በኅብረታችን የተገለጠ የማያረጅ የዓባይ ውበት

ዓባይ እና ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ እና ዓባይ በአንድ ስር ላይ የበቀሉ አበባና ፍሬ፤ የገዳም ፀሎት መባ፤ የአጥቢያ እግዚኦታ ብቃይ፤ እንዲያም ሲል ተጠላልፈውና ተደጋግፈው የቆሙ፣ ቅይጥ ውሕድ የብዙነት መልክ ናቸው። ተፈጥሮ ሾራ ዓባይን እንደመቀነት በኢትዮጵያ ወገብ ላይ አሸረጠችው። እናም ዓባይ የኢትዮጵያ መቀነቷ፤ ዙሪያን የታጠቀችው የደንብ ልብሷም ነው። ከዚህ አኳያም ዓባይ እና ኢትዮጵያ፣ ሰማይና ኮከብ፣ ጣት እና ቀለበት ናቸው፤ አንዳቸው ያለአንዳቸው የማይደምቁ፣ የማይከሰቱም ናቸው።

ተፈጥሮ ዓባይን በኢትዮጵያ ወገብ ላይ ሸምኖታል። ሸምኖት አላበቃም፤ አድርቶና አዳውሮ በድንቅ ሽመና በማያረጅ ውበት በማያልቅ ቁንጅና ሞገስን አልብሶታል። ይሄ የተፈጥሮ ሀጫ ኩታ ግን ኢትዮጵያውያንን ከብርድ ሳይታደግ፣ ከረሀብና ከርዛት፣ ከማጣትም ሳያወጣ ለባዕድ ሀገራት ሲያሸረግድ ዘመናት ነጉደዋል። ከሌለን ላይ እየወሰደ ለሌላቸው ሲሰጥ፣ በፊታችን በማንአለብኝነት ሲንጎማለል እልፍ ዘመናት ሄደዋል። እኛም በእንጉርጉሮ እያዜምን ወደ ግብፅ በርሀ ሸኝተነዋል።

ያ ትላንትና ምራቅ የሚተፋበት፣ ለብዙ ጸሐፍት የእርግማንና የቁጭት ስንኝ ስንቅ የነበረው ዓባይ፤ ዛሬ ግን ታሪኩን አድሶ ከዓባይነት ወደ ቁምነገርኛነት ተመልሶ ማመስገኛችን ከሆነ እነሆ አስራ ሦስት ዓመታት ተቆጠሩ። ሆኖም እነኚህ አስራ ሦስት ዓመታት የዋዛ አልነበሩም። እንደ መንግሥትም ይሁን እንደ ዜጋ ዓባይን ፀንሰን የወለድንበት፣ ከወለድንም በኋላ በብዙ ተግዳሮት ውስጥ ለቁም ነገር ያበቃንበት ነው። ዛሬ ዓባይ በታሪካችን ላይ ከደመቁት የደመቀ የዚህኛው ትውልድ የወንድማማችነት ዓርማ ሆኖ ቆሟል።

ብቻችንን ሆነን ከብዙዎች ጋር ታግለን ያሸነፍንበት፣ ብቻችን ተራምደን፣ ብቻችን አስበን ከዳር የደረስንበት የድላችን ፍሬ ነው። ዓባይ በልዩነት ውስጥ ኢትዮጵያዊነትን እንድናስብና እንድናስቀድም ያደረገን፣ አዋሕዶና አግባብቶ ስለአንድ ዓላማ በአንድ እንድንጸና ያደረገን ጣፋጭ ፍሬያችን ነው። ይሄ የድል ፍሬ ከሕዝብ የተወለደ የኢትዮጵያዊነት የመስዋዕትነት ዋጋ ነው። ዋጋው ዓባይን ገድቦ ብቻ አይቆምም። ሌሎች የድል ፍሬዎችን የምንበላበት፣ በአንድነትና በኅብረት ተጉዘን ኢትዮጵያዊነትን የምናስቀጥልበትም ጭምር ነው።

በዓባይ ጉዳይ ላይ ግብፅ የያዘችው አቋምና የመሠረተችው ትርክት ከዚህ በተቃራኒው ነው። ከእኛው ምድር የፈለቀውንና የተወለደውን ዓባይ፣ ከእኔው የወጣ የእኔው የብቻዬ ሃብት ነው፤ የምጠቀመውም በዚሁ አግባብ ነው የሚል ድርቅናዋን ለተመለከተ ደግሞ፤ የድፍረቷንም፣ የቅጥፈቷንም ጥግ ለመገንዘብ ያስችለዋል። ሆኖም ዓባይ በአቅም ማነስ ዋጋ የከፍልንበት፣ የተፈጥሮ ሀብታችንን ለሌሎች አሳልፈን የሰጠንበት ጥቁር ታሪካችን ነው።

አባቶቻችን ዓባይን ለመገደብ ያደረጉት ጥረት ምን ያክል እንደነበርና የግንባታ ዲዛይነር አስመጥተው እስከማሳየት የደረሱበትን በኋላም በአቅም ማነስና በተሰሚነት በማጣት እንዳልተሳካላቸው የምናውቀው ሐቅ አለን። ዛሬ ግን ይሄንን ጥቁር ታሪክ ለማንጻት፣ ቁጭቱንም ለመሻር ነው ዓባይን የገነባነው። ይሄም ተሳክቶልናል። ይሄ ግን ዛሬም ለግብፅ አልተዋጠላትም። እኛ ግን ታሪካችንን አድሰን፤ ሃብታችንን ልንጠቀምበት ጫፉን ይዘናል። ታዲያ ማን ሊገታን ይችላል?!

የማይታበየው ግን ፍትሕና እውነት አብረውን ሆነው እንጂ፣ ዛሬም ግብፅ ሂደቱን ለማስተጓጎል አልተኛችም። ሆኖም ግን ግብፅ እስከዛሬ በዓባይ ላይ ለነበራት የበላይነት፣ ለነበራት ሥልጣኔ እና መስፋፋት ኢትዮጵያውያንን ከማመስገን ባለፈ ብዙ ውለታ የምትቸርበት ነበር። ተመልሳ ልማትና እድገታችንን ለማወክ መነሳቷ ከእኩይ ጎርብትናዋ ሌላ ምን ያክል ራስወዳድ እንደሆነች የሚናገር ነው። ኢትዮጵያ ያልተስማማችባቸውንና ያልተሳተፈችባቸውን ስምምነቶችን አንጠልጥላም በሦስትዮሽ ድርድሩ ላይ እንደመከራከሪያ በማንሳት እንቅፋት እየሆነች ያለችውም በዚሁ ምስሏ ነው።

በዓባይ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያና የግብፅ ዓላማ ለየቅል ነው። ኢትዮጵያ በጋራ ተጠቃሚነት መርሕ ሠርቶ በጋራ ማደግን ይዛ የምትሠራ ናት፤ ግብፅ ግን እኔ ብቻ ተጠቅሜ ልበልጽግ የሚል የራስወዳድነት አስተሳሰብ የሙጥኝ ብላ የቆመች ናት። ከዚህ አስተሳሰቧ የተወለደ ሌላም መሳይ አቋም አላት። ይሄም ከእኔ ውጪ በዓባይ ወንዝ ላይ የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ የእኔን ፍቃድ የሚጠይቅ መሆን አለበት የሚል ነው። በዚህ ሥልጡን ዘመን ላይ የጋራ የሆነን ተፈጥሮ ከጋራም ከአንዲት ሀገር መንጭቶ የሚፈስን፣ ከፍተኛውን ድርሻ የምትይዝን ሀገር የባለቤትነት መብትን በመግፋት ለእኔ ብቻ ማለት እጅግ አስነዋሪ ድርጊት ነው።

ይሄን አይነት አካሄድ ደግሞ ጊዜው የማይፈቅደው፤ ለማንም የማይበጅም ነው። ለግብፅም ሆነ ለሱዳን የሚበጀው በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ የአብሮ መልማት መርሕ ነው። የጋራ ተጠቃሚነት መርሆች የጋራ አቋሞች የሚንጸባረቁባቸው፣ አብሮ መበልጸግን ማዕከል ያደረገ ነው። ይሄ ማንንም የሚጎዳ አይደለም። አንዳንድ አጀበ ብዙ ሀገራት ግን ሌሎች ያልተስማሙበትን የራሳቸውን መርሕ ይፈጥሩና ብዙኃኑን ያገለለ ራስ ተኮር አቅጣጫን ይተልማሉ። ይሄ አይነቱ አካሄድ ንትርክና አተካራን መፍጠር ካልሆነ ማንንም ተጠቃሚ አያደርግም።

