የግድቡን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳዎች ስናስብ …

ኢትዮጵያ ተፈጥሮ ከለገሳት ሀብቷ እንዳትጠቀም ሲሸረቡ የኖሩት ሴራዎች በፅናት ታልፈው፣ ‹‹ኢትዮጵያውያን የውጭ ርዳታ ካላገኙ በስተቀር ግዙፉን ግድብ አይገነቡትም…›› የሚሉት የንቀት ሃሜቶች ነጭ ውሸት መሆናቸው ተረጋግጦ፣ በዘር፣ በእምነትና በፖለቲካ ልዩነት ያላቸው ኢትዮጵያውያን በግድቡ ጉዳይ ግን ልዩነት እንደሌላቸው አስመስክረው … ኢትዮጵያውያን በዓባይ ወንዝ ላይ የጀመሩትን የዓባይ ግድብ ግንባታ ለማጠናቀቅ ከመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሰዋል፡፡

ምርታማነትን በመጨመር ዘላቂ የምጣኔ ሀብት እድገት ለማስመዝገብ አስፈላጊ ከሆኑ መሠረታዊ ግብዓቶች መካከል አንዱ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት አንዱ እንደመሆኑ የግድቡ ግንባታ ወደ ማጠናቀቂያ ምዕራፍ መሸጋገር ፋይዳ ከፍተኛ ነው፡፡

ዓለም አቀፍ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ የአንድ ሀገር ምጣኔ ሀብት በዓመት ስምንት በመቶ አማካይ እድገት እንዲያስመዘግብ ከተፈለገ፣ የሀገሪቱ ኃይል የማመንጨት አቅም በአማካይ 12 በመቶ ማደግ አለበት፤ ይህ ማለት ለአንድ በመቶ የምጣኔ ሀብት እድገት አንድ ነጥብ አምስት በመቶ የኃይል አቅርቦት እድገት ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ የኃይል አቅርቦት ሁሉንም የምጣኔ ሀብት ዘርፎች ማንቀሳቀሻ ሞተርና የምርታማነት መጨመሪያ መሳሪያ ነው፡፡

ዝቅተኛ ኃይል ተጠቅሞ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እድገት ያስመዘገበ ሀገር በየትኛውም የዓለም አካባቢ የለም፡፡ ዛሬ በምጣኔ ሀብታቸው የዓለም ቁንጮ የሆኑት ሀገራት ከፍተኛ ኃይል የተጠቀሙና ለኃይል አቅርቦትም ብዙ ገንዘብ ያፈሰሱ ናቸው፡፡ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት በሌለበት፣ አስተማማኝ የምጣኔ ሀብት እድገት ሊመዘገብ አይችልምና፡፡

የኃይል አቅርቦት እስትንፋሱ ከሆነው የአምራች ዘርፉ በተጨማሪ፣ የግብርናና የአገልግሎት ዘርፎችም አብዛኛው ተግባራቸው ያለ ኃይል (መብራት) የሚታሰብ አይደለም፡፡ በአጭሩ ኃይል የኢኮኖሚ ሞተር፣ የደም ስር፣ እስትንፋስና የህልውና ዋስትና ነው፤ የኃይል አቅርቦት ከሌለ፣ ትርጉም ያለው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አይኖርም፡፡

ኢትዮጵያም የኃይል አቅርቦትን አስተማማኝ አድርጋ ዘላቂ የምጣኔ ሀብት እድገት በማስመዝገብ ብልጽግናን እውን ለማድረግ፣ የአስተማማኝ ኃይል አቅርቦት ዋስትና እንደሚሆን የሚጠበቀውን የዓባይ ግድብን በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባች ትገኛለች፡፡ ሀገሪቱ ከድህነትና ኋላቀርነት ተላቅቃ ፈጣንና ዘላቂ ኢኮኖሚ በመገንባት ሕዝቦቿን ከረሀብና ከልመና ለማላቀቅ በምታደርገው ጥረት የተፈጥሮ ሀብቷን አሟጣ መጠቀም ግድ ይላታል። ከግድቡ ጀርባ ያለው መሠረታዊ ሐቅም ይኸው ነው።

ግድቡ በኢትዮጵያውያን ሀብት የሚገነባ የብሔራዊ ኩራት መገለጫ የሆነ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክት ነው፡፡ ግንባታው ሲጠናቀቅ የኢትዮጵያን ምጣኔ ሀብትና ፖለቲካዊ የመደራደር አቅም በእጅጉ እንደሚያሳድገው ይጠበቃል፡፡ ከሚያስገኘው የኃይል አቅርቦት ጥቅም በተጨማሪ፤ በግንባታ ሂደት ላይ ሆኖ ያስገኛቸው የሥራ እድል ፈጠራ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ የቁጠባ መጠን እድገትና ሌሎች ጥቅሞች በሀገራዊ ምጣኔ ሀብት ላይ ቀላል የማይባል አበርክቶ አላቸው፡፡

ግድቡ የኃይል አቅርቦትን በማሳደግ ለምጣኔ ሀብታዊ መነቃቃትና እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ በየቤቱና በየፋብሪካዎች የሚያጋጥመውን የኃይል መቆራረጥ በማስወገድ የሥራ እንቅስቃሴን ይጨምራል፡፡ የኃይል አቅርቦት ተደራሽ ያልሆኑ አካባቢዎች የኃይል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ እነዚህ አካባቢዎች ማገዶ እንጨትንና አካባቢን በካይ የሆኑ የኃይል ምንጮችን እየቀነሱ ወደ ታዳሽና ለአካባቢ ምቹ ወደሆኑ የኃይል አማራጮች እንዲሸጋገሩ ያስችላቸዋል፡፡ ይህም ጊዜን በመቆጠብ እንዲሁም በሌሎች ተጨማሪ ሥራዎች ላይ ለመሰማራት የሚያስችል እድል በመፍጠር፣ በተለይም የሴቶችን የሥራ ጫና በመቀነስ፣ ምርታማነትን ይጨምራል፡፡ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች እንዲቋቋሙና ተጨማሪ ምርት፣ የሥራ እድልና ገቢ እንዲገኝም ያደርጋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ለጎረቤት ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይል በመሸጥ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ያስችላል፡፡ ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ኃይል ስታቀርብ ከሀገራቱ የምታገኛቸው ሌሎች ጥቅሞች ስለሚኖሩ ግድቡ ሰጥቶ የመቀበል ፖሊሲን ያሳድጋል፤ የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ከሌሎቹ ሀገራት ሌሎች ጥቅሞችን በተሻለ ዋጋና መተማመን ለማግኘት ያስችላል፤ የኢትዮጵያን የመደራደር አቅም ያሳድጋል፡፡ የምጣኔ ሀብት ትስስርን ያጠናክራል፤ አንዱ ሀገር የሌላውን ሀገር ጥቅሞች እንዲያከብር ያደርጋል፡፡

በተለይም ግድቡ በኃይል እጥረት ለሚሰቃየው የአምራች ዘርፉ ሁነኛ መፍትሔ በመሆን መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግርን ለማሳካት ለተያዘው እቅድ ዓይነተኛ ግብዓት ይሆናል፡፡ በኃይል እጥረት ምክንያት ከአቅም በታች እያመረቱ ያሉና ሥራ ያቆሙ አምራቾች የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኙና በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ እድል ይፈጥርላቸዋል፡፡ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን በመሳብ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ፣ የሥራ እድልና ገቢ እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ ይህም የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ተጨባጭ ለውጥ እንዲያስመዘግብ ያስችላል፡፡

የግድቡ መገንባት ተጨማሪ ኢንቨስትመንቶችን ይጋብዛል፡፡ ባለሀብቶች ለኢንቨስትመንት ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ አንድ መስፈርት አድርገው የሚመለከቱት የሀገሪቱን የኃይል አቅርቦት አስተማማኝነት ነው፡፡ ግድቡ የኃይል አቅርቦትን አስተማማኝ ስለሚያደርግ ተወዳዳሪ የሆነ ዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንትን ወደ ኢትዮጵያ በመሳብ ረገድ ትልቅ ሚና ይኖረዋል፡፡ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት (Foreign Direct Investment-FDI) ሌላ የውጭ ምንዛሪ ይዞ ይመጣል፤ ወደ ሀገሪቱ የመጣው የውጭ ምንዛሪ ምርት ተመርቶበት ምርቱ ኤክስፖርት ሲደረግ ሌላ የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ግድቡ ሲጠናቀቅ በግድቡ አካባቢ ብዙ ደሴቶች ስለሚፈጠሩ አዳዲስ የቱሪዝም አቅሞች ይፈጠራሉ፡፡ እነዚህ የንግድና ምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴዎች ተጨማሪ የሥራ እድልና ገቢ ይፈጥራሉ፡፡ ይህም የግድቡ ኢኮኖሚያዊ ሚናዎች ተደራራቢ ውጤቶችን የሚያስገኙ በረከቶች እንደሆኑ መገንዘብ ይቻላል፡፡

በግድቡ ምጣኔ ሀብታዊ ሚና ላይ ያተኮረው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማኅበር (Ethiopian Eco­nomics Association) ጥናት እንደሚያሳየው፣ ግድቡ በኢትዮጵያ በዝቅተኛ የትምህርትና የገቢ ደረጃ ላይ የሚገኙትን ዜጎች ገቢያቸውን በዓመት በስምንት ነጥብ ስምንት በመቶ ያሳድጋል፡፡ ሱዳንና ግብጽም ከግድቡ ቀላል የማይባል የምጣኔ ሀብት ጥቅም እንደሚያገኙ የጥናቱ ውጤቶች ያሳያሉ፡፡ ይህም ግድቡን ለፍትሃዊና አካታች ጥቅም በአብነት ሊጠቀስ የሚችል ፕሮጀክት ያደርገዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በምጣኔ ሀብትና በፖለቲካ መስኮች የሚኖራትን ተፅዕኖ እንደሚሳድገው ይጠበቃል፡፡ የግድቡን ግንባታ በብርቱ የሚቃወሙ አካላት የተቃውሟቸው ዋናው ምክንያታቸውም ይህ ተጠባቂ ተፅዕኖ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ግድቡ የኢትዮጵያን የመደራደር አቅም በማሳደግ ምጣኔ ሀብታዊና ፖለቲካዊ ተፅዕኖዋ እንዲጨምር ዓይነተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡

ግድቡ ለኢትዮጵያ ዓለም አቀፋዊ የኢኮኖሚ ግንኙነት ከፍተኛ አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለኢትዮጵያ አዎንታዊ ምስል የሚያሰጥ ፕሮጀክት ነው፡፡ የግድቡ ግንባታ በርካታ መሰናክሎችን አልፎ የተከናወነ በመሆኑ ሌሎች ሀገራትና ተቋማት በሀገሪቱ ፕሮጀክት የማስፈፀም አቅም ላይ መተማመን እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡ ይህ አዎንታዊ ምስል ደግሞ ለጋሽ ሀገራትና ተቋማት ለኢትዮጵያ የሚሰጡትን ድጋፍና ብድር እንዲያሳድጉ ያግዛል፡፡ ለጋሾች ለኢትዮጵያ የልማት ፕሮጀክቶች በሚሰጧቸው ድጋፎች ውጤታማነት ላይ እምነት እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡ የውጭ ባለሀብቶችም ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በኢንቨስትመንት ለመሰማራት መተማመኛ ይሆናቸዋል፡፡

የግድቡ መጠናቀቅ በኢኮኖሚው ዘርፍ ብቻ ከላይ የተዘረዘሩትን ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ያስገኛልናል ማለት ነው፤ በርግጥ ከግድቡ የምናገኛቸው ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች እነዚህ ብቻ እንዳልሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ የግድቡ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች ደግሞ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ፋይዳዎችን የሚያስገኙ በረከቶች ናቸው፡፡ በአጠቃላይ የግድቡ ግንባታ ዋነኛ ዓላማ ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ በመሆኑ ግድቡ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት የማይተካ ሚና እንደሚኖረው የታወቀ ነው፡፡ እንግዲህ የግድቡን ግንባታ መጠናቀቅ ስናስብ ተዘርዝረው የማያልቁትን እነዚህን ጥቅሞቹ የሚያስገኙልንን ዓይነተ ብዙ በረከቶችን በተስፋና በጉጉት እንጠብቃለን፡፡ በተስፋ እንደጀመርነው በፅናት ጨረስነው!

ወንድይራድ ሰይፈሚካኤል

አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You