ስለኢትዮጵያ ሲነሳ፣ ሁልጊዜ አብሮ ከሚነሱ እሴቶች ውስጥ አንዱ የሕዝቡ እንግዳ ተቀባይነት ቀድሞ የሚታወስ ነው። ኢትዮጵያ እንደ ሀገር፣ ሕዝቡም እንደ ሕዝብ እንግዳ ተቀባዮች ናቸው። ይህ የእንግዳ ተቀባይነት መገለጫ ከድሮ እስከ ዘንድሮ የቀጠለና ወደ ፊትም አብሮን የሚኖር ነው።
ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የረመዳንን ጾም ምክንያት በማድረግ የተለያዩ የኢፍጣር (ጾመኞችን የማብላት) መርሃ ግብሮችን ሲያካሂዱ ቆይተዋል። ከእነዚህ መርሃ ግብሮች ውስጥ አንዱና ለዛሬው ጽሁፌም መነሻ የሆነኝ የተለያዩ ሀገር ስደተኞችን በቤተ መንግስት ጠርተው ያደረጉት የኢፍጣር ዝግጅት ነው።
ሀገራቸውን ጥለው የተሰደዱና ኢትዮጵያን መጠጊያ ያደረጉ የሶማሌ፤ የሶሪያ፤ የየመንና የተለያዩ ሀገር ስደተኞችን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቤተመንግስታቸው ድረስ ጠርተው አስፈጥረዋል። በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ስደተኞችን ቤተመንግስት ድረስ ጋብዞ ማስፈጠር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ስልጣን ከመጡ ጊዜ ጀምሮ የቀጠለ በጎ ተግባር ነው። በዚህ ተግባራቸውም ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ የነበራትን እንግዶችን የመቀበል ታሪክ አስቀጥለዋል።
ኢትዮጵያ ስደተኞችን የመቀበል ታሪኳ ደምቆ ከሚነገርባቸው ክስተቶች አንዱ ከመካ ተሰድደው የመጡ የእስልምና እምነት ተከታዮችን ተቀብላ ከማስተናገዷ ጋር የተያያዘው ነው። ነብዩ መሃመድ የእስልምና እምነትን ለማስፋፋት ሲነሱ፣ በመካ የነበሩ የባዕድ እምነት ተከታዮች ተቃወሟቸው። ተቋውሟቸውም እስከ ማሳደድና የአማኞችንም ሕይወት እስከማጥፋት የደረሰ ነበር።
በዚህ የጭንቅ ወቅት ነብዩ መሃመድ ተከታዮቻችን ለሁለት ጊዜ ያህል ወደ ኢትዮጵያ በመላክ ከባዕድ አማኞቹ ጨካኝ በትር ማዳን ችለዋል። በወቅቱም እነዚህን አማኞች ተቀብሎ ዋስትና መስጠት ይህን ዓለም አቀፋዊ መልዕክት መሠረት ለመጣል እንደ ሀገር፣ እንደ መንግሥትና እንደ ሕዝብ መስዋዕትነት የከፈለ ከሐበሻ በቀር ማንም የለም።
ኢትዮጵያ እንደ ሀገር፣ አስሃማ እንደ ንጉሥ፣ ሐበሾች እንደ ዜጋ በነቢዩ ሙሐመድ (ሰዐወ) በኩል በጊዜው የተሰጣቸው ክብር ምን እንደሚመስል ከነቢዩ (ሰዐወ) ሀዲሶች፣ ከሙስሊም ደራሲያን የተዘገቡትን በመጠኑም ቢሆን እናስቀምጣለን። አላህ (ሱወ) ምሁራንና ከሚጠቁማቸው እንጂ ከራሳቸው የማይናገሩት ነቢዩ ሙሐመድ (ሰዐወ) ባስተላለፉት መልዕክት፤ ሐበሻን፣-
1ኛ፡- ‹‹የእውነት ምድር» ብለዋታል፤ ይህ አባባል ምንም እንኳ መካ የተከበረው የአላህ ቤት የሚገኝበት ቢሆንም፤ በወቅቱ ፍትህና እውነት ስለጠፋ ነቢዩ ሙሐመድ (ሰዐወ) እና ተከታዮቻቸው ለስቃይና ችግር ተጋልጠው ነበር። የሚፈለገው ፍትህና እውነት ግን በሐበሻ መሬት በጊዜው ተግባራዊ መሆን ችሏል። ስለዚህ ነቢዩ ሙሐመድ (ሰዐወ) ሲታገሉለት የነበረው ፍትህና እውነት ከመካ ከ16 ዓመት በፊት በሐበሻ ምድር ተረጋግጦ ነበር። ለዚህ ነው ሐበሻ የፍትህና የእውነት ምድር በመሆን መካን የቀደመችው።
