ከወር ደሞዝተኝነት ወደ ላኪነት

ቡና አብቃይ ከሆኑ የኢትዮጵያ አካባቢዎች መካከል ጅማና አካባቢዋ ይጠቀሳሉ። በጅማ ዞን ዞኖችና ወረዳዎች ቡና በስፋት ይመረታል። የአካባቢዎቹ ሕዝብም በየጓሮው ቡና ያለማል። በእያንዳንዱ አርሶ አደር ጓሮ የሚለማው ቡና ከቤት ውስጥ ፍጆታ ባለፈ በአቅራቢዎችና በላኪዎች አማካኝነት ለዓለም ገበያ ይቀርባል።

በጅማና አካባቢዋ ከሚገኙ ቡና አልሚ አርሶ አደሮች፣ ሰብሳቢዎች፣ አቅራቢዎችና ላኪዎች መካከልም አቶ ናስር አብዱ አንዱ ናቸው። በዞኑ የቡ ወረዳ ኬላ ቢሎ አካባቢ ተወልደው ያደጉት አቶ ናስር፤ የአርሶ አደር ልጅ እንደመሆናቸው ቡናን ጨምሮ በተለያዩ የግብርና ሥራዎች ላይ እየተሳተፉ ነው ያደጉት።

በግብርና ሥራ ቤተሰባቸውን ከማገልገል ጎን ለጎንም የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለው በትውልድ አካባቢያቸው በጅማ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች በመምህርነት አገልግለዋል። ከመምህርነት ባሻገርም በወረዳ ትምህርት ቢሮዎች ሰርተዋል።

በመንግሥት ሥራ የሚያገኙት የገቢ መጠን ሕይወታቸውን ለመምራት እንዲሁም የቤተሰባቸውን ፍላጎት ለማሟላት በቂ አልሆን ያላቸው አቶ ናስር፣ ይህን ለመሙላት ወደ ንግድ ሥራ ገቡ። በአካባቢያቸው በስፋት የሚመረተውን ቡና መነገዱን ተያያዙት። አቶ ናስር ቡናን ከልማቱ ጀምሮ ያውቁታል። ‹‹ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል›› እንደሚባለው ሌሎች ቡና በስፋት እየነገዱ ሲለወጡ አቶ ናስር አስተውለዋል፤ እሳቸውም በቡና ንግዱ ቢሰማሩ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ አምነው ነው የቡና ንግዱን የተቀላቀሉት። በንግዱ ስራም ብዙም አልተቸገሩም።

እሳቸው እንዳሉት፤ ስለቡና ብዙ ቢያውቁም ንግድን የጀመሩት ግን በትንሽ በትንሹ ነው፤ ዝቅ ብለው ነው የተነሱት። ቡና በኩባያና በኪሎ ከአርሶ አደሩ በመግዛት በአካባቢው ለሚገኙ ቡና ሰብሳቢዎችና አቅራቢዎች መሸጡን ቀጠሉ።

በዚህ ሁኔታ የተጀመረው የቡና ንግድ ቀስ በቀስ ተሻሽሎ ወደ ማዕከላዊ ገበያ መድረስ ቻለ። የቡና ንግድ ሥራቸውን እያሳደጉ መጥተው በአሁኑ ወቅት በጅማ ዞን ከሚገኙ ቡና አቅራቢና ላኪዎች መካከል አንዱ መሆን ችለዋል፤ የጅማ ዞን ቡና አቅራቢዎች ማህበር ሊቀመንበር ናቸው።

አቶ ናስር ወደ ማዕከላዊ ገበያው መግባት ግን ቀላል አልሆነላቸውም፤ በርካታ ፈተናዎችን እና መሰናክሎች አጋጥመዋቸዋል። ያም ቢሆን በአካባቢው የለማውን ቡና ከአርሶ አደሩ በመግዛት ፈልፍለው፣ አበጥረው፣ ለቅመውና ለውጭ ገበያ ዝግጁ አድርገው ወደ ማዕከላዊ ገበያ አዲስ አበባ አጓጉዘው በጨረታ ሲሸጡ እንደነበር አስታውሰዋል።

ከልጅነት እስከ ዕውቀት የሚያውቁትን የግብርና ሥራ መነሻ አድርገው የቡና ንግድን የተቀላቀሉት አቶ ናስር፤ ላለፉት 25 ዓመታት ቡና ሲነግዱና ሲያለሙ ቆይተዋል። በእነዚህ ዓመታትም በቡና ንግድ ውስጥ የተለያዩ ውጣ ውረዶችን አሳልፈዋል።

የምርት ጥራትን አስጠብቆ በስፋት የማምረትና ለውጭ ገበያ የማቅረብ ሂደቱን ውጤታማ ለማድረግ ብርቱ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ያስታወሱት አቶ ናስር፤ ከብዙ ልፋትና ድካም በኋላ ዛሬ ቡና በጥራት እንዲመረትና በተለያዩ የግብይት አማራጮች መሸጥ የሚቻልበት ዕድል መፈጠሩን ይናገራሉ።

እሳቸው እንዳሉት፤ ከዚህ ቀደም ቡና በጨረታና በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በሚሸጥበት ጊዜ ፈተናዎች ነበሩ። የመገበያያ መንገዱ በተለይም ቡና አምራቹን፣ ሰብሳቢውንና አቅራቢውን በብርቱ ሲጎዳው ቆይቷል። አርሶ አደሩ የቡና ምርቱን በቀጥታ መሸጥ የማይችልበት ሁኔታ ነበር፤ መንገዱ ውስብስብና የተንዛዛ በመሆኑ ብዙ እንግልት ይገጥመው እንደነበርም ተናግረዋል።

የግብይት ስርዓቱ ጤናማ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ በወቅቱ በቡና ንግድ ውስጥ ትልቅ ፈተና ነበር፤ የግብይት ሰንሰለቱ ረጅምና ውስብስብ ነበር ያሉት አቶ ናስር፣ በተለይም ቡና እንደሌሎች ሸቀጦች በምርት ገበያ በኩል በሚሸጥበት ወቅት ተጠቃሚ እንዳልነበሩ ይናገራሉ። ይህም በተለይም ቡና አምራች አርሶ አደሩን ተስፋ ያስቆረጠ በመሆኑ አርሶ አደሩ ከቡና ይልቅ ወደሌሎች ምርቶች ሲያደላ እንደነበር አንስተዋል።

በወቅቱ የነበረው የግብይት አማራጭ አንድ ብቻ በመሆኑ አርሶ አደሩም ሆነ አቅራቢው ተጠቃሚ አልነበረም ሲሉ አቶ ናስር ይገልጻሉ፤ ለ25 ዓመታት ቡና ተሸክመው ለአቅራቢዎች ሲያቀርቡ መኖራቸውን ጠቅሰው፣ አሁን ግን የቀጥታ ትስስር የግብይት አማራጭ የፈጠረውን ዕድል በመጠቀም ቡና በቀጥታ ወደ ውጭ ገበያ መላክ ውስጥ ገብተው እየሰሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

አቶ ናስር እንዳሉት፤ የቡናውን ዘርፍ እየመራ ያለው የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ሲሆን፤ በተለይም የቀጥታ ትስስር የግብይት አማራጭን (Vertical In­tegration) ተግባራዊ ማድረግ በመቻሉ አርሶ አደሩ ጭምር የላኪነት ዕድል ተፈጥሮለታል፤ ይህም ሁኔታ በቡና ዘርፍ ተሰማርቶ የመሥራት ተነሳሽነቱ እንዲጨምር አድርጎታል።

የቀጥታ ትስስር የግብይት አማራጭ ለዘርፉ ዕድገት ትልቅ አበርክቶ እንዳለው አቶ ናስር ጠቅሰው፤ አርሶ አደሩ ያለማውን ቡና አቅም ካለው በቀጥታ ለውጭ ገበያ ማቅረብ አልያም ለላኪዎች ማቅረብ የሚችልበት ዕድል ተፈጥሯል ብለዋል። በዚህም አበረታች ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ጠቅሰው፤ የእርሳቸው ተሞክሮም ይህንኑ እንደሚሳይ ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ‹‹ቡና አምራቹም ሆነ አቅራቢው ቡና ላኪ መሆን ይችላል›› የሚል ሕግ በማውጣቱ ከአቅራቢነት ወደ ላኪነት የተሸጋገሩት አቶ ናስር፤ ጥሩ ገበያ ሲያገኙ ቡናቸውን በቀጥታ ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ለአገራቸው እንደሚያስገኙ ይገልጻሉ።

በሌላ አማራጭ ደግሞ ለውጭ ገበያ ያዘጋጁትን ቡና ለላኪዎች ማቅረብ እንደሚችሉ ተናግረዋል። ይህ አማራጭ የገበያ ዕድልም አርሶ አደሩና አቅራቢው ቡና ላኪ እንዲሆኑ ከማስቻል ባለፈ ቡና ወደ ውጭ ገበያ የመላክ አቅማቸውንም ከፍ ማድረግ እንዳስቻለ ተናግረዋል።

የግብይት አማራጮቹ ጉልህ አበርክቶ ያላቸው ቢሆኑም፣ አንዳንድ ችግሮች የለባቸውም ማለት አይደለም የሚሉት አቶ ናስር፤ በአምራቹ፣ በአቅራቢውና በላኪው መካከል ከክፍያ ጋር በተያያዘ አልፎ አልፎ ያለመተማመን ችግሮች እንደሚታዩም ጠቁመዋል። አቅራቢዎችና ላኪዎች ቡናውን ከተረከቡ በኋላ ክፍያ የማዘግየትና በአግባቡ ያለመፈጸም ችግሮች እንደሚታይባቸው ገልጸዋል። እነዚህንና መሰል ችግሮችን ለመፍታት መፍትሔ ማፈላለግ ተገቢ እንደሆነም ጠቅሰው፣ እያጋጠሙ ካሉ መካካዶች ውጭ ሌላ ችግር እንደሌለ ነው የተናገሩት። በግብይት አማራጮቹ የተገኘው ድል ከፍተኛ እንደሆነ ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል።

አቶ ናስር እንዳብራሩት፤ በቀጥታ ትስስር ከአርሶ አደሩ ጋር በመቀናጀት ቡናውን 120 ከሚደርሱ አርሶ አደሮች ይገዛሉ። በ10 ሄክታር መሬት ላይም በግላቸው ቡና ያለማሉ። ከአርሶ አደሩ የሚያገኙትን ቡና እንዲሁም በ10 ሄክታር መሬት ላይ የሚያለሙትን ቡና በቡና ማበጠሪያ ጣቢያቸው አዘጋጅተው ለውጭ ገበያ ያቀርባሉ።

በጅማ ዞን አካባቢ በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች አንድ የእሸት ቡና መፈልፈያ ጣቢያ እንዲሁም ሁለት የደረቅ ቡና ማበጠሪያ ጣቢያ ያላቸው ሲሆን፤ ቡናውን የሚያዘጋጁባቸው መፈልፈያ፣ ማጠቢያና ማበጠሪያ ጣቢያዎቹ የሚገኙትም በጅማ ዞን ማና ወረዳ ዱአ ቀበሌ እንዲሁም ሊሙ ኮሳ ነው።

የግብርና ሥራውን ጨምሮ በቡና መፈልፈያና ማበጠሪያ ጣቢያዎች ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል ፈጥረዋል። ቡናውን ከየአካባቢው ሰብስበው ወደ መፈልፈያ ጣቢያ የሚያቀርቡትን ጨምሮ 40 የሚደርሱ የአካባቢው ወጣቶች የሥራ ዕድል ከፍተዋል። እሸት ቡና /ቀይ ቡና/ በሚደርስበት ጊዜ ቡናውን ከማድረቅ ጀምሮ በሚፈለፈልበት፣ በሚለቀምበትና በሚበጠርበት ወቅት አራት መቶ ለሚደርሱ ዜጎች ጊዚያዊ የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ።

አቶ ናስር በውጭ ምንዛሬ ግኝት በኩልም ተጠቃሽ ተግባር እያከናወኑ ናቸው። በተያዘው በጀት ዓመት ከ20 እስከ 25 ሺ ኬሻ የሚደርስ ቡና ለውጭ ገበያ በማዘጋጀት ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት እየሠሩ መሆናቸውን አቶ ናስር ይገልጻሉ። ለዚህም ከውጭ ገዢዎች ጋር የገበያ ስምምነት ተፈራርመው እየሰሩ ሲሆን፤ እስካሁን አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዶላር ማግኘት ችለዋል። ቀሪውን ለማሟላትም በዝግጅት ላይ ናቸው። የገበያ አማራጩ አርሶ አደሩ ቡናን በቀጥታ ለውጭ ገበያ መላክ ከማስቻሉ ባለፈ ቡናው ሳይባክን በጥራት ተዘጋጅቶ እንዲላክም አበርክቶው የጎላ ነው።

አቶ ናስር፤ የቀጥታ ትስስር ግብይት አማራጭ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረግ የቻለና ውጤት ያሳየ መሆኑን ሲገልጹ፤ አርሶ አደሩ ከዚህ ቀደም በገዛ ቡናው ተጠቃሚ አልነበረም ይላሉ። አሁን በተፈጠረው የግብይት አማራጭ አርሶ አደሩ የልፋቱን ውጤት ማግኘት እየቻለ መሆኑን ይገልጻሉ።

እሳቸው እንዳሉት፤ ከዚህ ቀደም አርሶ አደሩ ቡና አልምቶ ቢሸጥም ሕይወቱን መቀየር አልቻለም። የእርሱን መኖሪያና የከብቶቹን ማደሪያም መለየት ሳይችል ኖሯል። በአሁኑ ወቅት ግን በቡናው ዘርፍ የተፈጠሩትን የግብይት አማራጮች በመጠቀም ኑሮውን ማሻሻል ሕይወቱን መቀየር ችሏል። የሳር ቤቱን በቆርቆሮ መቀየርና ልጆቹን ማስተማር ችሏል። ልጆቹን በማስተማሩም ቴክኖሎጂን በመጠቀም የዓለም አቀፍ የገበያ ዋጋውን አውቆና ተረድቶ ያለማንም ጣልቃ ገብነት ቡናውን መሸጥ የሚችልበት ዕድል ተፈጥሮለታል።

በማህበራዊ አገልግሎታቸውም ቢሆን የበኩላቸውን እየተወጡ እንደሆነ የገለጹት አቶ ናስር፤ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ለማገዝ ትምህርት ቤቶች ላይ ድጋፍ በማድረግ አቅም ለሌላቸው ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ እንደሚያሟሉ ጠቅሰዋል። የንጹህ የመጠጥ ውሃ በማውጣትና አቅመ ደካማ ለሆኑ አባወራዎች በተለያየ ጊዜ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ያደርጋሉ።

ከቡና ንግድ በተጨማሪ በጅማ ከተማ ሆቴል ገንብተው እየሰሩ ናቸው። የሕክምና አገልግሎት መስጫ ክሊኒክና ነዳጅ ማደያም ገንብተዋል። በትውልድ አካባቢያቸው ጅማ ዞን የቡ ወረዳ ላይም እንዲሁ ማደያ አቋቁመዋል።

በአካባቢው የነዳጅ እጥረት መኖሩን ተረድተው ያቋቋሙት መሆኑን ጠቅሰው፤ ማደያው ትርፋማ ያደርገኛል ብዬ ሳይሆን የአካባቢውን ማኅበረሰብ ለመጥቀም ያደረጉት ነው ሲሉ ያብራራሉ። አምቡላንስን ጨምሮ የአካባቢው ማኅበረሰብ ከዚህ ቀደም በችርቻሮ በውድ ዋጋ ሲገዛ የነበረውን ነዳጅ ከማደያው በአገር ዋጋ ማግኘት እንደቻሉ ተናግረዋል። ይህም ማኅበራዊ ኃላፊነትን የሚወጡበት ሌላኛው መንገድ እንደሆነ ነው የተናገሩት። ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት ለሚያቀርባቸው ማንኛቸውም አገራዊ ጥሪዎች እንዲሁ ምላሽ በመስጠት ግዴታቸውን እየተወጡ እንደሆነ አስታውቀዋል።

አቶ ናስር በቀጣይም በቡናው ዘርፍ በስፋት የመግባትና ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ሀሳብ አላቸው። በተለይም ባለ ልዩ ጣዕም ቡናን በጥራትና በብዛት አምርተው ለውጭ ገበያ በማቅረብ የአገሪቷን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ከፍ ለማድረግ አቅደው እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 21 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You