ተማሪዎች ከመደበኛው ትምህርታቸው ባሻገር በተጓዳኝ ትምህርትም ይሳተፋሉ። በተለይ ከመደበኛው ትምህርት ጎን ለጎን እየተሰጠ ያለው የተጓዳኝ ትምህርት በአግባቡ በሚካሄድባቸው የትምህርት ተቋማት የተማሪዎች የክበባት ተሳትፎ የጎላ ነው።
በትምህርት ዓለም ውስጥ በሚገባ እንደሚታወቀውና የሥነትምህርት ምሁራን እንደሚያረጋግጡት ተማሪዎች ከመደበኛው የዕለት ተዕለት ትምህርታቸው በተጓዳኝ በተቋሙ ውስጥ ያላቸውን ትርፍ ጊዜ የተለያዩ ተሳትፎዎችን ማድረግ እንዳለባቸው ይነገራል። ለዚህ አመቺ እንዲሆን በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ትምህርታዊ ክበባት ተዘጋጅተዋል።
ከነዚህ ክበባት ባለፈ እንደ ወይዘሮ ስህን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ አይነት የትምህርት ተቋማት ውስጥ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ጨምሮ የሕይወት ክህሎት ተሞክሮ፣ የአቻ ለአቻ ውይይት፣ የበጎ አድራጎት ስራዎችና የመሳሰሉት በተማሪዎች እንደሚከናወኑ ከተቋማቱ ከወጡ መረጃዎች መረዳት ይቻላል።
በትምህርት ተቋማት ውስጥ ባሉ ክበባት አባላት ከትምህርት ቤቱ ባለፈም ሌሎች አካባቢያዊና ሰብአዊ ተግባራትን ያከናውናሉ። ከእነዚህም ውስጥ በወይዘሮ ስህን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የተከናወነው ይጠቀሳል። በኮሌጁ አማካኝነት ለተፈናቃይ ወገኖች የአልባሳት ድጋፎች በአብዛኛው የተሰበሰቡት ወይም የተዘጋጁት በታታሪ የክበቡ አስተባባሪዎች እና አባላት ሰልጣኞች ነው። ይህም እንደጥሩ ማሳያ ይጠቀሳል።
ክበባት አባላት ተማሪዎች በየጊዜው እርስ በርስ ልምድ እና ተሞክሮ የሚለዋወጡባቸው መለስተኛ የምክክር መድረኮች መሆናቸው፤ ተማሪዎች ከመደበኛው ትምህርታቸው ውጪ የሆነውን ጊዜያቸውን በትምህርት ቤታቸው ውስጥ በፍቅር እያሳለፉ በተለያዩ እንቅስቃሴዎች ተግባራት እንዲሳተፉ እድል ፈጥሯል። በተጓዳኝ ትምህርቶች (ክበባት) ውስጥ የሚያልፉ ተማሪዎች በስነ-ምግባር፣ በሞራል፣ በግብረ-ገብነት እና በማኅበራዊ ክህሎታቸው ከፍተኛ እመርታ እንደሚታይባቸው በተለያዩ ጥናቶች ተረጋግጧል። በተጓዳኝ ትምህርት ያልተደገፈ መደበኛ ትምህርትም የራሱ የሆነ ክፍተት እንደሚኖረው በባለሙያዎች ተጠቁሟል።
ትምህርት ሚኒስቴር የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ስታንዳርድ 2001 ዓ∙ም በሚል ርእስ ወደ ስራ ያስገባው ሰነድ እንደሚያመለክተው ፕሮግራሙ በትምህርት ቤቱ ዕቅድና አቅም መሰረት በክፍል ውስጥ የሚሰጡትን ትምህርቶች በሚያግዝ መልኩ ከክፍል ውጪ የሚሰጥ ሲሆን፤ ልዩ ልዩ ክበባት እና ሌሎች ትምህርታዊ እንቅስቃሴዎችን በማቋቋም ተማሪዎች ባላቸው ዝንባሌ፣ ፍላጎትና ችሎታ እንዲደራጁ ማድረግ ያስፈልጋል።
ይህም ተማሪዎች እንደፍላጎታቸው በተለያዩ ክበባት እና ትምህርታዊ ፕሮግራሞች እንዲሳተፉ ከተደረገ ትርፍ ጊዜያቸውን በተለያዩና ጠቃሚ በሆኑ ስራዎች እንደ ፍላጎታቸው የመስራት ዕድል ስለሚያገኙ በክፍል ውስጥ ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት ያዳብራሉ። በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ዘመናዊ ተውኔት በተጀመረበት ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ማርቺንግ (ማርች) ባንድም የተመለከትነው ይሄንኑ ነው።
በሌላ በኩል በትምህርት ቤት ቆይታቸው ከጓደኞቻቸውም ሆነ ከመምህራኖቻቸው በሚያገኙት ልምድ፣ ከትምህርት ቤቱ ከሚሰጥ መመሪያና በትምህርት ቤቱ በሚደረጉ ልዩ ልዩ እንቅስቃሴዎች የወደፊት ዝንባሌያቸውን ሊያዳብሩላቸው የሚችሉ ክህሎቶችን ማግኘት ይችላሉ። ስለሆነም ከመማር ማስተማሩ በተጓዳኝ የሚሰጠውን ፋይዳ ግምት ውስጥ በማስገባት የተማሪዎች እድገትና ጥንካሬ እየታየ በሳምንት ከአራት ሰዓት በማይበልጥ ጊዜ ውስጥ ፕሮግራሙ መካሄድ አለበት።
ከምዕራብ ጎጃም ዞን ይልማና ዴንሳ ወረዳ፣ ድዋሮ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ በትምህርት ቤቱ በርካታ ክበባት ያሉ ሲሆን፣ አንዱም በርካታ ተማሪዎች የሚሳተፉበትና ብዙዎችም ከትምህርት ሕይወታቸው በኋላ ተሰማርተውበት የሚገኘው የቋንቋና ሚኒ ሚዲያ ክበብ ነው።
የኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት “ሀ″ ተብሎ በተጀመረበት ታሪካዊው የዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤቱ የቋንቋና ሚኒ ሚዲያ ክበብ ተጠሪ መምህር በለጠ መርከቡ በአካባቢው ኮሚዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት አማካኝነት እንደሚገልፁት በትምህርት ቤቱ ከስልሳ በላይ አባላት በቋንቋና ሚኒ ሚዲያ ክበብ የሚሳተፉበት ጊዜ ያለ ሲሆን ክበቡ ተማሪዎች የሥነ ጽሑፍ፣ የሥነ ስዕልና የውዝዋዜ ችሎታቸውን ለማዳበር ጉልህ ሚና አለው። ተማሪዎች በየአካባቢያቸው ያዩትንና የተመለከቱትን ክስተት በዜና መልክ በማቅረብ የቋንቋ ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ ያስችላቸዋል።
ይህ በሁሉም ትምህርት ቤቶች በሚሰጡ የቋንቋና ሥነጽሑፍ፤ የድራማና ሥነጽሑፍ ወዘተ ክበባት አስተባባሪዎች የሚሰጥ አስተያየት ሲሆን፤ የክበቡ አባላትም በሕይወት ዘመናቸው ወደ እነዚሁ ሙያዎች ተስበው ለሕይወታቸው ጥሪ ምላሽን ሲሰጡ ይስተዋላሉና የክበባት አስተዋፅኦ እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ለአራተኛ ጊዜ ባካሄደው ዓመታዊ ሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሰብአዊ መብቶች ምስለ ችሎት ውድድር ከክልል እና ከከተማ አስተዳደሮች ትምህርት ቢሮ አስተባባሪዎች ጋር የካቲት 14 እና 15 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ የማስጀመሪያ ውይይት ባካሄደበት ወቅት “ሰብአዊ መብቶችን በተጓዳኝ መንገድ ለማስተማር ብሎም በሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች መካከል ለሚካሄደው የሰብአዊ መብቶች የምስለ ችሎት ውድድር መሠረት ለመጣል የሰብአዊ መብቶች ክበባትን መመሥረት ስለሚኖረው ፋይዳ፤ እንዲሁም የተጓዳኝ ትምህርት ምንነት፣ ጠቀሜታ፣ አደረጃጀት እና አተገባበርን በተመለከተ ከትምህርት ሚኒስቴር″ ጋር መወያየትና የጋራ መግባባት ላይ መድረስ የሚገባ መሆኑን መግለፁም የዚሁ የተጓዳኝ ትምህርት አስፈላጊነት ላይ አፅንኦትን የሚሰጥ ነው።
