በሕብረት ችለናል-የግድቡ ግንባታ በማጠናቀቂያ ምዕራፍ

የተያዘው መጋቢት ወር ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ስፍራ አለው፤ የአድዋ ድል እንደ ተመዘገበበት የካቲት ወር ሁሉ ኢትዮጵያውያን በዚህ ወር ትልቅ ታሪክ ጽፈውበታል። ይህ ታሪክ ደግሞ የአባይ ግድብ ግንባታ የተጀመረበት ነው። 5ሺ 150 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያመነጭ የሚጠበቀው የዚህ ግድብ ግንባታ አጠቃላይ አፈጻጸም በአሁኑ ወቅት 95 በመቶ ደርሷል። በሁለት ተርባይኖቹም የኤሌክትሪክ ኃይል ወደ ማመንጨት መሸጋገሩ ይታወቃል።

መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም የዛሬ 13 ዓመት ለግድቡ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ በተቀመጠበት ወቅት የግድቡ ግንባታ ወጪ የሚሸፈነው በኢትዮጵያውያን መሆኑ ተጠቅሶ፣ ሕዝቡ ለግንባታው ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ተደርጎለታል። ኢትዮጵያውያንም በግንባታው መጀመር የተሰማቸውን ድጋፍ በተለያዩ መንገዶች መግለጻቸው ይታወሳል።

ከዚያን ጊዜም አንስቶ በተለያዩ መንገዶች ለግንባታው ድጋፍ ሲያደርጉ ቆይተዋል። የግድቡ ግንባታ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር የሚገኙ መላ ኢትዮጵያውያን ቦንድ ከመግዛት የዲፐሎማሲ ስራዎችን አስከመስራት ድረስ በነቂስ የተሳተፉበት እና በፈተናዎች መካከል ሆኖ በራስ አቅም ተገንብቶ በመጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ የሚገኝ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው።

የግድቡ ፕሮጀክት አፈጻጸምም ሲታይም አሁን በማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ ይገኛል። ከግድቡ ግንባታ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት የተገኘ መረጃ እንዳመለከተው፤ አጠቃላይ የግድቡ ግንባታ አፈጻጸም በአሁኑ ወቅት በአማካይ 95 በመቶ ደርሷል። የሲቪል ስራው (ግንባታው) 98 ነጥብ ዘጠኝ በመቶ ያህል ተጠናቅቋል። የውሃ ማስተላለፊያ አሸንዳ የብረታ ብረት ስራዎቹ ደግሞ 87 ነጥብ አንድ በመቶ ያህል ነው የተጠናቀቁት።

አሁን የቀረው የግደቡ ዋና ስራ የተርባይን ስራ ሲሆን፣ ይህም 76 በመቶ አካባቢ ተጠናቋል። ግንባታው ለውጡ ሲመጣ ከነበረበት 13 በመቶ ከፍተኛ እምርታ በማሳየት አሁን ያለበት ደረጃ ደርሷል። በቀጣይም ቀሪ የቴክኒክ ስራዎችን ጨምሮ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚፈልጉ ስራዎች የሚኖሩ ሲሆን፣ ለዚህም 50 ቢሊየን ብር ያህል ያስፈልጋል።

የግድቡ ግንባታ የተጀመረበት ቀን በየዓመቱ ሲከበር ቆይቷል፤ በዚህም ግንባታው የደረሰበትን ደረጃ፣ ለግንባታው የሚያስፈልግ ድጋፍ የማሰባሰብ ስራዎች ተሰርተዋል።

የግድቡ ግንባታ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ የግድቡ ግንባታ የተጀመረበት 13ኛ ዓመት “በህብረት ችለናል!” በሚል መሪ ቃል መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም በተለያዩ ሁነቶች ይከበራል። የፕሮጀክት ጽህፈት ቤቱ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ልማት ባንከ ጋር በመሆን በቦንድ ሳምንቱ የቦንድ ማሰባሰብ ስራ እንደሚካሄድ ጠቁሟል፤ በዚህም አንድ መቶ ሚሊየን ብር የማሰባሰብ እንቅስቃሴም አስጀምሯል።

የሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሐም የግድቡን ወቅታዊ የግንባታ ሁኔታ አስመልክቶ በተሰጠው መግለጫ ላይ እንዳስታወቁት፤ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላለፉት 13 ዓመታት ለግድቡ ድጋፍ አድርጓል፤ እስከ የካቲት 30 ቀን 2016 ዓ.ም ከ19 ቢሊየን ብር በላይ ከሕዝቡ ማሰባሰብ ተችሏል። ይህ ድጋፍ አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ይህን ሀብት በማሰባሰብ በኩል ከፍተኛውን ሚና የተጫወተው፣ የታላቁ ሕዳሴ ግደብ ቦንድ ሸያጭ ሲሆን፣ ቦንዱም በኢትዮጵያ ልማት ባንክ እና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች እና በርቀት አካባቢዎችም በተለያዩ የብድር እና ቁጠባ ተቋማት በኩል ሲሸጥ ቆይቷል፤ ላለፉት ዓመታት ለግድቡ ግንባታ ከሚያስፈልገው ውስጥ መላው ሕዝብ የሚጠበቅበትን ከ10 እስከ 20 በመቶ በአማካይ 15 በመቶ ድጋፍ አድርጓል።

የፕሮጀክቱ ግንባታ በማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ኃይሉ፣ ኃይል በማመንጨት ላይ ካሉት ሁለት ዩኒቶች ተጨማሪ ሌሎች ዩኒቶች ተጠናቅቀው በቅርቡ ኃይል ያመነጫሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም አስታውቀዋል። ሕዝባዊ ተሳትፎው ባለፉት 13 ዓመታትም ተጠናከሮ መቀጠሉን ጠቅሰው፣ ከሐምሌ 2015 ጀምሮ እስከ የካቲት 30 2016 ድረስም ባሉት ስምንት ወራትም 931 ሚሊየን 984 ሺህ ያህል ብር መሰባሰቡን ጠቅሰዋል።

አቶ ኃይሉ እንደገለጹት፤ የግድቡ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ 74 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ ይይዛል። በእስካሁኑ በአራት ዙር የውሃ ሙሊትም 42 ቢሊየን ኩዩቢክ ሜትር ውሃ የተሞላ ሲሆን፣ ቀሪው 32 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ ሙሊት በየዓመቱ እና በየደረጃው እንዲፈጸም በማድረግ በአጭር ዓመታት ውስጥ ይጠናቀቃል።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ አሁን በሁለት ተርባይን 540 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እየተመረተ ይገኛል። አንዱ ተርባይን 375 ሜጋ ዋት የማምረት አቅም ያለው ሲሆን፣ ሁለቱም ተርባይኖች በሙሉ አቅማቸው ማምረት ውስጥ ሲገቡ 750 ሜጋ ዋት የማምረት አቅም ይኖራቸዋል። አሁን ያሉት ተርባይኖች በአማካይ የሚያመነጩት 540 ሜጋ ዋት ወደ ብሔራዊ የኃይል ቋት እየገባ ነው።

በግንባታ ላይ የሚገኙ አምስት ተርባይኖች እና ሌሎች በቀጣይ የሚገነቡ ተርባይኖችን ጨምሮ አጠቃላይ ግድቡ ግንባታው ሲጠናቀቅ የሚያመርተው ኤሌክትሪክ ኃይል አምስት ሺህ 150 ሜጋ ዋት ይሆናል።

አሁን ከዋናው ግድብ ወደ ኋላ የተኛው ውሃ 160 ኪሎ ሜትር ሲሆን፤ ግንባታው ሲጠናቀቅ ደግሞ ከዋናው ግድብ ወደ ኋላ 256 ኪሎ ሜትር ላይ ውሃ ይተኛል።

የአባይ ግድብ ከኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት በተጓዳኝ ሌሎች በርካታ ፋይዳዎችም ይኖሩታል። ትላልቅ ክብደት ያላቸው ጭነቶችን በውሃው ላይ ለማጓጓዝ የሚያስችሉ መርከቦችን በውሃው ላይ ለመጠቀም ያስችላል። የባህር ኃይል ለጀልባ ማመረቻ ምቹ የሚሆነው የትኛው አካባቢ ነው በሚለው ላይ ጥናት ማድረጉን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በግድቡ ዙሪያ የተፈጠረው ሰው ሰራሽ ኃይቅ እየሰፋ ሲሄድና ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ ከ78 በላይ ደሴቶች ይፈጠራሉ። ይህም ዋነኛ የቱሪስት ማዕከል እንዲሆን ያደርገዋል የሚል እምነት እንዲጣልበት አድርጓል።

