የአባት ልብ – ስለ ልጅ…

አንድ- ለእናቱ ና ለአባቱ

ለቤቱ የመጀመሪያም የመጨረሻም ልጅ ነው። እናት አባቱ እሱን ካገኙ በኋላ ሌላ ልጅ አልወለዱም። ይህ እውነት ለአንድዬው ቅምጥል ለማ ለጌቦ የተለየ ዓለም ፈጠረ። ወላጆቹ ጠዋት ማታ በስስት እያዩ አሳደጉት። ትንሹ ለማ ከእኩዮቹ ይበልጥ ያሻውን ጠይቆ የማያጣ፣ የፈለገውን ሁሉ የሚያገኝ ልጅ ሆነ።

እንደ ዓይን ብሌን የሚታየው ለማ የቤት የደጁን በረከት አላጣም። ከምግቡ፣ ከልብሱ ከጫማው እየተመረጠ እንደልቡ ተሟላለት። ብላቴናው ለማ ‹‹አፈር አይንካህ፣ ጸሀይ አይጉዳህ›› ተብሎ በስስት አደገ። ዕድሜው ከፍ እንዳለ ወላጆቹ ስለ እሱ ነገ ማሰብ መጨነቃቸው አልቀረም። አንድዬ ልጃቸው ተምሮ፣ ተመራምሮ ስማቸውን እንዲያስጠራ፣ ይሻሉ። ራሱን አገሩን እንዲጠቅም ይፈልጋሉ።

ለማ ሰባተኛ ዓመቱን እንደያዘ ደብተርና እርሳስ ተገዛለት። ትምህርት ቤት እንደሚሄድ ባወቀ ግዜ ውስጡ ፈነጠዘ። ልብስ ጫማው ተሟላለት፣ ከባልንጀሮቹ ሁሉ አምሮና ደምቆ ከትምህርቱ መመለስ ጀመረ። ለማ የገበሬ ልጅ ነው። ደቡብ ምዕራብ ዳውሮ ዞን ተርጫ ላይ ተወልዶ አድጓል።

ዳውሮና አካባቢው ክረምት ከበጋ ያበቅላል። መሬቱ የሰጡትን ይቀበላል። በዚህ በረከት መሀል የተገኘው ለማ አንዳች አልጎደለበትም። ልጅነቱን በወላጆቹ ስስት ተከቦ፣ በፍቅር መንገድ ተመላልሶበታል።

ለማ ሁለተኛ ክፍል እንደገባ የልጅነት ልቡን የሰበረ፣ የውሰጡን ሀሴት ያጨለመ ክፉ አጋጣሚ ተከሰተ። በሙሉ ዓይናቸው የማያዩት፣ ከልብ የሚሳሱለት አባቱ በሞት ተለዩት። ይህ ግዜ ለትንሹ ልጅ እጅግ የከፋ ሆነ። ሞት ይሉት ንጥቂያ ዳግም ከእሳቸው እንደማያውለው ሲገባው አንገቱን ደፋ። ሌት ተቀን ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ።

ጊዜው የሰኔ ወር ነው። ተማሪዎች የድካማቸውን የሚያዩበት የዓመቱ መጨረሻ። ለማ እንደአምናው ትምህርት ቤቱ ደርሶ ካርዱን አልተቀበለም። ይህ ወር ሆን ብሎ አባቱን የቀማበት ቢመስለው በኩርፊያ፣ በዝምታ አለፈው። የለማ እናት የትዳር አጋራቸውን የአንድዬ ልጃቸውን አባት አጥተዋል። ይህ ግዜ ለእሳቸው ከሀዘን በላይ ነው። ከዚህ በኋላ ቀሪ ሀብታቸው ትንሹ ለማ ብቻ ሆኗል።

ውሎ አድሮ በቤቱ ሕይወት እንደትናንቱ ቀጠለ። የለማ እናት ልጃቸውን በተለየ ዓይን ማየቱ ባሰባቸው። እያደር ስስት ፍቅራቸው፣ ጨመረ። ወጥቶ አስኪመለስ ሰውን፣ መንገዱን አላምነው አሉ። ለማ ከአባቱ ሞት ወዲህ በትምህርቱ በርትቶ ቀጥሏል። አሁንም ግን እርሱ በእናቱ ዘንድ ገና እንደ እንደተወለደ ሕጻን ነው። ዛሬም ልክ እንደልጅነቱ ያዩታል፣ ይሳሱለታል።

ድንገቴው ጥያቄ…

ለማ አንደኛ ደረጃን አጠናቆ ዘጠነኛ ክፍል እንደገባ ከእናቱ አንድ ሀሳብ ተሰነዘረ። እሱ ለእሳቸው አንድና ብቸኛ ልጅ ነው። ከዚህ በኋላ እሀትና ወንድም አይወልዱለትም። እንዲያም ሆኖ ይህን ጉጉት በሌላ መንገድ ማግኘትን ይሻሉ። እሱ አግብቶ ቢወልድና ራሱን ቢተካ ምኞታቸው ነው። ይህን ስሜት ይዘው ዝም አላሉም። ትምህርቱን ትቶ ጎጆ እንዲቀልስ፣ ልጅ ወልዶ እንዲያሳቅፋቸው ጠየቁት። ለማ ይህን እውነት ከእናቱ በሰማ ግዜ ለፍላጎታቸው እጅ ሰጠ፣ እንደ ልጅነቱ ሊታዘዝም ጥያቄውን በይሁንታ ተቀበለ።

እንደታሰበው ሆኖ ለማ በእናቱ ቤት በወግ ማዕረግ ተዳረ። የወደዳት አጋሩ የግራ ጎኑን ሆነችለት። በምርቃት፣ በምስጋና የተጀመረው ጎጆ በበረከት ተሞላ። ከዚህ በኋላ የለማ እጆች ደብተር አይዙም፤. እስክሪቢቶ አይጨብጡም። ትጉህ ገበሬ ሆኖ ጎጆውን ይደጉማል፣ የእናቱን ሀሳብ ሞልቶ ምርቃቱን ይቀበላል።

ውሎ አድሮ የለማ ትዳር በልጅ ስጦታ ተባረከ። ወንድ ልጅ ወልዶ በሳመ ግዜ የእናቱ ደስታ በእጥፍ ጨመረ። ስለ እሳቸው ፍቅር የከፈለው ዋጋ የልብ ምርቃት ሆነው። መላው ቤተሰብ ሕጻኑን በፍቅር እያየ ማሳደግ ያዘ። በአያቱ እጅ ውሎ የሚያድረው ጨቅላ ልዩ ፍቅር ተቸረው፣ ቤተሰቡ ነገውን እየተነበየ መልካሙን ሁሉ ተመኘለት። ልጁ ዳዴን አልፎ ‹‹ወፌ ቆመች›› እያለ ዓመቱን ደፈነ። ግዜ ቆጥረው ሌሎች ዓመታት ተከተሉ። ደስተኛው ሕፃን ለእናት አባቱ ትርጉም የሚሰጥ ደስታን አጎናጸፈ።

ከቀናት በአንዱ ግን በቤቱ አስደንጋጭ ጉዳይ ተከሰተ። የአምስት ዓመቱ ልጅ በድንገት ታመመ። ለተሻለ ሕክምና ጅማ ሆስፒታል ገብቶ አልጋ ያዘ። አባት ለማ የሆነውን ማመን አልቻለም። ይህ ልጅ የልጅነት ስጦታው፣ የወላጅ እናቱ በረከት ነው። ትዳሩን፣ ጎጆውን በክብር አጽንቷል፣ ታሪኩን አድምቆ ቀይሯል። ልጁ ሕመሙን በእሱ አቅም የሚችለው አልሆነም፡ ክፉኛ ተንገላታ፣ ተሰቃየ።