2ኛ፡- የማይበድል ሀቀኛ ንጉስ ያለባት ሀገር ተብላለች። ይህም በዘመኑ በአካባቢው የተለያዩ ነገስታት ቢኖሩም ሀቀኛና ፍትሀዊ ንጉስ የነበረው ግን ነጃሺ ብቻ ነበር።
3ኛ፡- ‹‹እሱ ዘንድ ማንም በደል አይደርስበትም» የተባለውም ሀገሪቷ የእውነት ምድር በመሆኗ፣ ንጉሱም ፍትሀዊ በመሆኑ፣ እሱ ዘንድ ማንም ሰው ቀለም፣ ቋንቋ፣ ብሔር ሳይገድበው ሰብዓዊ መብቱና ክብሩ ይጠበቅለትና ይረጋገጥለት ነበር።
እውነት ነው፣ ስደተኞች ምንም እንኳ ከሐበሻ ጋር ቋንቋ፣ ብሔር፣ ባህል፣ ወግ፣ ቀለም ባያዛምዳቸውም ባደረጉት የ16 ዓመት ቆይታ በእነሱ ላይ የተፈፀመባቸው ግፍም ሆነ በደል ፈፅሞ አልነበረም። እምነታቸውን በነፃነት ተግባራዊ እያደረጉ ከመንግስትም ሆነ ከሕዝቡ አስፈላጊ ድጋፍ፣ ድጐማና እንክብካቤ እየተደረገላቸው መቆየት ችለዋል። የስደት ቆይታቸውን ጨርሰው እስከሚመለሱ ድረስ ከነሱ ውስጥ አንድም ቅሬታ ያቀረበ ስደተኛ አልነበረም። እንዲያውም ለሐበሻ ምድር፣ ለንጉሱና ለሕዝቧ ከፍተኛ ፍቅርና ክብር ነበራቸው።
4ኛ፡- በዘመኑ በመንግሥት ደረጃ እስልምናን በማስተናገድ ሐበሻ የመጀመሪያ የመንግሥት ሀገር ነች። እስልምናን በመቀበልም ከመካ ቀጥላ ሁለተኛ ነች። በግለሰብ ደረጃም ቢሆን በወንዶች ሐበሻ ሁለተኛ ነች። ይህም ቢላል ቢን ረባህ አል ሐበሺ (ረዓ) እስልምናን በመቀበል ከአቡበከር (ረዓ) ቀጥሎ ሁለተኛው አማኝ በመሆኑ ነው።
ኢብነል አቲር የሚባሉት ዘጋቢ እንደጠቀሱት፣ ነቢዩ ሙሐመድ (ሰዐወ) ኡካዝ በሚባል የገበያ ማዕከል ለተሰበሰበው ሕዝብ ኢስላማዊ ጥሪ ያስተላልፉ ነበር። አንድ አምር ቢን አበሳህ የሚባል ታዋቂ ግለሰብ ነቢዩን (ሰዐወ) እንዲህ ሲል ጠየቃቸው። «ይህን ጥሪህን ማን ተቀበለህ?» አላቸው «አቡበከርና _ ቢላል» _ ብለው መለሱለት። ኢትዮጵያዊው ቢላል (ረዓ) እስልምናን ቢቀበልም ከአሠሪዎቹ ችግር እንዳይፈጠርበት ነቢዩ ሙሐመድ (ሰዐወ) በሰጡት ምክር መሠረት እስልምናውን በግልፅ አላወጀም ነበር።
ከሴቶች ኢትዮጵያዊቷ ኡሙ አይመን (ረዐ) ከኸድጃ (ረዐ) ቀጥላ ነው እስልምናን የተቀበለችው። በሀገር ከመካ ቀጥላ ኢትዮጵያ ነች። በአህጉር አንደኛ አፍሪካ ነች። የእውነት ምድር በመባል ከመካ በ16 ዓመት እንቀድማለን። የእስልምና መመሪያን በተለይ ዘካና ፆምን በመቀበልና በመፈፀም ከመካ በ6 ዓመት ኢትዮጵያ ትቀድማለች። በጂሀድ በመሰዋት የመጀመሪያው መሀጃ አልሐበሺ (ረዐ) ነው። ኢስላማዊ ስደትን ዓለም አቀፋዊ ደረጃ በማስተናገድ ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሀገር ነች።
5ኛ፡- ሙሐመድ የሚባለው ስያሜ በአሁኑ ወቅት በዓለማችን አንደኛ ስያሜ ሆኖ ይገኛል። ይህ ስያሜ ከነቢዩ (ሰዐወ) ቀጥሎ በሐበሻ የተወለዱ የሙሀጅሮች ልጆች ነበሩ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰየሙበት። እነሱም ሙሐመድ ቢንጃዕፈር (ረዐ)፣ ሙሐመድ ቢን ሁዘይፋ (ረዐ)፣ ሙሐመድ ቢን ኻጣብ (ረዐ)፣ መሐመድ ቢን ሀጢብ (ረዐ) ናቸው።
6ኛ፡- በእስልምና ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የውርስ ሥነ ሥርዓትን በተመለከተ በሐበሻ ምድር በስደት ላይ በሞተው አዴይ ቢን ነዲላ (ረዐ) በሚባለው ስደተኛ ነው የተጀመረው። ይኸውም ነቢዩ ሙሐመድ (ሰዐወ) ሀብትና ንብረቱን ቤተሰቦቹ እንዲወርሱት ስለአዘዙ ኑ እማን (ረዐ) የሚባለው ልጁ ወርሶታል። ይህ የውርስ ሥርዓት ኢስላማዊ ደንብ ሆኖ እንዲቀጥል ተደረገ።
ነቢዩ ሙሐመድ (ሰዐወ) ዓለም አቀፋዊ የሆነው የመጨረሻውን ልዩ መልዕክት እንዲያስተላልፉ ነው የታዘዙት። ቀደም ሲል በጎሳቸው በኩል ትልቅ ከበሬታ ይሰጣቸው ነበር። ይህን ጥሪ በማስተላለፋቸው ብቻ ከመካ ቁረይሾችና ከመዲና ይሁዲዎች ትልቅ ችግርና ተቃውሞ አጋጥሟቸዋል። አላህ (ሱወ) እሳቸውን እንደሚጠብቃቸውና መልዕክታቸው ተግባራዊ ላይ ግን እንደሚሆን ቃል ገብቶላቸዋል። በተከታዮቻቸው ላይ ግን ተፅዕኖ፣ ግርፋት፣ ስቃይና ሰቆቃ አስከትሎባቸዋል።
በዚህ ጊዜ ነበር ለነቢዩ (ሰዐወ) ተከታዮች እፎይታ የሚያገኙበት ቦታ ያስፈለጋቸው። በወቅቱ እምነቱን በመቀበል ተግባራዊ የሚያደርጉ ምዕመናን ያስፈልጓቸው ነበር። ለዚህም ሐበሻ እንደ ሀገር፣ ንጉሥ አስሃማ እንደ ንጉሥ፣ ሐበሾች እንደ ዜጋ ነበሩ ለነቢዩ (ሰዐወ)፣ ለተከታዮቻቸውና ለመልዕክቱ በቅድሚያ አዎንታዊ መልስ የሰጡት። ይህን በማድረጋቸው በቁርዓንም ሆነ በነቢዩ (ሰዐወ) ሀዲስ በልዩ ሁኔታ ለሐበሾች ለየት ያለ ክብር ተሰጥቷቸዋል። እሳቸውም (ሰዐወ) በልዩ አቋማቸው ለሐበሾች ልዩ ከበሬታ ሰጥተዋል።
ከእነዚህ ከበሬታዎችም፡-
1ኛ፡- ኢትዮጵያን እና ሐበሻን በተመለከተ «ሐበሾች እስካልነኳችሁ ድረስ አትንኳቸው» የሚል ነቢያዊ መመሪያ ሰጥተዋል። ይህም ቃላቸው በሱነን ኢብን ዳውድ ተመዝግቦ ይገኛል። ተከታዮቻቸውም ይህንን ተግባራዊ በማድረግ እስልምናን ለማሰራጨት በምስራቅ እስከ ቻይና፣ በምዕራብ እስከ ፈረንሳይና ስፔይን፣ ወደ ሰሜንና ምዕራብ አፍሪካ ድረስ ዘመቻ ሲያካሂዱ ወደ ሐበሻ ምድር የተደረገ አንድም ዘመቻ አልነበረም።
ይህንን ነቢያዊ ትዕዛዝ ተግባራዊ ከማድረግ አንፃር ሐበሻ በነቢዩ (ሰዐወ) ጊዜ የተደረገውን ስደተኞችን መቀበል ብቻ ሳይሆን፣ ከዚያም በኋላ በተለያዩ ጊዜያት በተከሰቱ የፖለቲካ አለመግባባትም ሆነ የኢኮኖሚ ችግር የአካባቢው ኗሪዎች ወይም በውጊያ የተሸነፉ ሁሉ እየመጡ ተጠልለውባታል። ይኸውም በሙዓዊያዎች፣ በአባሲዮች፣ በዑስማኒዮች ዘመናት ተሸናፊ ሁሉ ወደ ሐበሻ እየተሰደዱ የመጡ ሲሆን፤ ሐበሻ ለሁሉም መጠለያና መጠጊያ ስትሆን ቆይታለች።
2ኛ፡- ነቢዩ ሙሐመድ (ሰዐወ) በ8ኛው ዓመተ ሂጅራ በእስልምና ታሪክ ውስጥ ትልቅ ክብርና ታሪክ የፈፀሙት መካን በመክፈት መሆኑ ይታወቃል። ይህም ከ21 ዓመት ትግል በኋላ ቁረይሾችን ድል በማድረግ ነበር መካን የከፈቱት። በዚያ ዕለት ፍትህና ሀቅ በመካ ስለተረጋገጠ ‹‹የእውነት ምድር» የሚለው ነቢያዊ አባባል ተግባራዊ መሆን ቻለ። አላህም (ሱወ) በቁርዓን ሱረት ኢስራ ምዕራፍ አንቀፅ 81 ላይ «እውነት ተረጋገጠ፣ ስህተት ተደመሰሰ» ሲል ያበሰረበት ዕለት ነበር።
በዚያን ዕለት የተቀደሰው የአላህ ቤት ካዕባ ከጣዖታት አምልኰ ነፃ ሆኖ ለባለቤቱ ለአላህ (ሱወ) ተመለሰ። በዚያም ከ360 ያላነሱ ጣዖታት ሲደመሰሱ የነቢዩላህ ኢብራሂም (ዐሰ) ጸሎት መልስ ያገኘበት፣ በሰማይ ያለው የአላህ ቤት በምድር ካለው ጋር ግንኙነት ያደረገበት፣ በሰማይ የሚገኙ መላዕክታት ሁሉ ሱጁድ በመውረድ ለጌታቸው ምስጋና ያቀረቡበት ዕለት ነበር።
በዕለቱም ነቢዩ ሙሐመድ (ሰዐወ) ሐበሾችን በተመለከተ ሁለት ልዩ ከበሬታ ሰጥተዋል። አንደኛው፣ በካዕባው ውስጥ የነበሩት ጣዖታትን ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ ስለፈለጉ ዑስማን ኢብን ጦልሃ (ረዓ) የሚባለውን የካዕባውን ቁልፍ ያዥ የተቀደሰውን ካዕባ እንዲከፍት አዘዙት፣ እሱም ትዕዛዙን በማክበር ከፈተላቸው። የካዕባው በር እንደተከፈተ ሁሉም _ የነቢዩ (ሰዐወ) ተከታዮች በተለይ የቅርብ ጓደኞቻቸው የሆኑት እነ አቡበከር (ረዓ)፣ ዑመር (ረዓ)፣ ዑስማን (ረዓ)፣ ዓሊ (ረዓ) እና ሌሎቹም ከነቢዩ (ሰዐወ) ጋር ወደ ካዕባው ውስጥ አብረው ለመግባት በጉጉት ይጠብቁ ነበር።
ነቢዩ (ሰዐወ) ግን አብረዋቸው እንዲገቡ የመረጡት በጣም የሚወዱትና የሚያከብሩት የአሳዳጊያቸው ልጅ የሆነውና መካን ድል ባደረጉበት በዚያ ዕለት ካዕባን ሰባት ጊዜ ጡዓፍ ሲያደርጉ ግመላቸው ላይ አብሮ ተቀምጦ አብሯቸው ካዕባን ሰባት ጊዜ ጡዓፍ ያደረገው የሐበሻይቱ እመቤት የኡሙ አይመን (ረዓ) ልጅ ዑሳማ ቢን ዘይድ (ረዓ) እና ልዩ ቃል አቀባያቸውና ሙአዚናቸው ቢላል ቢን ረባህ አል ሐበሺ (ረዓ) ብቻ ነበሩ።
3ኛ፡- ኢብኑ ዑመር በዘገቡት ሀዲስ ነቢዩ (ሰዐወ) «ሐበሻን በቤቱ ያስገባ ትሩፋት ያገኛል› ብለዋል።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ስደተኞችን ተቀብላ በማኖርና እምነታቸውንም በነጻነት እንዲያከናውኑ በማድረግ ደማቅ ታሪክ ያላት ሀገር ነች። የአይሁድ፤ የክርስትናና የእስልምና ኃይማኖቶችን ተቀብላ በአንድትና በወንድማማችነት በሀገራቸው እንዲኖሩ ያደረገች ድንቅ ሀገር ነች። ዛሬም ይህም አኩሪ እሴት ቀጥሎ ብዙዎችን እያስገረመ ይገኛል።
(ይህንን ጽሁፍ ስናዘጋጅ በዋነኝነት በረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል የተጻፈውን ‹‹አበሾች በነብዩ ዙርያ›› የሚለውን መጽሃፍ ተጠቅሜያለሁ።)
እስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም