀትና በእውቀት መቀረፋቸውን ገልጸው፤ የተገኘውን ልማት ለማጽናት ሁሉም ህብረተሰብ የሰላም ዘብ መሆን እንደሚኖርበት አመላክተዋል።

ባለፉት ዓመታት የፖለቲካ ምህዳርን በማስፋት ሰፊ ሥራ መሠራቱን ጠቁመው፤ የልማት ዕድሎችን አዋቅሮ በመተግበር ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደተቻለ ተናግረዋል።

የሀገሪቱን ለውጥ ለማሳካት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጭ ፈተናዎች ማጋጠማቸውን በመግለጽ፤ ችግሮችን በድል በመወጣት ለውጡን የተቃና እንዲሆን ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል።

ከለውጡ ወዲህ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት፣ የመሠረተ ልማት ዝርጋታና ሌሎችም በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል ያሉት ዶክተር ተሾመ፤ በግብርናው፣ በቱሪዝምና፣ በኢንዱስትሪው ዘርፍም በሀገሪቱ ጠንካራ ስራዎች ተከውነዋል ብለዋል።

በሀገሪቱ የተገኘውን ድል ደግፎ ማስቀጠል እንደሚጠበቅ ጠቅሰው፤ እንደሀገር ሌሎች ተጨማሪ ድሎችን ለመሥራት በር እንደሚከፍት ገልጸዋል።

በተጨማሪም የድጋፍ ሰልፉ ሸገርን ጨምሮ በሮቤ፣ በጊምቢ፣ በመቱ፣ በነቀምቴ፣ በአምቦ፣ በአዳማ ፣ በጅማ፣ በነጌሌ ቦረና፣ በሰንዳፋ በኬ፣ በደሌ፣ በቡሌ ሆራ፣ በደምቢዶሎ፣ በሂርና፣ በማያ፣ በሙከ ጡሪና በተለያዩ ዞኖችና ከተሞች ላይ ተካሂዷል።

ማርቆስ በላይ

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You