የምርመራው ውጤት፤ በሽታው ሜኔንጃይት መሆኑን አመላክቷል። መላው ቤተሰብ በእሱ ጭንቀት ከጭንቅ ወድቋል። ፈታኝ ቀናት አንድ ሁለት ብለው ተቆጠሩ። ዝምታ የዋጠው ጎጆ በድብርት ተያዘ። ልፋት ሙከራው ሁሉ አልተሳካም። ትንሽዬው የቤቱ ፋኖስ በድንገት አንቀላፋ። ሳይታሰብ የጎጆው ብርሀን ተዳፈነ።

የሕጻኑ ሞት መላውን ቤተሰብ ከከባድ ሀዘን ጣለ። ሁሉም በምሬት አንገቱን ደፍቶ አነባ። የአባትዬው ለቅሶ ግን በዋዛ አልተገታም። በቀላሉ መጽናናት፣ የተሳነው ለማ ዕንባውን መጥረግ ተሳነው። የልጁ ጠረን ሳቅና ጨዋታው በዓይኑ ውል እያለ ተቸገረ። ያወጣለት ስም፣ ያለመለት ነገ ሁሉ በዓይምሮው ተመላለሰበት።

የሀዘኑን መክፋት ያዩ ወዳጅ ዘመዶች ሽማግሌ ሰብስበው ‹‹ተው›› ሲሉ መከሩት፣ አስመከሩት። ለማ ጊዜ ወስዶ ከራሱ አወራ። ለፈጣሪው ልቡን ሰጥቶም መጽናናትን ለመነ ‹‹እምቢኝ›› ብሎ ያስቸገረው ማንነት በአንዴ ተመልሶ ቀልቡን ሲገዛ ታወቀው፤ ልክ እንደትናቱ ዛሬን እየኖረ ነገን ማሰብ ጀመረ።

ቁጭት…

አሁን ለማ ከሀዘኑ ተፅናንቷል። ዕንባውን ጠርጎ ሳቁን መልሷል። ይህ አጋጣሚ ራሱን መለስ ብሎ እንዲያይ አጋጣሚ እየፈጠረለት ነው። አጋጣሚው ደግሞ ከሌላ ቁጭት ይጥለው ይዟል። እሱ ወደ ትዳር ዓለም በገባበት ጊዜ ባልንጀሮቹ ትምህርታቸውን ጨርሰው ስራ ተቀጥረዋል። ጓደኞቹ ባገኙት ግዜ አርሶ አደር ሆኖ መቅረቱን እየጠቆሙ በአግቦ ይነካኩታል። ይህን መለስ ብሎ ሲያስብ ውስጡ ተፈተነ። የዛኔ ስለ ጎጆው በውሳኔው አምኖበት ነበር። አሁን ግን ሳይማር ቤት መቅረቱ እያንገበገበው ነው።

ለማ ይህን እውነት ይዞ ከእናቱ ጋር መከረ። እናት መጀመሪያ ሀሳቡን አልደገፉም። መቼም ከጎናቸው እንዲርቅ አይሹምና ‹‹ላስብበት›› ሲሉ አከላከሉት። ለማ የእናቱን ቃል ያከብራል። ዋጋ ከፍለው አሳድገውታልና ከሀሳባቸው ፈቀቅ አይልም። ቀስ እያለ አሳመናቸው። ውሎ አድሮ ይሁንታቸውን ሰጡት።

መስከረም ሲደርስ ምዝገባውን አጠናቆ ትምህርቱን ካቆመበት ቀጠለ። ስኬታማዎቹ የትምህርት ዓመታት በድል ተጠናቀቁ። በርቀት ቀጣዩን ዩኒቨርሲቲ ትምህርት ጀመረ። በሰው ሀብት አስተዳደር በዲፕሎማ ተመረቀ። መረጃውን እንደያዘ ተወዳድሮ የመንግስት ሰራተኛ ሆነ። ብዙ ሳይቆይ የተርጫ ከተማ አስተዳደር ስራ አስኪያጅ ለመሆን በቃ። ጥንካሬዎቹ በተግባር ተመሰከሩ። በርካቶችን የሚያግዝ፣ የሚያገለግል ቀኝ እጅ መሆኑን ቀጠለ።