የውሃ አካሉን ተከትሎ ሪዞርቶች የሚገነቡ ሲሆን፣ ለአሳ ልማትና ለመሳሰሉት ኢኮኖሚያዊ አማራጮች ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል። ቀደም ሲል ተካሂዶ ይፋ በተደረገ ጥናት መሰረትም በዓመት ከ10 ሺህ እስከ 50 ሺህ ቶን አሳ ሊመረትበት እንደሚችል ተጠቁሟል። እስከ 80 ኪሎ ግራም የሚመዝኑ የአሳ ዝርያዎች በግድቡ መገኘታቸውን ተመልክቷል። ይህ የአሳ ሀብት በከፍተኛ ደረጃ እየተራባ ሲሆን፣ ግድቡ በቀጣይም ለአሳ ልማቱ በጣም ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል ተብሎ ታምኖበታል።

ለዜጎች የስራ እድል በመፍጠርም ትልቅ ድርሻ ይዟል ሲሉ ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፣ በግንባታው ወቅት የውጭ ዜጎችን ሳይጨምር እስካሁን ወደ 12 ሺህ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የስራ እድል ፈጥሯል ብለዋል። ኢትዮጵያውያኑ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና በሌሎች ግድቦች ግንባታዎች ያልታዩ ማሽነሪዎችን የተዋወቁ መሆናቸውን አቶ ኃይሉ አመልክተው፣ በዚህም የካበተ ልምድ እና ተሞክሮ ይዘው እንደሚወጡ አስታውቀዋል። ወደፊትም መንግስት በዚህ ፕሮጀክት የሰሩትንና ከፍተኛ ከህሎት ያካበቱተን ባለሙያዎች በማሰባሰብ ሌሎች ፕሮጀክቶች ላይ እንደሚያሳትፍ ይጠበቃል ብለዋል።

ከሕዳሴ ግድቡ በመነሳት ወደ ብሔራዊ የኃይል ማስተላለፊያ ግሪድ የሚዘልቅ ከሕዳሴ ግድብ ጀምሮ እስከ ሆለታ 500 ኪሎ ቮልት የሚሸከም የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ግንባታም አስቀድሞ መጠናቀቁን ተናግረዋል።

የግድቡ ግንባታ ከፍፃሜው ሲደርስ ከዚህ ፕሮጀክት የሚወሰዱ በርካታ ተሞክሮዎችና ልምዶች መኖራቸውን ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ለልማቱ አንድ ሆኖ መነሳቱ በራሱ ትልቅ ስኬት መሆኑን ገልጸው፣ ግድቡን በራስ አቅም በራስ አገር ገንዘብ የመገንባት ልምድ የተወሰደበት መሆኑንም ተናግረዋል። ይህም ሌሎች ግድቦችን ለመስራት አቅም ማካበት የተቻለበት ነው ብለዋል።

በሕዳሴ ግድብ ብቻ ችግራችን አይፈታም፤ የሕዳሴ ግድብ የፈጠራቸውን በርካታ ልምዶች በመጠቀም በአባይ ወንዝ ላይ በቀጣይ ሊገነቡ የሚችሉትን ጨምሮ ሌሎች በግንባታ ላይ የሚገኙ እና በቀጣይ የሚገነቡ ፕሮጀክቶችን ለመስራት የሕዳሴ ግድቡ ፋና ወጊ መሆኑንም አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዚደንት አቶ ጌታቸው ዋቄ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ የዛሬ 13 ዓመት በዚህ ወር በራስ አቅም ግድቡን ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ሲቀመጥ አንስቶ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከመንግስት ውክልና ተሰጥቶት ቦንድ ለማሳተም ተመርጦ እየሰራ ይገኛል። ባንኩ ከ25 ብር እስከ 100 ሺህ ብር የሚይዙ ቦንዶችን ይዞ እስከታችኛው የባንኩ መዋቅር ድረስ እንዲሁም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ቅርጫፎቹ እንዲሁም በብድርና ቁጠባ ተቋማት በቅርንጫፎቻቸው በኩል ለሕብረተሰቡ ተደራሽ ሲያደርግ ቆይቷል።

እስካሁንም ድረስ በተለያየ መልክ በስጦታ የተሰበሰበውን ሳይጨምር በሶስቱ ተቋማት በቦንድ ብቻ 16 ቢሊየን 830ሚሊየን ያህል ብር ተሰብስቧል። ይህም ለግድቡ ግንባታ ሕብረተሰቡ ያደረገው ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑን ያመላከተ ነው። ባለፉት ስምንት ወራትም እስከ የካቲት 30 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ብቻ 767 ሚሊየን ሶስት መቶ ሺህ ብር መሰብሰቡን ምክትል ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል። በዚህ ሳምንትም የግድቡ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠበት 13ኛ ዓመትን በማስመልከት የበለጠ ገንዘብ ለማሰባሰብ ይሰራል ብለዋል።

እስካሁን ተመላሽ የሆነውን ቦንድ በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ አንድ ቢሊየን 250 ሚሊየን ብር ቦንድ ለገዙ ከነወለዱ ተመላሽ መደረጉንም ጠቁመዋል። ቦንዱን የገዙ ደንበኞች ለሌላ ዘመናት ገንዘቡ እንዲቆይ እና ለሕዳሴ ግድቡ አገልግሎት እንዲውል ማድረግ እንደሚችሉ ጠቅሰው፣ ገንዘቡ ይሰጠን ያሉም ጊዜውን ጠብቆ ከነወለዱ እንደሚከፈላቸው አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደንበኞች ግንኙነት ሂሳብ አስተዳደር ስርዓት ዳይሬክተር ወይዘሮ ቤቴል ታደሰ በበኩላቸው እንዳብራሩት፣ ባንኩ በሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሀገራዊ ኃላፊነቱን ሲወጣ ቆይታል። ባለፉት 13 ዓመታት ከ200 ሚሊየን ብር በላይ ቦንድ በመግዛት ድጋፍ አድርጓል። በክልሎች ጨምሮ ከአንድ ሺ 500 በላይ በሆኑ ቅርንጫፎቹ የቦንድ ሽያጭ በማከናወን ከዘጠኝ ነጥብ ስምንት ቢሊየን ብር በላይ በሰራተኞች መዋጮና በሽያጭ ሰብስቧል፤ ከ319 ሚሊየን ብር በላይ ደግሞ በስጦታ ሰብስቧል። በውጭ አገራት በሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም እንዲሁ 61 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ያህል፤ አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊየን ፓውንድ፤ 49 ሚሊየን ዩሮ ማሰባሰብ ችሏል።

ባንኩ ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ተያያዥ ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል። በዚህ ሳምንትም በሁሉም ቅርንጫፎቹ አስፈላጊውን የቦንድ ስቶክ በመያዝ በውጭ እና በሀገር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን የተለመደውን ጠንካራ ተሳትፎኣቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል። ሕብረተሰቡ በየትኛውም የባንኩ ቅርንጫፍ ቦንድ መግዛት እንደሚችል ጠቁመው፣ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም በኦንላይን አማራጮች በመረጡት አገር ገንዘብ ቦንድ ሊገዙ የሚችሉበት ፕላትፎርም መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የግድቡ አራተኛ ሙሊት በተሞላበት ወቅት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ለአሳ ምርት፣ ለመጠጥ ውሃ፣ ከምንም በላይ ደግሞ አካባቢን የማይበክል ንጹህና ታዳሽ የኃይል ምንጭ መሆኑን መናገራቸው የሚታወስ ነው። ከፍተኛ አቅም ያለው የኤሌክትሪከ ኃይል የሚያመነጭ በመሆኑም ለኃይል ምንጭ፤ ለቤት ውስጥ ስራ፤ ኢንዱስትሪ ለማስፋፋት ያለውን ጉልህ ፋይዳ አንስተዋል።

የሕዳሴ ግድቡ የተገነባበት አካባቢ፤ ከዚህ ቀደም ሞቃታማ እና በረሃማነት የበዛበት ሲሆን አሁን ግን ውሃ መያዝ ከጀመረ ወዲህ በከፍተኛ ደረጃ አካባቢውን እያቀዘቀዘውና ንጹህ እያደረገው ተፈጥሮኣዊ ውበቱን እንዲያገኝ የሚያስችል ነው። በመሆኑም የዱር አራዊቱ ወደ አካባቢው ይመለሳሉ፤ የተለያዩ እፅዋት ያድጋሉ። ከኢኮሎጂ ቱሪዝም አኳያም ለዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ይኖሩታል። ከቱሪዝም አኳያም ውብ የሆኑ ደሴቶች ይኖሩታል፤ ውሃው የሚተኛበት ሰፊ ስፍራ፣ ጥልቀትና ርዝመት የውሃ ላይ ተግባራትን ለማካሄድ ያስችላል። በመሆኑም አንዱ ትልቁ የቱሪዝም መዳረሻ ሆኖ ሊበለፅግ የሚገባው ነው ብለዋል።

‹‹ሕዳሴ ግድቡ ለብዙ አፍሪካውያን የዳግም አድዋ ነው›› ሲሉም የነፃነት፣ ራስን የመቻል፣ ከልመና የመገላገል ምልክት፣ እንዲሁም ለልማት፣ ለብልፅግና፣ ለዕድገት የመቆም እና አልንበረከክም የሚል ምልክት ነው። በመሆኑም ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለብዙዎችም ትምህርት ቤት መሆኑንም አመላከተዋል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 21 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You