የተቆረቆረችው የስምጥ ሸለቆ ምሥራቃዊ ክፈፍን እና የኢትዮ፤ ጅቡቲ የባቡር ሐዲድ መዘርጋትን ተከትሎ ነው። የንግድ ኮሪደርም ናት፤ ይህ ሁሉ ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚመጡ ዜጎች ዓይናቸውን እንዲያማትሩባት አድርጓታል። የተለያየ ባሕል እና የኑሮ ዘይቤ ያላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ያለ ልዩነት ተቻችለውና ተዋድደው ይኖሩባታል።
የሙቀት መጠኗ ከፍተኛ ቢሆንም ማኅበረሰቡ ኑሮውን በዚህች ከተማ ለማድረግ አልተቸገረም። የሀገር ውስጥና እና ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች በጉዞ እቅዳቸው ውስጥ ቀዳሚ ያደርጓታል። ፍቅር፣ አብሮ መብላት፣ መረዳዳት እና ግልፅነት የነዋሪዎቿ መገለጫ እንደሆነ ለዘመናት ተነግሮላታል። የንግድ እንቅስቃሴን ለማፋጠን የሚረዳ የባቡር መስመር ወደ ከተማዋ ጉያ መመላለሱ ሞቅ ደመቅ ያለ ድባብ እንዲኖራት ምክንያት ነበር።
በእነዚህ ምክንያት ተወዳጅና ተመራጭ ከተማ ሆና ከምዕተ ዓመታት በላይ ለዘለቀ ጊዜ ቆይታለች። ይህ ድባብ ግን ከዓመታት በፊት በቆመው የባቡር ትራንስፖርትና የንግድ መቆም ገጽታ አዳክሞት ነበር። ይሁን እንጂ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት መጀመር ዳግም እያነቃቃት ይመስላል። ይህቺ ለዘመናት በተወዳጅነቷና በቱሪስት መናኻሪያነቷ የምትታወቀው የድሬዳዋ ከተማ ነች።
የዝግጅት ክፍላችን በዛሬው የባሕልና ቱሪዝም ገጽ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በቱሪዝም ዘርፍ እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶችንና ዳግም የከተማዋን የተነቃቃ እንቅስቃሴ ለመመለስ ስለሚደረገው ጥረት ዳሰሳ ያደርጋል። ወይዘሮ ነኢማ ኢብራሂም ሸሪፍ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የቱሪዝም ዘርፍ ኃላፊ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ የከተማዋን የቱሪዝም እና ሆስፒታሊቲ ዘርፍ፣ ወደ ቀድሞው የተነቃቃ የንግድና ሰፊ ማኅበራዊ መስተጋብር ለመመለስ እየተሠራ ነው።
ዘንድሮ የቱሪዝም ሆስፒታሊቲ (አገልግሎት) ዘርፉን ለማላቅ ወደ ዘጠኝ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎችን ሥራ ለማስጀመር ባለሀብቶቹ እቃዎችን እንዲያሟሉ እየተደረገ ይገኛል። ጽሕፈት ቤቱም ሆቴሎቹ በሙሉ አቅም ሥራ እንዲጀምሩ ድጋፍ ያደርጋል። የድሬዳዋ ከተማ በስፖርት ቱሪዝም ዘርፍ ተጠቃሚ እንድትሆን ለማስቻል ዘንድሮ ውጤታማ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን የሚናገሩት ኃላፊዋ፣ የፕሪሚየርሊግ እና የብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ማስተናገድ የሚችል ብሔራዊ ስታዲየም ግንባታ መካሄዱን ይጠቅሳሉ።
የዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) የባለሙያዎች ቡድን የድሬዳዋ ስታዲየም በ54 ሚሊዮን ብር ወጪ ሰው ሠራሽ የሣር ንጣፍ የለበሰውን የድሬዳዋ ስታዲየምን ብቃትና ደረጃ መገመገሙንና ማፅደቁን የሚናገሩት ወይዘሮ ነኢማ፣ ይህም ከስፖርቱ ባሻገር በቱሪዝም ዘርፍ ከተማዋ እንድትነቃቃ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ያስረዳሉ። ወይዘሮ ነኢማ በድሬዳዋ ከሚገኙ የተፈጥሮ መስሕቦች ውስጥ ቀላአድ የዱር እንስሳት ፓርክ አንዱ መሆኑን ይገልፃሉ።
ላለፉት ስምንት ዓመታትም ፓርኩን በተመለከተ ከኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር በመተባበር በተከለለው ፓርክ ውስጥ የሚገኙ የተፈጥሮ እንዲሁም የዱር እንስሳት ሀብቶችን የሚጠበቁበት፣ የሚለሙበትና ለጎብኚዎች መዳረሻነት በስፋት የሚተዋወቁበት ማስፈፀሚያ መመሪያ፣ ሕግና ደንብ በያዝነው ዓመት ባለፉት ስድስት ወራት ተጠናቅቆ እንዲፀደቅ ወደ ምክር ቤት መላኩን ይናገራሉ።
ይህ ሲፀድቅ በተያዘው የበጀት ዓመት በቀጥታ ወደ ሥራ መግባት እንደሚገባ አስታውቀዋል። እሳቸው እንዳብራሩት፤ የቱሪዝም ዘርፍ ኃላፊዋ ከቀለዓድ የዱር እንስሳት ፓርክ በተጨማሪ ሌሎች አዳዲስ መዳረሻዎች የማልማት የመጠበቅና ለቱሪስቱ ተጨማሪ መስሕብ አማራጭ እንዲሆኑ የማስተዋወቅ ተግባር እየተከናወነ ነው፡፡ ለእዚህ በምሳሌነትም በሀርላ የሚገኘውን ታሪካዊ ጥብቅ ቅርስ ያነሳሉ። የመካከለኛ ዘመን ታሪክ ባለቤት በሆነችው በጥንታዊቷ ሀርላ ከተማ ከ6ኛ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ረጅም እድሜ ያስቆጠረ ኪነ ሕንፃ በአርኪዮሎጂስቶች በቁፋሮ መገኘቱን ይጠቁማሉ።
ጥንታዊቷ የሀርላ መንደር የተገነባችው በሁለት ዋና ዋና ኮረብታዎች እና ትንንሽ ኮረብታዎች፣ እንዲሁም ወደ ሰሜን አቅጣጫ ተዳፋት ቦታ ላይ በትልልቅ ድንጋዮች በተካቡ ስፍራዎች ላይ መሆኑን የሚናገሩት ኃላፊዋ፣ በዚህ መንደር ላይም በርካታ የአርኪዮሎጂካል ቆፋሪዎች በተለይም በመኖሪያ ቤቶች ፣ በመቃብር ስፍራዎች እና መስጊዶች ላይ የተለያዩ ጥናቶች ማድረጋቸውን ያስረዳሉ።
በፕሮፌሰር ቲሞቲ አሌክሳንደር የሚመራው የሀርላ የአርኪዮሎጂስት ጥናት ቡድን የተለያዩ ጥናትና ምርምሮችን እያደረጉ መሆኑን አንስተውም ጥናቶቹም መስጊዶች፣ የጌጣጌጥ መሥሪያ ድንጋዮች፣ ሕንጻዎች፣ መቃብሮች፣ ከኢንዱስትሪያል አገልግሎቶች ጋር ተዛማጅነት ያላቸው ቤቶች (ምናልባትም የልብስ ፋብሪካ ሊሆን የሚችል)፣ ሰፋ ያለ የኪነ ሕንጻ አካል ምናልባትም የሲቪል አገልግሎት የነበረው፣ በርካታ መኖሪያ ቤቶች፣ መሥሪያ ቤቶች ምናልባትም አልባሳት መሥሪያዎች እና የመሳሰሉት ጥንታዊ ቅርሶች በአርኪዮሎጂካል ቆፋሪዎች መገኘታቸውን የጥናት ቡድን መሪ ይፋ ማድረጉን ያስረዳሉ።
የመካከለኛ ዘመን ታሪክ በሆነችው ሀርላ ላይ የተለያዩ ጥናት እና ምርምሮች ተደርገው በርካታ ታሪካዊ ቅርሶች መገኘታቸውን የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ይፋ ማድረጉን አስታውቀው፣ እነዚህን የተለያዩ ተግባራት ይከናወንባቸው የነበሩ ጥንታዊ ቦታዎችን እና በቁፋሮ የተገኙ ጥንታዊ መስጊዶች ለጎብኝዎች በሚያመች ሁኔታ የተዘጋጁ ስለሆኑ በስፍራው በመሄድ መጎብኘት እንደሚቻልም ተጨማሪ ቅርሶችንም በቁፋሮ የመፈለግ ሥራው እንደሚቀጥል ወይዘሮ ነኢማ ለዝግጅት ክፍላችን ገልፀውልናል።
በየትኛውም ሀገር ላይ የማይገኙ ቅርሶች በኢትዮጵያ ሀርላ ላይ እንደተገኙና በተለይም አብዛኛዎቹ ጥናትና ምርምሮችም በኢትዮጵያውያን አርኪዮሎጂስቶች እየተጠኑ ያሉ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ሥራውን ልዩ እንደሚያደርገው የድሬዳዋ ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ማረጋገጡን ወይዘሮ ነኢማ ይናገራሉ። የድሬዳዋ ማኅበረሰብ እንግዶችን የሚቀበል በትና ባሕሉ፣ በወጉና በተወዳጅ መስተንግዶው እንደሚታወቅ የሚናገሩት የቱሪዝም ዘርፍ ኃላፊዋ፣ ከቅርስ፣ ከተፈጥሮ ቱሪዝም ባሻገር በሃይማኖታዊ ፌስቲቫሎችም እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው ጎብኚዎች ከተማዋን ተመራጭ እንደሚያደርጋት ይገልፃሉ።
ባለፉት ስድስት ወራትም በሐምሌና በታኅሣሥ የገብርኤል በዓል አከባበር የተገኙትን የሀገር ውስጥና የውጪ አገራት ጎብኚዎች በምሳሌነት ማንሳት እንደሚቻል ይገልፃሉ። ክብረ በዓሉን ተከትሎ በርካታ የድሬዳዋ ተወላጆች፣ ከተማዋን የሚወዱና ለመጎብኘት የሚፈልጉ (በሀገር ውስጥም በውጪም የሚኖሩ) ዜጎች ወደ ድሬዳዋ በብዛት መግባታቸውን የሚገልፁት ኃላፊዋ፣ ይህንን ተከትሎ በኢንቨስ ትመንት ላይ መሳተፍ የሚፈልጉትን በማበረታታት ውጤት መመዝገቡንም አስታውቀዋል፡፡ ይህም ድሬዳዋን ተጨማሪ የቱሪስት መዳረሻ እንዳደረጋት ያስረዳሉ።
‹‹የድሬዳዋ ሕዝብ ሙስሊም ክርስቲያኑ የሃይማኖት ልዩነት ሳይገድበው ተቻችሎና ተከባብሮ መኖር የሚያስችል ባሕል ያለው ነው›› የሚሉት ወይዘሮ ነኢማ፤ በፆም ወቅት ሙስሊሙ ምግቡን ከጎረቤት ከርስቲያን ወንድም እህቶቹ ጋር ተካፍሎ የሚመገብበት የወንድማማችነት ሥርዓት እንዳለው ነው ያስታወቁት፡፡ ክርስቲያኑም በልዩ ልዩ በዓላዊ ዝግጅቶቹ መሰል ድርጊት እንደሚያከናውን አመልክተዋል። ይህንን የመቻቻል ተምሳሌት ለመጠበቅና ለመላው ዓለም ምሳሌ እንዲሆን ለማስቻል ሥርዓቱ ወግ ባሕሉን እንዲጠብቅ የከተማዋ አስተዳደር እንዲሁም ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤቱ ድጋፍ እንደሚያደርግ ይገልፃሉ። ይህ አብሮነትን የሚያጎለብት የአንድነት እሴትን የሚያጠናክር በመሆኑ በትላልቅ ዝግጅቶች እንደሚከበር ተናግረዋል።
‹‹ነፃ የንግድ ቀጣና ድሬዳዋ ላይ ይገኛል›› የሚሉት የቱሪዝም ዘርፍ ኃላፊዋ፤ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን የሚያሳትፍ የንግድና የቴክኖሎጂ ኤክስፖ በድሬዳዋ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ ይናገራሉ። ይህ አጋጣሚም ድሬዳዋን በንግድ ቱሪዝም ለማስተዋወቅ የቀድሞ መልካም ትዝታዋንም ለመመለስ እንደሚረዳ ያስረዳሉ። በተጨማሪ በየካቲት ወር ላይ ታሪካዊውን የድሬዳዋ ምድር ባቡር ተርሚናልን በ13 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ጥገናና እድሳት ለማድረግ ከአሸናፊው ሥራ ተቋራጭ ጋር የውል ስምምነት መፈፀሙን ይናገራሉ።
ጽሕፈት ቤቱ ከ100 በላይ ዓመታት ያስቆጠረውና ከድሬዳዋ ሕዝብ ሥነ ልቦና ጋር እጅጉን የተቆራኘው የድሬዳዋ ምድር ባቡር ታሪካዊ ይዘቱንና ቅርስነቱን ጠብቆ ጥገናና እድሳት በማድረግ የቱሪዝም መዳረሻ ሆኖ ለትውልድ እንዲተላለፍ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሠራ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
የጽሕፈት ቤቱ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በከተማዋ የሚገኙ ታሪካዊ ቅርሶችን፣ ባሕላዊ እሴቶችን፣ ፌስቲቫሎችን የተፈጥሮ ሀብቶችን ለማልማት፣ ለመጠበቅ እንዲሁም ለመላው ዓለም በማስተዋወቅ ከተማዋን የቱሪስቶች መዳረሻ ለማድረግ ሰፊ ሥራ እየተሠራ ነው። ድሬዳዋ ከተማ በርካታ የመስሕብ ሀብቶች ያሏት ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል የጎብኚዎችን ቀልብ የሚስበው ቀፊራ ክፍት የገበያ ማዕከል ነው። ጽሕፈት ቤቱ ለዝግጅት ክፍላችን የላከው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ የገበያ ማዕከሉ በከተዋን ከሚገኙ የተለያዩ የገበያ ቦታዎች በትልቅነቱ የሚታወቅና በይዘቱም እንደ መርካቶ ካሉ የገበያ ቦታዎች ጋር የሚወዳደር ነው። ገበያውን ልዩ የሚያደርገው በቦታው ለገበያ የሚቀርቡ እቃዎችና ምርቶች በአይነታቸው መብዛት ብቻ ሳይሆን የገጠርና የከተማ ነዋሪዎች የሚገበያዩበት በመሆኑ ነው፡፡
የገበያ ማዕከሉ ስያሜውን ያገኘው ‹‹ቃፊር›› ከሚለው የዓረብኛ ቃል ሲሆን፣ ትርጉሙም ‹‹ዘብ ›› ማለት ነው ፤ የገበያው ውጫዊ አጥር የኪነ ሕንፃ ጥበብ ማራኪና ለየት ያለ በመሆኑ እንዲሁም ረጅም እድሜ ያስቆጠረ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በቅርስነት የተመዘገበ ሲሆን በርካታ የሃገርና የውጪ ሃገር ቱሪስቶች እየጎበኙት ይገኛል፡፡
ሌላው የድሬዳዋ ከተማ መስሕብ የድሬዳዋ ቤተ መንግሥት ነው፤ ቤተመንግሥቱ የከተማዋ እንብርት በሆነው በመሐል ከዚራ በከፍታማ ቦታ ላይ ያረፈ ነው። በጊዜው የነበሩት አስተዳዳሪዎች ከተማዋን ለመቆጣጠር እንዲያመቻቸው አስበው እንደሠሩት ይታመናል። የቤተ መንግሥቱ የኪነ ሕንፃ አሠራር የዓረቢክ የቤት አሠራር ጥበብን የተላበሰ ሲሆን፣ በራስ መኮንን እንደተሠራም ይነገራል።
ቤተ መንግሥቱ በአፄ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግሥት በ1955 ዓም የመጀመሪያ ቅርጹን እና ውበቱን ሳይቀይር ሁለተኛው ፎቅና የግንብ አጥር እንደተገነባ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በ1960 ዓ.ም አፄ ኃይለሥላሴ ቤተመንግስቱን በጎበኙት ጊዜ የሠላም አዳራሽ ብለው እንደሰየሙት መረጃዎች ያስረዳሉ።
የከተማዋ ባሕልና ቱሪዝም እነዚህንና ሌሎች ሀብቶች ለመላው ዓለም በማስተዋወቅ የጎብኚዎችን ፍሰት ለመጨመር እየሠራ ይገኛል። በተለይ ባለፉት ስድስት ወራት የሆስፒታሊቲ ዘርፉን ለማዘመንና አገልግሎት ሰጪዎችን ጥራት ለማላቅ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ነው፡፡ እቅዱም የድሬዳዋ ታሪካዊ፣ ባሕላዊ ሀብቶችን፣ ጥንታዊ ቅርሶችንና የተፈጥሮ መስሕቦችን ለመጎብኘት ወደ ከተማዋ የሚመጡ ጎብኚዎች የተሟላ አገልግሎት እንዲያገኙ ማስቻልን ያለመ ነው።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን እሁድ መጋቢት 22 ቀን 2016 ዓ.ም