“አልትራ-ፕሮሰስድ” ምግቦችና በዓለም ሕዝብ ጤና ላይ የሚያስከትሉት ጠንቅ

በእንግሊዝኛው “አልትራ-ፕሮሰስድ” ምግቦች ይባላሉ። በፋብሪካዎች ውስጥ ተመርተው እና ተቀነባብረው በየሱቁ መደርደሪያ ላይ የምናገኛቸው የታሸጉ ምግቦች ናቸው።

እነዚህ ምግቦች የልብ ሕመም፣ ካንሰር እና ጭንቀትን እንደምሳሌ በመውሰድ ከ30 በላይ የጤና ችግር ያመጣሉ የሚል ምርምር መኖሩን ቢቢሲ ዘግቧል።

በዩናይትድ ስቴትስና በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኙ ነዋሪዎች ከሚመገቡት ምግብ 50 በመቶውን እኒህ ምግቦች ይይዛሉ። አልፎም ኢትዮጵያን ጨምሮ በተቀረው ዓለም አሁን አሁን እየተለመዱ መጥተዋል።

እነዚህን ምግቦች በአንድ ቃል መግለጽ ከባድ ነው። ነገር ግን ብዙውን ጊዜ ቤት ውስጥ የማንጠቀምባቸውን ንጥረ ነገሮች በውስጣቸው የያዙ ናቸው።

አብዛኞቹ ኬሚካል ናቸው። ማቅለሚያ እና ማጣፈጫ ተካቶባቸው ምግቡ አምሮ እና ተውቦ እንዲሁም ጣፍጦ እንዲቀር ብለን ይሆናል። ጣፋጭ እና ኃይል ሰጪ መጠጦች፣ ከረሜላ እና መሰሎቹ፣ ከዶሮ ሥጋ የሚሠሩ ምግቦችን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል።

ነገር ግን እንዲህ በቀለማት ባሸበረቀ መጠቅለያ ታሽገው የሚመጡትን ብቻ ሳይሆን እንደ ዳቦ፣ የቁርስ ምግቦች እና እርጎን በጥንቃቄ መመልከት ያሻል።

አልትራ ፕሮሰስድ የሚባሉ ምግቦችን ከሌሎች የፋብሪካ ምግቦች የሚለዩት በምን እንደሆነ ለማወቅ በአራት ምድብ እንደሚለዩ ቢቢሲ ዘግቧል።

የመጀመሪያው ‘አንፕሮሰስድ’ (ተፈጥሯዊ) የሚባል ሲሆን፤ ሁለተኛው በትንሹ ‘ፕሮሰስ’ (በተወሰነ ለውጥ የተደረገበት) ነው። ሦስተኛው ምድብ ‘ፕሮሰስ’ (በምርት ሂደት ለውጥ የተደረገበት) ነው፤ አራተኛው ደግሞ አልትራ ፕሮሰስድ ወይም በከፍተኛ ደረጃ በፋብሪካ የምርት ሂደት ለውጥ የተደረገበት የሚባል ነው።

ፍራፍሬዎች፣ አትክልት፣ ለውዝ እና እንቁላል ፕሮሰስድ ከሚባሉ የምግብ ዓይነቶች መካከል ናቸው። ምግብ ለማብሰል የሚሆኑ አንዳንድ ሰብሎችም ከእነዚህ መካከል ይካተታሉ።

ለምሳሌ ከስንዴ ዱቄት፣ ውሃ፣ ጨው እና እርሾ የተሠራ ዳቦ ‘ፕሮሰስድ’ ምግብ ነው የሚባለው። ነገር ግን ይህ ዳቦ ቀለሙን ለመቀየር የሚሆን ንጥረ ነገር አሊያም ብዙ ጊዜ እንዲቆይ ማድረጊያ ኬሚካል ከተጨመረበት ‘አልትራ-ፕሮሰስድ’ ምግብ ይሆናል ማለት ነው።

ቢያንስ አምስት ዓይነት ንጥረ-ነገሮች የተካተቱበት ምግብ አልትራ-ፕሮሰስድ የመሆን ዕድሉ ከፍተኛ ነው ይላሉ የናቫራ ዩኒቨርሲቲው የኅብረተሰብ ጤና ፕሮፌሰሩ ማይራ ቤስ-ራስትሮሎ።

እነዚህ ምግቦች ብዙውን ጊዜ በርካታ ጨው ያላቸው፣ ስኳር የሚበዛባቸው እና የተጣራ ስብ የሚታከልባቸው ናቸው። በዩናይትድ ኪንግደም እና በአንዳንድ ሀገራት አምራቾች እነዚህን ንጥረ-ነገሮች ማሸጊያው ላይ የመፃፍ ግዴታ አለባቸው። አንዳንድ ምግቦች ገና “ትኩስ” ቢሆኑም ቶሎ እንዳይበላሹ የሚያደርግ ንጥረ-ነገር ይጨመርባቸዋል።

ተጠቃሚዎች ምግቦቹን ሲገዙ የሶዲየም ቤንዞየት፣ ናይትሬት እና ሰልፋይት መጠናቸውን እንዲመረምሩ ይመከራሉ። ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካ ያሉ ሰዎች አልትራ ፕሮሰስድ ምግቦችን በስፋት በመጠቀም ይታወቃሉ።

በአውሮፓውያኑ 2023 ብቻ የአሜሪካ አዋቂዎች ከተመገቡት ካሎሪ 58 በመቶው እነዚህ ምግቦች ናቸው። ሕፃናትም እንዲሁ ከተመገቡት ምግብ 66 በመቶው አልትራ ፕሮሰስድ ምግብ ነው። ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ሕፃናት እና አዋቂዎች ስንመጣ ይህ ቁጥር በአንድ በመቶ ብቻ ነው የሚቀንሰው።

እስያ ስንሄድ ደግሞ ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን ከ20 እስከ 30 በመቶ ምግባቸው ይህ ነው። እንደ ብራዚል እና ቺሊ ያሉ የደቡብ አሜሪካ ሀገራትም ተመሳሳይ መጠን ያለው አልትራ-ፕሮሰስድ ምግብ ይወስዳሉ። የደቡብ አፍሪካ አሀዝ 39 በመቶ ነው።

የዩኬ መንግሥት በአውሮፓውያኑ 2018 ጣፋጭ መጠጦች ላይ በጫነው ታክስ ምክንያት በርካታ አምራቾች የስኳር መጠናቸውን ቀንሰዋል። በ2023 ኮሎምቢያ ፕሮሰስድ ምግቦች እና ስኳር የሚበዛባቸው መጠጦች ላይ የ10 በመቶ ቀረጥ ጥላለች።

ከመጠን ያለፍ ውፍረት የሚያጠቃቸው በርካታ ሕፃናት ያሉባት ቺሊ በ2016 ባወጣቸው ሕግ መሠረት አምራቾች በርካታ ካሎሪ፣ ስኳር እና ስብ ያለባቸው ምግቦች ላይ ማስጠንቀቂያ የመፃፍ ግዴታ አለባቸው።

አልፎም ለሕፃናት የሚሆኑ ምግቦች ነገር ግን ከፍተኛ የስኳር፣ ጨው እና ካሎሪ መጠናቸው ከፍተኛ የሆኑ ምግቦችን ማስታወቂያ ከልክላለች። ነገር ግን አሁንም በቺሊ ከመጠን ያለፈ ውፍረት ያላቸው ሕፃናት ቁጥር እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አልመጣም።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You