ለማ ሩጫው አልተገታም። ቀጣይ ዓመታትን በዲግሪ ተምሮ አጠናቀቀ። ይህን ተከትሎ የመጣው ሹመት በፍጥነት አራመደው። አሁንም በጥሩ ምግባሩ የሚመሰከርለት የስራ ሰው መሆኑን አሳየ። ኃላፊነት ሲመጣ ሹመት ሲደራረብ ከራሱ መክሮ ከእናቱ ተነጋግሮ ኃላፊነቱን በፈቃዱ ለቀቀ። ቀጣዮቹን ዓመታት ባለሙያ ሆኖ ለመስራት ወሰነ።

ለማ አሁን የአራት ልጆች አባት ነው። ትዳሩን በሰላም በደስታ ይመራል። ዛሬም ለባለቤቱና ለእናቱ የተለየ አክብሮት ይሰጣል። ጸባየ ሸጋው አባወራ ስለቤተሰቡ ፍቅር የማይሆነው የለም። አራተኛ ልጁን ክብረዓለም ሲል ሰይሟታል። በእሷ ዕድሜ ብዙ የሕይወት ለውጥ፣ ሞገስና ክብር አግኝቷልና ስሟን ሲያወጣ በምክንያት ነው።

ክብረዓለም …

ትንሽዋ ክብረ ዓለም ሰባተኛ ዓመቷን ይዛለች። ዓይን የምትገባ ቆንጅየ ልጅ ናት። ካሉት ልጆች የመጨረሻ በመሆኗ ሁሉም ይወዳታል። ክብረ የሁለተኛ ዓመት የኬጂ ተማሪ ናት። ቀልጣፋና ጤናማ ልጅ እንደሆነች ዘልቃለች። ባህርይ፣ ጨዋታዋ ይለያል። ስታድግ ሀኪም መሆንን ትሻለች። አንድ ሰሞን የልጅቷ ገጽታ ላይ አንዳች ነገር ተነበበ። ትምህርት ውላ በገባች ግዜ የዓይኗን መቅላት የሚያስተውለው አባት ለምን ሲል መጠየቅ ያዘ።

አባት ስለ ምክንያቱ የሚያስረዳው አላገኘም። ውሎ አድሮ የሕፃኗ ቆዳ ያለቅጥ እንደወረቀት መንጣት ጀመረ። ቤተሰቡ በድንጋጤ ተዋጠ። ለማ ጤና ጣቢያ ወስዶ አሳያት። ጤና ጣቢያው ለሌላ ምርመራ ፈጥኖ ወደ ሆስፒታል ላካት። አልተሻላትም።

አልጋ ይዛ መታከም የጀመረችው ልጅ ሆዷ ማበጥ ያዘ። ሀኪሞች ከምርመራ በኋላ ጣፊያዋ ላይ ችግር እንዳለ አረጋገጡ። እንዲያም ሆኖ ለከፍተኛ ሕክምና ጅማ ሆስፒታል መሄድ ነበረባት። ለማ ልጁን አሳክሞ ለመመለስ ቀን መቁጠር ጀምሯል። እንዳሰበው አልሆነም። ሀኪሞች ለቀጣዩ የመቅኔ ምርመራ አባት ፊርማውን እንዲያኖር እየጠየቁት ነው። እንዲህ ሲባል በድንጋጤ ለምን? ሲል ጠየቀ። ለሚሰጣት ከባድ ማደንዣ የቤተሰብ ፊርማ ግድ መሆኑ ተነገረው። የተባለውን ከማድረግ ሌላ ምርጫ አልነበረውም።

