በፈጣሪ የታደለችውን ሀብት በመጠቀም ኢትዮጵያ በውጤታማ የኤሌክትሪክ ኃይል ልማት ላይ ትገኛለች። ልማቱ በተለያዩ የውሃ፣ የንፋስ እንዲሁም የፀሐይ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ልማቶች በኩል በተጨባጭ እየታየ ነው። በተለይ ደግሞ ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ሊጠናቀቅ በወሳኝ ምዕራፍ ላይ የሚገኘው ግዙፉ ታላቁ የዓባይ ግድብ ዕውን መሆን የልማቱ ስኬታማነት ጎልቶ ታይቷል።
በአፍሪካ ጭምር የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች ሁሉ አውራ የሆነው ታላቁ የዓባይ ግድብ ግንባታ ሙሉ ባልተጠናቀቀበት ሁኔታም በሁለት ተርባይኖቹ ከ700 በላይ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እያመረተ ይገኛል።
የኤሌክትሪክ ኃይል ልማቱ ውጤታማነት የሚመረተውን የኃይል መጠን በሜጋ ዋት በመግለጽ ማስረዳት ቢቻልም፣ በየቤቱ፣ በየኢንዱስትሪው፣ በየተቋማቱ፣ ወዘተ እየቀረበ ባለው አገልግሎት መግለጽም ይቻላል።
በሀገሪቱ በፈረቃ ይሰጥ የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል መቅረቱ፣ በከተማ እየተፈጠረ ያለውን አዲስ አኗኗር የሚሸከም የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት መገኘቱ፣ እያደገ የመጣውን የኢንዱስትሪ ዘርፍ የኤሌክትሪክ ፍላጎት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን መመለስ እየተቻለ ያለበት ሁኔታ ሌሎች የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦቱ ዕድገት ማሳያዎች ናቸው።
አዳዲስ የኤሌክትሪክ መስመሮችን በመዘርጋት ከመሠረተ ልማት ውጪ ያሉትን ደግሞ በገጠር ኤሌክትሪፊኬሽን በኩል የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል። በዚህም በገጠር በጨለማ ውስጥ ሲዳክሩ የኖሩ ዜጎች ብርሃን ያገኙበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ይህም የኤሌክትሪክ ልማቱ ከፍተኛ ደረጃ መድረስ ሌላው ማስረጃ ነው።
በቅርቡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሰጠው መግለጫም ይህንኑ ይጠቁማል። በሀገሪቱ ስምንት ሺ ከተሞችና የገጠር መንደሮች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ የተቻለበትን ሁኔታ ለእዚሁ ማሳያነት ሊጠቀስ ይችላል።
እንደሚታወቀው በሀገሪቱ አዳዲስ ከተሞች እየተፈጠሩ፣ ነባሮቹ ከተሞችም በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፉ ይገኛሉ። እነዚህ ከተሞች ከአዳዲስ የአኗኗር ዘይቤ ጋር የተዋወቁ እንደመሆናቸው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ፍላጎታቸው ከፍተኛ ነው። የኃይል ልማቱና አቅርቦቱ ይህን ፍላጎት በመመለስ ላይ ይገኛል።
በሀገሪቱ የኢንዱስትሪው ዘርፍ እየተስፋፋ ለመምጣቱ አንዱ ምክንያት የኤሌክትሪክ ኃይል በማምረት በኩል እያከናወነች ያለችው ተግባር ተስፋ ሰጪ በመሆኑ ነው። ሀገሪቱ ከሌሎች ሀገሮች አኳያ ስትታይ ዝቅተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ክፍያ የሚጠየቅባት መሆኗም ይገለጻል። ይህም ለኢንዱስትሪው ዘርፍ መስፋፋት አንድ ወሳኝ ምክንያት ተደርጎ ይወሰዳል።
ከራሷ አልፋ ጎረቤት ሀገሮችን ባለመብራት እያደረገችም ትገኛለች። ሱዳን፣ ጅቡቲ፣ ኬንያ የዚህ ኃይል ተቋዳሽ መሆን ችለዋል፤ ታንዛኒያም የኤሌክትሪክ ኃይሉን ለመቋደስ አቅዳለች። ይህ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ፍላጎት እስከ ደቡብ አፍሪካ ሊዘልቅ እንደሚችል እየተገለጸ ይገኛል።
ይህም ሁኔታ ሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ በምታገኝባቸው መንገዶች ላይ አዲስ መንገድ እንድትጨምር አድርጓታል። ኤሌክትሪክ እንደ ወርቅ፣ ቡናና አበባ ምርቶች ሁሉ የሀገሪቱ የወጪ ምርት መሆን ችሏል። የኤሌክትሪክ ኃይል ለእነዚህ ሀገሮች በመሸጥ የውጭ ምንዛሬ እያገኘች ነው። ይህም የኤሌክትሪክ ኃይል ልማቱ የደረሰበትን ከፍተኛ ደረጃ የሚያመለክት ሌላ ማስረጃ ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ለተሽከርካሪዎች የኃይል አማራጭ በመሆን ነዳጅን እየተካ ይገኛል። ሀገሪቱም ዜጎችም ዋጋው በየጊዜው እየተወደደ ከመጣው ነዳጅ ጥገኝነት ለመላቀቅ አንድ መፍትሄ እየሆነ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ በርካታ ተሽከርካሪዎች በነዳጅ ሳይሆን በኤሌክትሪክ ኃይል በአውራ ጎዳናዎች ላይ እየፈሰሱ ናቸው። በሀገሪቱ በኤሌክትሪክ የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ብዛት ከ100 ሺ በላይ መሻገራቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ። የእነዚህ ተሽከርካሪዎች በስፋት ወደ ሀገሪቱ መምጣት ያለውን ሰፊ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅም ታሳቢ ያደረገ ነው። የተሽከርካሪዎቹን የኤሌክትሪክ ፍላጎት ለማሟላት በአዲስ አበባ ብቻ 60 የኤሌክትሪክ ኃይል መሙያ ማሽኖች ተገጥመዋል። እነዚህን ተሽከርካሪዎች መጠቀም ውስጥ የተገባው በተለያዩ ምክንያቶች ሊሆን ቢችልም፣ ለኢትዮጵያ ግን አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ያላት ከመሆኑ ጋር ሊያያዝ ይችላል።
የኤሌክትሪክ ኃይል ከአካባቢ ጋር የሚስማማ እንደመሆኑም፣ ኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎችን በስፋት በማስገባት ላይ ያለችበት ሁኔታ፣ ኢንዱስትሪዎች፣ ድርጅቶች፣ ወዘተ በጀኔሬተር የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎታቸውን ለመመለስ የሚያደርጉትን ጥረት የሚቀነስ ከመሆኑ ባሻገር ሀገሪቱ እየገነባች ላለችው አረንጓዴ ኢኮኖሚም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
በቅርቡ ግንባታው እንደሚጠናቀቅ የሚጠበቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገባ ሀገሪቱ የሚያስፈልጋትን የኃይል አቅርቦት በወሳኝ መልኩ ሊመለስ እንደሚችል ይጠበቃል። በዚህ ላይ ሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ልማቱን አሁንም አጠናክራ ቀጥላለች። በኮይሻ፣ በንፋስ ኃይል ማመንጫና በመሳሰሉት እየተከናወኑ ያሉ ተግባሮችም ይህንኑ ያመለክታሉ።
ይህ ልማት የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እጥረት የሀገሪቱ ችግር እንዳይሆን ያደርጋል። መንግሥት በዚህ ልማት ሲያካሂድ የቆየውና የሚያካሂደው ተግባር፣ ሕዝቡም ከአምስት ሺ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመርተው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እውን እንዲሆን ላደረገው ድጋፍ አድናቆት ሊቸራቸው ይገባል!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 21 ቀን 2016 ዓ.ም