ጎብኚዎች ለሚከፍሉት ዋጋ ተመጣጣኝ አገልግሎት እንዲያገኙ የሆቴሎች ደረጃ ምደባ ያስፈልጋል

– የ31 ሆቴሎች የኮከብ ደረጃ ምደባ ይፋ ተደርጓል

አዲስ አበባ፡- ጎብኚዎች ለሚከፍሉት ዋጋ ተመጣጣኝ አገልግሎት እንዲያገኙ ጠንካራ የሆቴሎችና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የደረጃ ምደባ እንደሚያስፈልግ የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡የሆቴሎች ደረጃ የምደባ ውጤት በያዝነው ሳምንት ይፋ የማድረጊያ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል፡፡

በሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ እንደገለጹት፣ ጎብኚዎች ጥራቱ የተጠበቀና ለሚከፍሉት ዋጋ ተመጣጣኝ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል ጠንካራ ሥርዓት ዘርግቶ ሆቴሎችንና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን በደረጃ መመደብ ያስፈልጋል፡፡ አሁን ያለው ሆቴሎች ምደባ ሥርዓት በ2007 ዓ.ም ከዓለም የቱሪዝም ድርጅት ጋር በመተባበር የተዘረጋ ሲሆን 365 ሆቴሎች የደረጃ ምደባ ምዘና ተደርጎላቸዋል፡፡

እንደ ናሲሴ ገለጻ፤ የሀገር ውስጥ ባለሙያዎችን አቅም በማሳደግ በ2011 ዓ.ም 91 ሆቴሎች የደረጃ ምዘና መደባ ተደርጎላቸዋል፡፡ በአጠቃላይ ምዘና የተደረገላቸው ሆቴሎች 456 ቢደርስም 340 ሆቴሎች ብቻ ከአንድ እስከ አምስት ኮከብ ባለው ደረጃ ውስጥ መግባት ችለዋል፡፡
አሁን በተደረገው ምደባ መሠረት ኮከብ ደረጃ ያላቸው ሆቴሎች ቁጥር ወደ 369 አድጓል ያሉት ሚኒስትሯ፤ በቀጣይ የደረጃ ምደባ ሥራ ከዚህ ቀደም እንዳለው በሆቴሎች ብቻ የሚቀር አይደለም ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ደረጃ ምደባው በቱሪዝም እሴት ሰንሰለት ውስጥ አገልግሎት የሚሰጡ ሌሎች እንደ ሎጂ፣ ሬስቶራንት፣ አስጎብኝ ድርጅቶችና መሰል አገልግሎት ሰጪዎች ላይ ተግባራዊ እንደሚሆንም ገልጸዋል፡፡

እንደ ሚኒስትሯ ማብራሪያ፤ የአገልግሎቶችን ጥራት በማሻሻል ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታቸውን ለማረጋገጥና የጎብኚዎችን እርካታ ለማሳደግ የሆቴሎች ደረጃ ምደባ ሥርዓት ጉልህ ሚና አለው፡፡ የሆቴሎች ደረጃ ምደባ በሆቴሎች መካከል ጤናማ ውድድር እንዲሰፍንና የሚሰጧቸውን አገልግሎቶች የጥራት ደረጃ እንዲሻሻል የሚያስችል ቁልፍ መሳሪያ ነው፡፡

በተጨማሪም የምደባ ሥርዓቱ የመንግሥት ግዥ ፍትሐዊነትና ግልጽነት የሰፈነበት እንዲሆን እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የቱሪዝም ልማቱ በርካታ ማነቆዎች ያሉበት ነው ያሉት አምባሳደር ናሲሴ፤ ከዚህ ውስጥ የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የጥራትና የተወዳዳሪነት ደረጃ ዝቅተኛ መሆን አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከቱሪዝም ልማት ዘርፍ የምታገኘውን የኢኮኖሚ ጥቅም ለማሳደግና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን መንግሥት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፤ በ2014 እና በ2015 ዓ.ም በሀገሪቱ የተገነቡ አዳዲስ ሆቴሎችንና ከዚህ በፊት በተመደቡት ላይ ዳግም የደረጃ ምደባ ሥራ ከተሰራላቸው 64 ሆቴሎች ውስጥ 31 ሆቴሎች ከአራት እስከ አንድ የባለ ኮከብ ደረጃ አግኝተዋል፡፡

ከ31 ሆቴሎች ውስጥ ባለ አምስት ኮከብ ደረጃን ያገኙ ሆቴሎች የሉም፡፡ ሰባት ሆቴሎች ባለ አራት፣ ዘጠኝ ሆቴሎች ባለ ሦስት፣ አምስት ሆቴሎች ባለ ሁለት፣ ስምንት ሆቴሎች ባለ አንድ ኮከብ ደረጃ ውስጥ ተካተዋል፡፡

ሁለት ሆቴሎች ከደረጃ በታች ሲሆኑ በቀጣይ በሚያደርጉት ማሻሻያ ወደ ደረጃ እንዲገቡ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ሚኒስትሯ ገልጸዋል፡፡

ሞገስ ጸጋዬ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 21 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You