የወለደን አባት በሞት ….

ጥሩ አባትነት ከብዙ ዓመታት በኋላ ትርጓሜው እየተቀየረ የመጣ ይመስላል። በአሁኑ ሰዓት ስለ ልጆቻቸው ስሜት የሚጨነቁና በተሻለ መልኩ ከልጆቻቸው ጋር ጊዜ የሚያሳልፉ አባቶች እንደ ጥሩና አስተዋይ አባት ይታያሉ።

በአጠቃላይ በሚባል ደረጃ እስከ ጎርጎሳውያኑ 1970ዎቹ ድረስ ከሕጻናት ጋር በተያያዘ ስለአባቶች ኃላፊነት ብዙም እውቀት አልነበረም። ዋነኛውና ብዙ ጊዜ ብቸኛው ኃላፊነታቸው ኦኮኖሚያዊ የሆኑ ችግሮችን መፍታት ነበር። ብዙ ጥናቶች እንዳረጋገጡት ከአባቶቻቸው ጋር ጥሩ የሆነ ግንኙነት ኖሯቸው ልጅነታቸውን ያሳለፉ ሕጻናት የተሻለ የአዕምሮ እድገትና ጥሩ ባሕሪ ይታይባቸዋል። በሕይወታቸውም ደስተኛ የመሆናቸው እድል ከፍ ያለ ሲሆን ከሌሎች ሕጻናት ጋር ያላቸው ግንኙነትም ጥሩ ነው። በሌላ በኩል ከአባቶቻቸው እምብዛም ፍቅር ማግኘት ያልቻሉት ሕጻናት ግን ብዙ የሥነ አዕምሮ ችግሮች ይስተዋሉባቸዋል።

ቀን ሥራ ውለው ማታ ላይ ወደ ቤት የሚመለሱ አባቶች ሁሌም ቢሆን ከልጆቻቸው ጋር መጫወት ይፈልጋሉ። በዚህ ሰዓት አባትና ልጅ የማይረሱ የጨዋታ ጊዜዎችን ማሳለፍ ይችላሉ። ድብብቆሽና አባሮሽ እንዲሁም ሌሎች ጨዋታዎችንም ያዘወትራሉ።

አብዛኛውን የቀኑን ጊዜ ቤት ውስጥ ከልጆች ጋር የሚያሳልፉት እናቶች ደግሞ ከልጆቻቸው ጋር ረጋ ያለና በመርሕ ላይ የተመሠረተ ግንኙነት ለመመሥረት ይሞክራሉ። በተጨማሪም ምግብ መመገብ እንዲሁም ንጽሕናቸውን መጠበቅን ያዘወትራሉ። ይህ ደግሞ ልጆች ጨዋታና መዝናናትን ከአባቶቻቸው ብቻ እንዲጠብቁ ያደርጋቸዋል። ይህ በማይሆንበት ጊዜ ልጆች ላይ ድብርትና አንዳንዴም የከፋ የአዕምሮ ችግር ያስከትልባቸዋል።

የጽሑፋችን መግቢያ ላይ ስለ መልካም አባትነት ያነሳነው ከአባቱ ጋር ያላደገውና አድጎ አባቱን ሲያገኝ እንደ ጠላት የተመለከተው፤ ብሎም የአባቱን ሕይወት እስከ ማጥፋት የደረሰውን ልጅን ታሪክ በዛሬው የተናጋሪ ዶሴ ዓምዳችን ልናካፍላችሁ ስለወድድን ነው። መልካም ቆይታ።

የአባትየው ሕልም

አቶ ባሳ ኑሮን ለማሸነፍ በሚል አብዛኛውን ጊዜያቸውን ከቤተሰባቸው ተለይተው ነበር የሚኖሩት። ልጆችን ማቅረብ እንደ ማቅበጥ አደርገው ስለሚያስቡ ቤት በመጡ ሰዓትም ልጆቻቸውን እምብዛም አይቀርባቸውም ነበር። ዳዊትም የቤቱ ብቸኛ ወንድ ልጅ ነበር። በልጅነቱ በአባቱ ናፍቆት ሲሰቃይ ነበር ያደገው። ዘወትር ከአፉ የማይለያቸው፤ በመጡ ቁጥር አቅፈው እንዲያጫውቱት የሚፈልግ ልጅ ነበር። አባት ደግሞ በተቃራኒው ልፊያ የማይወዱ፤ አባትና ልጅ በርቀት ማደግ አለበት ብለው የሚያምኑ ነበሩ። በዚህም የተነሳ አንድም ቀን ብቸኛ ወንድ ልጃቸውን አቅፈው ስመውት አያውቁም ነበር። አንድም ቀን ፀጉሩን ዳብሰው ወይም እንደ ልጅ ከረሜላ ገዝተውለት አያወቁም። በዚህም የተነሳ የልጅነት ናፍቆትና ፍቅሩ ወደ ጥላቻ ተቀየረበት። አባቱን ለማየት የሚጋጓው ልጅ ለዓይኑ ጠላቸው። የፈለገውን ነገር በሙሉ በኃይል ማድረግ የሚወድ ልጅ ሆኖ አደገ።

አባት አቅማቸው ደክሞ የንግድ ሥራቸውን አቁመው ቤት መዋል ሲጀምሩ ነበር የልጆቻቸው አስተዳደግ ላይ ስህተት እንደሠሩ ያወቁት። ዘግይተው ሲያውቁ እጃቸውን አጣጥፈው ሳይቀመጡ ለማስተካከል በርካታ ጥረቶችን አድርገዋል። በተለይ የዳዊትን ባሕሪ ለማረቅ ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም። ግን ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ እንዲሉ አበው ከረፈደ ሆነና እንኳን ሊያርቁት ይቅርና ለራሳቸውም ጥርስ የሚነክስባቸው የሚያስፈራራቸው ልጅ ለመሆን በቃ።

አንድ ማለዳ ያዩት ሕልም በውናቸው እንዳይሆን እያለቀሱ ፈጣሪያቸውን ተማፅነው ተነሱ። ከባድ ሌሊትን ነበር ያሳለፉት። ተኝተው ይወራጩ ነበር። ልጃቸው ሰው ደብድቦ ሊታሰርብኝ ነው በሚል ጭንቅ ሲቃዡ ነበር ያደሩት። ልጃቸው ዱለኛ በመሆኑ የተነሳ ከማኅበረሰቡ ወቀሳ የሚደርስባቸው አባት ሥነ ልቦናዊ ሕመምን፣ ማስተናገድ የእለት ከእለት ሕይወታቸው አካል ነበረ። ልጃቸው በበርካቶች አፍ አሳዳጊ የበደለው ተበሎ ሲጠራ ከመመልከት በላይ ሕመመስ ከወዴት ሊመጣ?

ከሥነ ልቦናዊ ሕመሙ በተጨማሪ በዚህ ግልፍተኛ ልጃቸው የተነሳ አካላዊ ቁስልን፣ ስሜታዊ ሲቃንና ማኅበራዊ ሰቆቃን አደባባይ ላይ መፍራት አይነት ስሜቶችን አስተናግደዋል። በልጃቸው ከመዛት ያለፈ ምንም አያደርገኝም ቢሉም አንድ ቀን ግን ገፍትሮ የጣላቸውን ሲያስቡ ይሰቀጥጣቸዋል።

ልጃቸው ሰው ደበድቦ ፖሊሶች እያዳፉ ሲወስዱት ከኋላ ከኋላ እየተከተሉ ሲለምኑና ሲማፀኑ በሕልማቸው ያዩት አባት ከእንቅልፋቸው እንደተነሱ ነበር ልጃቸው ወደ ተኛበት ያቀኑት። ልጁ መኝታው ላይ አልነበረም። ደጅ ወጥተው ቢጣሩም ምላሽ የሚሰጣቸው ሲያጡ ተመልሰው ቁጭ አሉ።

ዳዊት ከዚህ ቀደም ሰው ደብድቦ አባቱ በሽምግልና እንዲጨርሱና ቢታሰር ግን እንደሚገላቸው ዝቶ ነበር። አባትየው ዛቻውን በመፍራት ሳይሆን አንድ ወንድ ልጃቸው እንዳይታሰርባቸው ሲሉ ጥረት አድርገው ነበር። የተደብዳቢው ወገን ግን የልጁ ጉዳት በካሣ የሚጠገን አይደለም ሕግ ይዳኘን ብለው አሻፈረኝ በማለታቸው ትተውታል።

በዚህም ምክንያት በከተማ ውስጥ ሰው ደብድቦ ጉዳት ማድረሱን ተከትሎ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ ተጣርቶበት ክስ እንዲመሠረትበት ለከተማው መጀመሪያ ፍርድ ቤት መዝገቡ መላኩን ይሰማል። አባቱ ያደረጉትን ጥረት ከግምት ውስጥ ሳያስገባ አባቱን ክሴን በእርቅ እንዲያልቅ አላደረክም በማለት ከፉኛ ደብድቦ የአባቱን ነፍስ በገዛ እጁ አጠፋ።

ዱለኛው ዳዊት ባሳ

በልጅነቱ ብቸኝነትን የሚያበዛ ዝምተኛ ልጅ ነበር። ከልጆች ጋር ተቀላቀሎ መጫወትን አይፈልግም ነበር። ብቻውን መሆን ስለሚወድ ብዙም ልጆች አይቀርቡትም ነበር። ሁልጊዜ ሲጫወት የአባቱን ስም እየጠራ ይውል እንደ ነበረ ጎረቤቶቹ ያስታውሳሉ።

ወደ ጉርምስና እድሜ ሲጠጋ ግን ዝም የሚለው ልጅ ተቀይሮ ቁጡ ሆነ። ሁሉንም ነገር በኃይል ማድረግ የሚችል የሚመስለው ልጅ ሆነ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በገባ በዓመቱ የጀመረው ይህ ባሕሪ ብዙ ጓደኞቹን ደበድቦ ትምህርት ቤት ደጅ እንዳይረግጥ አስወስኖበታል።

በዚህም የተነሳ ሰውነቱን በስፖርት ያዳበረ ሞተር ሳይክል የሚያሽከረክር ዱለኛ ጎረምሳ ወጣው። ዳዊት መጣ ከተባለ ምድር ተሰንጥቃ ብትውጣቸው የሚመርጡ በርካቶች ናቸው። ከእለታት አንድ ቀን በተራ ፀብ የተነሳ አንድ ወጣትን ክፉኛ ደብድቦ ጣለው። ተደብዳቢው ወጣትም ለወራት ሆስፒታል ቢተኛም ክፉኛ ስለተደበደበ ለማገገም ጊዜ ወሰደበት።

በድብደባው የተነሳ ክስ እንደተመሠረተበት ያወቀው ዳዊት አባቱ ጉዳዩ በእርቅ እንዲያልቅ እንዲያደርጉለትና እስከዛ እንደሚደበቅ ለአባቱ ይናገራል፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለም ሽምግልና ይልካል። ተደብዳቢው ክፉኛ በመጎዳቱ የተነሳ ቤተሰቦቹ የእርቅ ጥያቄውን ባለመቀበላቸው ፖሊስ ተይዞ እንዲቀርብ ይወስናል። ይሄን የሰማው ዳዊት ድጋሚ ወደ አባቱ ሄዶ በእርቅ የማያልቅ ከሆነ እገልሃለሁ ብሎ በመዛት ዳግም ወደ ተጎጂው ቤተሰብ ይልካቸዋል።

አባትም የግዳቸውን ሄደው ለእርቅ ቢማፀኑም ተቀባይነት አጥተው ይመለሳሉ። በዚህም የተነሳ ልጁ እንደዛተው ወላጅ አባቱን በእርግጫና በዱላ ደብድቦ ይገላቸዋል። ጉዳዩን የሰማው ፖሊሰም ጊዜ ሲያጠፋ በቦታው በመገኘት ዱለኛውን ዳዊት በቁጥጥር ስር ያውለዋል።

የፖሊስ ምርመራ

የፖሊስ የምርመራ መዝገብ በማጠናቀር ማስረጃውን በተገቢው መልኩ ሰንዶ ለዐቃቤ ሕግ ክስ እንዲመሠርት ይልካል። በዳውሮ ዞን የገሳ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ጽሕፈት ቤት የወንጀልና ትራፊክ አደጋ ምርመራ የፎረንሲክ ምርመራ የሥራ ሂደት አስተባባሪ እንደገለፁት ተከሳሽ ዳዊት ባሳ ጥቅምት 19 ቀን 2016 ዓ.ም ከምሽት አንድ ሰዓት ተኩል በሚሆንበት ጊዜ በገሳ ከተማ አስተዳደር በቦሳ ሾጋ ቀበሌ ልዩ ስሙ ከምባ ተብሎ በሚጠራበት የ48 አመት ወላጅ አባቱ ላይ በፈፀመው የድብደባ ወንጀል በቁጥጥር ስር ውሏል።

ፖሊስ በምርመራ እንዳረጋገጠው ተከሳሹ ከዚህ ቀደም በከተማ ውስጥ ሰው ደብድቦ ጉዳት ማድረሱን ተከትሎ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ ተጣርቶበት ክስ እንዲመሠረትበት ለከተማው መጀመሪያ ፍርድ ቤት መዝገቡን ልኳል፡፡ ‹‹ክሴን በእርቅ እንዲያልቅ አላደረክም›› በሚል መንስኤ ወላጅ አባቱን በእርግጫና በዱላ ደብድቦ ከባድ ጉዳት በማድረሱ ተጎጂው ወደ ሕክምና ቢወሰድም በደረሰበት ድብደባ ከፍተኛ በመሆኑ ሕይወቱ ማለፉን አረጋግጧል።

የዐቃቤ ሕግ ክስ

እንደ ፖሊስ ምርመራ ተከሳሹ በወላጅ አባቱ ላይ ከከሳሾቹ ጋር በእርቅ እንዲጨርስ ይህን ባታደርግ እገልሃለሁ ብሎ ሲዝት መቆየቱን በምርመራዬ አረጋግጫለሁ ያለው የገሳ ወረዳ ፖሊስ ግለሰቡ በፈፀመው ግድያ ወንጀል ምርመራ አጣርቶበት በሰውና በሕክምና ማስረጃ መዝገቡን አደራጅቶ ለዐቃቤ ሕግ ተቀብሎ ክስ መሰርቷል።

የዞኑ ዐቃቤ ሕግ ከፖሊስ የደረሰውን የምርመራ መዝገብ መሠረት በማድረግ ተከሳሹ ከሌላ ሰው ጋር ያለውን ክስ በእርቅ አላስጨረስክልኝም በማለት ወላጅ አባቱን በእርግጫና በዱላ የተለያዩ የሰውነት ክፍላቸውን በመደብደብ በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይወታቸው እንዲያልፍ በማድረጉ በፈፀመው ከባድ ሰው ግድያ ወንጀል ክስ መሥርቶበት ፍርድ ቤት አቅርቦታል፡፡

ውሳኔ

የዞኑ ፍርድ ቤትም ግራ ቀኙን ሲያከራክር ቆይቶ ተከሳሹን ጥፋተኛ ነው ሲል የጥፋተኝነት ብይን ሰጥቷል፡፡ የዳውሮ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የካቲት 14 ቀን 2016 ዓ.ም ባስቻለው የወንጀል ችሎት ተከሳሽ ዳዊት ባሳ በ22 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወስኗል ፡፡

አስመረት ብሥራት

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 21 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You