የሕብረተሰብ ተሳትፎ መገለጫ

የሁሉም ኢትዮጵያውያን ዐሻራ እያረፈበት ያለው የዓባይ ግድብ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ተጥሎ ግንባታው ከተጀመረ እነሆ 13 ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ ከምሥረታው ጊዜ አንስቶ አሁን ለደረሰበት የማጠናቀቂያ ምዕራፍ የሕብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ እንደመሆኑ፣ በተለያዩ ሕዝባዊ ንቅናቄዎች፣ ማህበራዊ ተሳትፎዎች ወዘተ፣ ለግንባታው ሀብት ሲሰበሰብ ቆይቷል፤ እየተሰበሰበም ይገኛል፡፡

ገቢ ለማሰባሰብ ይደረጉ ከነበሩ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ዋነኛው የቦንድ ሽያጭ ነው፡፡ ይህ የቦንድ ሽያጭ በተለያየ መጠን ዜጎች እንደየአቅማቸው በስማቸው በመግዛት ዐሻራቸውን እንዲያሳርፉ ትልቅ መነሳሳትን ፈጥሯል፡፡

በዚህም እንቅስቃሴ ሠራተኞች በመሥሪያ ቤታቸው፣ ተማሪዎች በትምህርት ቤታቸው፣ ወላጆች ከራሳቸው አልፎ በልጆቻቸው ስም፣ በተለያየ መጠን ቦንዱን በመግዛት በፕሮጀክቱ ግንባታ ላይ ዐሻራቸውን አሳርፈዋል፡፡ የመከላከያና የፖሊስ አባላት፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በየተቋሞቻቸው ስም እንዲሁም በውጭ ሀገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቦንድ በመግዛት ዐሻራቸውን አኑረዋል፡፡ በዚህ ቦንድ ግዥ ያልተሳተፈ ኢትዮጵያዊ የለም ማለት በሚያስደፍር ሁኔታ ነው ድጋፉ የተደረገው፡፡

ግድቡ በተጀመረበት ዓመት ግንባታው በአምስት ዓመት ውስጥ ይጠናቀቃል የሚል ግምት ተሰጥቶት የነበረ ቢሆንም፣ በተለያዩ ምክንያቶች በጊዜው መጠናቀቅ ሳይችል ቀርቶ የተለያዩ ሂደቶችን እያለፈ አሁን በ13ኛ ዓመቱ ከማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ ደርሷል፡፡

የግድቡ ግንባታ የተለያዩ ምዕራፎችን አልፏል፤ እያንዳንዳቸው ምዕራፎች የግንባታው ስኬቶች በመሆናቸው ኢትዮጵያውያንም በልዩ ሁኔታ እያሰቧቸው እዚህ ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ ዘንድሮ ደግሞ በማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ በመገኘት ታላቅ የምስራች ይዞ መጥቷል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ሊጠናቀቅ የጥቂት ወራት ግምት ብቻ ተሰጥቶት ግንባታው 95 በመቶ መድረሱ ይፋ ተደርጓል፡፡ በዛሬው እለትም ግንባታው የተጀመረበትና የመሠረት ድንጋይ የተጣለበትን 13ኛ ዓመት ‹‹ በሕብረት ችለናል ›› በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ሁነቶች እየተከበረ ይገኛል፡፡ 13ኛ ዓመቱን አስመልክቶ የገቢ ማሰባሰብ ሥራ እንደሚካሄድ ተጠቁሟል፡፡

ለግድቡ ግንባታ ገቢ ለማሰባሰብ ተብለው በሚዘጋጁት ሁነቶች እና እንቅስቃሴዎች ውስጥ በየዓመቱ ዜጎች በተለያየ አማራጭ ቦንድ እንዲገዙ የማድረጉ እንቅስቃሴዎች ይጠቀሳሉ፡፡ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ዜጎች የግድቡን ግንባታ ቦንድ በመግዛትና በመሳሰሉት ድጋፍ እያደረጉ ቆይተዋል፤ በአሁኑ ወቅትም እያደረጉ ናቸው፡፡ በርካታ ዜጎች የግንባታው መሠረት ከተጣለ አንስቶ ሳያቋርጡ በየጊዜው ቦንድ እየገዙ ይገኛሉ፡፡

ወይዘሮ ነጃት ሸረፋ አሁን ላይ በተለያዩ ቦታዎች ላይ እየተዘዋወሩ አነስተኛ ሥራዎችን እየሠሩ ኑሯቸውን የሚመሩ የአራት ልጆች እናት ናቸው፡፡ ወይዘሮ ነጃት የዓባይ ውሃ ለዘመናት ወደሌሎች ሀገራት የሚፈስ እና እነዚህ ሀገራትም ይህን ውሃ ተጠቅመው መሬታቸውን ሲያለሙ ኢትዮጵያና ዜጎቿ ግን በተለያዩ ችግሮች ውስጥ መኖራቸው ሁሌም የሚያሳስባቸው እና የሚቆጫቸው ጉዳይ ነበር፡፡

‹‹ዓባይ ሊገደብ የመሠረት ድንጋይ መቀመጡን ስሰማ ደስታዬ ወደር አልነበረውም›› የሚሉት ወይዘሮ ነጃት፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ያለማቋረጥ ለተከታታይ ሰባት ዓመት በእርሳቸው እና በልጆቻቸው ስም እያደረጉ ቦንድ ገዝተዋል፡፡ ‹‹ባገኘሁት አጋጣሚ በልጆቼ ስም ቦንድ ገዝቻለሁ፡፡ ግድቡ ሲጀመር የሁለት ልጆች እናት ነበርኩ አሁን የአራት ልጆች እናት ስሆን በልጆቼ ስም ቦንድ እየገዛሁ በእነርሱ ስም ዐሻራ ማስቀመጥ እፈልጋለሁ›› የሚሉት ወይዘሮ ነጃት፣ ልጆቻቸውም በትምህርት ቤታቸው ሲጠየቁ እንዲገዙ ያበረታቷቸዋል፡፡

በየጊዜው ይህን ቦንድ የሚገዙት ተርፏቸው ወይም በእቅዳቸው ውስጥ አካተውት ሳይሆን፣ ግድቡ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለው ሁሉ እንዲገነባው እና እንዲጠቀምበት ኃላፊነት የተጣለበት በመሆኑ ነው ይላሉ፡፡ ወይዘሮ ነጃትም በየሰው ቤቱ ተዟዙረው በሚሰሩት ሥራ ከሚያገኙት ገንዘብ ላይ ቀንሰው በአቅማቸው ቦንድ የሚገዙትም ለዚሁ ነው፡፡

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የሁሉም ኢትዮጵያውያን በመሆኑ ሁሉም የአቅሙን የራሱን ድርሻ የሚወጣበት ነው፡፡ ወይዘሮ ነጃትም ከ200 ብር ጀምረው ለተከታታይ ሰባት ዓመታት ያላቸውን እያወጡ ለግድቡ እዚህ መድረስ የራሳቸውን ዐሻራ አሳርፈዋል፡፡

ግድቡ ሲጠናቀቅም ብዙ ተስፋ እንዳላቸው ጠቅሰው፣ ‹‹ልጆቻችን ከስደት ተላቀው በሀገራቸው ኮርተው ሰርተው መግባት እንዲችሉ፣ መጪው ትውልድም ሰፊ የሥራ እድል አግኝቶ የሚኖርበት እንደሚሆን የኔም የሌሎች ኢትዮጵያውን ተስፋ ነው ብዬ አምናለሁ›› ብለዋል፡፡

ሌላኛዋ በቦንድ ግዢው የሚጠቀሱት ባለትዳር እና የሁለት ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ ምናሉ አረጋይ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምንት ነዋሪ ናቸው፡፡ የሚተዳደሩት በመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ የጽዳት ሥራ በመሥራት ነው፡፡

‹‹የግድቡ ግንባታ መጀመር በጣም አስደስቶኝ ነበር፡፡ ምክንያቱም ለረጅም ጊዜ የኢትዮጵያ ውሃ ያለ ጥቅም መፍሰሱ በጣም ይቆጨኝ ነበር፡፡ ከዚያም ደግሞ በዓባይ ውሃ ግብጽ ትልቋ ተጠቃሚ ስለመሆኗ መረጃ ነበረኝ›› የሚሉት ወይዘሮ ምናሉ፣ የዓባይ ውሃ በሀገራችን ጥቅም ላይ ቢውል ብዙ እናቶች በቂ የኃይል አቅርቦት ይኖራቸዋል፤ ኑሯቸው ይሻሻላል የሚል ተስፋ አላቸው፡፡

የዓባይ ግድብ ግንባታ ይፋ ከተደረገበት ጊዜ አንስቶ የአካባቢያቸው ሰዎችም በቦንድ ግዥው እንዲሳተፉ የማስተባበር ሥራን በቅርበት መሠራታቸውንም ይገልጻሉ፡፡ ወይዘሮ ምናሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የገዙት የአንድ ሺህ ብር ቦንድ ነበር፡፡ ‹‹አሁን ግንባታው እየተገባደደ ስለሆነ የመጨረሻውን ዐሻራዬን ማሳረፍ እፈልጋለሁ›› የሚሉት ወይዘሮ ምናሉ፤ የዓባይ ግድብ የማይመነዘር የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሀብት ነው ይላሉ፡፡ ለልጆቻቸውም ይህንን ትልቅ ታሪክ ባሳረፉት ዐሻራ አማካይነት እንደሚያስተላልፉ ተናግረዋል፡፡

ወይዘሮ ምናሉ ቦንዱን የሚገዙት ለዚሁ ተብለው በሚዘጋጁ የማስተባበሪያ ድንኳኖች እንዲሁም ቦንድ ወደሚገኝበት ባንክ ጭምር በመሄድ ነው፡፡ ያለማቋረጥ ቦንድ በመግዛት የሚታወቁት ወይዘሮ ምናሉ፣ በአንድ ወቅት ወዳጃቸው ቦንድ እየተሸጠ እንደሆነ ሲነግሯቸው እንዳያመልጠኝ ብለው የአንድ መቶ ብር ቦንድ በስማቸው እንዲገዙላቸው ያደረጉበትን ገጠመኝንም አስታውሰዋል፡፡

ወይዘሮ ምናሉ ለተከታታይ ስምንት ዓመታት ይሄን ያደረጉት ደመወዛቸውን ጠብቀው፣ ቤታቸውን ልጆቻቸውንም እያስተዳደሩ ነው፡፡ በአነስተኛ ደመወዝ የሚኖሩ ቢሆንም፣ ለግድቡ የምሰስተው የለኝም ብለው ነው ድጋፍ የሚያደርጉት፡፡ ድጋፉ ማድረጉ የኔም ኃላፊነት ጭምር ነው በማለት ነው በዚህ ልክ የተሳተፉት፡፡

አሁን ግድቡ ሊጠናቀቅ ጥቂት ወራት እንደቀሩት የተገለጸ መሆኑን ጠቅሰው፣ በእነዚህ ጊዜያት በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ አሁንም ቦንድ እንደሚገዙ አስታውቀዋል፡፡ ሌሎችም በግዥው እንዲሳተፉ ጥሪ አስተላልፈዋል ፡፡

በከሰል ንግድ የሚተዳደሩት የሻሸመኔ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ አሰለፈች ጸጋዬ ሌላዋ ቦንድ በተደጋጋሚ በመግዛት የሚታወቁ ናቸው፡፡ ወይዘሮ አሰለፈች ለግድቡ ግንባታ ከ100 ጊዜ በላይ ቦንድ በመግዛት ነው የሚታወቁት፡፡

ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩት ፌስታል፣ ከሰልና የመሳሰሉትን በመሸጥ እንደሆነ የሚናገሩት ወይዘሮ አሰለፈች፤ ‹‹የዓባይ ግድብ የእኔ ነው›› ሲሉ ይናገራሉ፤ ከሚያገኙት ገቢ እየቀነሱ ቦንድ እንደሚገዙም ገልጸዋል፡፡

የግድቡ ግንባታ በተጀመረበት የመጀመሪያ ዓመት ብቻ የአንድ ሺ ብር ቦንድ መግዛታቸውን አስታውሰው፣ እስከ አሁን ያለማቋረጥ እየገዙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የዘንድሮውን ሳይጨምር እስከ አሁን የ640 ሺ ብር ቦንድ ገዝተዋል፡፡ 120 ሺ ብር ደግሞ በልገሳ ሰጥተዋል፡፡

‹‹ካለኝ አነስተኛ ገቢ የዓባይ ግድብ ቦንድ እንድገዛ ያነሳሳኝ የሀገር ፍቅር ስሜት ነው›› ሲሉም ጠቅሰው፣ ‹‹መኖር የሚቻለው ሀገር ስትለማና ስትኖር ነው›› ብለዋል፡፡ እሳቸው ከሚያደርጉት የቦንድ ግዥና ለግሳ በተጨማሪ ሌሎች ሰዎችን በማነሳሳት በርካታ ቦንድ እንዲገዙ ማድረጋቸውንም አስታውቀዋል፡፡

ወይዘሮ አሰለፈች የግድቡ ግንባታ የደረሰበትን ደረጃ ለመመልከት ሶስት ጊዜ ጉብኝት ማድጋቸውን ጠቅሰው፣ አሁን በደረሰበት የማጠናቀቂያ ምእራፍ ልዩ ደስታ እንደተሰማቸውም ገልጸዋል፡፡

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ዘንድሮ የሚከበረውን የግድቡ ግንባታ የተጀመረበትን 13ኛ ዓመት አስመልክቶ በቅርቡ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ሕዝቡ ለግንባታው ቦንድ በመግዛትና በመሳሰሉት የሚያደርገው ተሳትፎ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

ባለፉት 13 ዓመታት ከ18 ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን በላይ ብር ለማሰባሰብ ተችሏል፡፡ የፕሮጀክቱ አፈፃፀም በማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ ይገኛል ያለው መግለጫው፣ ኃይል በማመንጨት ላይ ካሉት ሁለት ዩኒቶች በተጨማሪ ሌሎች ዩኒቶች ተጠናቀው በቅርቡ ኃይል ያመነጫሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ጽሕፈት ቤቱ የደረሰውን የስምንት ወራት ሪፖርት ዋቢ አድርጎ በመግለጫው ላይ እንዳስታወቀውም፤ በ2016 በጀት ዓመት ከሐምሌ 2015 ዓ.ም እስከ የካቲት 30/2016 ዓ.ም ድረስ 931 ሚሊዮን 984 ሺ 102 ብር ከሕብረተሰቡ ሊሰበሰብ ችሏል፡፡

ይህ ተሳትፎ ሀገራዊ በመሆኑ በግድቡ ላይ የራሳቸውን ዐሻራ ማሳረፍ ከፈለጉ በሌሎች የዓለማችን ክፍል ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎችም እንዲሁ በቦንድ ግዢ እና ስጦታ ባለፉት ስምንት ወራት አራት ሚሊዮን 614 ሺህ 884 ብር መሰብሰብ ተችሏል ፡፡

በየዓመቱ በዓሉን ለማክበር በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ ዜጎች የግድቡን ግንባታ ሊያግዙ በሚችሉ የቦንድ ግዢ እና ስጦታ ፣ ለዚሁ ተብሎ በተዘጋጀው የ8100 አጭር የጽሑፍ መልዕክት፣ በተለያዩ ሀብት ለማሰብሰብ ተብለው በተዘጋጁ ኹነቶች ገቢ የማሰባሰብ ሥራ ተሰርቷል፡፡

የግድቡ ግንባታ የተጀመረበት 13ኛ ዓመት ‹‹ በህብረት ችለናል! ›› በሚል መሪ ቃል በበለጠ ተሳትፎ እና የሀብት ማሰባሰብ ተግባራት ለማክበር ዝግጅት መደረጉን ጽሕፈት ቤቱ አስታውቋል፡፡ ከመጋቢት 18 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በመላው ሀገሪቱ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የቦንድ ሳምንት እንደሚካሄድ ጠቁሟል፡፡ በቦንድ ሳምንቱ 100 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ የታለመ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ሌሎችም ቦንድ የሚሸጡ የገንዘብ ተቋማት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ዝግጅት ቦንድ ለመሸጥ መሰናዳቸውም በመግለጫው ላይ ተመልክቷል፡፡

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You