የአፈር አሲዳማነትን ለማከም የተጀመረ ቁርጠኛ ርምጃ የሁሉንም ተሳትፎ ይፈልጋል

መንግሥት በግርብናው ዘርፍ ያከናወናቸውን ተግባራት ተከትሎ ምርትና ምርታማነቱ እየጨመረ መጥቷል፡፡ በዚህ ረገድ መንግሥት ብዙ ቢሊዮን ብር እየመደበ በየዓመቱ ማዳበሪያ በድጎማ እያቀረበ ይገኛል፡፡ ቴክኖሎጂ ለመጠቀም ሰፊ እድል የሚሰጠው የኩታ ገጠም እርሻ መስፋፋትም ሌላው ትኩረት የተሰጠው ነው፡፡

በዝናብ ጥገኝነት ላይ ተመስርቶ በዓመት አንዴ እየተመረተ የኖረውን የግብርና ልማት ለመለወጥም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን በማስፋፋት በዓመት ሦስቴ ማምረት መቻሉም ለምርትና ምርታማነቱ እድገቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

በተለይ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱ የሚሸፈነው መሬት ልማቱ በተጀመረበት ዓመት ከነበረበት ሦስት ሺህ አምስት መቶ ሄክታር ዘንድሮ ከሦስት ሚሊዮን ሄክታር በላይ ደርሷል፡፡ ልማቱ ሲጀመር ከተገኘው 100 ሺህ ኩንታል ምርትም፣ ዘንድሮ ወደ 120 ሚሊዮን ኩንታል ደርሷል፡፡

ለግብርናው ምርትና ምርታማነት እድገት አስተዋጽኦው ከፍተኛ እንደሆነ የሚታመንበት የግብርና ሜካናይዜሽንም እየተስፋፋ ነው፡፡ አርሶ አደሮች ትራክተሮችን ኮምባይነሮችን መግዛት የሚያስችሏቸው ሁኔታዎች በኢትዮጵያ ልማት ባንክ በኩል ተመቻችተዋል፤ የኢንተርፕራይዞቹ ብዛትና የሚሰጡትም አገልግሎት እየጨመረ ነው፡፡

በአንጻሩ ደግሞ ምርትና ምርታማነቱን የማሳደጉን ሥራ አመድ አፋሽ የሚያደርግ ሁኔታም በሀገሪቱ ተንሰራፍቷል፡ ፡ ይህ የዘርፉ ዋንኛ ችግር ሆኖ የዘለቀው የአፈር አሲዳማነት ነው፡፡ ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ እንዳመለከተው፤ ወደ ሰባት ሚሊዮን ወይንም አሁን ከሚታረሰው መሬት 43 ከመቶው በአሲዲቲ እየተጠቃ ነው፡፡ ከዚህም ውስጥ ሦስት ሚሊዮኑ በከፍተኛ ደረጃ በአሲዲቲ ተጠቅቷል፡፡

ከዚህ አኳያ በዚህ መሬት ላይ ማዳበሪያ መጠቀም ቢቻል እንኳ በቂ ምርት ሊገኝበት እንደማይችል መረጃዎች ያስገንዝባሉ፡፡ መንግሥትም ይህንን ችግር በሚገባ ተገንዝቦ የአፈር አሲዳማነትን የማከም ሥራን በትኩረት እያከናወነ ይገኛል፡፡ ግብርና ሚኒስቴር በዚህ በጀት ዓመት የአፈር አሲዳማነትን ለማከም ንቅናቄ እንደሚያደርግ ባለፈው ዓመት ባስታወቀው መሠረት ሰሞኑን ወደ ንቅናቄው ገብቷል፡፡

በ2016/17 የምርት ዘመን አሲዳማ መሬትን ለማከም የሚረዳ የግብርና ኖራ አቅርቦትና ስርጭት ሀገራዊ ማስጀመሪያ የንቅናቄ መርሀ ግብር በቅርቡ በተካሄደበት ወቅት እንደተጠቆመው፤ በዚህ ንቅናቄ በመላ ሀገሪቱ ከ100 ሺህ ሄክታር በላይ አሲዳማ መሬትን በማከም ምርታማነትን ለማሳደግ ታቅዷል፡፡