ልጅቷ ማደንዘዣውን ተወጋች። በታሰበው ግዜ ቶሎ አልነቃችም። በድንጋጤ የሚይዘው ጠፋው። ሕክምናው እንዳበቃ የምርመራው ውጤት በሕፃኗ ደም ካንሰር መኖሩን አመላከተ። ይህ ክፉ ዜና ለትንሽዋ ልጅ አባት እጅግ ልብ ሰባሪ ነበር።

ለማ አምርሮ እያለቀሰ ነው። ስለ ሕክምናው ግን ምርጫ ተሰጥቶታል። ወጪው እጅግ የበዛ ቢሆንም አዲስ አበባ ለመሄድ ወስኗል። በመልካም ሰዎች እገዛና ምክር አዲስ አበባ የገባው አባወራ ታማሚ ልጁን ታቅፎ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ደረሰ። የያዘው የሪፈር ወረቀት ደጅ አላስጠናውም። አልጋ ተሰጠው። ምርመራው በአዲስ መልክ ዳግም ተጀመረ። ውጤቱ ቀድሞ ከነበረው የተለየ አልሆነም።

ለሰው እንግዳ ለአገሩ ባዳ

ኑሮና ስራውን ትቶ ከሆሰፒታል የተገኘው ለማ የ2015 ዓዲስ ዓመትን ከቤቱ ርቆ አሳለፈ። ሕጻኗ በየቀኑ የምትወሰድው ምርመራ እያዳከማት ነው። የኬሞ ሕክምናው ባህርይ ወራትን በስቃይ እንድትገፋ አስገድዷል። ለማ ‹‹ለአገሩ እንግዳ ለሰው ባዳ›› ነው። ‹‹የኔ›› የሚለው ጠያቂ ዘመድ የለውም።

በየአፍታው የልጁ ሕመም ያስጨንቀዋል። ስለ በሽታው ለእናቷ አንዳች ቃል አልተነፈሰም። አሁን በእጁ ያለውን ገንዘብ ጨርሷል። ቀጥሎ የሚሆነውን አያውቅም። በዚህ መሀል አልጋውን ለሌሎች ሕሙማን መልቀቅ እንዳለበት ተነገረው። ለማ ዕንባ ያዘው፣ ሆድ ባሰው። ይህ ለእሱ መራራ ግዜ ሆነበት። ታማሚ ልጁን ወዴት ይዞ እንደሚሄድ ግራ ተጋባ።

ከሆስፒታሉ መልቀቅ ግድ መሆኑን ሲያውቅ ዶክተር ትዕግስት ከተባሉ ሀኪም ፊት ቀርቦ እያለቀሰ ለመናቸው። ዶክተሯ ከልብ አድምጠው ሀዘኑን ተጋሩት። ዕንባውን ለማበስ መንገድ የሚሆን አቅጣጫ ባመላከቱት ግዜ ዓይኑን አላሸም። የተነገረው መፍትሄ ቢያስደስተውም እውነት ነው ብሎ ለመቀበል አመነታ። ዶክተሯ ከሚመለከታቸው ሰዎች አገናኝተው አስተዋቁት። ለእሱና ለልጁ የሚበጅ ‹‹ማቲዎስ ወንዱ›› የተባለ የካንሰር ሕሙማን ማዕከል መኖሩን ባወቀ ግዜ ፈጣሪውን ደጋግሞ አመሰገነ።

አይረሴዎቹ ቀናት…

ለማ አይረሴ የፈተና ቀናትን አልፏል። በሻካራ መንገዶች ተመላልሷል። ከሁሉም የልጁን ፍላጎት ለመሙላት የነበረበትን ችግር ፈጽሞ አይረሳውም። የሆስፒታሉን ምግብ ለልጁ ፈጥኖ ማጉረስ አይችልም። ወተቱን ተቀብሎ እንደ አቅሙ ምግብ ይገዛል። እንዲህ ለማድረግ ደግሞ ሁሌም አይሞላም። እጅ አጥሮት፣ ኪሱ ሲጎድል በትካዜ ይውላል።

