ዓባይ-የኢትዮጵያውያን ብርሃን

ብዙ የተባለለትና ብዙ የተወራለት የዓባይ ግድብ ከብዙ ውጣውረድና መሰናክል በኋላ ዘንድሮ አስራ ሶስተኛ ዓመቱን ደፍኖ እነሆ ሊጠናቀቅ ጥቂት ወራቶች ብቻ ይቀሩታል። ያኔ በቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስቴር አቶ መለስ ዜናዊ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉባና ሰዳል ወረዳ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠለት የዓባይ ግድብ ገና ከመነሻው ነበር ከታችኛው የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት በተለይም ከግብፅና ሱዳን ተቃውሞ የገጠመው። ሁለቱ ሀገራት በተለይም ግብፅ የቀድሞ የቅኝ ግዛት ሕጎችን በማምጣትና በኢትዮጵያ ላይ ዓለም አቀፍ ጫና እንዲበረታ በማድረግ የግድቡን ግንባታ እንዳይከናወን በብርቱ ጥራለች። እንዲያም ሆኖ ግን ኢትዮጵያ በቁርጥ ቀን ልጆቿ የዲፕሎማሲ ጥረት ፈተናዎችን ተጋፍጣና አልፋ የግድቡን ግንባታ አስጀምራለች።

የዓባይ ግድብ ግንባታ ገና ሃሳቡ ሲፀነስ ነበር መላው ኢትዮጵያውያን ከዳር እስከዳር ድጋፋቸውን የገለፁት። ግድቡ በሕዝብ ትብብር የሚገነባ እንደመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ነበሩ የግድቡን ግንባታ ዳር ለማድረስ በሚችሉት ሁሉ ድጋፋቸውን ለመቸር ቃል የገቡት። ግድቡ የነገ ኢትዮጵያውያን ብርሃንና ተስፋ ነበርና በጊዜው ኢትዮጵያውን ለግድቡ ግንባታ የሰጡት የትብብርና ድጋፍ ምላሽ ድንቅ ነበር። ኢትዮጵያውያን ለጋራ ጠላቶቻቸው ብቻ ሳይሆን ለጋራ ልማት ‹‹ሆ›› ብለው እንደሚነሱ ያሳየም ጭምር ነበር የዓባይ ግድብ።

ብረት እንደጋለ ነውና ነገሩ ኢትዮጵያውያን ወዲያው ነበር የግድቡን ግንባታ ያስጀመሩት። የግድቡ ግንባታ ሲጀመር ኢትዮጵያውን የገንዘብና የዓይነት መዋጮ፣ የጉልበት አስተዋፅኦ፣ የሙያና እውቀት አበርክቶ አድርገዋል። እናት ከመቀነቷ ፈታ ለግድቡ አዋጥታለች። ተማሪዎችም አምስትም አስር ሳንቲም ቆጥበው ለግሰዋል። የመንግሥት ሠራተኛውም ቢሆን ቦንድ ገዝቶ የአንድ ዓመት ደሞዙን እንካችሁ ብሏል። መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ተቋማትም ለግድቡ ያልተቋረጠ ድጋፍ አድርገዋል። ባለሀብቶችም እንደዛው።

መላው ኢትዮጵያውያንን ባስተባበረና ባሳተፈ መልኩ የተጀመረው የዓባይ ግድብ ግንባታ ከታችኛው የወንዙ ተፋሰስ ሀገራት የገጠመውን ጫና እየተቋቋመ፣ ለግድቡ ግንባታ አስፈላጊ የሆነውን የብድር ገንዘብ ለማግኘት ተዘዋዋሪ ክልከላና ጫና እየተደረገበት ግንባታው መቀጠሉ አልቀረም። ቀንና ሌሊት ያለእረፍት የሚከናወነው የዓባይ ግድብ ግንባታ እለት በእለት ለውጥ ይታይበት ጀመር። ሕዝቡም የግንባታውን ሂደት በንቃት ነበር የሚከታተለው። የግድቡ መጠናቀቅ ሊያመጣ የሚችለውን ትሩፋት አስቀድሞ የተገነዘበው ሕዝቡ ግድቡ የዓይኑ ማረፊያውም ጭምር ነበር ማለት ይቻላል።

በእንዲህ ሂደት የቀጠለውና እለት በእለት ለውጥ እያሳየ የመጣው የዓባይ ግድብ ግንባታ በመሃል ግን ችግር ገጠመው። በተለይ የብረትና ኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራውን የያዘው የቀድሞው ሜቴክ ድርጅት ሥራውን በአግባቡ ባለመወጣቱ በግድቡ ግንባታ ሂደት ላይ መስተጓጎል ፈጥሯል። የሚጠበቅበትን ሥራ በጊዜው ባለማከናወኑ የግንባታ ሥራ ተቋራጭ የሆነው ሳሊኒ ያለሥራ ቁጭ እንዲል አድርጎታል፤ ለኪሳራም ዳርጎታል። በዚህም ኩባንያው ለደረሰበት ኪሳራ ካሳም እስከመጠየቅ ደርሷል። በዚህ መሃል ታሪካዊ ጠላቶች ጮቤ እስከ መርገጥ ደርሰው ነበር። አጋጣሚውን ተጠቅመው የግድቡን ግንባታ ለማስቆም በብርቱ ጥረዋል።

በአዲስ አበባ ዙሪያና በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ብሎም በአማራ ክልል በተለይ ጎንደር የተቀጣጠለው አመፅ ጫናው አይሎ የኢህአዴግን መንግሥት አስወግዷል። በተለይ ኢህአዴግን ከሥልጣን በማውረድ ረገድ ከኦሮሞ ወጣት እንቅስቃሴ በተጨማሪ በራሱ በኢህአዴግ ውስጥ የነበሩ የኦህዴድና የብአዴን ፖለቲከኞች ትልቅ ታሪካዊ ሥራ ሰርተዋል። በዚህም በኢትዮጵያ አዲስ የለውጥ መንግሥት መጥቷል።

የመንግሥት ለውጥን ተከትሎ የዓባይ ጉዳይ ለጊዜው የተረሳ ቢመስልም የለውጡ መንግሥት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የፖለቲካ ጉዳዮች ከቋጨ በኋላ በቀጥታ ፊቱን ያማተረው ወደ ዓባይ ግድብ ነበር። በመጀመሪያ መንግሥት የዓባይ ግድብ የገጠመውን ችግር ለመፈተሽ ቁጭ ብሎ ገመገመ። ቀስ በቀስ ግደቡ ለገጠመው ችግር መፍትሔ በማምጣት ግንባታው ካቆመበት እንዲጀምር አደረገ። አሁንም የዓባይ ግድብ ሕዝቡ ሀብት ነውና ሕዝቡ አዲሱ የለውጥ መንግሥት ከመጣም በኋላ ለግድቡ ግንባታ የሚያደርገውን አስተዋፅኦ አላቋረጠም።

መንግሥትም ቢሆን ሊጠፋ የነበረውን የኢትዮጵያውያን ብርሃን የሆነውን የዓባይ ግድብ ነፍስ ዘርቶበት ሥራውን ባስጀመረ በመጀመሪያው ዓመት የመጀመሪያውን የውሃ ሙሌት አጠናቆ ለሕዝቡ አበሰረ። በዚሁ ዓመት የዓባይ ግድብ ሁለት ዩኒቶች ኃይል ማመንጨት መጀመራቸውንም ተናገረ። ሕዝቡም ይህን ብስራት ሲሰማ ለለውጡ መንግሥት ያለው አመኔታ ጨመረ። ወትሮም ቢሆን ለዓባይ ግድብ ግንባታ ሕይወቱንም ጭምር ለመስጠት የማይሳሳው ይህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብሥራቱን ሲሰማ ከዚህ ቀደሙ በበለጠ ለግድቡ የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚያጠናክር ቃል በመግባት ጭምር አረጋገጠ። መንግሥትም የግድቡን ሥራ ማፋጠን ቀጠለ።

አንድ ብሎ የጀመረው የዓባይ ግድብ የውሃ ሙሌት ሁለት ሶስት እያለ አምና ክረምት አራተኛውና የመጨረሻው ሙሌት መከናወኑ በክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተበስሯል። ከሰባት ወር በኋላ ደግሞ የዓባይ ግድብ ሙሉ እንደሚጠናቀቅና ኃይል እንደሚያመነጭ ተነግሯል። ይህም የሕዝቡን መፃኢ ተስፋ ያፈካ ነው። የዓባይ ግድብ መጠናቀቅ በብዙ መልኩ የኢትዮጵያውያንን ሕይወት የሚለውጥ ነው። ከኢትዮጵያውያንም አልፎ ለሌሎች የጎረቤት ሀገራት የሚተርፍ ነው። የታችኛው የወንዙ ተፋሰስ ሀገራትንም ከተደጋጋሚ ጎርፍና የደለል ሙላት የሚታደግ ነው።

በዚህ የዓባይ ግድብ ግንባታ ኢትዮጵያውያን አንጡራ ሀብታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ገንዘባቸውን፣ እውቀታቸውን ሁሉ አፍሰዋል። ግድቡ የነገ ተስፋና ብርሃናቸው ነውና የአቅማቸውን ሁሉ ለግድቡ ግንባታ አድርገዋል። ዛሬም ቢሆን የኢትዮጵያውን ለግድቡ ያላቸው አስተዋፅኦ አልቀነሰም። ይልቁንም ጨምሯል። ዛሬም የኢትዮጵያውያን ለግድቡ ግንባታ ያላቸው ድጋፍ ቀጥሏል። ነገም ይቀጥላል።

በእያንዳንዱ ኢትዮጵያውን አበርክቶ እየተገነባ ያለው የዓባይ ግድብ በቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስቴር አቶ መለሰ ዜናዊ የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦ በጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ግንባታው ሊጠናቀቅ ከጫፍ ደርሷል። ባጠቃላይ 13 ተርባይኖችን የያዘው የዓባይ ግድብ 145 ሜትር ቁመትና 1 ሺ 780 ሜትር ርዝማኔ አለው። ከ 6 ሺ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያመነጭም ይነገርለታል። በእያንዳንዱ ዩኒቶች ወይም ተርባይኖች የሚያመነጨው የኃይል መጠን ደግሞ ከ375 እስከ 400 ሜጋ ዋት መሆኑም ታውቋል።

ግድቡ 74 ቢሊዮን ሜትሪክ ቲዩብ መጠን ያለው ውሃም የሚይዝ ሲሆን ግንባታው ሲጠናቀቅ ግደቡን ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም ደግሞ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ያስቀምጠዋል። ይህም ለመላው ኢትዮጵያውያን ድርብ ድል ነው። ከግድቡ የሚመነጨው 2 ሺ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለጎረቤት ሀገራት በሽያጭ እንደሚቀርብም ይገመታል። ግድቡ በአጠቃላይ የሚይዘው የቦታ ስፋትም 1 ሺ 686 ካሬ ሜትር ነው። ግድቡ ከተገነባ በኋላ ውሃ የሚተኛበት ቦታ ርዝመት ወደኋላ 240 ኪሎ ሜትር እንደሚሆን ተገምቷል።

እንዲህ ብዙ የተወራለትና በብዙ ትግልና ሕዝብ የነቃ ተሳትፎ እየተገነባ ያለው የዓባይ ግድብ ወደ መጠናቀቂያ ምዕራፉ እየተጠጋ ነው። በለውጡ መንግሥት ቁርጠኝነትና በሰፊው ሕዝብ ተሳትፎና ያላሰለሰ ጥረት የግድቡ ግንባታ ሊጠናቀቅ እነሆ ሰባት ወራት ብቻ እንደቀሩት ተነግሯል።ሕዝቡም የኔ ነው ብሎ የሚጠራው የዓባይ ግድብ ተጠናቆ ብርሃኑን ለማየት በጉጉት እየተጠባበቀ ይገኛል። ዓባይም የዘመናት የሕዝብ ቁጭትን አስረስቶ መላው ኢትዮጵያውያንን ሊክስና ብርሃን ሊሰጥ ተዘጋጅቷል።

ታዲያ በቀሩት የሰባት ወራት ጊዚያት ውስጥ መንግሥት ከዚህ በፊት ያሳየውን ቁርጠኝነት በመድገም ግድቡ በተባለው ጊዜ ግንባታው እንዲጠናቀቅ እንደ ሁልጊዜው ሁሉ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል። የግድቡን ግንባታ ከግብ በማድረስ ሕዝቡ በጉጉት የሚጠብቀውን የልማት በረከት እንካችሁ ማለትና ማስደሰት ይጠበቅበታል። በተለይ አሁንም ያላባራውንና ከግብፅና ከሱዳን በኩል የግድቡን ሥራ ለማስተጓጎል እየተሸረበ ያለውን ሴራ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ማክሸፍ ይኖርበታል። ለግድቡ ግንባታ የተመደበውን ገንዘብም በአግባቡ ማዋል ይጠበቅበታል።

ሕዝቡም ቢሆን የዓባይ ግድብ ገና የመሠረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ ጀምሮ በገንዘቡ፣ በጉልበቱ፣ በሞራሉ፣ በእውቀቱ ወዘተ ድጋፉን በማሳየት ባለውለታነቱን አሳይቷል። ምን ያህል በጋራ የመልማት ፍላጎት እንዳለውም አስመስክሯል። የግድቡን ግንባታ ሥራም እዚህ ደረጃ ያደረሰው ይኸው ከእለት ጉርሱ ላይ ቀንሶ አስተዋፅኦ ያደረገው ድንቅ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። ዛሬም የግድቡ ሥራ ተጠናቆ ከግድቡ የሚጠብቀውን በረከት ለማግኘት አሁንም በሁለንተናዊ መልኩ ድጋፉን አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። ግድቡ ሊጠናቀቅ ጥቂት ጊዚያት ብቻ ናቸውና የቀሩት ወገቡን ጠበቅ አድርጎ ለግድቡ ሥራ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል።

የግድቡ ሥራ ከተጠናቀቀ በኋላ ዓባይ የኢትዮጵያውያን ብርሃን ይሆናል። ዓባይ ኢትዮጵያውያን በራሳቸው አቅም፣ ጉልበት፣ ችሎታና ገንዘብ እንዲህ ዓይነት ግዙፍ ፕሮጀክቶችን መገንባትና ለዓለም ማሳየት እንደሚችሉ ቋሚ ምስክር ይሆናል። ዓባይ ኢትዮጵያውያንን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል። ዓባይ ኢትዮጵያውያን በሌሎችም ወንዞቻቸው ላይ አልምተው መጠቀም እንዲችሉ መንደርደሪያ ይሆናል። ዓባይ ኢትዮጵያውያን መጪው ጊዚያቸው የፈካ ብርሃን እንዲሆንም ብርሃን ይሆናቸዋል። እውነትም ዓባይ ብርሃን ነው!!

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You