በንቅናቄ መድረኩ ላይ እንደተጠቆመው፤ የሀገር ህልውና የብዙ ነገሮች ድምር ውጤት ሲሆን፤ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ደግሞ የብዙ ችግሮች መፍትሔ ነው፡፡ የኑሮ ውድነትን የመቀነስ አጀንዳ ሲነሳም ምርትና ምርታማነት ላይ ትኩረት ማድረግን ይጠይቃል፡፡ አጠቃላይ የሀገር ኢኮኖሚ እድገት የሚመጣውም ምርትና ምርታማነትን ማረጋገጥ ሲቻል ነው፡፡

ይህን ምርታማነት አጠናክሮ ለማስቀጠል የተያዘው ንቅናቄ ፋይዳ ከፍተኛ ይሆናል፡፡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ይህ በአፈር አሲዳማነት የተጠቃ ማሳ በግብርና ኖራ ቢታከም ምርትና ምርታማነትን ከ10 ኩንታል በሄክታር ወደ 40 እና 50 ኩንታል ማሳደግ ይቻላል፡፡

በዚህም በሀገሪቱ አሲዳማ አፈርን በግብርና ኖራ በማከም የሰብል ምርትና ምርታማነትን ማሳደግም ተችሏል፡፡ የግብርና ኖራ የተጨመረባቸው ማሳዎችም ከፍተኛ የምርት ጭማሪ ማሳየት የቻሉ ሲሆን፤ ለአብነትም ስንዴ 71 በመቶ፣ ገብስ መቶ በመቶ፣ በቆሎ 28 በመቶ ባቄላ 88 በመቶ ምርታማነትን ማሳደግ ተችሏል፡፡

የአፈር አሲዳማነት የሀገራችን ምርታማነት ጸር መሆኑ እስከታወቀ ድረስ ይህን አሲዳማነት በሚገባ መፋለም ወቅቱ የሚጠይቀው አብይ ተግባር ነው፡፡ አሲዳማ አፈርን በማከም በዚህ ልኩ ምርታማነትን ማሳደግ ከተቻለ፣ ንቅናቄው የሚጠይቀውን ሁሉ በማሟላት የማከሙን ሥራ በስፋት ማካሄድ ይገባል፡፡

መንግሥት ኢሲዳማነቱን ለማከም የያዘው ቁርጠኛ አቋምና ወደ ትግበራ በዚህ ልክ መግባቱ ለግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት እድገት ያለውን ቁርጠኝነት አጠናክሮ መቀጠሉን ያመለክታል፡፡ ይህ ሥራ ግን በመንግሥት ቁርጠኝነት ብቻ የሚፈጸም አይደለም፡፡ የአፈር አሲዳማነትን ለማከም የተጀመረው ይህ ቁርጠኛ እርምጃ የተለያዩ ወገኖችን ርብርብ ይጠይቃል፡፡ ሌሎች የዘርፉ ተዋንያንም ለእዚህ ሀገራዊ ተግባር ቅድሚያ ትኩረት በመስጠት በዘርፉ እየተመዘገበ ያለውን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ርብርባቸውን ማጠናከር ይኖርባቸዋል፡፡

ለእዚህ ታላቅ ተልእኮ የሚያስፈልገው የግብርና ኖራ በሀገሪቱ በስፋት እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ አፈሩን አዘጋጅቶ በማቅረብ በኩል ያሉት ፋብሪካዎች ውስን መሆናቸው ይገለጻል፡፡ ለተያዘው ዓመት ንቅናቄ ያሉትን የኖራ ፋብሪካዎች አቅም አሟጦ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ የአፈር አሲዳማነቱ የደቀነው ስጋት ከፍተኛ እንደመሆኑ፣ በቀጣይ ተመሳሳይ ፋብሪካዎች ወደዚህ ሥራ እንዲገቡ መሥራት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ተግባር መሆን ይኖርበታል፡፡

መንግሥት ለግብርናው ዘርፍ ካለው ቁርጠኝነት ተጨማሪ ፋብሪካዎች ወደ ልማቱ እንዲገቡ ለሚደረገው ጥረት ትልቅ አቅም ተደርጎ መወሰድና መሥራት ያስፈልጋል፡፡ የአፈር አሲዳማነቱን ለማከም የተጀመረው ሰፊ ርብርብ፣ ይህን ለማድረግ የሚያስፈልገው የግብርና ኖራ በሀገሪቱ በስፋት መገኘቱ ተጨማሪ ፋብሪካዎች ወደ ልማቱ እንዲመጡ እድል የሚከፍት እንደመሆኑ፤ የግሉ ዘርፍም በእዚህ ርብርብ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆን ይኖርበታል፡፡

አዲስ ዘመን መጋቢት 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You