ትንሽዋ ልጅ አንዳንዴ ፍራፍሬ መብላት ትፈልጋለች። አንዳንዴ ደግሞ ደርሶ ስጋ ያምራታል። እንደ እናት አባት የሆነው አባወራ ያሰበችውን ለመሙላት ይሞክርና ግራ ይጋባል። እንደማይሆን ሲያውቅ ዓይኖቹ በዕንባ ይሞላሉ። እንደልጅ ሆድ ይብሰዋል።

ለማ ሥራውን አቋርጦ ልጁን ማስታመም ከጀመረ ጊዚያት ተቆጥረዋል። አባወራነቱን ትቶ ካገሩ ከራቀም ሰነባብቷል። በየቀኑ ለምግብ፣ ለመድሀኒት ግዢ ብዙ ያስፈልገዋል። የሥራ ባልደረቦቹን ጨምሮ ወዳጅ ዘመዶቹ አዋጥተው የላኩለት ገንዘብ አግዞታል። በእሱ ብቻ ግን እፎይታ አላገኘም።

ባለቤቱ እሱን አሳርፋ ሸክሙን ማቅለል ትሻለች። ስለ ልጃቸው ሕመም መንገር መርዶ የሆነበት ለማ እንዲህ ማድረጉን አልፈለገም። የመጣውን ችግር ሁሉ ለብቻው መወጣትን መርጧል። ሕጻኗ ክብረዓለም ልዩ ትኩረት ትሻለች። ብዙ ግዜ የበላችው ሁሉ አንዳች ሳይቀር ይወጣል።

ልጁ አቅም ስታጣ፣ ስትዳከም አባት መፈጠሩን ይጠላል። ብቸኝነት፣ ያንገዳግደዋል። ከጎኑ ‹‹አይዞህ›› ባይ አጋዥ የለውም። ለአፍታ አየር ሳያገኝ፣ እግሩን ሳያፍታታ ቀኑ መሽቶ ይነጋል። ለማ ሀኪሞች የሰጡትን ማሳሰቢያ ፈጽሞ አይዘነጋም። ሕክምናው ቢቋረጥ ልጁን ሊያጣት እንደሚችል ተነግሮታል።

ይህን ሲያስብ ሁሉን ረስቶ መማረሩን ይተዋል። ጊዜ ወስዶ፣ ምቾት ክብሩን ትቶ ስለ ልጁ መጎዳትን ይመርጣል። በአባወራው ዙሪያ መልካም ሰዎች አልጠፉም። ሀኪሞች ችግሩን አይተው ማስረጃ ፅፈውለታል። መስሪያቤቱ ሁሉን ተረድቶ በሚያስፈልገው ሁሉ ከጎኑ ቆሟል። ስለ ልጃቸው ሕመም ለእናቷ ለመንገር ብዙ ተፈትኗል። እውነቱን ካሳወቃት በኋላ ችግሩን ተጋርታዋለች።

ዛሬን …

አባወራው ለማ ዛሬም ከልጁ ጎን እንደቆመ ነው። እሱ በልጅነቱ ያላለፈበት ስቃይ በልጁ ላይ ሆኖ ማየቱ ከልብ ያሳዝነዋል። ትንሽዋ ልጅ የኬሞ ቴራፒ ክትትሏ አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። የካንሰር ሕክምናው ጉበቷ ላይ ያሳየው ምልክት አሳሳቢ በመሆኑ ለጊዜው እረፍት ላይ ነች።

እረፍት አልባው አባቷ ግን ዛሬም ለመልካም አባቶች ድንቅ ምሳሌ ሆኖ እስትንፋሷን ይጠብቃል። ነገ ለእሱ ተስፋ ያለው ብርሀን ነው። ክብር ያገኘባት ፍሬውን ዳግም ዓለሟን እስኪያይ አንዳች ሸብረክ አይልም፣ ፈጽሞ እጅ አይሰጥም።

መልካምሥራ አፈወርቅ

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 21 ቀን 2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You