የዓባይ ግድብ (የኢትዮጵያ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ) ገጥሞት ከነበር የኮንትራት አመራርና አስተዳደር ችግር፣ የማስፈጸምና የመፈጸም ውስንነት፣ ከውስብስበ ሙስና ፣ ብልሹ አሠራርና ዝርክርክነት ተላቆ ከለየለት ክሽፈት ድኖ ነፍስ የዘራው በለውጡ ማግሥት በተሰጠው አመራር ነው። ስለሆነም የዓባይ ግድብ የለውጡ ትሩፋትና ደማቅ ዐሻራ ያረፈበት ሜጋ ፕሮጀክት ነው ማለት ይቻላል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ እንደ ስሙ አንድምታው ከኢኮኖሚያዊ አውታርነት አድማስ ባሻገር ነው። የኢትዮጵያን የሕዳሴ ጉዞ ችቦ የለኮሰም ነው ይቻላል። ሲጠናቀቅ የብርሃን ጭላንጭል ለናፈቃቸው ከ50 ሚሊየን በላይ ወገኖች ጸዳል ሊሆን አሽቷል። በተደጋጋሚ በሚከሰት የኃይል መቆራረጥና እጥረት አሳሩን እየበላ ለሚገኘው ኢንዱስትሪም ሆነ ሌላ የኢኮኖሚ ዘርፍ የምስራች ይዟል።
የኤሌክትሪክ ኃይል በመሸጥ በዓመት ከአንድ ቢሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘትም አልሟል። ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያ በቀጣናው ከፍ ሲልም በአፍሪካም ሆነ በዓለም የሚኖራትን ጂኦፖለቲካዊ ተጽዕኖ ከፍ ያደርጋል። ይህ አንድ ላይ ሲደማመር ለኢትዮጵያ ሕዳሴ መበሰር ነጮች እንደሚሉት የመስፈንጠሪያ ሰሌዳ /spring- board/ ይሆናል ።
የኢትዮጵያ ሕዳሴ ወሳኝ መታጠፊያ /critical juncture/ የሆነው ይህ ግዙፍ ሕልምና ራዕይ እውን ሆኖ ከአንድም በሁለት ተርባይን 550 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት የበቃው በመላው ኢትዮጵያዊ ርብርብ ነው። ከሊስትሮ እስከ እንጨት ለቃሚ ፤ ከሕጻናት እስከ አረጋውያን ፤ ካጣ ከነጣ ድሃ እስከ ባለጠጋና ባለሀብት ፤ ከሀገሬው እስከ ዲያስፓራው ፣ ወዘተረፈ ጠጠር ያልጣለ የለም። ከዓመት ልብሱ ከእለት ጉርሱ ቀንሶ ፣ ከልጆቹ ጉሮሮ ቀምቶ የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ቦንድ ገዝቷል። ገንዘብ አበርክቷል። ለግሷል። ጉልበቱንና እውቀቱን አዋጥቷል። ከፍ ሲልም ሕይወቱን ሰውቷል።
በሀገሪቱ ታሪክ ኢትዮጵያዊ በሞላ ያለ ልዩነት እስላም ክርስቲያን ፤ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ ጉራጌ፣ ሀድያ፣… ሳይል በአንድነት ሠራዊትና ደጀን የሆነለት ግዙፍ ፕሮጀክት ነው። በነገራችን ላይ በሀገሪቱ ታሪክ በብዙ ሚሊየን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ለአንድ ሜጋ ፕሮጀክት ይሄን ያህል ገንዘብ አዋጥተው አያውቁም። የዛሬው ትውልድ በሕዳሴው ያሳየው ርብርብ የቀደሙትን ትውልዶች ክብረ ወሰን ሁሉ ሰባብሯል ማለት ይቻላል። ተደቅኖበት ከነበረ የለየለት የክሽፈት አደጋ ታድጎ በእነዚህ ቀውጢና ፈታኝና እልህ አስጨራሽ ዓመታት ሁሉ ጥርሱን ነክሶ በአጭር ታጥቆና ህልቆ መሳፍርት ለሌለው ጫና አንድ ጊዜም ሸብረክ ሳይል ለዚህ ያበቃው የለውጥ ኃይልም ያለ ምንም ስስትና ንፍገት በልኩ እውቅና ሊቸረው ይገባል።
