ሁሉም ነገር መነሻ አለው፤ ሁሉም ጉዳይ ፈጻሚ አለው፤ ሁሉም ጅምር የሚጠናቀቅበት ጊዜና የሚያጠናቅቀው ኃይል አለው። ትናንት ለዛሬ፣ ዛሬም ለነገ መነሻ እንደሆነው ሁሉ፤ ቀደምቶች ለአሁኑ፣ የአሁኖቹም ለመጪዎቹ ትውልዶች የታሪክም የግብርም መሰናሰል መሠረቶች ናቸው።
ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያንም ከትናንት እስከ ዛሬ በታሪክ ጅረት ውስጥ የሚገለጥ፤ የትውልዶች የተግባርም፣ የታሪክም፣ የባህልና እሴትም፣… ቅብብሎሽና መሰናሰሎች የተሳሰሩ ማንነት ያላቸው ሀገርና ሕዝቦች ናቸው። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ስንል የሚታየን የገናን ታሪክ ባለቤትነቷ፤ የነፃነትና ብዝሀነት ገጿ ከዚሁ እውነት የተቀዳ ነው።
ኢትዮጵያውያንም እንደ ሕዝብ የደመቀ ታሪክ ባለቤትነታቸው፤ የብዝሀ ማንነት ስሪታቸው የዚሁ የትውልዶች ከትናንት እስከ ዛሬ የዘለቀው የማህበራዊም፣ የኢኮኖሚያዊም፣ የሥነ ልቡናዊም ውቅር ውጤት ነው። የተናበበ ሃሳባቸው፤ የተሰናሰለ ተግባራቸው፤ ያልተቆራረጠ ገድላቸውም የዚህ የጠነከረ የወል ጉዳያቸው ስሪት ነው።
በዚህም ረገድ በሺህ ዘመናት የሚለካ ታሪክን ሰርተዋል፤ ያልተቆራረጠ ሥርዓተ መንግሥትን አኑረዋል፤ የሕዝቦች አብሮነትና መተሳሰብን አጽንተዋል። ዓድዋን የመሳሰሉ ከራስ አልፎ ለመላው ዓለም የነፃነት ችቦን በደማቁ ያበራ ድል የተገኘው በዚሁ መንገድ ነው። የዓባይ ግድብን ያህል ታላቅ ፕሮጀክት አስቦ ለመጀመር፣ ጀምሮም ለመፈጸም ከጫፍ ማድረስ የተቻለውም በዚሁ ልዕልና ነው።
ከ128ኛው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ማግስት፣ 13ኛ ዓመት ልደቱ የሚከበርለት ይሄ ግድብ ታዲያ፤ የትናንት አባቶች የመሠረቷትን ነፃ ሀገር ወደ ሙሉ ነፃነቷ ለማሸጋገር አቅም የሚሆን ነው። ምክንያቱም የዓድዋ ድል ለዓባይ ግድብ ዛሬ ላይ ለዚህ መድረስ አቅምም፣ የሞራል ስንቅም ሆኗል።
ከዚህ ባሻገር ደግሞ፣ የዓድዋ ዘመን ትውልዶች ለዛሬው የዓባይ ዘመን ትውልድ የመቻል ሰብዕና፤ የመፈጸም ልዕልናን፤ የነፃነትንም ከፍ ያለ ዋጋ በልኩ እንዲገነዘብ የሚሆን የመንፈስ ጥንካሬን እንዲላበስ አርአያ ሆነውታል። እናም የትናንቱ ድል ለዛሬው ፕሮጀክት ስንቅ፤ የትናንቶቹ ባለ ድሎች ለዛሬዎቹ ታሪክ አስቀጣዮች አብነት ሆነዋቸዋል።
ይሄ የታሪክ መሰናሰል፤ የትውልድ ቅብብሎች፤ የግብር ምግግቦሽ ታዲያ፤ ለቀደሞት ክብርን፣ ለጀመሩትም ምስጋናን በመቸር ውስጥ የሚራመድ ሊሆን ይገባል። ምክንያቱም የቀደሙትን ያከበረ ትውልድ፣ ለራሱም ይከበራል። የሰሩትን የሚያመሰግን ትውልድ ተመስጋኝነትን ይጎናጸፋል።
የዓባይ ግድብ ጉዳይ ሲነሳም እውነቱ ይሄው ነው። ቀደምቶቹ አሰቡት፤ ሃሳባቸውን በንድፍ አኖሩት፤ ግን ለመፈጸም አቅሙም ወቅቱም አልፈቀደላቸውም፤ እናም ለትውልድ በአደራም በኃላፊነትም ሰጡት። ይሄ የቀደምቶች ምኞት፤ የትናንት ሕልም ነበር።
ዛሬ ያ ምኞት እውነት ሊሆን፤ ሕልሙም ሊፈታ ቀኑ ደረሰ፤ የአደራ ተቀባዩ ትውልድ ምኞቱን ወደ ተጨባጭ እውነት፤ ሕልሙንም በተግባር ፈታው። እናም የዓባይ ግድብ የዛሬ 13 ዓመት የሚታይ እና የሚዳሰስ እውነት ሆነ። ዘመን ለዘመን ሥፍራውን ሲለቅቅ፤ ትውልድ ለትውልድ አደራውን ሰጥቶ ሲያልፍ፤ የማያልፈው እውነት፣ የማይደበዝዘው ተግባር ቦታውን ያዘ።
ለዚህም ነው ቀደምቶችን ማክበር፤ ለተግባር የሚተጉትን ሁሉ ማመስገን የሚገባው። ይሄ በማክበርና በማመስገን የተቃኘ ትውልድና ማንነት ደግሞ፤ መንገዱ ያማረ፣ ተግባሩም የቀና ይሆናል። አመስግኗልና የሚመሰገንበትን ለመሥራት፤ አክብሯልና የሚከበርበትን ዐሻራ ለማኖር የሚያግደው አንዳችም ሁኔታ አይኖርም።
ዛሬ ላይ የዓባይ ግድብ ተጨባጭ እውነት የሚገልጠውም ይሄው ነው፤ በማክበርና በማመስገን የተጀመረ ፕሮጀክት ምንም እንኳን ፈተናው የበዛ ቢሆንም ከችግሩ ባሻገር ለመገለጥ ያገደው ነገር አልነበረም። ዓባይ ከባይተዋርነት ወደ ቤተኝነት ተደምሮ ለሕዝቡ ብርሃንን ማቀበል መጀመሩም የዚሁ ቅኝት ውጤት ነው።
ይሄን መሰሉ የአመስጋኝነት ቅኝት የወለደው ውጤት ደግሞ፣ ዛሬ ላይ በርቶ የሚጨልም አልያም የሚደበዝዝ አይደለም። ይልቁንም የዛሬው ስኬትና ውጤት እንደ ትናንቱ ሁሉ ለነገው አቅምም፣ ስንቅም የሚሆንን ሰብዕና የሚያላብስ ነው። ምክንያቱም ስኬት ጫፍ የለውም። ስኬት በቃኝ የሚል እሳቤም አይቀበልም።
ስኬት እያመሰገኑ መሥራትና ለውጤት መብቃትን ይጠይቃል። ስኬት ዛሬን የተሻለ ሰርቶ ለነገዎቹ በኃላፊነት የሚወጡትን አደራ ማኖርን አብዝቶ ይሻል። ዓባይም እንዲሁ ነው። ትናንቶች አሰቡት፤ ዛሬ ላይ ያሉ ጀምረው ከፍጻሜው አደረሱት። ዓባይ ግን አንድ ብቻ አይደለም። ዓባይ መልከ ብዙ ነው። እናም በዚሁ የበዛ መልኩ የሚገባቸውን እያከበርንና እያመሰገንን፤ የተገኘውን ውጤትም እያላቅን መጓዝ፤ ነጋችንን በዚሁ ልዕልና ቃኝነት የላቀ ማድረግ የተገባ ነው።
አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም