ታላቅ መፍትሔን ለሴቶች የሰነቀው የህዳሴው ግድብ

አነስ ያለች የገጠር ቀበሌ ነች። የአካባቢዋ ልምላሜ ዓይን የሚገዛ ነው። ከዳር ዳር አረንጓዴ ምንጣፍ መስሎ የተዘረጋው ቡቃያ ልብን የሆነ አንዳች ስሜት እንዲሰማ ያደርጋል። ከየጎጆዎቹ የሳር ክዳን ላይ የሚትጎለጎለው ጭስም ለአካባቢው ሌላ ድባብ ሰጥቶታል። ግብርና ሥራቸውም ኑሯቸውም የሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ቡቃያው ለአረም እስኪደርስ በየደጃፋቸው አረፍ የሚሉበት ወቅት ነው። ይሄን ጊዜ ጠላውንም ምግቡንም በአይነት በአይነት ለማሰናዳት ከግብርና በተረፈ ጉልበቷ የምትታትረው ሴቷ ናት።

መብራት አይታ የማታውቀውን የገጠር ጎጆ በብርሃን ለመሙላት፤ ገበያ ወርዶ ላንባ መግዛት የእሷን ጉልበት ይጠይቃል። የቤቱን ሙቀት ለመጠበቅም ምድጃ የሚፈልገውን እንጨት ለማምጣትም አሁንም ሴቷ ጫካ ገብታ እንጨት ለቅማ ተሸክማ መምጣት አለባት። ጠላ ለመጥመቅ ለሰባት ቀናት የተዘፈዘፈውን ደረቆት ለመቁላትም የሚሆኑ ወፋፍራም እንጨቶችን አዘጋጅታ ሌሊት ተነስታም ለማዘጋጀት ኃይልና ብርሃን ወሳኝ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ እንደገና ማልዳ ለቤተሰቡ ያሰናዳችውን ቁርስና ቡና ከአፍ ካደረሰች በኋላ ደግሞ ከሴት ልጆቿ ጋር በመተባበር የተቆላውን ደረቆት ሙሉ ቀን በእጇ ስትፈጭ ትውላለች።

ለድግሱም ፣ለማህበሩም፣ ለደቦውም ብቻ ባጠቃላይ ለሚያስፈለግ ድግስ በሙሉ እንጨት ከመልቀም አንስቶ ምግቡም መጠጡም ተሰናድቶ ሰው አፍ እስኪደርስ ድረስ የሴቷ ሙሉ አቅም ፈሶ አይኗ በጭስ ተጨናብሶ ወገቧ ጎብጦ ያለእድሜዋ አርጅታ እንድታልፍ ትሆናለች። ከጉልበት ጠያቂው ሥራ በተጨማሪም አርግዞ መውለድ፤ ልጅ ማሳደግም አሁንም የሴቷን ሙሉ አቅም የሚፈልግ ተግባር ነው።

ይህ ሰቆቃ በእኔ ይብቃ ያለች እናትም ልጆቿን ትምህርት ቤት ብትልክም ልጆቿ ትምህርት ቤት ከመሄዳቸው በፊት በሌሊት ተነስተው ውሃ ቀድተው ነው ጉዞን የሚጀምሩት። ልጆችም ትምህርት ቤት እንዳይረፍድባቸው እህል ቢጤ አፋቸው ላይ ጣል የሚያደርጉትም መንገድ ላይ ነው ። ቀን ትምህርቱና መንገዱ አድክሟቸው ቤት ሲያደርሳቸው ቤት የተገኘችውን ቀማምሰው ወንድ ልጆች ደብተራቸውን ይዘው ለእረኝነት ሲወጡ ሴቶቹ ልጆች ቤት ማጀት ውስጥ እናታቸውን ሲያግዙ ያመሻሉ።

ሥራው ሲያበቃ ምሽቱን የቤት ሥራ ለመሥራትም ሆነ የተማሩትን ለመመልከት ኩራዝ አብርተው የሚያመሹ ሲሆን፤ ጭሱ አፈንጫቸውን ሞልቶ ለተለያዩ ችግሮች ያጋልጣቸዋል። ላንባ መግዣው ሳንቲም ሲያጥርም ሆነ በተለያየ ምክንያት ሲጠፋ ማጥናቱም ቀርቶ በጨለማ ይታደራል።

በዚህ ሁሉ ሰቆቃ ውስጥ ኑሯቸውን ለሚገፉት ሴቶች መሰረተ ድንጋዩ ከተጣለ 13ኛ ዓመቱን ያስቆጠረው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ይዞ የሚመጣው ተስፋ ብሩህ ነው። የኃይል አቅርቦቱ በቀጭኑ መስመር የገጠር መንደሮችን በሙሉ ሲያዳርስ ጭስ ያጠፋው አይን ዳግም በተስፋ ይበራል።

ይህ ተስፋ የተጣለበት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ማክሰኞ 13ኛ ዓመቱን ይደፍናል፡፡ የግድቡ ግንባታ ከዛሬ 13 ዓመታት በፊት መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ነበር የተጀመረው፡፡ በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊም ኢትዮጵያ በታላቁ የዓባይ ወንዝ ላይ ከአፍሪካ ቀዳሚ ከዓለም ደግሞ ተጠቃሽ የሆነ ግዙፍ ግድብ መገንባት መጀመሯን በማብሰር በይፋ የመሠረት ድንጋዩን አኑረዋል፡፡

ከዚያም ወዲህ ግድቡ በበርካታ ውጣ ውረዶች ውስጥ አልፏል፡፡ የነበሩበትን እንደ ጨለማ የከበዱ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎች ተሻግሮ ከወር በፊት የመጀመሪያውን ኃይል ለማመንጨት ችሏል፡፡ ኢትዮጵያውያን ራሳቸው መሐንዲስም የፋይናንስ ምንጭም ሆነው ይገነቡታል የተባለለት ግድቡ 5 ዓመታትን እንደሚፈጅ ነበር በወቅቱ የተገለጸው፡፡ ሆኖም ግንባታው በተለያዩ ምክንያቶች ተጓቶ እነሆ 13ኛ ዓመቱ ላይ ደርሷል።

ለውጥ ከመጣበት ከ2010 ዓ.ም ወዲህም በግድቡ የግንባታ ፕሮጀክት ተስተውለዋል የተባሉ ህጸጾች ተነቅሰውና የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች ተቋራጩን እስከ መቀየር እንዲሁም የተርባይኖቹን ቁጥር ከ16 ወደ 13 እስከመቀነስ የደረሱ እርምጃዎች ተወስደው ግንባታው ቀጥሎ አሁን አጠቃላይ ግንባታው ወደመጠናቀቁ ቀርቧል።

ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው የግድቡ ሥራ ተጠናቆ 95 በመቶ ላይ ደርሷል። ጉባ ላይ የከተመው ይህ ታላቁ የህዳሴ ግድብ በአሁኑ ወቅት ከ42 ቢሊዮን ሜትር ኩዩብ በላይ ውሃ ይዟል።

ኢትዮጵያውያን ከመቀነታቸው ፈተው፤ ካላቸው ላይ አውጥተው የሰበሰቡት ገንዘብም በአስራ ሦስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ 18 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር መድረሱም ተሰምቷል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ በተገኘው መረጃ መሠረት የሲቪል ሥራው ግንባታው 98 ነጥብ 9 በመቶ የደረሰ ሲሆን፤ የኤሌክትሪክ መካኒካል ሥራዎች አፈጻጸም 76 በመቶ፤ የውሃ ማስተላለፊያ የብረታብረት ሥራዎችም 87 ነጥብ 1 በመቶ መድረስን ተመልክተናል።

ከዚህም በተጨማሪ አጠቃላይ የግድቡ ግንባታ የደረሰበት አማካኝ ደረጃ 95 በመቶ ሲሆን ግድቡ የያዘው የውሃ መጠን 42 ቢሊዮን ሜትር ኩብ፤ ከዋና ግድቡ ኋላ የተኛው ውሃ መጠንም 160 ኪሎ ሜትር ነው። ግድቡ ሲጠናቀቅ የሚይዘው የውሃ መጠን 74 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ሲሆን ከግድቡ ኋላ የሚተኛው የውሃ መጠን 256 ኪሎ ሜትር መሆኑን ያመለክታል።

አሁን ላይ በሁለት ተርባይኖች እየተመረተ ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል 540 ሜጋ ዋት ሲሆን፤ ግድቡ ሲጠናቀቅ የሚመረተው የኤሌክትሪክ ኃይልም 5 ሺ 150 ሜጋ ዋት ነው። በሰአት የሚመነጨው ኤሌክትሪክ ኃይልም 15 ሺ670 መሆኑን ሰምተናል።

ታዲያ ይህ ሁሉ ኃይል ተመርቶ አርሶ አደሩ ደጅ ሰተት ብሎ ሲደርስ በእጅ መፍጨት ቀርቶ ወፍጮው በቅርብ ሲተከል፤ እንጨት መሸከም ቀርቶ ምጣዱም ወጡም በኤሌክትሪክ ምድጃ ሲጣድ ጭስ ያጠፋው አይን አይበራም ትላላችሁ? ጥቀርሻ አፍንጫቸውን ሞልተው ጥናት ሲሉ የሚታመሙት ተማሪዎችስ ሌሊቱን ሙሉ አጥንተው ከቁም ነገር ለመድረስ ማን ከልካይ ኖሯቸው እላለሁ።

ድካምን ቀናሽ ሀብት የሚያከማች፤ ለኢንዱስትሪው አቅም የሚሆነው ይህ ፕሮጀክት በፍጥነት አልቆ ወደ ሥራ ሲገባ በተለይም ሴቶች ቀናቸው ይበራል። የኃይል አቅርቦቱ ተሟልቶ ከእኛ ተርፎ ለጎረቤት ሲቀርብ አይችሉም ላሉቱ ችለን ከማሳየት በቀር ምን ደስ የሚል እውነት ይገኛል።

ለዚህም ነው መሰል የዘንድሮው የ13ኛው ዓመት መሪ ቃል በኅብረት ችለናል የሆነው። እውነትም በኅብረት ችለናል፡፡

ለብስራት

አዲስ ዘመን መጋቢት 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You