የእንችላለን መንፈስን ለኢትዮጵያውያን ከፍ ሲልም ለመላው አፍሪካ ያጋባው የሕዳሴው ግድብ ዳግማዊ ዓድዋ ነው። ካለምንም ርዳታና ብድር በዜጎች አበርክቶና በመንግሥት በጀት እየተገነባ ያለ ተምሳሌታዊ ብሔራዊ ፕሮጀክት ነው። እስካሁን ወደ 200 ቢሊየን ብር የሚጠጋ ወጪ የተደረገለት ሲሆን ፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ አፈፃፀም 95 በመቶ፤ የግድቡ አጠቃላይ የሲቪል ሥራው ግንባታ ደረጃ ደግሞ 98.9 በመቶ ደርሷል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ሁለተኛ ተርባይንን የኃይል ማመንጨትን ካስጀመሩ በኋላ አስተላልፈውት የነበር ጥልቅና ወካይ መልዕክት ለዚህ ጥሩ አብነት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ መልዕክታቸው፡-
“በታሪክ ውስጥ ማለፍና ታሪክ ሠርቶ ማለፍ የሚባሉ ሁለት ነገሮች አሉ። በታሪክ ውስጥ ማለፍ ዕድል፣ ታሪክ ሠርቶ ማለፍ ግን ዕድልም ድልም ነው። ይሄ ትውልድ በዓባይ ግድብ ጉዳይ ባለ ዕድልም ባለ ድልም ነው። የሺ ትውልድ ጥያቄ በሚመለስበት ዘመን ተገኝቶ ግድቡ ሲገደብ በዓይን ማየት፣ በእጅ መዳሰስ፣ በእግር መርገጥ ባለ ዕድል ሲያደርግ፤ ለግንባታው ገንዘባቸውን፣ ዕውቀታቸውንና ጉልበታቸውን ከለገሡት፣ በዲፕሎማሲና በሚዲያ ለዓባይ ከሚከራከሩት፣ ታሪክ ሠሪ ጀግኖች ወገን መሆን ደግሞ ባለ ድል ያደርጋል። እነሆ አሁን የሕዳሴ ግድብ ከንድፍ አልፎ፣ ግንባታው ተገባድዶ፣ ግዙፍ ውኃ በጉያው ይዞ ኃይል ማመንጨት ጀምሯል። ዛሬ ዓባይ ተረት ሳይሆን የሚጨበጥ እውነት ነው፤ ከዘፈንና እንጉርጉሮ ወጥቶ ኢትዮጵያን ኃይል ሆኖ ሊያበረታት ከጫፍ ደርሷል። በፈጣሪ ርዳታና በኢትዮጵያዊ ወኔ ሙሉ በሙሉ ግንባታውን አጠናቅቀን የልባችን እንደሚሞላ አልጠራጠርም። እንኳን ደስ ያለን!!” ነበር ያሉት።
የመጀመሪያውን የውሃ ሙሊት ሐምሌ 15 ቀን 2012 ዓ.ም 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ እንዲይዝ ተደርጓል። ሁለተኛው የውሃ ሙሊት ደግሞ ሐምሌ 12 ቀን 2013 ዓ.ም 13 ነጥብ 5 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ በመያዝ ተጠናቋል። በሶስተኛው የውሃ ሙሊት ደግሞ 22 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ገደማ ውሃ መያዝ ችሏል። ይህ ሀገራዊ ግዙፍ የብርሃን እሸት የምስራች እንካችሁ ብሏል።
ከየካቲት 13 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በአንድ ተርባይን ብቻ 275 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት ጀምሯል። የሁለተኛው ተርባይን ደግሞ 275 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ጀምሯል። አራተኛው የውሃ ሙሊትም ተጠናቋል። ግድቡ የያዘው የውሃ መጠንም ወደ 42 ቢሊየን ሜትር ኩብ አድጓል። ግድቡ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ የሚያመርተው ኤሌክትሪክ ኃይል 5ሺ150 ሜጋ ዋት ይደርሳል። ግድቡ ሲጠናቀቅ የሚይዘው ውሃ መጠን ወደ 74 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ከፍ ይላል ተብሎ ይጠበቃል።
በ2016 በጀት ዓመት ስምንት ወራት ውስጥ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባት ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን እና የግድቡ ግንባት ከተጀመረበት 2003 አንስቶ እስከ ታኅሣሥ 30 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ከሀገር ውስጥ፣ ከውጭ እና ከቦንድ ሽያጭ ልገሳ እና ከልዩ ልዩ ገቢዎች 19 ቢሊዬን ያህል ሀብት ማመንጨት ተችሏል። ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሌላ ንግግር ስንመለስ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ 3ኛ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቁን በግድቡ ቦታ ተገኝተው ሲያበስሩ፡-
“የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እዚህ ደረጃ ላይ መድረሱ ደስ የሚያሰኝ ታላቅ ድል ነው ። ሆኖም ዓባይ ለኢትዮጵያ ብቻ የተሰጠ ሳይሆን ለዓለም ተሰጥቷል።” ብለዋል። በእሳቸው አመራር ግድቡ ገጥመውት የነበሩ ስር የሰደዱ ብልሹ አሠራሮች፣ ሙስናና ደካማ የኮንትራት አስተዳደር ተለይተው የእርምት ርምጃ መወሰዱ ታላቁን የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ከክሽፈትና ከለየለት ውድቀት ከመታደግ አልፎ ለኢትዮጵያውያን እራትና መብራት ሊሆን ሁለተኛ እሸት የምስራች ብሎ ለአጠቃላዩ ተዘጋጅቷል።
የግብፅን፣ የሱዳንን፣ የአሜሪካና የምዕራባውያንን፣ እንዲሁም የዓረብ ሊግን ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ጫናን በጥበብና በማስተዋል መቋቋም ተችሏል። ግብፅ የግድቡን ጉዳይ የዓለም የደህንነትና የሰላም ስጋት አድርጋ ለማሳየት መጀመሪያ ራሷ በኋላ በዓረብ ሊግ አይዞሽ ባይነት ቱኒዚያን በመጠቀም ጉዳዩን ከአፍሪካ ሕብረት በማውጣት ወደ መንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት አጀንዳነት ለማሳደግ ጥራለች። ሆኖም ሀገራችን በጥብቅ ዲፕሎማሲያዊ ዲስፕሊንና በጥበብ በተመራ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሀገራትን ከጎኗ በማሰለፍ የተደገሰላት ደባ እንዲከሽፍ አድርጋለች። የግድቡ ጉዳይ የተፋሰሱ ሀገራትና የአፍሪካ ሕብረት እንጂ የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ጉዳይ አለመሆኑን ማረጋገጥ ችላለች።
