የዓባይ ግድብ ግንባታ ከ13 ዓመታት በኋላ ሊጠናቀቅ ጫፍ ደርሷል። ይህም የግድቡን ግንባታ በገንዘብ፣ በጉልበትና በጸሎት እያገዙ ለሚገኙ ሁሉም ኢትዮጵያውያን፣ ግድቡን ቀን ከሌሊት ለሚጠብቁ የፀጥታ ኃይሎች፣ ሀሩር ተቋቁመው ግንባታውን ለሚያከናውኑ ባለሙያዎች እና የኢትዮጵያን እውነታ ለዓለም ላስገነዘቡ መገናኛ ብዙሃን ሁሉ ትልቅ ብስራት ሆኗል።
የኢትዮጵያውያን የጋራ ፕሮጀክት የሆነው የዓባይ ግድብ እዚህ ደረጃ መድረስ የጋራ ጥረት ውጤት ነው። ከሁሉም በላይ የግድቡ ግንባታ በስኬት መጠናቀቅ ፈተናዎችን ተቋቁሞ ለትውልድ የሚሸጋገር አሻራ ማስቀመጥ እንደሚቻል ትምህርት የሰጠ ነው።
ዓባይ የኢትዮጵያ ማንነት ግድቡ ደግሞ የዛሬው ትውልድ አሻራ የነገው ትውልድ ገጸበረከት ነው። የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የሚነጋገሩበት የጋራ ቋንቋቸው ነው። የግድቡ መጠናቀቅ ኢትዮጵያ በፈተናዎች ውስጥም ሆና ማንኛውንም ፕሮጀክት ማሳካት እንደምትችል በግልጽ ያሳየ ነው። ድህነትን በማሸነፍ ለመጭው ትውልድ ብልጽግናን የምናወርስበት የአንድነታችን አርማ፤ የማሸነፋችን ምልክትም ነው።
ግድቡ አሁን የደረሰበት ደረጃ ኢትዮጵያውያን በኩራት አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዲሄዱ ኢኮኖሚያዊ መሰረት የሚጥል ነው። ትናንት ያጋጠሙንን ፈተናዎች በድል ተሻግረን እዚህ ደርሰናል፤ የዛሬ ፈተናዎችንም አልፈን የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን እንደምናደርግ ያለፍንበት መንገድ ማሳያ ነው።
የዓባይ ግድብ ከታላቁ የአድዋ ድል በኋላ ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ አስተሳሰብ፣ ኢኮኖሚያዊ ልዩነት፣ እንዲሁም ቋንቋና ሃይማኖት ሳይገድባቸው ዳግም የተሰባሰቡበት የኩራት ካስማ ነው። ኢትዮጵያም በዓባይ ወንዝ ላይ የመጠቀም ሉዓላዊ መብቷን ያስከበረችበት ድርብ ድል በመሆኑ ልንኮራና ለሌሎች የልማት ስራዎች እንድንነሳ ትልቅ የመንፈስ ስንቅ ሊሆነን ይገባል።
የዓባይ ግድብ ኢትዮጵያውያን በኩራት አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዲሄዱ ኢኮኖሚያዊ መሰረት ጥሏል። እንደ ሀገር ብዙ ፈተናዎችን ተቋቁመን በዚህ ልክ መለወጥ ከቻልን ሰላማችንን በጋራ ብናረጋግጥ የት እንደርስ ነበር? የሚለውን መላው ኢትዮጵያዊ ቆም ብሎ ሊያየው ይገባል።
ግድቡ ኢትዮጵያ ከዓባይ ጋር ያላትን ትስስር የሚያጸናም ነው። የግድቡ በስኬት መጠናቀቅ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፋዊና ውስጣዊ ጫናዎችን በመቋቋም ያስመዘገበችው ድል ማሳያም ነው። በተለይም የግድቡ ግንባታ ከጅምሩ እስከ አሁን ውጫዊና ውስጣዊ ፈተናዎች ባሉበት ሁኔታ አልፎ በመገባደድ ላይ መሆኑም፣ ኢትዮጵያ ፈተናዎችን በፅናት እየተሻገረች ስለመሆኗ ምልዕክት ነው።
በግድቡ ዙሪያ ከፍተኛ ውጫዊ ጫና እንደነበርና አሁንም እንዳለ ለማንም ግልፅ ነው። ኢትዮጵያ የማንንም ሀገር ጥቅም አደጋ ላይ በማይጥል ሁኔታ ግድቡን እየገነባች መሆኑን በማስረዳት ጫናውን መቀልበሷን ግን ቀጥላለች።
በተለይም በዓባይ ተፋሰስ ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ ውሃውን ለብቻችን እንጠቀም የሚሉ ሀገራት ኢትዮጵያን ያላሳተፉ የቅኝ ግዛት ውሎች ዳግም ለማጽናት የዓረብ ሊግን በመጠቀም ዘመቻዎች ሲደረጉ ቆይተዋል። አሁንም ከማድረግ ወደ ኋላ አይሉም። ሆኖም የኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ቁርጠኝነት፣ ብርቱ የዲፕሎማሲ ጥረትና የማኅበረሰብ ተሳትፎ ተደምረው ጫናዎችን በማለፍ የግድቡን ግንባታ ከጫፍ አድርሰዋል።
በቀጣይም ከግድቡ በሚገኘው የኃይል ምንጭ ጠንካራ የማኅበራዊ ተቋማትን ለመገንባትና ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ውህደትን ለማጠናከር እንደሚያግዝ እሙን ነው። ከኢትዮጵያውያን አልፎ ለአፍሪካ ቀንድና ለተፋሰሱ ሀገራት መረጋጋትም ሆነ የጋራ ተጠቃሚነት ለሚሰራ ሁሉ የግድቡ መጠናቀቅ ትልቅ የምስራች ነው።
ኢትዮጵያ ዓባይን በማልማት ሂደትና የግድቡን ግንባታ በማጠናቀቅ ሂደት ውስጥ ብዙ የዲፕሎማሲ ጥረትና ትግል አድርጋለች። በዚህም የግድቡን ግንባታ በፀጥታው ምክር ቤት አጀንዳ ለማድረግ የሞከሩና የግጭት መነሻ ሊያደርጉ ሲሰሩ የነበሩ አካላትን ሴራ ማክሸፍ ችላለች።
ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን የመጠቀም ሉዓላዊ መብቷን፣ መርህን ባከበረ መልኩ እየተገበረች ስለመሆኗ እውነታውን ለዓለም በማስረዳትም የተዛቡ አካሄዶችን መቀልበሷም ለዚህ ማሳያ ነው። በተለይም የዓባይ ተፋሰስ የጋራ ልማት እንጂ የግጭት ምንጭ መሆን የለበትም የሚለው አቋሟ ብዙዎች ቆም ብለው እንዲያዩ ማድረግ ችሏል። አሁንም በዲፕሎማሲው መስክ ትላልቅ የቤት ስራዎች አሉ። የትብብር ማዕቀፉን ያልፈረሙ ሀገራትን በማስፈረም የዓባይ ተፋሰስ ኮሚሽን እንዲቋቋም ለማድረግ ኢትዮጵያ በተፋሰሱ ውስጥ ካላት ትልቅ ተሰሚነት አኳያ ፖለቲካዊ ሚና መወጣት አለባት።
ከዓባይ ተፋሰስ የውሃ አጠቃቀም አንጻር የዘመኑን የዲፕሎማሲ ከፍታ ለማስመዝገብም አሁንም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ድጋፍ ማድረጉን መቀጠል አለበት። በመሆኑም የዓባይ ግድብ ከልመና የምንወጣበት ድህነትን የምናሸንፍበት ፕሮጀክት ነውና መላ ኢትዮጵያውያን ለግንባታው መጠናቀቅ ጥረታቸውን አጠናክረው መቀጠል ይጠበቅባቸዋል።
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም