በከፋፋይ ትርክት የደበዘዘ ውበታችንን ለመመለስ

ሰላም ጠል በሆኑና ለማንም በማይበጁ ነጣጣይ ትርክቶች ይዘው አደባባይ በወጡ ግለሰቦች እና ቡድኖች ሀገር ችግር ውስጥ ከወደቀች ሰንበትበት ብላለች። በነዚሁ በለው በሚሉና ወደሌላው ጣት በሚቀስሩ ተረት ተረት ተራኪ ግለሰቦች እና ቡድኖች ሰላሟንና አንድነቷን ፈተና ውስጥ መውደቁም የአደባባይ ሚስጥር ነው።

እኛም የትርክቶቹን ምንጭ በአግባቡ ሳንረዳ እና ሳይገባን፤ ማን ፈጠራቸው? እንዴት ተፈጠሩ?… ወዘተ ለሚሉት ጥያቄዎች ምላሽ ሳንፈልግ ለትርክቶቹ አባባሽ ምላሽ በመስጠት ችግሮቹ ከአቅማቸው በላይ እንዲገዝፉ አድርገናል “እያደረግንም ነው።

ሰፊ ታሪክ፣ ብዙሀነት እና ባህል ያጸናት ሀገር ይዘን፣ በባህል ውርርስ ፊተኝነትን ያገኘች ምድር ባለቤቶች ሆነን ፤ በሴረኞች ጠብ በተደረገ ከፋፋይ ትርክት የቀደመ ውበቷ ደብዝዟል። በብዙሀነት የሚገለጽ ጥንተ ስማችን በጽንፈኛ ብሔረተኞች ከፋፋይ ትርክት ጥላ ጥሎበት ዋጋ እያስከፈለን ነው።

የጥላቻ ትርክት እንደሰደድ እሳት ነው። ሰደድ እሳት ያገኘውን የሚበላ ነው። የጥላቻ ትርክትም እንዲሁ ነው። የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ ያገኘውን መብላቱ አይቀሪ ነው። እንደ ሀገር በዚህ ዓይነቱ ትርክት ብዙ ዋጋዎችን ከፍለናል። በጋራ ታሪኮቻችን ላይ የብኩርና ግፊያ ጀምረን እኛ የሚለውን የኃይልና የህብረት ስም ወደእኔ ለውጠን ከገዘፈ ማንነት ወደጠበበ እኔነት ተራምደናል። በታሪክ ሽሚያ፣ በፖለቲካ ሽኩቻ ደም ተቀባብተን፣ ቂምና ቁርሾ ቋጥረናል።

በመጥፎ የምናወሳቸው የእርስ በርስ ጦርነቶች፣ የብሔርና የጎጥ ግጭቶች አጉል ትርክት የወለዳቸው ናቸው። እንዲሁም ደግሞ ለማንም ያልተቻሉ ደማማቅ ታሪኮችን የጻፍነው በበጎ ትርክቶቻችን አቅም አግኝተን ነው። ነገ ላይ ለምናሰባቸው ብሩህ ቀናትም እነዚህ ትርክቶች መሠረት እንደሚሆኑን ይታመናል።

አሁን ላይ ዋጋ እያስከፈሉን ካሉ ከአጓጉል ትርክቶች ወጥተን የጀመርነውን ልማት ለማስቀጠል፤ ሰላም ለሚፈልገው ሕዝብና አንድነቱ እንዲመለስ ለሚመኘው ትውልድ ብዙሀነትን ያነገበ፤ የፈረሰውን የሚገነባ፣ የላላውን የሚያጠብቅ የጋራ ትርክት ያስፈልገናል። ለጀመርነው የሰላም መንገድ፣ የእርቅና የተግባቦት መድረኮች ስኬት እንዲህ ዓይነቱ ትርክት ወሳኝ ነው።

የተበላሸውን አስተካክለው በአዲስ ሕዝባዊነት ለመቀጠል፤ ሲያቃቅሩን የነበሩ መሠረት የለሽ ተረት ተረት አሉባልታዎች መስተካከል አለባቸው። አንድነትና ህብረ ብሔራዊነት የሚያብብበት፣ ጥንተ ታሪካችን ለሚታደስበት አግባቢና አስማሚ ታሪኮች ትኩረት ሰጥተን ልንሰራ ይገባል። ለዚህ ደግሞ እያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት አለበት።

የሰላም ጉዳይ ለአንድ ወገን ብቻ የሚተው አይደለም። የሀገር ጉዳይ፣ የትውልድ ጥያቄ ለመንግሥት ወይም ለሆነ አካል የሚሰጥና እልባት የሚገኝለት አይደለም፤ የዜጎችን ሁለንተናዊ ጥረት የሚፈልግ ነው። ለችግሮች ሁሉም እራሱን የመፍትሔ አካል አድርጎ ሲሰለፍ ብቻ ነው።

የጥላቻ ትርክት ፈጣሪዎች ለትርክቶቻቸው አቅም ለመፍጠር ብዙ አስበው፤ በጥንቃቄ ተዘጋጅተው ነው ወደ አደባባይ የሚወጡት፤ ለተልዕኳቸው ስኬት የማያንኳኩት ደጃፍ የለም። በብዙ አስበውና ተዘጋጅተውበት ነው ወደ ተግባር የሚሻገሩት። እኛም ከነሱ የጥላቻና እና ከፋት ትርክት በማምለጥ፤ አንድነታችንን ለማጽናት፤ ኢትዮጵያዊነታችንን ለማጎላት ለጋራ / ለበጎ ትርክት እራሳችንን መዘጋጀት ይጠበቅብናል።

ተያይዘንና ተቃቅፈን እኩይ ትርክት ፈጣሪዎችን የሚያሳፍርና ዳግም ጥፋት መሥራት ወደማይችሉበት ደረጃ እስኪደርሱ ድረስ ስለአብሮነታችን በብዙ አስበን መንቀሳቀስ ይጠበቅብናል። ለዚህ ደግሞ አጋጣሚዎችን በአግባቡ ከመጠቀም ጀምሮ፤ አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር ይኖርብናል።

ለችግሮቹ ዘላቂ መፍትሔ ለማፈላለግ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቋቋሙ እንደ ብሔራዊ ምክክር በኮሚሽን ያሉ ተቋማት ስኬታማ እንዲሆኑ መንቀሳቀስ ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ነው። ዛሬ ላይ የምናዋጣት የሰላም መዋጮ ለነገ ነፃነታችንና አብሮነታችን የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ነው።

እንደዘበት በተወረወሩ ቃላቶችና ንግግሮች ብዙ ዋጋ ለመክፈል እንደተገደድን ሁሉ፤ የሆነ ቀን በሆነ ሰው የተነገሩ፣ የተሰራጩ መሠረት የለሽ የራስ አመለካከቶች ለእንግልት እንደዳረጉን ሁሉ፤ እኛም ስለ እውነት ዘብ መቆም፤ እውነቱን ያለ ይሉኝታ፤ ከወገንተኝነት ወጥተን መናገር አለብን።

ተደናግረው ያደናገሩን ትርክት ፈጣሪዎች፣ ተሳስተው ያሳሳቱን ጠላቶቻችን የሚያፍሩትና ከድርጊታቸው የሚቆጠቡት ስንታረቅ፣ ስንግባባ፣ ስንወያይ፣ በአንድነት ስንቆም፣ ሕዝባዊነት ሲመለስ፣ እኛነት ሲያብብ፣ አብሮነት ሲጎመራ ከሁሉ በላይ ደግሞ ለጥላቻ ትርክቶቻችን የአብሮነት ትርክት ስንፈጥር ብቻ ነው።

እንዲህ ካልሆነ አናሸንፋቸውም። የእኛ መለያየት ለእነሱ ኃይል ነው። የእኛ መራራቅ ለነሱ ጉልበት ነው። የምናሸንፋቸው ነውራቸውን የሚገልጥ የአንድነትና የአብሮነት የወንድማማችነትም ህብረት ሲናበጅ ነው።

እኛ ኢትዮጵያውያን በማንም እና በቀላሉ የምንከሽፍ አይደለንም። ማንም የመሰለውን እየተናገረ የሚያቃቅረንና የሚያሰጋን ሕዝቦች አይደለንም። ማን ምናለ እያልን በወሬና በአሉባልታ ጥንተ ህንደኬነታችንን የምንሰውርም አይደለንም። በብዙ ፈተና ውስጥ አልፈን አብሮነታችንን ያስመሰከርን እንዳንለያይ ሆነን የጸናን የአንድ መዳፍ ጣቶች ነን።

በወሬ የማይፈርስ፣ በአሉባልታ በማይላላ ጽኑ ወንድማማችነት ውስጥ የቆምን ነን። በጠበቀና በጠነከረ የአብሮነት ታሪክ ውስጥ ሀገርና ሕዝብ የሆንን ነው። በተዋረሰና በተዋሃደ ቅይጥ ማንነት ውስጥ ነፃነትን የሠራን፣ ፍትህን ያወጅን፣ ለሰው ልጅ ሁሉ ደጀን የሆንን አስጠላይ ዋርካ ነን።

ማንም ተነስቶ በመካከላችን ልዩነትን እንዲፈጥር መፍቀድ የለብንም። የሚማረውን ማስተማር የማይማረውን ደግሞ መቅጣት ስለኢትዮጵያዊነት የምንከፍለው ዋጋ መሆን አለበት። ግፊያ በበዛበት በሻከረና በለዘበ ጉርብትና ውስጥ ወደፊት መራመድ አንችልም። ከሁሉ አስቀድመን በመንገዳችን ላይ እንቅፋት ለሆኑ መጥፎ ትርክቶች መልስ እንስጥ።

እንቅፋቶቻችን ከመንገዳችን ላይ ገለል ሲሉ ነው ሰላምም ሆነ ልማት የሚመጣው። ባልጸዳና ባልተስተካከለ ፖለቲካ ውስጥ፣ ባልተማመነና ባልተጎራበተ ማህበረሰብ ውስጥ ምንም ብንደክም ትርፍ አይኖረንም።

እንደ እኛ የረጅም ዘመን የሀገረ መንግሥት ታሪክ ያላቸው ሕዝቦች ጥቂት ናቸው።

ብዙ ነገራችን የተዋረሰና የተቀየጠ ነው። እኔ ብለን ራሳችንን እንዳናገል በሆነ ትስስር ውስጥ ያረፍን ነን። ተፈጥሯዊ ልዩነታችን ውበታችን ነው። ከሰማንያ በላይ ብሔረሰብ፣ ከሰማንያ በላይ ቋንቋና ከሰማንያ በላይ ባህል ይዘን ኢትዮጵያዊነትን ማስቀጠል መቻላችን ብርቱነታችንን የሚያሳይ ገሀድ እውነታ ነው። ይሄ ጥንካሬ ለዘመናት መለያችን ሆኖ ቆይቷል። ይህም የትልቁ የጋራ ትርክታችን ዋነኝ አካል ነው።

አሁን ላይ ይሄ የጋራ ትርክቶቻችን እየደበዘዙ የልዩነት /የብቻ ትርክት ውስጥ ገብተናል። በሰፊ ሀገር ላይ የልዩነት ትርክት ለያይና አራራቂ ነው። የራስ ፍላጎትና አላማ የሚንጸባረቅበት ተጠጋግቶ የቆመውን ብዙሀነት የሚያቃቅር ነው። ከሁሉ በላይ ኢትዮጵያዊነታችን እያደበዘዘ ያለ ሰንካላ አስተሳሰብ ነው።

ለሰፊ ሀገር የጠበበ ፖለቲካ እና ፖለቲከኛ ጠንቅ ነው። ከሰፊው ሕዝብ ውስጥ ራስን ብቻ ማውጣት፣ ከብዙሀነት ውስጥ የራስን ብቻ ማግነን ከእኩይ ትርክቶች በላይ የከፋ ጥፋት ነው። በብዙሀነት ውስጥ የራስ ብቻ ታሪክ፣ የራስ ብቻ እውነት የለም። በትልቅና ሰፊ ሀገር ውስጥ መንዝረንና በርብረን የምናወጣው የብቻ ልዕልና የለም።

በሰፊ ሀገር ላይ የሚያስፈልገው ሰፊና ብዙሀኑን የነካ ትርክት ነው። ሀገር አጥበን የምናሰፋው ብሔር የለም። እንደ ሀገር ኢትዮጵያዊነትን አሳንሰን የምናገዝፈው ማንነት አይኖርም። መነሻችን ለመድረሻችን ወሳኝነት አለው። የጥላቻ ትርክት ፈጣሪዎች ትርክት ሲፈጥሩ ሁልጊዜም መነሻቸው ልዩነትን የሚያሰፉ ትርክቶች ናቸው። በተቃራኒው የአንድነትና የአብሮነት ትርክት ፈጣሪዎች መነሻቸው ሀገርና ሕዝብ ነው።

መቼም መነሻውን ሀገር ያላደረገ ፖለቲካና ፖለቲከኛ ፍጻሜው ጥፋት ነው። ለዚህ ደግሞ የመጣንባቸውን የታሪክ መንገዶቻችንን ማየት ተገቢ ነው። እየኖርንበት ካለው የግጭት አዙሪት ለመውጣት የምናደርጋቸው ጥረቶች የቱን ያህል እየፈተኑን ያሉት ከምን የተነሳ ነው የሚለውንም ማጤን ተገቢ ነው።

እኛ ኢትዮጵያውያን በልዩነት አንድነት የደመቅን ሕዝቦች ነን። አንድነታችን የኃይል ምንጭ ልዩነታችንን ደግሞ ውበት ሆኖን ብዙ ዘመን ተጉዘናል። ቀጣይ እጣ ፈንታችንም የሚወሰነው በዚሁ ነው። ተለያይቶ የበረታ ሀገር የለም። እንደ ሀገር የወደቀብንን የሰላም ጥያቄ፣ የማደግና ራስን የመቻል ፍልሚያ ከዳር ለማድረስ በጎ በጎ ትርክቶቻችንን ማጎልበት ያስፈልጋል ።

የጥላቻ ትርክቶች የሁላችንንም ጓዳ እንደነኩ ሁሉ፤ እነሱን ተሻግሮ ለማለፍ የሁላችንንም ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው። ተናጋሪና አድማጭ ሆነን የራሳችንን የመፍትሔ ሃሳብ ሳናቀርብ ችግራችንን ማርገብ አንችልም። ኃላፊነት እንደሚሰማው ዜጋ በመነጋገርና በመግባባት ለችግሮቻችን መፍትሔ ማፈላላግ ቀዳሚ የቤት ሥራችን ሊሆን ይገባል። በሚዘጋጁ መድረኮች ላይ ሃሳብ በመስጠትና ሃሳብ በመቀበል አብሮነታችንን ማጠናከር ይጠበቅብናል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ሲቋቋም ዋነኝ አላማው የጥላቻ ትርክቶችን አስወግዶ ኢትዮጵያዊ ቀለሞችን ለማጉላት ነው። የታሪክ ስብራቶችን በመነጋገር /በመመካከር አክሞ ለራስ ሆነ ለመጪ ትውልዶች የተሻለች ሀገር ለመፍጠር ነው። ይህ ጉዳይ የማይመለከተው ዜጋ የለም።

የጥላቻ ትርክቶች ወደሞት ጥፋት እንጂ፤ ማንንም ወደ ሕይወት አይወስዱም። ሰላም የሌለባቸው፣ የወንድማማች መገፋፋቶች የበረከተባቸው ታሪኮች ስረ መሠረታቸው የጥላቻ ትርክቶች ናቸው። የናዚው መሪ አዶልፍ ሂትለር በአይሁዶች ላይ ሲነሳ መጀመሪያ ያደረገው በጀርመናውያን ልብ ውስጥ ስለአይሁዳውያን እኩይ ትርክቶችን መፍጠር ነበር።

እንዳሰበውም ስለአይሁዳውያን ረጅም ጊዜ በወሰደ የፈጠራና የአሉባልታ ታሪክ መጥፎ ትርክት ፈጥሮ በጀርመናውያን ልብ ውስጥ አሰረጸ። ይሄ እኩይ ታሪክ በአራጋቢዎች ተራግቦ ነዶ በመቀጣጠል ብዙዎችን በላ። በታሪክ አስከፊ የሆነውን ከስድስት ሚሊዮን በላይ ንጹሃን ያለቁበትን ክስተት ፈጥሯል።

በሩዋንዳም የሆነው ተመሳሳይ ነው፣ የጥላቻ ትርክት በፈጠረው ጦስ ሩዋንዳውያን መቼም ለማይረሱት ፤ ከስምንት መቶ ሺ በላይ ዜጎቻቸውን ላጡበት ታሪካዊ ቀውስ ዳርጓቸዋል። ከነዚህ ታሪኮች እንደ ሀገር ትምህርት የምንወስድባቸው ብዙ ጉዳዮች እንደሚኖሩ ለመናገር የሚከብድ አይደለም። ዓይናችንን ከፈተን ልናያቸው፤ ጆሮ ሰጥተን ልናዳምጣቸው የተገቡ ተመሳሳይ ታሪኮችም አሉ። ትልቁ ነገር ከራሳችንም ሆነ ከሌሎች ተምረን በደመቀ የጋራ ማንነት የተሻለች ሀገር ለመፍጠር የመዘጋጀታችን እውነታ ነው።

ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You