የዓባይ ግድብ ግንባታ የይቻላልን መንፈስ ያጎናጸፈ የድል አክሊል ነው!

መጋቢት 24 ቀን በ2003 ዓ.ም የተጀመረው የዓባይ ግድብ ግንባታ ተሳክቶ ከመገባደጃው ጫፍ ደርሷል። ተማሪዎች ከዕለት ጉርሳቸው፣ የመንግሥት ሠራተኞች ከደመወዛቸው፣ የጉሊት ተዳዳሪዎች ከመቀነታቸው፤ የጉልበት ሠራተኞች ከዕለት ምንዳቸው፣ የፀጥታ ኃይሎች ከሬሽናቸው፣አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ከፍሬያቸው እየቀነሱ ግድቡን ከማጠናቀቂያ ምዕራፉ አድርሰውታል።

የግድቡ ግንባታ ኢትዮጵያ በዘመኗ ከሠራቻቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች አቻ አይገኝለትም። በአፍሪካ አንደኛ በዓለም ሰባተኛ የሆነው ይህ ግዙፍ ግድብ ያለማንም የፋይናንስ ድጋፍ ብዙ ተግዳሮቶችን አልፎ ወደ ፍጻሜው የመምጣቱ ጉዳይ የኢትዮጵያውያንን ጽናት በአደባባይ ማስመስከር ያስቻለ፤ የትውልዱን አይበገሬነት በተጨባጭ ያሳየ ነው።

ግንባታው ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ በዓመት በአማካይ 15 ሺ 759 ጊጋ ዋት ሰዓት ኢነርጂ በማመንጨት ለሀገር አቀፍ የኤሌክትሪክ ትስስር ሥርዓት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፤ ኤሌክትሪክ ያልተዳረሰባቸው የገጠር መንደሮችና ከተሞች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግና አቅርቦቱን አሁን ካለበት 44 በመቶ ወደ 90 በመቶ ከፍ ለማድረግ የተያዘውን ሀገራዊ ግብ ለማሳካት ትልቅ አቅም ነው።

ግድቡ ኃይል ከማመንጨት ባለፈ በባህር ትራንስፖርት ፣ በዓሳ ሀብት ልማት እና በቱሪዝም ዘርፍ የሚኖረው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ፤ በተለይም በግድቡ ምክንያት ሊፈጠሩ የሚችሉ ከ78 በላይ ሰው ሰራሽ ደሴቶች አካባቢውን ዋነኛ የቱሪስት ማዕከል ሊያደርጉት እንደሚችል ይታመናል።

ግንባታው አሁን የደረሰበት የመጨረሻ ምእራፍ ለመድረስ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፏል። የመሠረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ አንስቶ የኢትዮጵያን መልማት የማይፈልጉ ሀገራት እና ኃይሎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያም ሆነች ግድቡ በጥርጣሬ እንዲታዩ፤ አልፎ ተርፎም ግንባታው በዓለም አቀፍ ጫና እንዲቆም ሰፋፊ ዘመቻዎችን አካሂደዋል።

የኢትዮጵያዊያን የፖለቲካ ቁርጠኝነት፣ ብርቱ የዲፕሎማሲ ጥረትና የማህበረሰብ ተሳትፎ ተደምረው ጫናዎችን በማለፍ ፤ በአሁኑ ወቅት የግድቡ የሲቪል ሥራው ግንባታው ሐ98 ነጥብ 9 በመቶ ፣የኤሌክትሪክ መካኒካል ሥራዎች አፈጻጸም 76 በመቶ፤ የውሃ ማስተላለፊያ የብረታ ብረት ሥራዎችም 87 ነጥብ 1 በመቶ ደርሷል። አጠቃላይ የግድቡ ግንባታም 95 በመቶ ላይ ነው።

ግድቡ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር የኢትዮጵያን የኃይል አቅርቦት በከፍተኛ ሁኔታ በማሳደግ በገጠርና በከተማ የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ለማሳደግ ያስችላል። በኃይል እጥረት የተነሳ በሙሉ አቅማቸው ምርት ማምረት ያቆሙ ኢንዱስትሪዎች ሃያ አራት ሰዓት እንዲያመርቱ እድል ይሰጣል።

በርካታ ኢንቨስተሮች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ ፣ ሰፊ የሥራ እድል መፍጠር ያስችላል። በኃይል ሽያጭም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማስገባት ለኢኮኖሚው ትልቅ መነቃቃት ይፈጥራል። ከጎረቤት ሀገራት ጋር ቀጣናዊ ትስስሮችን ለማጠናከር ያግዛል። የፋይናንስ ፣ የትምህርት፣የጤናና መሰል ተቋማት አገልግሎታቸውን እንዲያዘምኑና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጡ ያስችላቸዋል።

ላለፉት 13 ዓመታት ኢትዮጵያውያን እንደ ዓይናቸው ብሌን ሲጠብቁት የቆዩት የዓባይ ግድብ ለኢትዮጵያውያን ሌላኛው የዓድዋ ድል ነው። ለመላው ሕዝቦቿ የይቻላልን መንፈስ ያጎናጸፈ፤ኢትዮያውያን ከተባበሩ ከአቅማቸው በላይ የሚሆን ፈተና እንደማይኖር በተጨባጭ ያመላከተ ነው ።

ከዚህም ባለፈ ኢትዮጵያውያን ልዩነታቸውን ወደ ጎን በመተው በአንድ ላይ መቆም ከቻሉ ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ጀምረው መጨረስ እንደሚችሉ በተግባር ያሳየ፤ ለተጨማሪ ተመሳሳይ ታሪካዊ የልማት ሥራ እንዲነሳሱ መንፈሳዊ ጉልበት የሚያቀዳጅ፤ የይቻላልን መንፈስ ያጎናጸፈ የድል አክሊል ነው።

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You