የከተሞች፣ በተለይም የመዲናችን አዲስ አበባ ጉዳይ (ልማቷ፣ ውበቷ፣ ፅዳቷ ወዘተ) ሲነሳ ስማቸው ሳይነሳ የማይቀሩ፤ ሁሉንም እንዳማረሩ፤ አልፎ አልፎም እንደ ተወቀሱና እንደተረገሙ የኖሩ ተቋማት አሉ።
“ለምን። እንደ ሆነ እንጃ እንጂ፣ እነዚህ ተቋማት ላይ አንዳንድ ሰፈሮችና ሰዎች አብዝተው ሲማረሩባቸውና ሲያወግዟቸው መስማትም ሆነ ማየት የሚገርም ጉዳይ አይደለም። አንዳንዶቹማ “የስራችሁን ይስጣችሁ። እስከ ማለት ሁሉ ሲዘልቁ ተደምጠዋል። ግን ለምን?
አዲስ አበባ ያው እንደ ማንም አገር መዲና የአገሪቱ ዋና ከተማ ብትሆንም፤ እንደ ሌሎቹ ሁሉ እሷ ግን ስትቆፈር ውላ ስትቆፋፍር ብታድር የሚበቃት ሆና ልትታይ አልተቻላትም። ሁሌም በዶማ፣ ሁሌም በስካቫተር፣ ሁሌም በዲጂኖ፣ ሁሌም በመዶሻ ወዘተርፈ ስትነደል ውላ ስትነደል ማደር እጣ ፋንታዋ ሆኗል (እዚህ ጋ ሌሎች ከተሞቻችን አይነደሉም አልተባለም)።
ችግሩ የመነደሏ ጉዳይ አይደለም፤ ነዳዩ ከአስነዳዩ፣ ቆፋሪው አስቆፋሪው፤ ስካቫተሩ ከዶዘሩ፤ ቆፋሪው ካስቆፋሪው፤ ባለ ገመዱ ከባለ ሽቦው፤ ባለብረቱ ከባለ ቱቦው ወዘተርፈ ሊግባቡ አለመቻላቸውና ሚስተር ኤክስ የተከለውን ሚስተር ዋይ ሲነቅለው ውሎ ሲነቅለው ማደሩ ነው። ሚስተር ዋይ ያፀናውን ሚስተር ኤክስ መጥቶ መንደሉ ነው የመዲናዋ አደጋ፤ የከተማና ከተሜው መከራ ሆኖ የኖረው።
የዚህ ሁሉ ተቃርኖ መሰረታዊ ችግር ተቋማቱ የተለያዩ ከተሞችን የሚያለሙ እስኪመስሉ ድረስ መለያየታቸውና ከተሜው የሚገነባውን ከሚያፈርሰው ተቋም ለመለየት መቸገሩ ነው። በዚህ ላይ ገደምዳሜውን ትትን በግልፅ እንነጋገር።
እስከ ዛሬ ያለው እውነታ ቴሌ የሰራውን መንገዶች “ጉዳይ አለኝ። በማለት ሲያፈርሰው መኖሩን አገር ያወያቀው፣ ፀሀይ የሞቀው እውነታ ነው። መብራት ኃይል ሰራሁት፣ ጨረስኩት ∙ ∙ ∙ ያለውን ውሀና ፍሳሽ ወይም ሌላ “በሕግ አምላክ፤ እኔ መንገዴ በዚህ ነው ∙ ∙ ∙ ዞር በልልኝ። ማለት እስኪመስል ድረስ መንግሎ ይጥለዋል። መንገዶች ያነጠፈውን ወይ መብራት ኃይል ወይ ቴሌ መጥቶ ጢብ ጢብ መጫወት ብቻ ሳይሆን አሽቀንጥሮ ሁሉ ይጥለዋል።
ችግሩ የሱ ጢብ ጢብ የመጫወትና አሽቀንጥሮ የመጣሉ ጉዳይ ሳይሆን፤ መንገዶች አንጥፏቸው የነበሩትና ቴሌ ወይም ውሀ “ስራዬን ልስራበት፤ ከፊቴ ዞር በሉ። ያሏቸው ድንጋዮች በስንትና ስንት ንፁሀን እግሮች ጢብ ጢብ መጫወታቸው ነው። ባጭሩ፣ ያሳለፍናቸው ዘመናት ቴሌ — መብራት ኃይል — መንገዶች — ውሃና ፍሳሽ እና ሌሎችም ሳይግባቡ የኖሩበት ብቻም ሳይሆን፤ ላይግባቡ የተማማሉበት እስኪመስል ድረስ አንዳቸው የአንዳቸውን ተቃራኒ አቅጣጫ ሲከተሉ፤ የተለያዩ ከተሞችን የሚያለሙ መስለው የታዩባቸውና የኖሩባቸው ናቸው፤ ወይም ነበሩ።
ወደ ኋላ መለስ ብለን ስናስታውስ ችግሩ ከጣራ በላይ የሆነበት የከንቲባ ዘመን ቢኖር የአቶ የኩማ ደመቅሳ የከንቲባነት ዘመን ነበር። በወቅቱ ከንቲባ ኩማ ደመቅሳ ብለው ብለው ቢቸግራቸው፤ የሕዝብ ጩኸት አናታቸውን ቢበጠብጣችሁ፣ እየባከነ የነበረው ገንዘብ ያስቆጫቸው፣ ለ“የመጨረሻ መፍትሄ። ፍለጋ ከተማ አቀፍ ጥምር ኮሚቴ በማቋቋም፣ እና ያቋቋሙትን ኮሚቴ ለከተማው ነዋሪ በማስተዋወቅ ሕዝቡን እፎይ ማሰኘትና ተናብበው መስራት ያቃታቸውን ችግር በዘላቂነት እንዲፈቱ አቅጣጫ አስቀመጡ።
በሰዓቱ ይሄን የሰማው ከተሜ ሁሉ ማለፊያ ተግባር ነው አለ። ታዲያስ፣ ንክች ያባ ቢላዎ ልጅ እንዲሉ፣ ምንም የተገኘ ለውጥ የለም። “ኮሚቴ። የተባለው እራሱ እምጥ ይግባ ስምጥ የታወቀ ነገር የለም። ዘፈኑ ሁሉ “እየከፋ ሄደ እየከፋ ∙ ∙ ∙። ሆነና አረፈው። ከዛስ? ሕዝቡም ተወው፤ ከንቲባዎቹም ተውት መሰለኝ በቃ፤ አለመናበብ ባህል ሆነና ቁጭ። ዛሬስ??? ጥያቄው እዚህ ጋ ነው።
አሁን ያለንበት ወቅት፣ በተለይ ከዚህ ከመጋቢት ወር መጀመሪያ ጀምሮ በተለይ አዲስ አበባ አዲስ ግዙፍ (ግራንድ ፕሮጀክት)ን ጀምራ መልኳ ሙሉ ለሙሉ ተቀይሮ እየታየች ያለችበት ወቅት ነው። ከመሀል ፒያሳ (ከአገሪቱና ከተማዋ እምብርት) ተነስቶ በአራቱም አቅጣጫ አዲስ አበባ የበፊቱ እሷ አይደለችም፤ አዱ ገነት እጅጉን ተቀይራለች። “ምን እየሆነች ነው?። ለሚለው፤ መልሱን “ወደ ፊት፣ ሲጠናቀቅ የምናየው ይሆናል። የሚለውን እናድርግና ወደ ተነሳንበት እንሂድ።
ይህ ጸሐፊ በዚህ “አዲስ እና ግዙፍ ፕሮጀክት። በተባለው የመልሶ ማልማት እንቅስቃሴ አማካኝነት አንድ የታዘበው፤ ያደነቀውና ይቀጥል ዘንድም አምላኩን የተማፀነበት አቢይ ጉዳይ ቢኖር፣ ከላይ (እየወቀስናቸውም ቢሆን) የጠቀስናቸው መንግስታዊ ተቋማት ከፍፁም አለመናበብ ወደ ፍፁም መናበብ መሸጋገራቸው ነው።
ጸሐፊው ቢሮው አራት ኪሎ እንደ መሆኑ መጠን፣ እየተሰራ ያለውን የግንባታ ስራና እየሆነ ያለውን ሁሉ ሰዓት በሰዓት እያየ ነው፡፡ የእነዚህን፣ ለአንድ ከተማ ከተማነት ወሳኝ የሆኑ የተቋማት እርስ በርሳቸው፣ ያለ ምንም ሚና መደበላለቅ፣ ያለ ምንም ግርታና ተመሰቃቅሎ ሁሉም የየራሳቸውን ተግባራት ሲያከናውኑ እየተመለከተ ይገኛል።
እንደ አጋጣሚ ሆኖ ይህ ጸሐፊ እየተሰሩ ካሉት ስራዎች ውስጥ አንዳቸውም ሙያው አይደሉም። ይሁን እንጂ፣ እንደ አንድ ተራ ሰው የሚገባው ሁሉ ይገባዋል። በተለይም እስከ ዛሬ የነበረውን የሚና መደበላለቅና አፍርሶ የመገንባትና አንዱ የገነባውን ሌላው የማፍረሱን ስር የሰደደ ችግር አሳምሮ ያውቀዋልና እየተሰሩ ባሉት ስራዎችና በደጋፊ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎቹ መደነቁን መደበቅ አይችልም። ሁሉም የየራሱን ይሰራል፤ መጨረሻ ላይ አንድ መንገድ፤ አንድ አስፋልት ይወጣል።
እንደ አንድ የከተማዋ ነዋሪ፣ አራት ኪሎም ሆነ፣ ከአራት ኪሎ ተነስቼ እስከሄድኩባቸው ስፍራዎች ድረስ ይሄንን ተናቦና በከፍተኛ ዲሲፕሊን የመስራት መሰረታዊ ተግባር ተመልክቻለሁ። ይህንን እስከ ዛሬ የሌለንን፣ ዛሬ ግን እየሆነልን ያለውን ተግባር አይቼ “ለካ ይቻል ነበር። ሁሉ ብያለሁ። “ያ የቀድሞው ከንቲባ ኩማ ያቋቋሙት ኮሚቴስ ለምን አቃተው?። ብዬም ጠይቄያለሁ፤ ታዝቤያለሁም። የቀድሞው አለመናበብ ተመልሶ እንዳይመጣና የአሁኑ የመናበብ ድንቅ ችሎታም ወደ ኋላ እንዳይመለስና ነገ ደግሞ ይሄንኑ መልሰን እንዳንቆፍር ፈጣሪን ተማፅኛለሁ።
ምንም እንኳን፣ የገንዘብ አመራር እውቀት ቢያጥረን የሰው ላብ ግፍ አለውና ዳግም ተመልሶ ያ ክፉ አለመናበብ ደዌ እንዳይመጣ ተመኝቻለሁ። እንደ ከተማ ነዋሪነቴም፣ እየተሰራ ካለው ስራ የሚመለከተው ሁሉ የመናበብን ልምድ እንዲቀስም አደራ እላለሁ።
መናበብ ለዘልአለም ይኑር!!!
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም