ድህነትን አሸንፈው ለሌሎች የተረፉ የቸሃ ወጣት አርሶአደሮች

ግብርና የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ የኑሮ መሰረት፣ የሀገር የምጣኔ ሀብት ዋልታ መሆኑ ይታወቃል። መንግስትም ለዚህ ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ማደግ በዋናነትም በምግብ እህል ራስን ለመቻል ለሚያግዙ የልማት መርሃ ግብሮች ትኩረት ሰጥቶ መስራቱን አጠናክሮ ቀጥሏል። ይህን ተከትሎም ምርትና ምርታማነት እየጨመረ ነው።

ከእነዚህ መርሀ ግብሮች መካከል አንዱ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ነው። በዚህ መርሀ ግብር አማካኝነት ሁሉም ክልል በአካባቢው ያለውን የልማት ፀጋ በመመልከት እያከናወነ ያለው የተቀናጀ ግብርና ልማት ሥራ ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ ነው። ይህ ውጤት መርሀ ግብሩ የአርሶ አደሩን ሕይወት በመለወጥ፤ ድህነትን ለመቀነሱ ተግባር አስተዋጽኦ የሚያደርግ ስለመሆኑ ጉልህ ማሳያ ነው።

በዚህ የተቀናጀ ግብርና ልማት ውጤታማ እየሆኑ ከመጡ ክልሎች መካከል ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አንዱ ነው። ክልሉ ከቀድሞ ደቡብ ብሄሮችና ብሄረሰቦች ክልላዊ መንግስት ሥር ወጥቶ አዲስ ክልል ከሆነ የወራት እድሜ ብቻ ቢያስቆጥርም፣ የክልሉ መንግስትና ሕዝብ እያደረጉት ባለው ርብርብ የግብርናው ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ እየጎለበተ ይገኛል።

በተለይም ለሶስት ዓመታት በሚተገበረውና የክልሉ ኢኒሼቲቭ በሚባለው ‹‹ሰላሳ አርባ ሰላሳ›› በሚለው መርሃግብር እንዲሁም በሌማት ትሩፋት የልማት ግብ አማካኝነት እየተከናወኑ ያሉት የጥምር ግብርና ስራዎች ውጤት እያስገኙለት ነው። ይህንን የልማት ሥራ ለመመልከት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የጋዜጠኞች ቡድን በቅርቡ በክልሉ ተገኝቶ በመስክ ምልከታው ከዳሰሳቸው የክልሉ ዞኖች መካከል የጉራጌ ዞን አንዱ ነው።

በዞኑ የቸሃ ወረዳ ወጣት አርሶ አደሮች የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬዎችን ያለማሉ፤ በመስክ ጉብኝታችንም ወጣት አርሶ አደሮቹ አልምተው አዝመራው የተሰበሰበውን ሰፊ የሃብሃብና ቲማቲም ማሳ አልፈን ከተንጣለለው የቃርያ ማሳ ደርሰናል። ይሄ በስተግራችን የተመለከትነው ነው። በስተቀኝ ደግሞ ሽንኩርት፣ ኪያር፣ ጥቅል ጎመን፣ ዝኩኒና ሌሎችም የደረሱና የሚያጓጉ የጓሮ አትክልቶች በስፋት ለምተው ይታያሉ። በቅርብ ርቀት ደግሞ በርከት ያሉ ሴቶችና ወጣቶች ዋናው ምርት ከተሰበሰበ በሁዋላ የቀረውን ቃሪሚያ በመሰብሰብ ስራ ተጠምደዋል።

ይህ ከሰላሳ ሄክታር በላይ የሚልቀው ማሳ ከዓመታት በፊት ባሕር ዛፍና ምንም አገልግሎት የማይሰጥ ሜዳ ብቻ ነበር የሚታይበት ሲሉ የአካባቢው አርሶ አደሮች ገልጸውናል። ባሕር ዛፉ በቅርብ ርቀት የሚገኘውን ወንዝ ውሃ በመምጠጥና የመሬቱን ለምነት በማራቆት ሕልውናን አደጋ ውስጥ ጥሎት እንደነበርም ይነገራል።

ወጣት ዳንኤል ሽፈታ ቸሃ ወረዳ ወድሮ ቀበሌ ነው ተወልዶ ያደገው። ከሰመራ ዩኒቨርሲቲ በሆርቲካልቸር ትምህርት ዘርፍ ተመርቆ በአንድ የአበባ ልማት ድርጅት የመቀጠር እድል አግኝቶ የነበረ ቢሆንም፣ በስራውም ሆነ በሚያገኘው ደመወዝ ደስተኛ ባለመሆኑ ስራውን ይለቃል። ከአራት ጓደኞቹ ጋር ይመክራል፤ የራሳቸውን ስራ ለመጀመር የሚያግዛቸውን 70 ሺ ብር ከቆጠቡ በኋላ ከቸሃ ወረዳ አስተዳደር 28 ሺ ብር ብድር፣ ምርጥ ዘርና እንደ የውሃ ፓምፕ የመሳሰሉ ግብዓቶችን በማግኘት በአንደኛው ጓደኛቸው አባት ጓሮ ሽንኩርትና መሰል አትክልቶችን ማልማት ይጀምራሉ።

ወጣቶቹ ከአንድ ሄክታር በማይልቀው መሬት ላይ አልምተው 70 ሺ ብር ሲያገኙ ልባቸው የበለጠ ለማልማት ተነሳሳ፤ እናም ከአንድ ሄክታር ወደ ሁለት፤ ከሁለት ወደ ሶስት ሄክታር መሬት አሰፉ። የምርት አይነታቸውንም ከዚህ ቀደም በአካባቢው ሕብረተሰብ ብዙም ያልተለመዱ ግን ደግሞ በከተሞችና በውጭ ገበያ ተፈላጊ የሆኑ እንደ አበባ ጎመን፣ ብሮኮሊና ኪያር ያሉ የጓሮ አትክልቶችን እንዲያለሙ ወረዳው ሰባት ሄክታር መሬት አመቻቸላቸው። እነዚህ ብርቱ ወጣቶች ሳይታክቱ ማልማታቸውን ቀጠሉና አድገታቸውን ጨመሩ። ይህን ያየው የወረዳው አስተዳደርም የብድር አቅርቦቱን ወደ 300 ሺ ብር ከፍ በማድረጉ አቅማቸውን ከፍ ማድረግ ቻሉ።

‹‹በስምንት ዓመት ጉዞ አሁን የምታዩት የእርሻ መሬት 30 ሄክታር ደርሷል፤ በዚህም ጎመን፣ ቲማቲም፣ ሽንኩርት፣ ብሮኮሊ፣ አበባ ጎመን፣ ሃብሃብና ሌሎችም ተፈላጊ ምርቶችን በስፋት በማልማት ለገበያ እናቀርባለን›› የሚለው ወጣት ዳንኤል፤ በተለይም በወረዳው አማካኝነት በተፈጠረላቸው የገበያ ትስስር በመጠቀም ያለ ብዙ ድካምና እንግልት ምርታቸውን ወደ ተጠቃሚው እንደሚያደርሱ ይገልፃል። በአሁኑ ወቅት ካፒታላቸውን ወደ አስር ሚሊዮን ብር ማድረሳቸውን አመልክቶ፤ ከ100 በላይ ለሚልቁ የአካባቢው ወጣቶች በቋሚነት የስራ እድል መፍጠራቸውንም ጠቅሷል።

በተጨማሪም በየቀኑ ከ100 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች በእርሻው ላይ በጊዜያዊነት ተቀጥረው የሚሰሩበት ሁኔታ የተመቻቸላቸው መሆኑንም ተናግሯል። ከዚህም ባሻገር አቅም የሌላቸውና ደካማ እናቶች ምርት ከተሰበሰበ በኋላ በሚቀረው ቃርሚያና ተረፈ ምርት በነፃ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረጋቸውንም ነው ወጣት ዳንኤል የሚያስረዳው።

ወጣት ዳንኤል እንደሚገልፀው፤ ምርቶቻቸውን ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ባሻገር ለአጎራባች ወረዳዎችና የክልሉ ዞኖች በስፋት ያቀርባሉ። ከዚሀም ባሻገር በኢትዮጵያም ሆነ በውጭ ገበያ ተወዳዳሪ ሆነው ለመቅረብ ተግተው እየሰሩ ናቸው። በተለይም የተሻሻሉ ዝርያዎችን በመጠቀምና ምርታማነታቸውን በከፍተኛ መጠን በማሳደግ ኢትዮጵያ ለተያያዘችው በምግብ እህል ራስን የመቻል የልማት ግብ ስኬት ወሳኝ ሚና የመጫወት ትልም ይዘው እየሰሩ ይገኛሉ። በአሁኑ ወቅትም ምርታማ ዘሮችን በማባዛት ለአዳዲስ ማኅበራትና አርሶአደሮች ያሰራጫሉ፤ ይህንንም ዘር የማባዛት ስራቸውን በማጠናከር ክልሉ የግብርና ምርትና ምርታማነት እንዲጎለብት የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ ነው ያሉት።

በተጓዳኝም የእርሻ ተረፈ ምርታቸውን በማቀነባበርና መኖ በማዘጋጀት ከብቶችን የማደለብና የወተት ልማት ስራ ለመስራት ማቀዳቸውን ወጣቱ አርሶአደር ይናገራል። በተጨማሪም ከአነስተኛ እርሻ ልማት ወደ ኢንቨስትመንት ለመሸጋገር አቅደው እየሰሩ ነው። በአሁኑ ወቅትም ለዚህ ስራ የሚያስፈልጋቸውን ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ይጠቅሳል። በዚህም ለበርካታ የአካባቢው ወጣቶች የስራ እድል በመፍጠር ድህነትን ታሪክ የማድረግ ትልማቸውን ለማሳካት እየተረባረቡ መሆኑን ያመለክታል። ለእዚህ ዘርፈ ብዙ ውጥናቸው መሳካት ግን አሁን ያለው የብድር መጠን ሊሻሻል እንደሚገባ ወጣቱ አርሶአደር ሳይጠቁም አላለፈም።

ወጣት ዳንኤል እንደሚለው፤ የገበያ ትስስር በመፍጠር ረገድ ከወረዳ ጀምሮ እስከ ክልል ድረስ ያሉ አመራሮች ድጋፍ እያደረጉላቸው ቢሆንም ቋሚ የመሸጫ ሥፍራ የሌላቸው በመሆኑ ከኅብረተሰቡ ጋር በቀጥታ የሚገናኙበት እድል የለም። በተለይም በኅብረተሰቡና በአምራቹ መካከል ደላሎች የሚገቡ በመሆኑ እነሱም ሆኑ ሸማቾቹ የሚገባቸውን ያህል ተጠቃሚ መሆን አልቻሉም። በመሆኑም የሚመለከተው አካል አምራቹ በቀጥታ ምርቱን ለሸማቹ የሚሸጥበትን ሁኔታ ሊፈጥር ይገባል።

በሌላ በኩል ግን እንደእሱ ከተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመርቀው ሥራ አጥተው የተቀመጡ ወጣቶች አሁን ላይ መንግስት ያመቻቸውን ምቹ እድል ሊጠቀሙ እንደሚገባ ነው ወጣት ዳንኤል የመከረው:: ‹‹ወጣቱ ሊነቃና ራሱን ከድህነት ሊያወጣ ይገባል፤ በተለይ በወረዳችን ያሉ ወጣቶች በመንግስት የተመቻቸውን እድል በመጠቀም አካባቢያቸውን ሊያለሙ፤ ራሳቸውንም ከችግር ሊያወጡ ይገባል›› ይላል።

‹‹በእርግጥ የግብርና ስራ ፈታኝ ነው፤ ለዓላማ ቆራጥ መሆንን ይጠይቃል፤ ሆኖም የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በፅናት በማለፍ ከስኬት መድረስ ይቻላል›› ይላል። በመንግስት በኩልም ወጣቱን ይበልጥ በመቀስቀስ፤ የብድር አቅርቦትና፣ መስፈርቶችን በማስተካከል የበለጠ ሊደግፍ እንደሚገባ አመልክቷል።

አቶ አህመድ መሃሙድ የቸሃ ወረዳ ግብርና ልማት ፅህፈት ቤት ኃላፊ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ በወረዳው 18 ቀበሌዎች ላይ በመስኖ ማልማት የሚያስችሉ የውሃ አማራጮች አሉ። ይሁንና የአካባቢው አርሶአደር የተወሰኑ የሰብል አይነቶችንና ባሕር ዘፍ አልምቶ ከመጠቀም ውጪ እምብዛም ተጠቃሚ አልነበረም። በተለይም ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ይህንን ለመስኖ ምቹ የሆነ መሬትም ሆነ ሌሎች የውሃ አማራጮችን በመጠቀም የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ ከፍተኛ ርብርብ አድርጓል። ወረዳው ሶስት ሺ417 ሄክታር በመስኖ ለማልማት እየተሰራ ነው። በዋናነትም ለአካባቢው ስራ አጥ ወጣቶች መሬት በነፃ ከማቅረብ ጀምሮ የብድር፣ ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያና እንደውሃ ፓምፕ የመሳሰሉ ግብዓቶችን በማመቻቸት ከጠባቂነት እንዲወጡ እየተደረገ ነው።

‹‹ በጠቅላይ ሚኒስትራችን አነሳሽነት በተጀመረው የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር መሰረት ኩታ ገጠም የሆኑ አነስተኛ የእርሻ መሬቶችን በክላስተር በማደራጀት ገበያ መር የሆኑ የሰብል፤ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች በስፋት በወረዳችን እየተመረተ ነው›› ይላሉ። በአሁኑ ወቅት እየተገነቡ ያሉ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ በወረዳው ሶስት ጊዜ ለማልማት የሚቻልበት እድል ይፈጠራል የሚል እምነት እንዳላቸው ይናገራሉ። ይህም በዘርፉ ሰፊ የስራ እድል እንዲፈጠር ከማድረጉም ባሻገር አሁን እንደሃገር የሚስተዋለውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት የላቀ ሚና እንደሚጫወት ጠቁመዋል። ለዚህም ሥራ መሳካት ከክልል ጀምሮ እስከ ቀበሌ ድረስ ያለው አመራር ቅንጅታዊ ትስስር ፈጥሮ መንቀሳቀሱን ያመለክታሉ።

በአሁኑ ወቅትም እንደነ ዳንኤል ያሉ በርካታ ወጣቶችን ለመፍጠር ተሞክሮውን የማስፋት ስራ በወረዳው እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ‹‹ዘንድሮ ደግሞ በልዩነት ገበያ መር በሆኑና በኢትዮጵያ ገበያ ላይ ተወዳዳሪ መሆን በሚቻልበት መልኩ የተሻሻሉ ዝርያዎችን በማስፋት የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚ ለማሳደግ እየተረባረብን ነው›› ሱሉም ነው ያብራሩት።

በዚህም መሰረት በወረዳው የሽንኩርት፣ የድንች፣ የቃሪያና መሰል አትክልቶችን በክላስተር እርሻ በስፋት እየለሙ መሆኑን ይጠቅሳሉ። በተለይም ከዚህ ቀደም በአካባቢው ያልተለመዱ እንደ ዝኩኒ፣ ኪያርና ሃብሃብ አትክልትና ፍራፍሬዎች ዝርያዎችን እያለሙ ያሉትን እነ ዳንኤልን ለአብነት አንስተው ሌሎችም አርሶ አደሮች እንዲያለሙ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

የጉራጌ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አክሊሉ ካሳ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ ዞኑ በዋናነትም በበጋ መስኖ ልማት በ30 ሺ ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ ሰብሎችን እያመረተ ይገኛል። ከዚህ ውስጥም አምስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታል ምርት መሰብሰብ ተችሏል። ዞኑ በስሩ ባሉ የወረዳና ቀበሌ መዋቅሮች የሚገኙ አርሶ አደሮችን የመደገፍ ስራ እያከናወነ ነው። በተለይም የዞኑ የባለሙዎች ቡድን እስከ ቀበሌ ደረስ በመውረድ ተከታታይና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ያደርጋል። ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘርና ቴክኖሎጂዎች በተገቢው መልኩ እንዲገኙ የዞኑ ከፍተኛ አመራር ጭምር ይከታተላል። በዚህም ዞኑ ከሌላው ጊዜ በተለየ ዘንድሮ እቅዶቹን አመርቂ በሚባል ደረጃ መፈፀም ችሏል።

በዞኑ በዋናነትም እንደ እነ ዳንኤል ድህነትን ታሪክ የሚያደርጉ በርካታ ወጣቶችን በመፍጠር የአካባቢውን ብሎም እንደ ሃገርም በምግብ እህል ራስን የመቻል ግብ እንዲሳካ እየተሰራ ነው። ከዚሁ ጎን ለጎንም ወጣቶቹን በማደራጀት ፍራፍሬ በስፋት እንዲያለሙ የዞኑ አስተዳደር ድጋፍ እያደረገላቸው መሆኑን አቶ አክሊሉ ጠቅሰዋል።

በተለይ በሰላሳ ፣ አርባ፣ ሰላሳ ኢኒሼቲቭ እንደ አቦካዶ፣ ሙዝ፣ አፕልና መሰል ፍራፍሬና አትክልቶች ላይ ትኩረት በማድረግ እንደሚሰራ አስታውቀው፣ አርሶ አደሩ በመጀመሪያው ዓመት ሰላሳ፣ በሁለተኛውም ዓመት አርባ፣ በሶስተኛው ዓመት ደግሞ ሰላሳ ችግኞችን በመትከል በሶስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ 100 የፍራፍሬ ዛፎች ባለቤት ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You