የመንግሥታት መቀያየር ያላነቀፈው የሕዝብ ራዕይ

የዛሬ 13 ዓመት መጋቢት 24 የመሰረት ድንጋዩ ተጥሎ የተጀመረው የዓባይ ግድብ 95 በመቶ ያህሉ ግንባታ መጠናቀቁን ይፋ ተደርጓል። የመላው ኢትዮጵያውያን የዘመናት ሕልም የሆነው ግድብ በመጨረሻም መሬት ነክቶ ወደ መጠናቀቂያ ምእራፍ ላይ ደርሷል። በፕሮጀክቱ ላይ ከትንሽ እስከ ትልቅ፣ ከደሃ እስከ ሀብታም ሁሉም የድርሻውን ተወጥቷል፤ ዛሬም ይህ ጥረት አልቆመም።

ከጥንታዊት እስከ ዘመናዊቷ ኢትዮጵያ አታካችና አድካሚ ታሪካዊ ሂደት ታልፎ በግድቡ እውን መሆን ዜጎች የሚኮሩበት ትውልድም አንገቱን ቀና የሚያደርግበት ጊዜ ላይ ተደርሷል። ‹‹የአባይ ግድብ ውሃ ለብቻችን ይገባናል›› በሚል ትምክህት ለዘመናት የጎነጎኑት ሴራ ያልበገረው የኢትዮጵያውያን ትግል ፍሬ አፍርቶ ወደ ይቻላል ልእልና እየተንደረደረ ነው። እዚህ ለመድረስ ግን የመጣነው ርቀት በእጅጉ ረጅም ነበር።

ነገስታት በአባይ ውሃ ጉዳይ ከጠላት ጋር ተናንቀዋል፤ አድካሚ ዲፕሎማሲያዊ ንትርክ ውስጥ ገብተዋል። መሪዎች ካለፉት ስርዓቶች የተቀበሉትን አደራ መሬት ለማውረድ ብዙ ኳትነዋል። በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ጉዳይ ልዩነት የነበረ ቢሆንም፣ በዓባይ ጉዳይ ግን አንድ አይነት ራዕይ ከመያዝ የገደበ አልነበረም። ይህ ቅብብሎሽ ማብቂያው 2003 ዓ.ም ሆኖ ግድቡን ገንብቶ የኤሌክትሪክ ኃይል ከማመንጨትም በላይ የሆነው የኢትዮጵያውያን በድህነት ላይ የመዝመት ‹‹ሀሁ›› መሬት ሊነካ ችሏል።

በግንባታ ሂደቱ አያሌ እሰጣ ገባና ዲፕሎማሲያዊ ግብግቦችም ላለፉት 13 ዓመታት ተደርገዋል፤ አሁን ላይ የአሸናፊነት ድምዳሜው ማብሰር የሚቻልበት ምእራፍ ላይ ተደርሷል።

ከላይ ለማንሳት እንደሞከርነው ለግድቡ ግንባታ እውን መሆን ሕዝብ የከፈለው መስዋዕትነት ታላቅ ነው። የዜጎችን ጥቅም ለማስጠበቅና የኢትዮጵያን ሉዕላዊ የመልማት መብት እውን ለማድረግ ደግሞ ለዘመናት አገሪቱን ያስተዳደሩ መሪዎችና መንግሥታት ጉልህ አስተዋፆኦ አበርክተዋል።

ዛሬ የአባይ ግድብ ግንባታ የተጀመረበት 13ተኛ ዓመት በመላ ኢትዮጵያ ይከበራል፡፡ በአሉ ዘንድሮ የሚከበረው ግንባታው በማጠናቀቂያ ምእራፍ ላይ ሆኖ ነው፡፡ የዝግጅት ክፍላችን የግድቡ ግንባታ መሰረተ ልማት የተጣለበትን ይህን 13ተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ምእተ ዓመትን ወደ ኋላ ዘልቆ፤ ወደፊት ደግሞ በርካታ አስርት ዓመታትን ተንደርድሮ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ መንግሥታትና መሪዎች›› ለአባይ ግድብ ግንባታ ያበረከቱትን አስተዋፆኦና ተጋድሎ እናወሳለን።

አምባሳደር ጥሩነህ ዜና ኢትዮጵያን ዘለግ ላሉ ዓመታት በዓለም አቀፍ መድረክ በዲፕሎማትነት አገልግለዋል። ኢኮኖሚስትም ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ አገሪቱን ያስተዳደሩ መሪዎች በአባይ ውሃ ዙሪያ ብሄራዊ ጥቅም የሚያስጠብቅ ሚናን ተወጥተዋል። ወደ ኋላ መለስ ብለውም ንጉሰ ነገስት ዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ ከእንግሊዝ መንግሥት ጋር የድንበር ጉዳይን አስመልክቶ ያደረጉት ስምምነት፤ የአባይን ውሃ በተመለከተ የደረሱት ውሳኔም አንዱ ማሳያ መሆኑን ያስታውሳሉ።

በወቅቱ የእንግሊዝ መንግሥት ጫና የኢትዮጵያን ከአባይ ውሃ የመጠቀም መብት የሚነፍግ ስምምነት ለማድረግ ቢሞከርም አፄ ሚኒሊክ ግን ለድርጊቱ እንዳልተበገሩ የሚገልፁት አምባሳደሩ፤ ግብፅን ጨምሮ በርካቶች ጉዳዩን በጥልቀት ሳይመረምሩ ወቀሳ ሲሰነዝሩ ይደመጣል ይላሉ። ነገር ግን ንጉሱ በጊዜው የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ የማይሰጥ ከዓለም አቀፍ ሕግም ጋር የማይጣረስ ስምምነት ማድረጋቸውን ይናገራሉ።

ውሃውን ጨርሶ ላለማቆም ስምምነት ላይ ቢደርሱም ኢትዮጵያ ከአባይ ተጠቃሚ እንዳትሆን የሚደነግግ ፊርማ አለማኖራቸውን ያስረዳሉ። ይህ ውሳኔ የሚኒሊክን ብልህነትና የሚያሳይ ከመሆኑም ባሻገር ግድቡም በእርሳቸው የአስተዳደር ዘመን ባይገነባ እንኳን መጪው ትውልድ እንዲሰራው መንገድ የጠረገ ነው ሲሉ ይገልፃሉ።

የአባይ ግድብ ሲነሳ በአስተዳደር ዘመናቸው ለትውልዱ መነሳሳት ታላቅ ራዕይን ያሻገሩት ሌላኛው መሪ አፄ ኃይለስላሴ መሆናቸውን አምባሳደር ጥሩነህ ዜና ጠቅሰዋል። ንጉሱ በአስተዳደር ዘመናቸው ከኢትዮጵያ ሕዝብና ከቀደሙት ነገስታት የተቀበሉትን አደራ ለማስጠበቅ የሚያስመሰግን ስራ መስራታቸውን ይገልፃሉ። በተለይ በእርሳቸው የንግስና ዘመን ግብፅ የአስዋን ግድብን መስራት ስትጀምር ሊግ ኦፍ ኔሽንን ጨምሮ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች፣ በሁለትዮሽ ግንኙነት ወቅት ሰፊ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ማድረጋቸውን ይናገራሉ። የግብፅ ድርጊትም የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥ መሆኑን በመግለፅም ‹‹ኢትዮጵያ አልፈቀደችም፣ ጥቅማችንንም በግልፅ ይነካል›› በማለት ተቃውሞ ያሰሙ እንደ ነበር ይገልፃሉ።

አፄ ኃይለስላሴ የግብፅን ድርጊት በይፋ ከመቃወም ባሻገር ኢትዮጵያ የአባይን ውሃ ለመጠቀም የሚያስችላት የግድብ ግንባታ እንድታከናውን ጥረት ማድረጋቸውን የሚናገሩት አምባሳደሩ፤ በጊዜው የገንዘብና የፖለቲካው ሁኔታ ምቹ ስላልሆነላቸው ጥረታቸው ሳይሳካ ቢቀርም ዲዛይን እስከማሰራት የደረሰ ሙከራ ማድረጋቸውን ይናገራሉ። ይህም ንጉሱ እንደ ቀደምት መሪዎች ኢትዮጵያ የአባይ ውሃ ተጠቃሚ እንድትሆን ራዕይ እንደነበራቸው የሚያሳይ እርምጃ መሆኑን ያስረዳሉ። ‹‹እኛ ባንሰራው መጪው ትውልድ ጊዜው ሲፈቅድ እውን ያደርገዋል›› በማለት ለመጪው ትውልድ አደራ ማስቀመጣቸው የሚያስመሰግናቸው መሆኑን ይገልፃሉ።

‹‹ኢትዮጵያ ለዘመናት ከጉያዋ የሚፈሰውን የአባይ ወንዝ ገድባ ተጠቃሚ እንድትሆን ከጥንት ጀምሮም የሕዝቡ ፍላጎት ነበር። መሪዎችም ይህንን ራዕይ ለማስፈፀም ይጥሩ ነበር›› የሚሉት አምባሳደር ጥሩነህ ፤ አፄ ኃይለስላሴ ከመንበረ ስልጣናቸው ወርደው የደርግ መንግሥት በሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም ኢትዮጵያን ለማስተዳደር ሲሞክር የዓባይ ወንዝን ለመገደብና ለማልማት ብርቱ ጥረት ያደርግ እንደነበር ይገልፃሉ። መንግሥታት ቢቀያየሩም በአባይ ጉዳይ ግን አንድ አይነት አቋም በመያዛቸው ምክንያት ዘመናት ሲቀያየሩ ከአባይ ወንዝ የመጠቀም ተፈጥሯዊ መብትን ለማስከበር የሚደረገው ጥረት በዚያው ልክ እየጠነከረ መምጣቱን ያስረዳሉ።

የደርግ መንግሥት በአባይ ጉዳይ ላይ የነበረው አቋም ከአፄ ኃይለስላሴም የጠነከረ እንደነበር የሚናገሩት አምባሳደር ጥሩነህ፤ በሚከተለው ርዕዮተ ዓለም ምክንያት ግን የምእራባውያኑን ድጋፍ ማግኘት እንዳልቻለ ይገልፃሉ። እሳቸው እንዳሉት፤ የደርግ መንግሥት ፍላጎትና እቅዱን መሬት ላይ ለማውረድ እንቅፋት አልተፈጠረበትም። በዚህ ምክንያት ከጣሊያን መንግሥትና ከሳሊኒ ኮንስትራክሽን ጋር በመተባበር ለኢንዱስትሪ፣ ለእርሻ ለመሰል የልማት ስራዎች የአባይ ውሃን ለመጠቀም የተግባር ስራዎችን ጀምሮም ነበር።

ከሕዝቡና ከቀደሙት መንግሥታት የተጋራው ከአባይ ውሃ የመጠቀም ተፈጥሯዊ መብትና ራዕይ መሬት ለመንካት ጫፍ ላይ ደርሶ እንደነበር ያስረዳሉ። በዚህ ድርጊት የተበሳጩት ግብፆች የጣሊያን መንግሥት ለኢትዮጵያ ብድር እንዳይሰጥ በሴራ አስከልክለው የነበረ ቢሆንም ደርግ ግን ውጥኑን መሬት ለማስነካት ጥረት ማድረጉን ቀጥሎ እንደነበር ያስታውሳሉ። የመንግሥት ለውጥ በመምጣቱና በፕሮጀክቱ ለመቀጠል ፍላጎት በመጥፋቱ ምክንያት በጊዜው እውን ሳይሆን መቅረቱን ያስረዳሉ።

ኢሕአዴግ የሚያስተዳድረውን መንግሥት ይመሩ የነበሩት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ የኢትዮጵያ ሕዝብ የዘመናት ራዕይ የነበረውን የአባይን ወንዝ የመገደብ ጥልቅ ፍላጎት በድፍረት እውን የሚያደርግ መሰረተ ድንጋይ በመጣል ታሪክ ሰርተዋል የሚሉት አምባሳደር ጥሩነህ፤ ወቅትን ያገናዘበ ብልህነት፣ ድፍረትና የአመራር ጥበብ በአባይ ግድብ ዙሪያ መውሰዳቸው ሊያስመሰግናቸው እንደሚገባ ይናገራሉ።

ከአንድ መሪ የሕዝብን ፍላጎት አገናዝቦ ተገቢውን ጊዜና አጋጣሚ ጠብቆ መሰል ውሳኔ ላይ መድረስ የሚጠበቅ ነው የሚሉት አምባሳደሩ፣ ያ ጊዜ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ይጠብቁት የነበረው ጊዜ እንደነበር ይናገራሉ። የሕዝብን ምኞትና ሕልም እውን ያደረገና መሬት የወረደ እርምጃ እንደሆነም ይገልፃሉ። በዚህ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ሊመሰገኑ እንደሚገባቸው ደግመው ይገልፃሉ። ይህ ውሳኔያቸውም የአባይ ግድብ የህዝብ ራዕይ እንደሆነ የታየበት፣ የቀደሙት መንግሥታትንም ጥረት መሬት ያወረዱበት አጋጣሚን የፈጠረላቸው መሆኑን አስታውቀዋል። በጥቅሉ የመንግሥታት መለዋወጥ የመላው ኢትዮጵያውያንን ፍላጎት የሆነው ራዕይ ላይ እንቅፋት እንዳልፈጠረ ያስረዳሉ።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የአባይ ግድብ ከመገንባት ባሻገር የናይል ተፋሰስ አገራት በፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም ዙሪያ የጋራ አቋም እንዲይዙ፣ ኢትዮጵያም ተፈጥሯዊ መብቷን እንድትጠቀም፣ ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡም የኢትዮጵያን የመልማት ፍላጎት እንዲረዳ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ማድረጋቸውን አምባሳደሩ አመልክተዋል፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕልፈት በኋላም ጠቅላይ ሚኒስትርነቱን የያዙት አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ በሶስትዮሽ ድርድርና ዲፕሎማሲያዊ ጥረት የግድቡ ግንባታ ሳይቋረጥ እንዲቀጥል ማድረጋቸውን አምባሳደር ጥሩነህ መናገራቸውን አስታውቀዋል። በተለይ በሱዳን በተደረገው ድርድር ላይ ‹‹ኢትዮጵያ ግንባታውን እያካሄደች ስምምነት ላይ ትደርሳለች›› የሚለው ሃረግ፣ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም መጠበቅ ወሳኝ እንደነበር ይገልፃሉ።

የመንግሥታቱ ተመሳሳይ አቋምና ቁርጠኝነት የተሞላበት ትግል የግንባታው ሂደት ፈተናዎችን እየተሻገረ ወደ ውጤት እንዲደርስ ያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም ትልቅ እውቅናና ምስጋና ሊቸረው እንደሚገባ ይገልፃሉ።

የአባይ ግድብ ጥቅል አፈፃፀም 95 በመቶ አልፏል። አራት ጊዜያትም የውሃ ሙሌት ተከናውኖ ከ42 ቢሊዮን ሜትር ኪዩቢክ ውሃ በላይ ይዟል። ሁለት ተርባይነሮችም የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ጀምረዋል። ይህን ኃይል የማመንጨት ስራ በያዝነው ዓመት ወደ አምስት ተርባይነሮች ለማሳደግና ኃይል ማመንጨት እንዲጀምር ስራዎች እንደሚሰሩ መንግሥት አሳውቋል። ይህንን ሂደት አስመልክቶ አምባሳደሩ በስልጣን ላይ የሚገኘው መንግሥት በግድቡ ግንባታ መፋጠንና ዳር መድረስ ላይ ያለውን ሚና እንደሚከተለው ገልጸውታል።

ኢሕአዴግ በለውጡ መንግሥት ብልፅግና ሲተካ የአባይ ግድብ ግንባታን ለማስቀጠልና በርካታ ማስተካከያዎች ለማድረግ ተገድዶ ነበር ሲሉ ጠቅሰው፤ በተለይ የኢትዮጵያን ውስጣዊ የፖለቲካ ቀውስ እንደ ልዩ አጋጣሚ ተጠቅመው ግንባታውን ለማስተጓጎል ደፋ ቀና ሲሉ የነበሩትን ግብፅና መሰል ኃይሎች ሕልም የተቀጨበት ዲፕሎማሲያዊ ድል መመዝገቡን ይናገራሉ።

የልእለ ሃያሏ አገር አሜሪካ መሪ ሆነው የመጡት ዶናልድ ትራምፕ እና አስተዳደራቸው ኢትዮጵያ እየገነባች ያለችውን የአባይ ግድብ ግንባታ ለማስተጓጎል ግልፅ ጫና በማድረግ ለግብፅ ወግነው እንደነበረም አስታውሰው፣ በተለያየ ጊዜ በነበረው የሶስትዮሽ ድርድር ሂደት ላይ ዲፕሎማሲያዊ ብልጠት የተሞላባቸው ውሳኔዎች በኢትዮጵያውያን ተደራዳሪዎችና በመሪዋ በመወሰዱ ሴራው ሊከሽፍ መቻሉን አምባሳደር ጥሩነህ ያስረዳሉ።

‹‹ ያ ወቅት ግብፆች ‹የግንባታ ሂደቱን ማስተጓጎል የምንችለው አሁን ነው› በማለት ተደራጅተው የመጡበት ጊዜ ነበር›› የሚሉት አምባሳደሩ፤ የአሜሪካ መንግሥትም የአረብ አገራትን ከእስራኤል ጋር ለማስማማት ያደርግ በነበረው ጥረት ግብፅን ለመጠቀም በማሰቡ ኢትዮጵያን የመስዋዕትነት በግ በማድረግ በጋራ የተነሱበት እንደነበር ያነሳሉ።

የለውጡ መንግሥት ባልተረጋጋበት፣ ኢኮኖሚውም ፈተና ውስጥ ገብቶ በነበረበት ወቅት ይህን መሰል ጫና መምጣቱ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ስጋት የደቀነበት እንደነበርም አስታውሰው፣ ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ተዳክማና ኢኮኖሚዋ ደቅቆ የነበረ ቢሆንም ወኔው፣ ጥንካሬውና አንድነቱ በመኖሩ ምክንያት መንግሥት የትራምፕ አስተዳደርን ግፊት ተቋቁሞ ሕዝቡን ዳግም ለአንድ ዓላማ በማሰለፍ፣ ሀብት በማፍሰስ አሁን የደረሰበት 95 በመቶ የግንባታ አፈፃፀም ላይ አድርሶታል ብለዋል። ይህ የሚያሳየው የሕዝብ ራዕይን ሁሉም መንግሥታትና መሪዎች ተፈፃሚ ለማድረግ ያሳዩት ቁርጠኝነትን መሆኑን አመልክተው፣ በዚህም ምስጋና ሊቸራቸው እንደሚገባ ይገልፃሉ።

የአባይ ግድብ ዛሬ ለደረሰበት አፈፃፀም እንዲበቃ የሕዝቡ ራዕይ እና ለዘመናት የዘለቀ ቁጭት ምክንያት መሆኑን አምባሳደር ጥሩነህ ዜና ይገልፃሉ። ‹‹አባይ የኔ ነው። የተፈጥሮ መብቴን መጠቀም አለብኝ›› የሚል ተነሳሽነት በየዘመናቱ በሕዝቡ ውስጥ ማደሩም ከነገስታቱ ጀምሮ ያሉ አስተዳዳሪዎች ራዕይን እንዲጋራና ማስቻሉን ይጠቁማሉ። የማድረግ አቅምን ገንብቶና ምቹ ወቅትን ጠብቆ ራዕዩ እንዲሳካ ለማስቻል መሪዎች የተጠቀሙት የአመራር ሰጪነት ጥበብም ሊደነቅ ይገባል ይላሉ። በዚህ ቅብብሎች የአባይ ግድብ ሊጠናቀቅ የመጨረሻው ምእራፍ ላይ መድረሱ የመላው ኢትዮጵያውያን ድል ነው ብለዋል።

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You