አሁንም እሴቶቻችን ላይ እንሥራ

ኢትዮጵያውያን ባለ ብዙ እሴቶች ነን፤ እነዚህ እሴቶቻችን መገለጫዎቻችን ናቸውና እንታወቅባቸዋለን፤ እንለይባቸዋለን። የአብሮነት፣ የመከባበር፣ የመቻቻል፣ ወዘተ. እሴቶቻችን ዘመናትን ተሻግረው አብረውን አሉ።

የመቻቻል እሴቶቻችን በትንሽ በትልቁ ከመጋጨት ያወጡንና የሚያወጡን ከመሆናቸው ባሻገር፤ ግጭቶች ተከስተው ሲገኙም መፍትሔ ለማምጣት የሚያስችሉ መላ ያላቸው ናቸው። የመረዳዳት እሴቶቻችን ብቻችንን እንዳንቆም፣ እንድንተሳሰብ አድርገውናል።

አብሮነታችን በክፉ ቀን እርስ በርስ ለመረዳዳት፣ በደግ ቀን ደግሞ ተጋግዞ ለመልማት አቅም የሚሆን ፋይዳ አላቸው። ባለፉት ዘመናት የሀገርን ሉአላዊነት በማስጠበቅ የተገኙ ድሎች ከአብሮነትና አንድነት እሴቶቻችን የተቀዱ ናቸው። ሀገርን ከቅኝ ገዥዎች ለመከላከል በዓድዋ የተመዘገቡ ድል፣ በዚህ ዘመን ደግሞ በልማቱ መስክ በዓባይ ግድብ ኢትዮጵያውያን ከመንግሥታቸው ጋር ተረባርበው የጻፉት ታላቅ ገድል አንድነታቸው የት ድረስ ሊዘልቅ እንደሚችል ጥሩ ማሳያ ነው።

“ባህሎቻችን፣ ወጎቻችንና ልማዶቻችን በመልካምነት ላይ የታነጹ ከመሆናቸው ባሻገር ከየትኛውም ሃይማኖታዊ አስተምህሮት ጋር የማይጻረሩ እንዲያውም በሃይማኖታዊ አስተምሮት የሚደገፉ ፣ የሚጠናከሩ ፣ የሚንጸባረቁ የኢትዮጵያዊነት መገለጫዎች ናቸው።

ምንም እንኳ መበርከት ያለባቸው ቢሆንም፣ ኢትዮጵያውያን ኑሮ የደቆሳቸውን ዜጎች ጎጆ ለማቅናት፣ ያጡ የነጡትን ለመደጎምም ርብርብ ሲያደርጉ እየተመለከትን እንገኛለን። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያለውን ብንጠቅስ በርካታ አቅመ ደካሞች የቤት ባለቤት ተደርገዋል፤ አያሌ ዜጎች የምገባ መርሀ ግብር ተጠቃሚ ሆነዋል፤ ወዘተ ።

የሰው አንመኝም፤ የኛንም አላግባብ ሲወስዱብን እንቆጣለን። መስረቅ፣ የእጅ አመል ነውራችን ነው። ተፈጽሞ ቢገኝ ቀደምቶቹ ምን አይነት እርምጃ ይወስዱ እንደነበር ይታወቃል፤ ይህ ባይፈጸም መገለል ይደርሳል። እናም ያደግነው የኖርነው በዚሁ አግባብ ነው። በዚሁ እየኖርንም ነው።

በእነዚህ እሴቶቻችን በሥነ ምግባር የታነጸ ዜጋ ለማፍራት ጥረቶች እየተደረጉ ባሉባት ሀገር፣ ከዚህ በተቃራኒው የቆሙ ጥቂት የማይባሉ ዜጎች አሳፋሪ ተግባር ሲፈጽሙ ይስተዋላል፤ በቅርቡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አጋጠመኝ ያለውን የዲጂታል ባንኪንግ የሲስተም ብልሽት በመጠቀም በውድቅት ሌሊት የባንኩን ገንዘብ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ጤነኛ ያልሆነ የገንዘብ ዝውውር ያደረጉ ጥቂት ብለን የማንተዋቸው ዜጎች ድርጊትም ይህንኑ ይጠቁመናል።

ከእነዚህ ሕገወጦች ውስጥ አብዛኛዎቹ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መሆናቸው ደግሞ በእጅጉ ያስገርማል፤ ያሳስባልም። ነገ ሀገር ይረከባሉ ተብለው የሚጠበቁ ወጣቶች በእዚህ ዓይነቱ አሳፋሪ ተግባር ተዘፍቀው መገኘታቸው አሳፋሪ ከመባል ሌላ ምን ያስብላል።

በሕገወጦቹ ላይ ጠንካራ ሕጋዊ እርምጃዎች ሊወሰዱ ይችላሉ። በእርግጥም ጠንካራ መሆን ይኖርበታል። በተለይ ገንዘቡን መልሱ እየተባሉ ባልመለሱት ላይ አስተማሪ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል መገመት ይቻላል።

ግን ደግሞ ይህ ችግር ለምን በእዚህ ልክ ተፈጠረ ብሎ ደጋግሞ መጠየቅ ይገባል። ድርጊቱ ለእሴቶቻችን ያለንን ቅርበት በእጅጉ እንድንፈትሽ ያደርጋል። ዛሬ ላይ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተን በደንብ ውስጣችንን ማየት ካልቻልንና እንዲህ ዓይነት ድርጊቶች ሲፈጸሙ እያየን በዝምታ ካለፍን ነገ ብዙ ከባድ የሚባሉ ድርጊቶች ሲፈጸሙ ማጣፊያው ሊያጥረን ይችላል።

ሕገወጥ ድርጊቱን ተከትሎ ሌላም የሚገርም ነገር ሆኗል። ለማህበራዊ ሚዲያ ምስጋና ይግባውና ይህን ጉድ ሹክ ብሎናል። ድርጊቱን በርካታ ወገኖች ቢያወግዙትም፣ በአድናቆት የተመለከቱትም ተገኝተዋል። ይህ ደግሞ ሌላ አሳፋሪ ተግባር ነው።

ያም ሆነ ይህ ባንኩ ላይ የተፈጸመው ድርጊት እንደዜጋ ሁሉንም ዜጋ የሚመለከት ጉዳይ በመሆኑ እንደዋዛ በቀላሉ የሚታለፍ አይሆንም። ድርጊቱን የፈጸሙት አካላት እነማንም ይሁኑ እነማን ጉዳዩ እንደ ሀገር ሁላችንም ይመለከታል፤ የጉዳዩ ባለቤቶቹም ሁላችንም ነን።

የሰው ልጅ በምድር ላይ ጥሮ ግሮ መኖር እንዳለበት ሃይማኖታዊ አስተምህሮው ያመለክታል። የማህበረሰቡ የተለያዩ ባህላዊ ሥርዓቶችም ቢሆኑ ሠርቶ መብላትን እንጂ ስርቆትን የሚያበረታቱ አይደሉም። የሀገራችን ሕዝብ በዚህ ተቃኝቶ ያደገና የሚኖርም ነው። በዚህ ሃይማኖታዊ አስተምህሮ፣ በዚህ ማህበረሰብ ወግና ሥርዓት አድጓል ተብሎ የሚጠበቅ ትውልድ መላ ዓለምን ጭምር ጉድ ሊያሰኝ የሚችል ሕገወጥ ድርጊት ፈጽሟል።

ይህን ሁሉ ምን አመጣው ብሎ መጠየቅ ይገባል። በሀገሪቱ በአቋራጭ መክበር የጥቂቶች ፍላጎት ብቻ ነው ተብሎ አይወሰድም፤ ሠርቶ ስለመክበር ሳይሆን በሆነ መንገድ ብቻ ሀብት ማማ ላይ መቀመጥ የሚፈልጉ ጥቂት አይደሉም። እነዚህ ሕገወጦች ከእነዚያ መካከል አይደሉም አይባሉም። እነዚህን ድርጊቶች በአደባባይ ከማውገዝ በቀር ድርጊቶቹን የፈጸሙትን በአግባቡ የመቅጣት የማስተማር ነገር ችላ መባሉ ይህን ችግር አባብሶታል እላለሁ።

አሁን ላይ ዋናው ጉዳይ መሆን ያለበት እስካሁን ስንገነባ የመጣነውን መልካም እሴት ማስቀጠል ለምን አቃተን። ይህም ውስጣችንን በደንብ በማየት እንደዚህ ዓይነት ድርጊቶች እየተስፋፉ እንዳይመጡ ማድረግ ላይ የተጠናከረ ሥራ መሥራት ይኖርብናል። ይህ ካልሆነ ግን እንደሀገር ትልቅ ዋጋ ሊያስከፍሉን የሚችሉ ክስተቶች ሊገጥሙን መቻላቸው አይቀሬ ነው።

እስካሁን ባሉን መልካም እሴቶች ላይ መሥራት ባለመቻላችን ብዙ አጥተናል፤ ወደፊት ከዚህ የበለጠውን እንዳናጣ እሴቶቻችንን በማስገንዘብ፣ መሬት ላይ አውርደን በተግባር በማሳየት ላይ ከወዲሁ መሥራት ይገባናል።

ይህን አስነዋሪ ድርጊት የፈጸሙ አካላት በአስቸኳይ የወሰዱትን ገንዘብ እንዲመልሱ ባንኩ ሲያሳስብ ቆይቷል። ይህን ተከትሎም በርካቶቹ ገንዘቡን መልሰዋል፤ ከ500 የማያንሱት ደግሞ ይህን ባለማድረጋቸው ስማቸውን ይፋ አድርጓል። እነዚህ ሕገወጦች ይህን ማድረግ ካልፈለጉ ደግሞ ወደ ሌላ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚገባ አስገንዝቧል።

እነዚህ የድርጊቱ ፈጻሚዎች ለሕግ ቀርበው ሕጋዊ ቅጣት ተቀብለው፣ ተገቢውን ትምህርት አግኝተው ከስህተታቸው እንዲማሩ ማድረግ ያስፈልጋል። ይህ ብቻውን ግን በቂ አይደለም፤ ዛሬ ችላ ብለን የተውነው ነገር ነገ ተንዶ መፍረሱ አይቀርምና ትውልዱን በጽኑ መሠረት ላይ የማነጹ ሥራ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

ይህ ትውልድ እንዲህ ዓይነቱን ነውረኛ ተግባር ከየት እንዴት ተማረው ብሎ መጠይቅና መልሱ ሲገኝ ለአስፈላጊው እርምጃ መዘጋጀትም ይገባል። ለዚህም አሁንም ጊዜው ገና አልረፈደምና እንደ ሀገር መልካም ገጽታ በመገንባት አሁን ከገባንበት አጣብቂኝ መውጣት ይገባናል።

ይህን ማድረግ መቻል ማለት በተለያዩ አካባቢዎች ለሚስተዋሉ ተመሳሳይ ችግሮችም መፍትሔ ማስቀመጥ ይሆናል። መፍትሔው በእጃችን እያለ ሌላ መፍትሔ ፍለጋ ከመባዘን እሴቶቻችንን ማስረጽና መተግበር መቻል ላይ ትኩረት አድርገን እንሥራ። ይህን ማድረግ ደግሞ የሁላችንም ኃላፊነት ይሆናል።

በተለይ ደግሞ ከ99 በመቶ በላይ ሕዝቧ ሃይማኖተኛ ነው ተብሎ የሚነገርላት ኢትዮጵያ በሃይማኖት በኩል ያለውን አስተምህሮ የሃይማኖት አባቶች ኃላፊነት ወስደው መሥራት ይኖርባቸዋል። እነዚህ አባቶች ሠርተናል፤ እየሠራንም ነው ሊሉ ይችላሉ፤ ብዙ ላለመሠራቱ በሀገሪቱ የሚፈጸሙ ከእምነትም ከባህልም ያፈነገጡ ይህን ዘረፋ የመሳሰሉ ድርጊቶች አመላክተዋል።

መንግሥትም ማህበራዊ መስተጋብሮች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በማድረግ መልካም እሴቶችን ሊያስቀጥሉ የሚችሉ ሥራዎች ላይ በመሥራት ኃላፊነቱን መወጣት ይጠበቅበታል። የነገውን ትውልድ የመቅረጽ ትልቁ ኃላፊነት ያላቸው ትምህርት ቤቶች እና ወላጆችም ኃላፊነታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል። በተለይ በሥነምግባርና ፀረሙስና ኮሚሽን በኩል ይህ ሥራ መሠራት ይኖርበታል። ቸር እንሰንብት።

ትንሳኤ አበራ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 21 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You