“በኢሰመኮ አዘጋጅነት በየዓመቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሰብአዊ መብቶች የምስለ ችሎት ውድድር ምናባዊ በሆነ የሰብአዊ መብቶች ጉዳይ (hypothetical case) ላይ በመነሳት ተማሪዎች የአመልካች እና ተጠሪ ወገንን በመወከል የጽሑፍ እና የቃል ክርክር የሚያደርጉበት፤ ከሞላ ጎደል የመደበኛ ፍርድ ቤት የክርክር ሥርዓትን የሚከተል ወድድር ነው። በተወዳዳሪ ተማሪዎች እና በትምህርት ቤት ማኅበረሰብ ዘንድ የሰብአዊ መብቶች ዕውቀትን እና ክህሎትን ለመገንባት፣ አመለካከትን እና ባሕርይን ለመቅረጽ ያለመ እንደ ሆነ ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ከሳምንት በፊት ሰኞ፣ መጋቢት 2 ቀን 2016 ዓ.ም “የዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ማርሽ ባንድ″ በሚል ርእስ ለንባብ ባበቃነው ጽሑፍ ከ1977 ዓ.ም. እስከ 2011 ዓ.ም. ድረስ ከባህር ኃይል የክላርኔት ተጫዋችነት እስከ የመከላከያ የሙዚቃ ትምህርት ክፍል መምህርነትና ኃላፊነት የቆዩትን፤ ለ40 ዓመታት ተቋርጦ የነበረውን የዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን የማርች ባንድ በማስቀጠል የትምህርት ቤቱ ማርቺንግ ባንድ አሰልጣኝ የሆኑትን በራሳቸው ተነሳሽነት፣ ሙሉ የሙዚቃ መሳሪያዎችን በነፃ በማቅረብ በአሰልጣኝነት እየሰሩ ያሉትን የቀድሞው የባህር ኃይል ባልደረባና በኋላም የአገር መከላከያ አባል (ጡረታ እስከወጡበት 2011 ዓ∙ም ድረስ) የሆኑትን፣ ሌ/ኮሎኔል ሲሳይ ፍቃዱን ይዘን መውጣታችን ይታወሳል። ዛሬ ደግሞ የሳቸው ፍሬዎች የሆኑትን ሁለት የዳግማዊ ምኒልክ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ይዘን ቀርበናል።
በተለያዩ መገናኛ ብዙሀን ሲገለፅ እንደቆየው፣ እኛም በስፍራው ተገኝተን በማየት እንዳረጋገጥነውና ለንባብ እንዳበቃነው ለረዥም ዓመታት በአጠቃላይ የሙዚቃ መምህርነትና ኃላፊነት ያገለገሉት ሌተና ኮሎኔል፣ በአብዛኛው ለፕሮቶኮል ሥራዎች የሚለውንና በሠልፍ ትርዒት መልክ የብራስ፣ ውድዊንድ፣ ሳክስፎን፣ ክላርኔት፣ ፍሉት፣ ትራምፔት፣ ዩፎኒየም፣ ሱዛፎንና ሌሎች የሙዚቃ መሣሪያዎች ጥቅም ላይ ውለውና በርካታ ባለሙያዎች ተቀናጅተው በጎዳና ላይ የሚሠሩትን የማርቺንግ ባንድ ትዕይንት በትምህርት ቤቶች ያንሰራራ ዘንድ በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት የበጎ ፈቃድ ሥራቸውን በመጀመር ወጣቶችን ለፍሬ አብቅተዋል። የዛሬዎቹ እንግዶቻችንም የዚሁ የኮሊኔሉ ልፋትና በጎፈቃደኝነት ውጤቶች ናቸው።
ከመደበኛ ትምህርታቸው ጎን የማርች ባንድ የሙዚቃ መሣሪያዎችንና የተለያዩ የሙዚቃ ሥልቶችን በንድፈ ሐሳብና በተግባር እየሰለጠኑ ካሉት ተማሪዎች መካከል በመጀመሪያ ያነጋገርነው ወጣት ናትናኤል ሠለሞን ይባላል። በአሁኑ ሰዓት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ነው። ወደ ዩኒቨርሲቲ ሊገባ የቻለውም ባለፈው ዓመት የማትሪክ ፈተና ጥሩ ውጤት በማምጣቱ ሲሆን፤ አጥጋቢ ውጤት ያመጣውም እዚሁ አሁን ባገኘነውና በትንፋሽ መሳሪያው ልምምድ እያደረገ ባለበት ዳግማዊ ምኒልክ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው።
ናትናኤል እንደሚለው እኔ የዚሁ ትምህርት ቤት ተማሪ ነበርኩ። ማትሪክን የወሰድኩት እዚሁ ነው። ጥሩ ውጤት ያመጣሁትም እዚሁ ተምሬ ነው። ለዩኒቨርሲቲ ያበቃኝም ይሄው ዳግማዊ ምኒልክ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው። ወደዚህ ማርቺንግ ባንድ ልቀላቀል የቻልኩትም የዚሁ ትምህርት ቤት ተማሪ በመሆኔ ነው። በኮሎኔል ሲሳይ አማካኝነት በነፃ እየተሰጠ ያለውን ስልጠና ላገኝና ልመረቅ የቻልኩትም በዚሁ ትምህርት ቤት ተማሪነቴ ነው። አሁንም እዚህ ልምምድ ሳደርግ ልታገኘኝ የቻልከው ከትምህርት ቤቴና ኮሎኔል ሲሳይ ጋር ያለኝ ግንኙነት ያልተቋረጠ በመሆኑ ነው።
የትንፋሽ መሳሪያውን ይዞ ልምምድ ሲያደርግ ያገኘነው ተማሪ ናትናኤል “ትምህርት እና የሙዚቃ መሳሪያ ልምምድ እንዴት ነው፤ አብረው ይሄዳሉ?″ ብለነውም “ምንም ችግር የለውም። በደንብ አብረው ይሄዳሉ። ዋናው ነገር በእቅድ፣ በፕሮግራም መመራቱ ላይ ነው። እኔ ከ11ኛ ክፍል ጀምሮ ነው የምከታተለው፤ እስካሁን ምንም ያጋጠመኝ ችግር የለም። ሁሉንም በእቅድና ፕሮግራም ነው የማስኬደው። በመሆኑም፣ ማትሪክም ላይ ሆነ አሁንም የዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን እየተከታተልኩ ባለሁበት ሰዓት ምንም የገጠመኝ ችግር የለም። ሁሉንም በሚገባ እየሰራሁ ነው ያለሁት″ በማለት መልሶልናል።
ለሙዚቃ መሳሪያዎች ያለውን ፍቅር በተመለከተም ከልጅነቱ ጀምሮ የሙዚቃ መሳሪያዎችን መጫወት እንደሚያስደስተውና ያንን ፍላጎቱንም በኮሎኔል ሲሳይ አማካኝነት እውን እያደረገ እንደ ሆነ አጫውቶናል።
ሌላዋ በእለቱ በማርቺንግ ባንድ ማሰልጠኛው መለስተኛ አዳራሽ አግኝተን ያነጋገርናት ተማሪ ሥምረት ሙላቱ ስትሆን፤ እሷም ዘንድሮ 12ኛ ክፍል ማትሪክ ተፈታኝ እንደሆነች አጫውታናለች።
እንደ ተማሪ ሥምረት ከሆነ የሌተናል ኮሎኔል ሲሳይ ፍቃዱ ውለታ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። የትም የማይገኝ፣ በእንደነዚህ አይነት የሙዚቃ መሳሪያዎች የመሰልጠን እድል ማግኘት መታደል ሲሆን፤ ተማሪ ሥምረት አስቀድማም ፍላጎቱና ፍቅሩ ስለነበራት እድሉን ማግኘቷ በራሱ ሌላ ትልቅ እድል ነው።
ተማሪ ሥምረት ሙላቱ እንደ ነገረችን ዳግማዊ ምኒልክ ከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ በርካታ ክበባት ያሉ ሲሆን፣ ሁሉም እንደየ ዝንባሌና ፍላጎቱ በየክበባቱ እየገባ ይሳተፋል። እንደ መታደል ሆኖ የእሷ ፍላጎት ወደዚህኛው ሆነና አስፈላጊውን የመግቢያ ፈተና ወስዳ በማለፍ የማርቺንግ ባንዱ አባል ለመሆን ችላለች።
“የትኛው የሙዚቃ መሳሪያ ነው ምርጫሽ?″ ብለናትም ነበር። የትንፋሽ (ቢፍላት ስላይድ ትሩምቡን) መሆኑን የነገረችን ተማሪ ሥምረት መሳሪያውን ስታንቀባርረውም ለማየትና መስማት ችለናል።
ልክ እንደ ተማሪ ናትናኤል ሁሉ ትምህርትና የሙዚቃ መሳሪያ ልምምድ እንዴት አብረው ሊሄዱ እንደሚችሉ ጠይቀናት ነበር።
“ምንም ችግር የለውም። አንደኛ ይኸው እንደምታየው ልምምዱ ከትምህርት ሰዓት ውጪ ነው″ ያለችን ተማሪ ሥምረት “ዋናው ነገር በእቅድ፣ በፕሮግራም መመራቱ ነው። እኔ በዚህ አምናለሁ። እምመራውም በዚሁ መሰረት ነው። ለምሳሌ ዘንድሮ ማትሪክ ወሳጅ ነኝ። ለእሱም አስፈላጊውን ጊዜ ሰጥቼ በመዘጋጀት ላይ ነኝ። ለዚህ፣ ለልምምዱም እንደምታየው ጊዜ ሰጥቼ እየተለማመድኩ ነው። ባጠቃላይ ካሰብክበት ምንም ችግር የለውም፤ እንደውም ጊዜህን እያቀያየርክ መጠቀሙ እንደ መዝናኛም ሆኖ ሊያገለግል ይችላል።″ ስትል በፈገግታ መልሳልናለች።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም