ዓባይ ግድብን እየተቃወሙ በዓባይ ግድብ ሌላ ወንዝ የመገንባት ተቃርኖ

ግብጽ በግዙፍነቱ ከዓለም አንደኛ ሊሆን የሚችል ሰው ሰራሽ ወንዝ ለመስራት እቅድ ይዛ ወደ ተግባር ገብታለች፡፡ ትልቁ ሰው ሰራሽ የግብጽ ወንዝ ውሃ ለማግኘት እንደምንጭነት ከሚጠቀማቸው የውሃ አካላት የዓባይ ወንዝ ዋነኛው ስለመሆኑም ተገልጿል፡፡ ለመሆኑ የግብጽ ሰው ሰራሽ ወንዝ የመስራት እውነታ የዓባይ ወንዝና ግድብ ላይ ካላት አቋም አንጻር እንዴት ማየት ይቻላል?

በዓባይ ውሃ ፖለቲካ ላይ ሰፊ ጥናት ያደረገው ሃጋይ ኤርሊክ፤ የኢትዮጵያና ግብጽ ግንኙነት ከጥንት ጀምሮ ከውሃ ጋር የተሳሰረ ነው ይላል፡፡ በጥንት ዘመናት በተነሱ የተፋሰሱ ኃያላንም ሆነ የመካከለኛው ምሥራቅ ኃይሎችና የ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቅኝ ገዢዎች የዓባይ ተፋሰስን ጠቅልለው ለመያዝ ያደረጉት ሙከራ ኢትዮጵያ ላይ ሲደርስ ከሽፏል። ይህ በ20ኛውና 21ኛው ክፍለ ዘመንም መልኩን እየቀያየረ ቀጣይነት ያለው ሙከራ ሆኖ ቀጥሏል።

የዓባይ ንጉሶች ሚዲያ ባለቤትና የዓባይ ጉዳይ የኢትዮጵያ ተሟጋች ዑስታዝ ጀማል በሽር እንደሚሉት፤ ግብጽ የዓባይ ወንዝን በባህር መልኩ በመስህብነት ደረጃ ከፍ ያለ ቦታ እንዲኖረው አድርጋ ናይል ሲባል ግብጽ እንዲባል፤ ግብጽ ሲባል ናይል እንዲባል ማድረግ የሚያስችል የቱሪዝም መስህብ ሰርታ ለዓለም አሳይታለች። ይህንን ከማስቀጠል አኳያ የዓባይን ውሃ በመጠቀም አሁንም በዓለም አንደኛ ሊባል የሚችል ሰው ሰራሽ ወንዝ እየሰራች ነው።

እንደ ዑስታዝ ጀማል ማብራሪያ፤ አስገራሚው ነገር ለግብጽ አብዛኛው የውሃ መጠን የሚሄድላት ከኢትዮጵያ ሲሆን፤ 86 ነጥብ አምስት በመቶው ከኢትዮጵያ የሚሄድ ውሃ ላይ ተንተርሶ የሚሰራ ወንዝ ግን ኢትዮጵያን ያማከለ፣ ኢትዮጵያን ያላማካረ መሆን ነበረበት። ይህንን ሥራ ሊያስቀጥሉም ሆነ ላያስቀጥሉ የሚችሉ ነገሮች ይፈጠራሉ ወይ ተብለው ከኢትዮጵያ ጋር ቢያንስ ተወያይቶ ተደጋግፎ መሥራት ተገቢ ነበር። ነገር ግን የግብጽ የሁልጊዜ አካሄድ “ይህንን ውሃ በምንም መልኩ አላጣውም። የራሴም ነው። ምክንያቱም ናይል የኔ ስጦታ ነው። ግብጽ ራሱ የናይል ስጦታ ናት” ብላ ስለምታስብ ኢትዮጵያን በታሳቢነት የምታስቀምጥበት ሁኔታ የላትም።

ግብጽ ዓባይን በመጀመሪያ ከምንጩ የመቆጣጠር አባዜ አለባት የሚሉት ዑስታዝ ጀማል፤ በዚህም እስከ ጉንደት ጦርነት ውስጥ እንዲገቡ ማድረጉም የዚህ ማሳያ እንደሆነ ይገልጻሉ። ይህ ስላልተሳካ ከዛ በኋላ በተለያዩ ዘዴዎች ይህንን ውሃ ማንም ሳይነካው ወደ ግብጽ ኮለል ብሎ እንዲፈስ የሚያደርጉ የተለያዩ ውሎችን ለማስፈረም ሙከራ ማድረጋቸውንም ያነሳሉ።

አሁንም በዚህ አይነት እሳቤ ውስጥ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በማስፈራራትም ይሁን በተለያዩ የፖለቲካ ሴራ እንዲሁም በተለያዩ ጫናዎች የዓባይን ወንዝ ማንም አይነካብንም ብለው ስለሚያስቡ ኢትዮጵያን ሂሳብ ውስጥ እየከተቷት አይደለም ነው ያሉት።

ዑስታዝ ጀማል እንደሚሉት፤ ይሄ ጉዳይ መቀጠል የለበትም። የዓባይን ውሃ ተንተርሶ በግብጽ የሚሰሩ ማናቸውም ትላልቅ ፕሮጀክቶች በማንኛውም ሁኔታ ነገ ኢትዮጵያ በምትሰራቸው ሥራዎች ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው የሚሆነው። ምክንያቱም እነሱ በሚሰሩት የውሃ ልማት ላይ ትንሽም እክል ገጠማቸው በሚባልበት ወቅት ኢትዮጵያ ከምትሰራው የመስኖ ስራ ጋር ሊያያይዙ ይችላሉ። በአጋጣሚ በተወሰነ ደረጃ እንኳን ውሃው ቢቀንስ እንደምክንያት የሚያስቀምጡት አሁንም ኢትዮጵያን ነው። ስለዚህ እንዲህ አይነት ትላልቅ ፕሮጀክቶች ሲሰሩ ኢትዮጵያን ማማከር ይገባል።

“ኢትዮጵያ ውሃ አመንጪ ሀገር ሆና ግድብ ስትሰራ እኛን ሳታማክሩ አትሰሩም እያሉን፤ እነርሱ ደግሞ የታችኛው ተፋሰስ ሆነው ምንም ነገር ሳያማክሩን ሊሰሩ የሚችሉበት ሁኔታ ሊኖር አይችልም። ተቃርኖ ያለው አካሄድ ነው እየሄዱ ያሉት” በማለት ነው ዑስታዝ ጀማል የሚናገሩት።

ግብጽ አዲስ ለምትገነባው ግዙፉ ሰው ሰራሽ ወንዝ እንደ ምንጭነት ከምትጠቀማቸው መካከል አንዱ የዓባይ ወንዝ እንደመሆኑ የዓባይ ግድብ ላይ የምታንጸባርቃቸው ክርክሮችና ጫናዎች የራሷን ጥቅም ብቻ ከማየት የመጣ መሆኑን ዑስታዝ ጀማል ይናገራሉ። “ግብጾች ትልቅ ወንዝ ለመስራት ከዩጋንዳ ብቻ የሚሄድላቸው ውሃ በቂ እንዳልሆነ ያውቁታል። ምክንያቱም 15 በመቶ ብቻ ነው ከዛ የሚሄደው። የተረፈው ውኃ በሙሉ የሚሄደው ከኢትዮጵያ ነው። ስለዚህ እዛ ላይ ተንተርሰው ይህን ያክል ትልቅ ወንዝ ሲሰሩ ኢትዮጵያን አለማማከር ተገቢ አይደለም” በማለት ይገልጻሉ።

ኢትዮጵያን ማማከር ቀርቶ በተቃራኒው ኢትዮጵያ ይሄን ውኃ እንዳትጠቀም እየሞገቱ መሆናቸውንም ዑስታዝ ጀማል ያነሳሉ። “ሌሎች ፕሮጀክቶቻችን የምንሰራው ኢትዮጵያን ሳናማክር፤ ሳንጠይቃት ነው” የሚል እሳቤ ውስጥ ስላሉ ምን ያህል ራስ ወዳድ እንደሆኑና የራሳቸውን ጥቅም ብቻ እያዩ የሚሰሩ መሆኑን በግልጽ ያሳያል ብለዋል።

እንደ ዑስታዝ ጀማል ገለጻ፤ ከኢትዮጵያ የሚመነጨው ውሃ ላይ ኢትዮጵያ ግድብ ስትሰራ እኛን ልታማክረን ይገባል፤ ለኤሌክትሪክ ማመንጫነት በቋሚነት ሊያገልግል የሚችለውንና ወደ ግብጽ የሚፈሰውን ውሃ እንኳን የሚያዝበትን አግባብ እኛ ነን መወሰን ያለብን፤ በ10፣ በ20 ዓመት ይለቀቅ የሚለውን የግድቡን ሂደት ራሱ እኛ ነን መወሰን ያለብን የሚሉበት አግባብ አለ። እነርሱ ግን አስዋን ግድብን ሲገድቡ ኢትዮጵያን አላማከሩም፤ አሁንም ደግሞ ይሄንን የሚያክል ትላልቅ ወንዞችና ሌሎችንም ነገሮች በሚሰሩበት ወቅት እያማከሩን አይደለም። ይሄ ምን ያህል በራስ ወዳድነት ዓለም ውስጥ ያሉ እንደሆነና የኢትዮጵያንም ሀቅ በደንብ የሚያሳይ ነው።

የዓባይ ውሃ ጉዳይ ተመራማሪው ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ በበኩላቸው፤ ግብጽ የአስዋንን ግድብ ጨምሮ መሠረታቸው በዓባይ ውሃ ላይ የሆኑ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በራሳቸው በረሃማ ግዛት ላይ መስራቷን ይጠቅሳሉ። አሁንም በዚሁ መልክ የራሷን ወንዝ መገንባቷን ቀጥላለች ብለዋል።

ግብጽ አሁንም የወሰን ተሻጋሪ የውሃ ባህሪያትን በትክክል አልተረዳችም የሚሉት ተመራማሪው፤ ግብፅ በነፃ በምታገኘው ውሃ ተጨማሪ ግድቦችን ሰርታ ውሃ ማቆየት እንደምትሻው ሌሎች ህዝቦችና ሀገራትም ውሃቸውን እንዳይጠቀሙ ማድረግ እንደሌለባት ይመክራሉ። በወሰን ተሻጋሪ ውሃ አጠቃቀም ዙሪያ ኢትዮጵያ፤ ግብጽና ሌሎች የተቀሩ ሀገራት ተሰብስበው የጋራ ጥቅምን ሊያስጠበቅ የሚችል ፖሊሲ ቀርፀው መስራት እንዳለባቸውም ያመላክታሉ።

የወሰን ተሻጋሪ ውሃዎች የኢትዮጵያ ልማት ግብፅን ለመደገፍ፣ የግብፅ ልማት ደግሞ ኢትዮጵያን ለመደገፍ ዓላማ መዋል አለባቸው። ይህ በግብፅ ውስጥም ሆነ በኢትዮጵያ ያለው የተሻለ ነገር ምን እንደሆነ ለመለየትና በጎ ተግባራትን እርስበርስ ለመመጋገብ ያስችላል ነው ያሉት። ግብጽ በእንዲህ መልኩ ተረድታ መስራት አለባት ሲሉም ገልጸዋል።

ግብጽ ወንዙን ለመስራት ኢትዮጵያን እስካላስፈቀደች ድረስ፤ ኢትዮጵያ ደግሞ በራሷ ሀብት ላይ ግድብም ሆነ ሌላ ነገር ለመስራት የታችኛውንም ሆነ የላይኛውን ተፋሰስ ሀገራት ፍቃድ ማግኘት የለባትም የሚለውን ነገር እያጎላው መሆኑን ያሳያል ያሉት ደግሞ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ናቸው።

እንደ አምባሳደር ዲና ገለጻ፤ ከዚህ ቀደም ግብጽ በዓባይ ውሃ ስትጠቀም ቆይታለች። በርካታ የልማት ሥራዎችን መስራት ችላለች። ይህ የሆነው ከኢትዮጵያና የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት በተገኘ ፍቃድ አይደለም። ያለ ፈቃድ የራሷን ወንዝ እስከገነባች ድረስ በዛው ልክ ኢትዮጵያንም በዓባይ ግድብ ጉዳይ መቃወምና መከራከሯ ተገቢ አይደለም።

ዑስታዝ ጀማል በበኩላቸው፤ “ግብጽ በኢትዮጵያ ላይ የምታሳየው አቋም ትክክል አይደለም። የራሷን ግዙፍ ልማት ባካሄደች ቁጥር በዚያው ልክ ያንን ሊያግዝ ይችላል ብላ የምታምናቸው ኢትዮጵያ ላይ የሚደረጉ ብዙ የልማት አቅጣጫዎችንም ልትደግፍና ልታግዝ ይገባል” ብለዋል።

ግብጽ የዓባይን ውሃ በመጠቀም ለራሷ ግዙፍ ልማት እያከናወነች ኢትዮጵያ ላይ የምታሳየው አቋም ትክክል አይደለም የሚሉት ዑስታዝ ጀማል፤ በእርግጥም ግብጽ የፈለገችውን የልማት አይነት እንድትሰራ ኢትዮጵያ ፈጽሞ እንቅፋት ሆናባት እንደማታውቅ፤ የአስዋን ግድብ ሲገደብ ለምን የሚል ጥያቄ ያቀረበችበት ሁኔታ እንደሌለ፤ በተለያዩ የግብጽ የልማት ሂደቶች ውስጥ ኢትዮጵያ ምንም ቦታ ላይ ጣልቃ ገብታ ስትናገር እንደማትታይ ያብራራሉ። ስለዚህ የኢትዮጵያ ልማት፤ የኢትዮጵያ መጠቀምና በውሃው ላይ የተለያዩ ልማቶችን መስራት ግብጾቹን ሊያስደስታቸው ይገባል ነው ያሉት። ግብጾች በተባበረ አካሄድ ከኢትዮጵያ ጋር የሚሰሩ ከሆነ እንዲያውም ካሰቡት በላይ ውሃውን የበለጠ ማጎልበት የሚቻልባቸው ሁኔታዎች እንዳሉም ነው የገለጹት።

ዑስታዝ ጀማል እንደሚያብራሩት፤ ግብጾች በኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ላይ ምንም አይነት አሻራቸውን አላሳዩም። የኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ ላይ የምትሰራው ስራ ግን በውኃው ላይ በጎ የሆነ ተጽዕኖ አለው። ምክንያቱም ዛፎች በበዙ ቁጥር የአየር መስተካከል ይመጣል። የአየር መስተካከል ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የዝናብ ምንጭ ይሆናል። ስለዚህ ዝናብ በመጣ ቁጥር አሁንም የሚሄደው ወደ ግብጽ ከመሆኑ አንጻር በተዘዋዋሪ ግብጽ ተጠቃሚ ናት። ስለዚህ በእንደዚህና መሰል የሆኑ የልማት ሂደቶች ውስጥ ግብጽ ብትሳተፍ ውሃዋን የበለጠ ጥሩ ሆኖ እንዲሄድላት የማድረግ ሁኔታ ይፈጠራል።

በውሃ ፖለቲካ ላይ የሚጽፉ ምሁራን እንደሚገልጹት፤ ከሆነ ድንበር ተሻጋሪ የሆኑ የውሃ ሀብቶችን ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር በጋራ ከመጠቀም አኳያ ወደ ትብብርም ሆነ ወደ ግጭት ሊገቡ ይችላሉ። የተለያዩ የህግ ስምምነቶች ላይ በመድረስና ፖለቲካዊ መፍትሄ በማምጣት ሀገራት ወደ ስምምነቱና በጋራ ወደ መስራቱ መምጣት አለባቸው።

አዲሱ ገረመው

አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You