
አዲስ አበባ:- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመኖሪያ ቤት ኪራይ ላይ የሚስተዋለውን ኢ-ፍትሐዊ የዋጋ ጭማሪን በመቆጣጠር ጊዜያዊ መፍትሔ ይሰጣል ያለውን የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥርና አስተዳደር አዋጅን አጸደቀ።
ምክር ቤቱ ትናንት በሦስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን 19ኛ መደበኛ ስብሰባው አዋጁን በአብላጫ ድምጽ ያጸደቀው ሲሆን፤ በአዋጁ መሠረት የመኖሪያ ቤት ውል ስምምነት ለሁለት ዓመት እንዲሆንና በሁሉም መኖሪያ ቤቶች ላይ እንደሚተገበር እንዲሁም የቤቶች ዋጋ ተመኑ በመንግሥት እንደሚወሰን ተገልጿል።
አዋጁ በመኖሪያ ቤት ኪራይ ላይ የሚስተዋለውን የዋጋ አለመረጋጋትን በመቆጣጠር በቤት አቅርቦት ላይ የሚስተዋለውን ችግር እንዲረጋጋ ያስችላልም ተብሏል።
ለምክር ቤት አባላቱ ማብራሪያና ምላሽ የሰጡት የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)፤ አዋጁ የአከራይና ተከራይ መብትን ሚዛናዊነት ለመጠበቅ ያስችላል ብለዋል። ሕጋዊነትን የሚያጸና፣ ግልጸኝነትን የሚያረጋግጥና ሥርዓቱን ከደላሎች ተጽእኖ የሚያላቅቅ መሆኑንም ጠቁመዋል።
አዋጁ ወደ ትግበራ ሲገባ አቤቱታ የሚሰማ ኮሚቴ እንደሚሰየም ጠቁመው፤ ተግባራዊ መደረግ ሲጀምር ያልተጠበቁ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙ በሚሰየመው ተቆጣጣሪው አካል ታይተው እንዲታረሙ ይደረጋል ብለዋል።
ነባሩ የቤቶችን ውል የመነሻ ጣሪያ በመውሰድ በየሁለት ዓመቱ የገበያ ሁኔታና ሌሎች ነባራዊ ሁኔታዎች ታይተው ዋጋው ይወሰናል ያሉት ሚኒስትሩ፤ በአዋጁ ከተቀመጡት ምክንያቶች ውጪ ከሁለት ዓመት አስቀድሞ ተከራይን ማስለቀቅም ሆነ ዋጋ መጨመር እንደማይቻል በአዋጁ መመላከቱንም ተናግረዋል።
የቤቱ ኪራይ መነሻ ዋጋ የሚሆነው አከራይና ተከራይ በውላቸው መሠረት በተስማሙበትና በነበረው ሁኔታ ይሆናል ያሉት ሚኒስትሩ፤ መንግሥት በየሁለት ዓመቱ የገባውን ሁኔታ፣ ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶችን ባገናዘበ ሁኔታ የኪራይ ጣሪያውን እንደሚወስን አመልክተዋል።
ተከራይ የተከራየበትን ቤት ከዓላማ ውጪ ቢጠቀም፣ የአካባቢን ሰላምና ፀጥታ ቢያውክ፣ የተከራየው ቤት ላይ አደጋ የሚያደርስ ከሆነና በተገባው ውል መሠረት የኪራይ ዋጋ ካልፈጸመ አከራይ ውል ተቀባይን ሊያስወጣ እንደሚችል በአዋጁ መደንገጉንም አመልክተዋል።
አከራይ ቤቱን በእዳ ቢያስይዝ፣ ቢሸጥና ገዢው ሊገባበት ቢፈልግ ለተከራይ ለስድስት ወራት ማስጠንቀቂያ በመስጠት ማስለቀቅ እንደሚቻል በአዋጁ መደንገጉም ተመልክቷል። ቤቱ በስጦታ ለሌላ አካል ቢተላለፍ ግን ተከራዩ ሙሉ የውል ጊዜው እንደሚጠበቅለት ተጠቁሟል።
ተከራይ ከሁለት ዓመት በፊት ከውሉ ቀድሞ መውጣት ቢፈልግ ከሁለት ወራት በፊት በማስታወቅ
መልቀቅ እንደሚችልም በአዋጁ መቀመጡን አስረድተዋል።
በተከራይና አከራይ በኩል ውልን አለማስመዝገብ አስተዳደራዊ ቅጣትን ያስከትላል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ያልተመዘገበ ውልም እንዳልተደረገ ይቆጠራል፣ የግብር ስወራ በሕግ የሚያስጠይቅ መሆኑን በመገንዘብ ምዝገባ እንዲደረግ ይበረታታልም ብለዋል።
የአዋጁ ትግበራ ተዋዋዮችን በማያቃቅርና መልካም ግንኙነትን ባስጠበቀ መልኩ ተግባራዊ እንደሚሆንም አመልክተዋል።
ግልጽ፣ ተገማች፣ በተዋዋዮች መካከል መከዳዳት የማይኖርበት ጥሩ ግንኙነትን ለማስቀጠል እንቅፋት በማይሆን መንገድ አዋጁ መውጣቱንም ነው የጠቆሙት።
አዋጁ ከጸደቀ በኋላ በአንድ ወር ውስጥ የውል ምዝገባው መከናወን እንዳለበት በመጠቆም፤ ምዝገባው እስከ ሦስትና አራት ወራት ድረስ ሊራዘም የሚችልበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችልም አመልክተዋል።
ቤት ማከራየት ይበረታታል ያሉት ጌዲዮን (ዶ/ር)፤ ቤት ገንብተው ያለጥቅም ባዶ ቤት የሚያስቀምጡ ባለንብረቶች ሳያከራዩ ከአንድ ዓመት በላይ ቢያስቀምጡ የታክሱን 25 በመቶ ድረስ በተጨማሪ እንዲከፍሉ የሚደረግበት አሠራርን በአዋጁ መዘርጋቱንም ነው የጠቆሙት።
እንዲህ አይነት አሠራር በሌሎች ሀገራትም ይተገበራል፣ ከፍተኛ የሆነ የቤት እጥረት ባለበት ነባራዊ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት የተወሰነ ነው ሲሉ አመልክተዋል። ተመሳሳይ አሠራር በቀጣይም በንግድ ቤቶች ላይ ሊታይ እንደሚችልም ገልጸዋል።
የመኖሪያ ቤት ችግር ሰፊ ቢሆንም የተደራጀ መረጃና ደረጃውን የጠበቀ ግንባታ ባለመኖሩ፣ የሥነምግባር ብልሹነትና መሰል ችግሮች እንዳይፈጠሩ መንግሥት መስፈርት እያወጣ ዋጋ የሚተምንበት አሠራርን ተግባራዊ ማድረግ አልተቻለም ብለዋል።
አዋጁ መሠረታዊ የቤት አቅርቦት ባይፈታም ቢያንስ አንድ ሰው በተከራየው ቤት ለሁለት ዓመታት ተገቢውን ኪራይ እየከፈለ እንዲኖር እንደሚያስችለውም አስረድተዋል።
አዋጁ በአዲስ አበባና ድሬዳዋ እንዲሁም ተጠሪነታቸው ለክልል በሆኑ ከተሞች ተግባራዊ እንደሚሆን አስታውቀው፤ ክልሎች ነባራዊ ሁኔታን ተመልክተው በሚወስኑት ሁኔታ እንደሚፈጸም ተናግረዋል። ነገር ግን በሆቴል፣ ሪዞርት፣የእንግዳ ማረፊያና ሌሎች በንግድ ፍቃድ መሠረት በሚከራዩ ቤቶች ላይ ተፈጻሚነት የለውም ብለዋል።
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 25 ቀን 2016 ዓ.ም