በዚህም ድርድሩም ለሁለተኛ ጊዜ ወደ አፍሪካ ሕብረት ተመልሷል። ምንም እንኳ ግብጽና ሱዳን ሰበብ አስባብ እየደረደሩና ፍላጎታቸውን በሌላ መንገድ ለማራመድ ላይ ታች እያሉ ቢሆንም፤ ጣልቃ ለመግባት አሰፍስፈው የነበሩ ምዕራባውያንም እርማቸውን እንዲያወጡ አድርጋለች። ሆኖም ዛሬም ሆነ ጥንት ግብፅ አልተኛችልንም። ዓባይን ከመነሻው ለመቆጣጠር ከ11 ጊዜ በላይ ልትወረን፣ ልታስገብረንና ቅኝ ልትገዛን ሞክራ እንዳልተሳካላት የታሪክ ድርሳናት ያትታሉ። በዲፕሎማሲው መድረክ ብትረታም ሀገርን ለከዱ ጡት ነካሾች የገንዘብ፣ የጦር መሳሪያ የዲፕሎማሲና የፖለቲካ ድጋፍ በማድረግ ሀገራችንን ወደ ለየለት ቀውስና ትርምስ ለመክተት ቀን ከሌት እየሰራች ነበር።
ግድቡ በአሁኑ ሰዓት ከ42 ቢሊዮን ሜትር ኩብ በላይ ውሃ በመያዝ ራሱን መከላከል የሚችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ግብፅ ለዘመናት ኢትዮጵያ ሰላም ሆና አንድነቷ የሚጠናከርና ልማቷም የሚፋጠን ከሆነ ዓባይን ጨምሮ ገና የውሃ ሀብቷን ታለማለች በሚል በስጋት ላይ ያነጣጠረ ስጋት ከውስጥ ተላላኪዎቿ ጋር በመሆን ኢትዮጵያውያንን ለመበታተን ሰርታለች። ሆኖም የግብፅና የተላላኪዎቿ የቀን ቅዠት በጀግኖች ልጆቿ ይመክናል። እየመከነም ይገኛል ።
ያለ ችግር ለአራት ዙር የውሃ ሙሌት እንዳከናወንን ሁሉ ከዚህ በኋላ የሚቀረን ሙሊት ያለ ምንም ስጋት ይከናወናል። በዚህም ቅኝ ካለመገዛት ጋር ብቻ ተያይዞ የነበረውን ነፃነትና ሉዓላዊነት በኢኮኖሚያዊ በብልፅግና ለመድገም የተጀመረው ጉዞ እውን ይሆናል። እናም ኢትዮጵያ በድህነትና በተመፅዋችነት አንገታቸውን ደፍተው የነበሩ ዜጎች አንገታቸውን ቀና አድርገው በኩራት እንዲራመዱ የሚያደርግ ብሔራዊ (ፍላግሺፕ) ፕሮጀክት ባለቤት መሆን ችላለች።
ነጋድራስ ገብረህይወት ባይከዳኝ እንዳሉት፣ በድህነትና በኋላ ቀርነት የሚማቅቅ ሕዝብ የተሟላ ሉዓላዊነት ሊኖረው አይችልም። ስንዴ እየለመኑ፣ እየተመጸወቱ ሉዓላዊነቷን ያላስደፈረች ፤ በነፃነት ታፍራና ተከብራ የኖረች ብሎ መመጻደቅን ድሉን ሙሉ አያደርገውም። ሆኖም የመጀመሪያው፣ ሁለተኛው፣ ሶስተኛውና አራተኛው የሕዳሴው ግድብ ውሃ ሙሊት መከናወኑ፤ 2ኛው ዩኒት ኃይል ማመንጨት መጀመሩ የቀጣናውን ጂኦፖለቲክስ እንደ አዲስ በይኖታል። የግብፅን የውሃ ዲፕሎማሲና ፖለቲካም ከንቱ አድርጎታል። ሆኖም ከዚህ ትልቅ ሥዕል ዓይንን ለማንሳት የሚያስገድዱ ጦርነቶችና ቀውሶች በሰላም እንዲፈቱ ጎን ለጎን ጥረት ሊደረግ ይገባል። ሰላም በሌለበት የተሟላና የተሳካ ልማት ማረጋገጥ ያዳግታልና።
የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄ በአንድ መድረክ ላይ እንደተናገሩት፤ ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ፤ ከግድብ በላይ ተምሳሌታዊ የሆነ ፣ የለውጡ ዐሻራ ፤ የትውልዱ ርብርብ ዳና በጉልህ ያረፈበት ሀገራዊ ፕሮጀክት ነው። ለኢትዮጵያውያን ከኃይል ማመንጨትም በላይ ፋይዳው የጎላ፤ ግንባታው ለይቻላል መንፈስ መሠረት የጣለ ፤ በአሁኑ ወቅት ግድቡ ሕዝቡ ባሳየው ቁርጠኝነት እና ተሳትፎ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑንም ያበሰረ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ታሪክ በመተባበር እንደ አንድ ሀገርና ሕዝብ በመሆን ድል የተደረገበት መድረክ የዓድዋ ድል ነው:: በወቅቱ የዘመቱት ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፣ ተዋግተውም ማሸነፋቸው ለኢትዮጵያ ታላቅ ድል እና ዛሬም ድረስ የሚዘከር ገድል መሆን ችሏል:: ዓባይ ግድብም በተመሳሳይ በመላው ኢትዮጵያውያን ጥረት የተገነባ አኩሪ ገድል ነው።
ግድቡ ፖለቲካዊም ሆነ ዲፕሎማሲያዊ እንድምታ ያለው ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ኢትዮጵያ እንዳታድግ ለሚጥሩ ኃይሎች ወሽመጣቸውን የቆረጠ ታላቅ ገድል ነው ብለዋል። የኢትዮጵያን ዕድገት የማይፈልጉ ሀገራት ቀድሞ ይዘው በቆዩት ያረጀ ያፈጀ አቋም ሊቀጥሉ ይፈልጋሉ:: ይሁንና ልክ የአንድነት ተምሳሌት እንደሆነው ዓድዋ አንድ መሆን ሲቻል በትብብር የማይገረሰስ ነገር አይኖርም:: በትብብር ውስጥ መሆን ጠላትም ሆነ ሌላ ፈተና ከፊት ለፊት እንዳይቆም የሚያደርግ ነው:: የሕዳሴ ግድቡንም በተባበረ ክንድ እዚህ ማድረስ የተቻለ በመሆኑ ማንም ወደ ኋላ ሊመልሰው አይችልም::
በመላው ሕዝብ ጥረት ከለውጡ በኋላ ለግድቡ የሚደረገው ድጋፍ ከወትሮው አይሎ መቀጠሉን ገልጸው፤ ለግድቡ እየተበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ፤ ግድቡን ለማጠናቀቅ እስከ አሁን ገቢ እየተሰባሰበ ያለው በቦንድ ሽያጭ ፣ በ8100 A አጭር የጽሁፍ መልዕክት አማካኝነት እንዲሁም በደረት ላይ የሚደረግ ፒን በመሸጥ ሲሆን ፤ ድጋፉ አሁንም ቀጥሏል። ለግድቡ ግንባታ የሚሰበሰበው ገንዘብ በየዓመቱም እየጨመረ መጥቷል። ለአብነት በአጭር የጽሑፍ መልዕክት 8100 A ላይ በሚደረጉ ድጋፎች አማካኝነት በአንድ ወር ውስጥ እስከ 13 ሚሊዮን ብር ድረስ መሰብሰብ ተችሏል። ይሄ ደግሞ ይበል የሚያሰኝ ተግባር እንደመሆኑም መላው ኢትዮጵያዊ ለሕዳሴው የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። በመሆኑም አስቦ መጀመር ብቻ ሳይሆን፤ ከመጀመር ማግስት የሚታዩ ሕጸጾችን አርሞ መፈጸም የሚችል፤ ፕሮጀክትን ከውድቀት መታደግ የለውጥ መንግሥት ሲተባበር ደግሞ ከሕዳሴው በላይ እልፍ ህፋሴዎችን እውን ማድረግ እንደሚችልም የታመነ ነው።፡
ሻሎም ! አሜን ።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም