የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ አንደበት ቢኖረው፤ “ለኢትዮጵያ ሕዝብ ምስጋና ይግባውና ለዚህ በቅቻለሁ።” ይለን ነበር። ግንባታው የተጀመረበትን 13ኛ ዓመት በተለያዩ ዝግጅቶች ለማክበር የሚመለከታቸው አካላት ሽር ጉድ እያሉ እንደሆነ ይሰማኛል። ከተሰናዱ መርሐ ግብሮች አንዱ እውቅና ለሚገባቸው በአደባባይ እውቅና መስጠት ይሆናል ብዬ አምናለሁ። ይህ እንዳለ ሆኖ ግን በዚህ ሀገራዊ ፕሮጀክት ተግባራዊነት የማይተካ ሚና የነበረውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በግሌ እውቅና ለመስጠት ወደድሁ።
ግድቡ ዛሬ ለደረሰበት ስኬት የበቃው በብዙ ተዋንያን የሌት ተቀን ርብርብ እንደሆነ ብረዳም፣ ሕዝባዊ ተሳትፎው ግን ግዘፍ ይነሳብኛል። ሕዝብ ለዚህ የሰንደቅ ዓላማ ፕሮጀክት ስኬት ገንዘቡን፣ ጉልበቱንና እውቀቱን ያለስስት አበርክቷል። እያበረከተም ይገኛል። ከ1ኛ ደረጃ ተማሪ እስከ መምህራን፣ ከጉልት ነጋዴ እስከ ባለሀብት፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣ ከአባት አርበኛ እስከ ወታደር፣ ከቀን ሠራተኛ እስከ ደመወዝተኛ፣ ወዘተረፈ በነቂስ ወጥቶ ተሳትፏል።
በዚህ መልኩ በገንዘብ ብቻ ወደ 19 ቢሊዮን ብር ለግሷል። ቦንድ ገዝቷል። አሁንም ተሳትፎውን አጠናክሮ ቀጥሏል። ለዚህ ታላቅ ተግባሩም ለሕዝቡ ያለኝን ምስጋና እየገለጽሁ፤ ይሄ ሕዝብ ሊመሰገንባቸው የሚገቡ በርካታ ሠናይ ተግባራት ስላሉ እግረ መንገዴን ሰብሰብ አድርጌ ላወድሰውና ላሞካሸው ወደድሁ።
ለዘመናት ፈተናዎቹን ሁሉ ተቋቁሞ፤ ከምንም ነገር በላይ ሀገርን አስቀድሞና ሕልውናዋን አስቀጥሎ ከትውልድ ወደ ትውልድ እያስተላለፈ ያለ ታላቅ ሕዝብ ሚሊዮን ጊዜ ቢደነቅ፣ ቢመሰገንና ቢወደስ፣ ቅኔ ቢቀኙለት ያንስበታል እንጂ አይበዛበትም። ከጥላቻ፣ ከልዩነት፣ ከቂም በቀል፣ ከሴራና ከደባ፣ ከሐሰተኛና የተዛባ መረጃ በላይ ከፍታ ላይ ያለ ሕዝብ በቅጽል ጋጋታ ሌት ተቀን ቢሞካሽ ያንስበታል እንጅ አይበዛበትም።
ከርዕዮተ ዓለም፣ ከተቋም፣ ከሐሰተኛ ትርክት፣ ከታሪክ ምርኮኛነት፣ ከመደበኛና ከማኅበራዊ ሚዲያ በላይ የሆነ ታላቅ ሕዝብ ምስጋናና አድናቆት ቢጎርፍለት ያንሰዋል እንጂ አይበዛበትም። ማንነትን ዒላማ ካደረጉ ጥቃቶች፣ ግጭት፣ መፈናቀልና ብዝበዛ በላይ ሆኖ በሰውነት ማማ ላይ የተቀመጠ አስተዋይና አርቆ አሳቢ የሆነ ሕዝብ ለሰዓታት ቆመው እጅ እስኪቃጠል ቢያጨበጭቡለት ያንስበታል እንጂ አይበዛበትም። እየተራበ፣ እየተራዘና በድህነት እየተጎሳቆለ ለሀገሩ ሕልውና ሲል በምንም የማይተመንና የማይገለጽ ውድ ዋጋ እየከፈለ ላለ ሕዝብ ቅኔ ቢቀኙለትና መወድስ ቢፈስለት ያንሰዋል እንጂ አይበዛበትም።
በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ የሰሞነኛውን ጨምሮ እርስ በርሱ እንዲጋጭ፤ ወደለየለት አመፅና ተቃውሞ እንዲገባ ሺህ ጊዜ ቢተነኮስ፤ ሐሰተኛ መረጃ እንደ ፍላጻ ከየአቅጣጫው ቢንበለበልበት ሀገሬና አብሮነቴ ይበልጥብኛል ብሎ አርፋችሁ ተቀመጡ ያለ ልዩና ታላቅ ሕዝብ በአደባባይ ቢደነቅና ቢሸለም ያንስበታል እንጂ አይበዛበትም። የሟርተኞችና ክፉዎች የሚመኙትን ድሞፆች ሳይሆን የራሱን ድምፅ የሚያሰማ የሰከነ ሕዝብ ቢደነቅና ቢሞካሽ ያንስበታል እንጂ አይበዛበትም። ለዚህ ነው “መኅልዬ መኅልዬ ዘኢትዮጵያ ሕዝብ”ያልሁት።
መኀልየ መኀልይ ዘሰሎሞን፣ ከሁሉም የሚበልጥ የሰለሞን መዝሙር ማለት ነው፡፡ የሁለት ፍቅረኛሞች ንግግር ተደርጎም ይወሰዳል፡፡ የፍቅረኞች ንግግር በግጥም ነውና ምት፣ ዜማ አለው፡፡ ሰለሞን ስለ ሙሽራውና ሙሽሪት፣ ስለፈጣሪና ስለ ቤተ ክርስቲያን የዘመራቸውን 1005 መዝሙሮችን ይመለከታል፡፡ ሙሽራው ልዑል እግዚአብሔርን ሲወክል ሙሽራይቱ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡ መኅልይ እንደ ለዘብና ወረብ አይነት በፍጥነት የሚዘመር ጥዑም ዜማ ነው፡፡ መዝሙሮቹ በተለያየ ስልተ ዜማ ቢደጋገሙም ያው ስለፈጣሪና ቤተ ክርስቲያን ክብር፣ ቅድስና የሚመሰክሩ ናቸው፡፡ ይህ መጣጥፍ ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚዘክር፣ የሚያወድስና የሚያከበር ሆኖ ስለአገኘሁት “መኅልዬ መኅልዬ “ዘኢትዮጵያ ሕዝብ” ማለትን መርጫለሁ፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ታላቅነት በታላቁ መጽሐፍ በመጽሐፍ ቅዱስና በቅዱስ ቁርዓን ስሙ ተደጋግሞ ከመወሳት ይጀምራል። የሀገራችን ታሪክ ከካም ይመዘዝ ከኩሽ ወይም ከኢትዮጲስ ይሁን ከሳባ አልያም ከማክዳ፣ ከቀዳማዊ ምኒሊክ ወይም ከሳባውያን፣ ከሀበሻ ይሁን ከአግዓዚ፣ ወዘተ. መዳረሻው ታላቅነት ነው። የቀደምት ሥልጣኔያችን እርሾ የተጣለው ተቦክቶ የተጋገረው በዚህ የታላቅነት እልፍኝ ነው፡፡
ኢትዮጵያዊነት የተገመደበት ገመድ የተፈተለበት ቃጫ የበቀለው ከዚህ ታላቅ ምድር ነው፡፡ የሥነ ሕንጻ፣ የመርከብ፣ የንግድ፣ የመጀመሪያው የመገበያያ ገንዘብ፣ የእርሻ፣ የሥነ ፈለክ ከፍ ሲልም የሥነ መንግሥት መሠረታችን የተጣለው ኢትዮጵያም የተቀለሰችው በዚሁ ምድር ነው፡፡ ዛሬ ካስማዋ ድንኳኗ ጠቦ ጦቦ ቀይ ባሕርን ሱዳንን ደቡብ ዓረቢያን ባይሻገርም። የዚህ ሁሉ ከፍታችን ልዕልናችን የማዕዘን ድንጋይ ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡
ከእስክንድርም ይሁን ከፕቶሎሚ አልያም ከግሪክ መናገድ እንዲሁም ዲፕሎማሲ አሀዱ ያልነው በታላቋ ኢትዮጵያ በአዶሊስ ነው፡፡ ቀዳሚው የግንብ ቤተ መንግሥትም በኪንግሀም አልያም ኋይት ሐውስ ወይም ብሉ ሐውስ ሳይሆን አክሱም ነው፡፡ በዩኔስኮ በቅርስነት የተመዘገቡት እስከ 33 ሜትር የሚረዛዝሙ ከአንድ ድንጋይ የተቀረፁ ሐውልቶች፤ በቦና ጊዜ የተገነባው ምን አልባትም የመጀመሪያው የውሃ ማከፋፈያ፤ ዘብን በማቆም ንግድ መነገድ፤ የጽሕፈት ሥርዓት የተጀመረው፤ ከሁሉም በላይ በተለይ ንጉሥ አፍላስ ከሱዳን የተወሰነው ክፍል፤ ቀይ ባሕርን ተሻግሮ ደቡብ ምዕራብን ቆርሶ ከማስተዳደሩ ባሻገር የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥታዊ አገዛዝ መሥራች እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያትታሉ፡፡
ከእሱ በኋላ የነገሡት ኢላ አሚዳ፣ ኢዛና እና ካሌብ የአክሱምንና የኢትዮጵያን ሥልጣኔ አስቀጥለዋል። ሦስቱ አብርሃማዊ እምነቶች ክርስትና፣ አይሁድና እስልምና ወደ ሀገራችን የገቡትም በዚሁ ዘመን በዚሁ በር ነው፡፡ የመጀመሪያዎቹ የነብዩ መሐመድ ተከታዮች በነብያቸው ምሪት ተሰደው ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ እጁን ዘርግቶ የተቀበላቸው የክርስቲያን ንጉሥ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ የዛሬው የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት አስኳል እንበለው እራስ ወይም ዲ.ኤን.ኤ አልያም ልብ እንበለው የደም ሥር የሚመዘዘው ከዚህ ታላቅነት ነው።በዘመናት ጅረት፣ በትውልድ ቅብብሎሽ፣ በአይዶሎጂ ውርክብ አያረጅም፡፡ አይፈዝዝም፡፡ አይደበዝዝም፡፡ አይወይብም፡፡ አይጠወልግም፡፡ ለዚህ ነው ወጀቡን ማዕበሉን አልፎ ዛሬ ላይ የደረሰው። ሀገርንና አብሮነትን እያስቀጠለ ያለው።
የጥንታዊ ሥልጣኔ ፋና ወጊነት ከሚገለጽባቸው አንዱ በሆነው ሥነ ፈለክ ኢትዮጵያውያን ከፊተኛው ረድፍ ነበሩ። በኪነ ሕንጻና በጽሑፍም ቀዳሚ ነበሩ። ሀገራችን ከሦስት እና አራት ሺህ ዓመታት በፊት በሕዋ ምርምር ዘርፍ የዛሬዎቹን ልዕለ ኃያላን ከፊት ሆና ስትመራ እንደነበር፡፡ ለዚህም የጥንት ብራና መጽሐፍትና ስንክሳሮች ዋቢ ከመሆናቸው ባሻገር አለማቀፉ የአስትሮኖሚ ኅብረት በሀገራችን ልዕልት፣ ንግሥትና ንጉሥ ስም ኅብረ ከዋክብት (constellations) መሰየሙን ስንቶቻችን ይሆን የምናውቀው!? ስለ ቀደምት ኢትዮጵያውያን የሥነ-ፈለክ /የሕዋ/ እውቀትና በዘመን አቆጣጠር ምን ያህል የተራቀቁ እንደነበሩ በማስረጃ የሚተነትነው ዶክተር ሮዳስ ታደሰ እና የዶክተር ጌትነት ፈለቀ በጋራ በደረሱት፤ “አንድሮሜዳ” መጽሐፍ 5ኛ ዕትም ላይ፤ “…ከጥንት ጀምሮ እስከ ዛሬ ያሉ የውጭው ዓለም ታሪክ ጸሐፊዎች…’ጥንታዊ ዘር’ በመባል የምትታወቀውን ኢትዮጵያን …አውሮፓና እስያ ባልሠለጠኑበት ዘመን …ፍልስፍና፣ ሥነ ጽሑፍ፣ ሒሳብ፣ ግብርና፣ ሕክምና፣ የክዋክብት ጥናት …የኢትዮጵያውያን ነባር ሀገር በቀል እውቀቶች እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡…”ብለዋል፡፡ ይህም ቀደምት ኢትዮጵያውያን ለሥነ ፈለክ የማይናወጥ መሠረት እንደነበራቸው ያረጋግጣል ፡፡ የዛሬው ታላቅነቱ ምስጢር ቋጠሮ ከዚህም ይፈታል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የጥንት ሥልጣኔ ባለቤት መሆኗን እና ለሥነ-ፈለክ ምርምር ወረት፣ መነሻ እንደነበራት የሚያረጋግጡ የቀደምት ሊቃውንት እማኝነት ከፍ ሲል በተገለፀው መጽሐፍ እንደሚከተለው ተዘግቧል፡፡ “60 ዓመት ቅድመ ልደት ክርስቶስ የነበረው ዲዎዶርስ ሴኩለስ የተባለ የታሪክ ሊቅ ‘አውሮፓውያን ኋላ ቀር እድገት አኗኗር ላይ በነበሩበት ወቅት ኢትዮጵያ ታላቅ ሥልጣኔ ላይ የነበረች …ኢትዮጵያውያን ለግብፃውያን ሥልጣኔ ያስጀመሩና እስከ ሕንድ ድረስ የገዙ ናቸው ፡፡ ‘ …
በ700 ዓ.ም የነበረው የቤዛንታይኑ እስቲፋንስ ባካሄደው ጥልቅ ጥናት ‘ ኢትዮጵያ መሬታችን ላይ የተመሠረተች የመጀመሪያ ሀገር ናት’ ሲል አርኖልድ ኸርማን ሉድዊግ የተባለ የጀርመናዊ የታሪክ ጸሐፊ ደግሞ፣ ‘ኢትዮጵያን የመሰለ ጥንታዊ ሀገር ወዴት ይገኛል!?’ ሲል ይሞግታል፡፡ ከ800 ዓመት ከክርስቶስ ልደት በፊት የኖረው ሆሜር አሊያድና እና ኦዲሴይ በተባሉ ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎቹ ኢትዮጵያውያን ‘እስከ መሬት ጫፍ ድረስ የሚኖሩና ከአምላክ ጋር ቅርበት ያላቸው’ በማለት ይገልጻቸዋል፡፡
የታሪክ አባት በመባል የሚታወቀው ሔሮዶቶስ ኢትዮጵያውያንን ‘ከሰሐራ በታች የሚኖሩ፣ ጥቁር ቆዳ ያላቸው …ብልሆች፣ በዓላቶቻቸውና ሐሴታቸውም ሳይቀር አማልክትን ስለሚያስደስት የአማልክት አምላክ እየሄደ በዓላቱን በደስታ አብሯቸው ያሳልፋል’ ብሏል። … ዲዮዶር የተባለ የሮም ጸሐፊ ደግሞ ‘ ከግብፅ በፊት ሥልጡንና ገናና ነበረች ፡፡ ግብፅን ቅኝ ገዝታ 18 የኢትዮጵያ ነገሥታት ተፈራርቀውባታል፡፡ …’ ይላል ፡፡
ሲያወጋ ውሎ ቢያድር የማይሰለቸው ደራሲ ዓለማየሁ ገላጋይ (በግሌ ከብዕሩ ትዕባት ይልቅ አንደበተ ርዕቱነቱ ስለሚበልጥብኝ፤ ተመርጎ እንደከረመ የጨፋቂት ጊዎርጊስ የገብስ ጠላ ስለሚያረካኝ “ደራሲ” የሚለውን ማዕረጉን በተሰጠኝ ሥነ ጽሑፋዊ መብቴ poetic license ” አፈ ማር ” ብየዋለሁ ፡፡ ) በፍትሕ መጽሔት 2ኛ ዓመት ቁ 60 ታኅሣሥ 2012 ዓ.ም ዕትም፤ “ከሮኬት ሮክ ወደ ሳተላይት ሀልዮት” በሚል ርዕስ ‘ባወጋን’ መጣጥፉ “…ከእኛ ይልቅ አባቶቻችን ለሳተላይት ምንጠቃ የሚያበቃ የሕዋ እውቀት ነበራቸው፡፡ ሕዋውን በአቅጣጫ፣ ፕላኔቶችን በደረጃ መድበዋል፡፡ በጀት ባይኖር ትኩረት ፣ ሙከራ ባያደርጉ ሃልዮት ነበራቸው፡፡ ሰማየ ሰማያትን እግዚአብሔርን ባማከለ ዕውቀት (Theocentric) ለሰባት ከፍለው አንብረዋል፡፡ ሰባቱ ዓለማት (ሰማያት) መንበረ መንግሥታት ፣ ፅርሃ አርያም፣ ሰማየ ውድድ፣ ኢዮሪያሌም ሰማያት ፣ ኢዮር ፣ ራማ እና ኤረር ብለው ከፋፍለው አጥንተዋል፡፡ …”፣ ብሎናል፡፡
ሀገራችን የጥንታዊ ሥልጣኔ ባለቤት መሆኗን በአደባባይ ካስመሰከረ በኋላ በዓለማቀፉ የአስትሮኖሚ ኅብረት የተሰጣትን ቦታ ይተነትናል፡፡ “…ኅብረ ከዋክብት (constellations) ማለት በሰማይ ላይ የሆነ አይነት ቅርፅ የሚሠራ የከዋክብት ስብስብ ሲሆን ቅርጹም ከማይቶሎጂ ጋር በተያያዘ መልኩ የሰው፣ የእንስሳት ወይም ሕይወት የሌለው ነገር ሆኖ ሊገለጽ ይችላል፡፡ …ዓለማቀፉ የአስትሮኖሚ ኅብረት በ1930 ዓ.ም ከ88 ኅብራተ ከዋክብት ውስጥ ሦስቱን ማለትም አንድሮሜዳን ፣ ካሲዮፕያንና ሴፌውስን በኢትዮጵያውያን ስም መዝግቧል፡፡ … አንድሮሜዳ የኢትዮጵያ ልዕልት ስትሆን፤ ካሲዮፕያን ደግሞ የኢትዮጵያ ንግሥት ናት፡፡ ሴፌውስ ደግሞ የኢትዮጵያ ንጉሥ ነው ፡፡ …”
በአለት ላይ ስለተመሠረተው የኢትዮጵያ ሕዝብ የኋላ መነሻ ይሄን ያህል ካልሁ፤ ይሄን ታላቅ ሕዝብ የማመሰግንበትና የማወድስበት ሚሊዮን ምክንያቶች ቢኖሩኝም ሰሞነኛ መግፍኤዎችን እመለስባቸዋለሁ። ከዚያ በፊት ግን ይቺ ሀገር ከ3ሺህ በላይ ዓመታትን ነፃነቷን፣ ሉዓላዊነቷንና የግዛት አንድነቷን አስከብራና አስጠብቃ ያስቀጠለችው በሀገረ መንግሥቷ ፣ በአገዛዟ፣ በተቋማቷ፣ በመሪዎቿ ብቻ አልነበረም፡፡ ይልቁንም በታላቁና ንዑዱ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንጂ።
እንደ ሀገር የገጠሙን ፈተናዎችና ቀውሶች እንደዛሬው ሀገረ መንግሥትን፣ ተቋማትን፣ መሪዎችንና ልሒቃንን ተሻግረው ከአንዴም ሁለት ሦስት ጊዜ …ሊያንበረክኩንና ሊረቱን ሳለ የመጨረሻ ምሽግ ሆኖ የታደገን፤ ወደፊትም የሚታደገን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዝብ ስለመሆኑ ቅንጣት ታክል ስለማልጠራጠር ነው፤ ያለምንም ስስትና ንፍገት ታላቁን የኢትዮጵያን ሕዝብ “መኀልዬ መኀልዬ ዘኢትዮጵያ ሕዝብ፤” ስል መወድስ የያዝሁለት።
ወደተነሳሁበትና የዚህ ታላቅ ሕዝብ ትሩፋት ወደሆነው የህዳሴው ግድብ ስመለስ፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አፈፃፀም 95 በመቶ መድረሱን፤ የግድቡ አጠቃላይ የሲቪል ሥራው ግንባታ ደረጃ ደግሞ 98.9 በመቶ የደረሰ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ከታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ በሁለት ተርባይኖች 540 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እያመነጨ ይገኛል። አሁን ላይ ግድቡ የያዘው የውሃ መጠን 42 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ሲሆን፣ ሲጠናቀቅ የሚይዘው ውሃ መጠን ወደ 74 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ከፍ ይላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በ2016 በጀት ዓመት ስምንት ወራት ውስጥ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ931 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን እና የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት 2003 አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ከሀገር ውስጥ፣ ከውጪ እና ከቦንድ ሽያጭ ልገሳ እና ከልዩ ልዩ ገቢዎች ወደ 19 ቢሊየን ብር ከሕዝቡ በድጋፍ ተሰብስቧል፡፡
ሻሎም ! አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
አዲስ ዘመን መጋቢት 22 ቀን 2016 ዓ.ም