ተገቢ አገልግሎት – በተገቢው ሂደት

የሰው ልጅ ከጥንታዊው የጋርዮሽ ስርአት አንስቶ አሁን እስከሚገኝበት ዘመን ስለማንነቱ ለውጥ በትጋት ሲታገል ቆይቷል ። በየጊዜው ዘመናቱን ዋጅቶ በሚያደርገው እንቅስቃሴም በራሱ የፈጠራ ስራዎች ታግዞ በበርካታ የስኬት መንገዶች ተመላልሷል። ይህ እውነት ህይወቱን ለመለወጥ፣ ትውልዱን በስልጣኔ ለማሻገር ብ ርታት ሆኖ አ ራምዶታል።

ዛሬ ዓለማችን ዘርፈ ብዙ በሚባሉ መስኮች ከላቀ የቴክኖሎጂ ዕድገት ላይ ትገኛለች። ደረጃው ይለያይ እ ንጂ ሁ ሉም ሀ ገራት በ ዚህ ጎ ዳና ለመራመድ ብርቱ ውድድር ላይ ናቸው። በየአፍታው የሚታየውን ዘመን ወለድ ቴክኖሎጂ ጨምሮ ቀደም ሲል የነበሩ እሴቶች ለሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎቶች ወሳኝነታቸው አያጠራጥርም ።

ከሰዎች የዕለት ተዕለት ህይወት ጋር የሚገናኙ እንቅስቃሴዎች ጊዜ ወለድ እንደሆኑ ይቀጥላሉ። ጅማሬያቸው አነስተኛ ቢሆንም ውሎ አድሮ በተሻለ ፈጠራና የለውጥ እንቅስቃሴ ከታሰበው ግብ መድረሳቸው አይቀሬ ይሆናል።

ጥንታዊው ሰው ኑሮው ጫካና ዱር በነበረ ጊዜ ለብርሀን ብልጭታ ድንጋዮችን ከድንጋዮች አፋጨ። ይህ ሰበቃ ውሎ አድሮ ከሌላ ዕድል አገናኘው። ከብርሀን አልፎ እሳት እንደጫረለት ሲገባው ምግቡን ጠብሶና ቀቅሎ መመገብ እንደሚቻለው ተረዳ። ከዚህ በኋላ የነበሩ ሂደቶች ከየዕለት ርምጃዎቹ ጋር የሚራመዱ ለውጦች ሆኑ።

የሰው ልጅ ስልጣኔ መሻሻል ሲጀምር ከሻማና ኩራዝ የዘለለ፣ ጨለማን የሚያሸንፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ዕውን መሆን ያዘ። ይህ አይነቱ አገልግሎት በአጭር ጊዜ ለሁሉም ፍላጎት የሚበቃ አልነበረም። በሰለጠኑት ዓለማት የተሻለ ተደራሽነት ቢኖረውም አፍሪካን በመሰሉ አህጉራት ለሚገኙ ሕዝቦች ሲያዘግም የኖረ ቴክኖሎጂ እንደነበር ግልጽ ነው።

በሀገራችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ አስቆጥሯል። በ1890 ዓ.ም ከጀርመን መንግሥት በእርዳታ በተገኘ የኃይል ማመንጫ ጄኔሬተር አማካኝነት በቤተ መንግሥቱ እልፍኝ የመጀመሪያው ብርሀን እንደፈነጠቀ ታሪክ ያስታውሰናል። ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይልን ለመተዋወቅ መንገድ አላጣችም።

ከዘመናት በኋላ ሌላው ታሪክ በአዲስ ሂደት ሊቀየር ግድ ሆነ። ዓመቱን ሙሉ በሚፈሱ ወንዞቿ ላይ ግድቦችን በመስራት አቅም የመፍጠር ጥቅምን ያወቀችው ሀገር የኤሌክትሪክ ኃይል የማዳረስ ፕሮጀክቶችን መተግበር ጀመረች። ይህ እንቅስቃሴ በቀላሉ እውን ባይሆንም ዛሬ ላይ ከራሷ አልፎ ለሌሎች የማዳረስ አቅምን አስገኝቶላታል።

ባለንበት ዘመን የኤሌክትሪክ ኃይል ለአንድ አምፖል አገልግሎት ብቻ አይውልም። እንደየሥራው ባህርይ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ይከወኑበታል። በቅርብ ጊዜ የወጣውና ኢነርጂን መሠረት ያደረገው መረጃ እንደሚጠቁመው፤ በፈረንጆቹ 2022 ዓለም 29 ነጥብ 652 ቴራዋት ሀወርስ ኤሌክትሪክን አመንጭታለች። ይህ ምጣኔ ከአንድ ዓመት በፊት ከነበረው አቅም ጋር ሲነጻፀር የ2 ነጥብ 3 በመቶ ጭማሪ እንዳለው ያሳያል።

የዓለም ሀገራት ሰፊ የሚባል የፀሀይና ንፋስ ኃይል ማመንጫዎችንና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን መጠቀም የሚችሉበትን መንገድ ለማስፋት እየሰሩ ነው። ወደፊት ተሽከርካሪዎችን በኤሌክትሪክ የመተካት ዕቅድ በአግባቡ መተግበር ሲጀምር በ2030 በቀን አምስት ሚሊዮን በርሜል ዘይት እንደሚተካ ይገመታል።

በዓለማችን ኤሌክትሪክን ሊተኩ የሚችሉ ማመንጫዎች በርካታ ተግባራት ማከናወን እየቻሉ ነው። ተሽከርካሪዎች በኤሌክትሪክ የመተካት ሂደት በሀገራችንም ጅማሬውን ማሳየት ጀምሯልና ‹‹ይበል..›› የሚያስብል ነው። ኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ተጠቃሚውን ተደራሽ ለማድረግ የተለያዩ የኃይል ማመንጫዎችን ታንቀሳቅሳለች።

የኤሌክትሪክ ኃይል ለአንድ ሀገር የምግብ ዋስትና ማረጋገጫ ነውና ያለ ኤሌክትሪክ ኃይል ግዙፍ ፋብሪካዎችን፣ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን መዘወር አይቻልም። ይህ ኃይል በሰው ልጆች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች እጅግ ወሳኝ በመሆኑ ተፈላጊነቱ ወደር የለሽ ነው። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ ኢትዮጵያ በተያዘው በጀት ዓመት ከውጭ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትና ከሀገር ውስጥ አገልግሎት 30 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት አቅዳለች።

ለጎረቤት ሀገራት ካቀረበቸው የኃይል ሽያጭም 182 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ለማግኘት በእንቅስቃሴ ላይ ናት። ሀገራቱ ለሚያስፈልጋቸው ተጨማሪ የኃይል ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆኗንም በተግባር አረጋግጣለች። ሀገራችን በኤሌክትሪክ ኃይል ባላት የበርካታ ዓመታት ተሞክሮ በዘርፉ የሚገኙ ተቋማትን አቅም ለማጠናከር ተችሏል።

ይህ እውነታም በተፈጥሮ ፀጋዋ ምቹነትና በምታሳየው የማያቋርጥ ውጤት ሀገራት በየጊዜው የኃይል ግዢ ፍላጎት እንዲኖራቸው ምክንያት ሆኗል። በአሁኑ ጊዜ ጂቡቲ፣ ሱዳንና ኬንያ በኤሌክትሪክ ኃይል የመተሳሰር ዕድል አግኝተዋል። በተለይ የኬንያው ትስስር ታንዛንያን ይዞ እስከ ደቡብ አፍሪካ የሚዘልቅ ሂደት አለው።

የቅርብ ጊዜ መረጃ እንዲሚጠቁመውም፤ ታንዛንያ የኤሌክትሪክ ኃይልን ከኢትዮጵያ ለመግዛት ከስምምነት ላይ ደርሳለች። ታንዛንያ ከአፍሪካ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት ካለባቸው ሀገራት አንዷ ነች። የኃይል ሽያጩ የኖረችበትን የችግር ታሪክ እንደሚቀርፍላት ይታመናል። በዚህም ኢትዮጵያ ቀጣናውን በኤሌክትሪክ ኃይል በማስተዳደር የላቀውን ድርሻ እየተወጣች ነው ለማለት ያስደፍራል።

የኤሌክትሪክ ኃይሉ ከውሃ የሚመነጭ መሆኑ ተፈጥሮን የማይጋፋ እንዲሆን አድርጎታል። በማንኛውም አጋጣሚ የአየር ብክለትን ለመቆጣጠር የሚኖረው ጉልበትም ተመራጭነቱን የሚያሰፋ ነው። ኢትዮጵያ ለሀገራቱ የምታቀርበው ኃይል ተመጣጣኝና ኢኮኖሚን የሚጎዳ አለመሆኑ ደግሞ የኃይል ተሳትፎውን በማጎልበት ረገድ ሚናውን ከፍ የሚያደርግ እንደሆነ ይታወቃል።

ይህ እውነታም የጎረቤት ሀገራት የኃይል ፍላጎት በየዓመቱ አስራ አምስት በመቶ ጭማሪ እንዲያሳይ አድርጓል። ከኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በተያያዘ የቀጣናው ሀገራት ለሚያቀርቡት ጥያቄ ኢትዮጵያ ምላሹን በተግባር ለመስጠት ዝግጁ መሆኗን አስታውቃለች። በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን ስምንት ሺህ ከተሞችና የገጠር መንደሮች በኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ሆነዋል።

በቅርቡ ይፋ የሆነው መረጃ እንደሚጠቁመው፤ በሀገራችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ደንበኞች ቁጥር ከ 4 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ደርሷል።ይህ አይነቱ ውጤት ኢትዮጵያን ለመሰሉ ሀገራት በዓለም ተወዳዳሪነት እንዲኖራቸው ለማስቻል ሚናውን ላቅ ያደርገዋል። በዘርፉ የሚኖረውን ተጠቃሚነት ለማጉላትም ድርሻው በቀላሉ የሚገመት አይሆንም።

ከዚሁ ታላቅ እመርታ ጎን ለጎን ግን በግልጽ የሚስተዋሉ ክፍተቶች እግር በእግር ሊቀረፉ ግድ ይላል። በአገልግሎቱ ላይ ከደንበኞች የሚነሱ ቅሬታዎችና ለብልሹ አሰራሮች የሚያጋልጡ ተግባራትም መፍትሄ ሊበጅላቸው ያስፈልጋል።

በተለይ ከኃይል መቆራረጥ ጋር ተያይዞ ለሚያጋጥሙ ቆይታዎች ፈጣን እርምጃ ያለመወሰዱና ተጠቃሚውንና አንዳንድ የተቋሙን ባለሙያዎች በሙስና የማስተሳሰሩ ሀቅ ተደጋግሞ ይስተዋላል። አጥፊዎችን ከስራ ከማግለልና በደመወዝ ከመቅጣት ባሻገር ሁሉንም ወገን የሚያካትት የሕግ ተጠያቂነት ሊዘረጋ ያስፈልጋል።

ዘመናዊነትን በቴክኖሎጂ አዋዝቶ ስራን የማቀላጠፉ ሂደት መልካም የሚባል ጅማሬ ነው። እንዲህ መሆኑ ጊዜን፣ ጉልበትንና የአእምሮ ድካምን ይቀንሳል። ይህን አሰራር በወጉ ማዘመን ካልተቻለ ግን የሚጠበቀውን ያህል ለውጥ ማምጣት አይታሰብም።

ለዚህ ማሳያ አሁን ላይ በአብዛኞች ዘንድ ወቀሳ የሚሰማበትና ከመብራት ካርድ አሞላል ጋር የሚታየውን አሰልቺ አሰራር መጥቀስ ይቻላል።እንዲህ አይነት ክፍተት ባለበት የአገልግሎቱን ብቃት ሙሉ ማድረግ አይቻልም።

በየጊዜው የሚጨምረውን የደንበኞች ቁጥር በማዘመን የአገልግሎቱን ተደራሽነት ዕውን ለማድረግ ቴክኖሎጂውን በወጉ የሚተገብር አሰራር ሊፈጠር ይገባል። የአንድ ተቋም መሉዕነት የአገልግሎት ጥራትን ለተገቢው አካል በማድረስ ጭምር ይገለጻል። እንደ ደንበኞች ቁጥር ማየል ሁሉ የአገልግሎቱ የአሰራር ዘመናዊነትም ከፍታው በጉልህ ሊነበብ ይገባል። እንዲህ ሲሆን ውጤት በተግባር ይታያል፣ ስኬት በማስረጃ ይረጋገጣል ።

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You