የውሃውን 86 ከመቶ ድርሻ ባላትና የእትብቱ ማደሪያ በሆነች ሀገርን ከሃብቷ እንዳትጠቀም ለማድረግ ይሄን አይነት ደባ የተሞላበት አካሄድ የሚያዋጣ አይደለም። ለሁሉም የሚጠቅመው በመነጋገርና በጋራ ጥቅም መርሕ በጋራ መበልጸግ ነው። ከዚህ ውጪ ያለው መርሕ አልባነት ብቻም ሳይሆን፣ ከጊዜው ጋር ተስማምቶ ያለመሄድን የሚያሳይ ነው። የኢትዮጵያውያን ማንነት ደግሞ በአንድ ማዕድ ተጋርቶ መብላት ነው። ይበቃናል ተጋርተን እንብላ ስንላቸው ከብቻነት ሌላ ተጋርቶ መብላትን የማያውቁ ስግብግቦች አብሮነትን ጠልተው በብቻነት በዓባይ ላይ የበላይ ሆነው ቆይተዋል። አብሮ መብላት ለማያውቅ መልስ ያለው ትውልድ ከራሱ በራሱ ለራሱ ችሎ ዓባይን በመገደብ ተጋርቶ መብላትን ለማስተማር ተገድዷል።

ምክንያቱም ዓባይ ለም አፈራችንን፣ ለም የተፈጥሮ ሃብታችንን እየወሰደ ለግብፅ እንጀራ ሆኖ ኖሯል። እትብቱን ሰከላ ላይ ጥሎ ያለማንም ከልካይ በግጥምና በቀረርቶ በቁጭትም ዜማ ታጅቦ ጸጋና በረከቷን እያጠበ ለተፋሰስ ሀገራቱ ሲለግስ ዘመናት ሄደዋል። አሁን ያ ጊዜ አልፎ በሕዝቦች የተባበረ ክንድ ተፈጥሮ ሀብታችንን የምንጠቀምበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። ዓባይን በተመለከተ ወደኋላ የሚቀለበስ ታሪክ የለንም። ከመጣንበት ፍጥነት በበለጠ ፈጥነን ከሕዝባችን ጋር ወደፊት የምንሄድበት ጊዜ ላይ ነን። ድህነት የታከተው፣ ተረጂነት የመረረው ሕዝብና ትውልድ ተፈጥሯል። ይሄ ትውልድ በጦርነት ሳይሆን በመነጋገር ርስቱን፣ ክብሩን፣ ሉዓላዊነቱን ሊያስጠብቅ፤ የአባቶቹን አደራ ሊወጣ ታጥቆ የተነሳ ነው።

ለዚህ ምስክር የሚሆነን በዓባይ ላይ ያሳየው ቁርጠኝነት ነው። ዓባይ ከምንምነት ተነስቶ እንዴት እዚህ ደረጃ ላይ እንደደረሰ ብንጠየቅ የምንመልሰው መልስ አለን። ወዳጆቻችን ለብድርና ለእርዳታ ፊታቸውን ባዞሩብን ሰሞን፤ አይችሉምና አይሆንላቸውም የስላቅ ዜማቸው በሆነበት ጊዜ፤ የቻልነው ‹የይቻላል ታሪካችን› ነው። በጠላቶቻችን ፊት ለንክሻቸው ሳንፈራ፣ አብረውና ተባብረው ተቧድነውም ሊያስቆሙን በሞከሩበት ፈታኝ ጊዜ ላይ ወደኋላ ሳናፈገፍግ ጀምረን የጨረስነው የክፉ ጊዜ ማስታወሻችን ነው።

ይሄ ቁርጠኝነት ኢትዮጵያን ባለተስፋ ያደረገ፣ መጪውን ጊዜ በመልካም ያሳየ ነው። በተጨማሪም ሀገራችንንና ሕዝባችንን ከተረጂነት በማውጣት ራሷን የቻለች ባለታሪክ ሀገርም በመፍጠር ረገድ የማይናቅ ሚና እንዳለው ይታመናል። ይሄ ሕዝባዊ አቋም አሁን ላይ እንደሀገር የተገነባንበት ሥነልቦናችን ነው። በጀመርነው ለመቀጠል ቀጥለንም ለመሰለስ በማይቆምና በማይታክት አዕምሮና ልብ የተቃኘንበትም ነው። ሕዝብ የተነሳበት የትንሳኤ ጉዞ ደግሞ መቆሚያ የለውም። ዓባይ የተገነባው በኢትዮጵያውያን አንድነት ነው። ቀጣይ ስኬቶቻችንም አንድነታችንን የለበሰ፣ ኅብረብሔራዊነታችንን ያስቀደመ መሆኑ ነው።

መሠረታዊ የሕዝብ ፍላጎት ባልተሟላባት ሀገር፣ በየእለቱ በሚጨምር የሕዝብ ቁጥር ተፈጥሮ የራስ የሆነን ተፈጥሮ አትጠቀሙ ብሎ መከልከል ዓይን ያወጣ ራስ ወዳድነት ከመሆኑም በላይ ሰብዓዊ ጭካኔም ነው። ተደጋግሞ በባለሙያ እንደሚነሳው በዓባይ ጉዳይ ላይ ጽንፍ ይዘው የቆሙ ሀገራት ምክንያታቸው ፍራቻ ነው። ኢትዮጵያ የምትባለው ምሥራቅ አፍሪካዊት ሀገር መላውን አፍሪካና መላውን ጥቁር ሕዝብ በባርነት በወደቀበት ሰሞን ብቻዋን በርትታ ለዓለም ነፃነትን የፈጠረች፣ ፍትሕና ሚዛናዊነትን እውን ያደረገች እንደሆነች ደምቆ የሚነሳ ታሪክ አላት። የቀጣዩም ስጋት ይሄው ነው፤ የእኩልነትን ችቦ ያቀጣጠለችው ሀገር፤ የኢኮኖሚ ነፃነት ፋና ወጊ ሆና ሌሎችን ትቀሰቅሳለች የሚል።

የግብፅ ሥልጣኔና ሉዓላዊነት ከናይል/ዓባይ ወንዝ እንደሚጀምር በርካታ መረጃዎች ይጠቁማሉ። የዓባይን ታሪክ ከታሪኳ ጋር አስማምታ ለመኖር ስትል መነሻውን ከመቀየር ጀምሮ በትምህርት ቤት ተማሪዎችን እስከማስተማር የደረሰ ሥርዓተ ትምህርት ቀርጻ እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች። ሌላው አስገራሚው ነገር ደግሞ በግብፅ የሁለተኛና የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች አብዛኞቹ የመመረቂያ ጽሑፋቸውን በዓባይ ዙሪያ እንደሚሠሩ መነገሩ ነው። ከዚህ ጋር አብሮ የሚነሳው ግብፅ ውስጥ ለዓባይ የተዘፈነውን ያክል ለየትኛውም ጀግና አለመዘፈኑ ነው። ስለናይል ወንዝ ብቻ ከ2000 የሚልቁ አወዳሽና አሞጋሽ ዘፈኖች ተሠርተዋል። ይሄ ሁሉ የሆነበት ምክንያት ግብፅ የዓባይን ታሪክ የእኔ ብቻ ወደሚል ራስተኮር ተረክ ለመመለስ ከመሻት የመነጨ ነው።

ሀገራችን ኢትዮጵያ ብዙዎች በምዕራባውያን ጣልቃ ገብነትና ቅኝ ግዛት ስር ወድቀው ታሪካቸውን፣ ባሕላቸውን፣ ማንነታቸውን፣ ርስትና እሴታቸውን በተነጠቁበት ወቅት ቅኝ ሊገዛት የመጣውን ወራሪ ያባረረች ሀገር ናት። ይቺ ሀገር አሁንም ትከበራለች፤ ይፈሯታልም። መንገድ ዘጋግተውብን በድህነትና በተረጂነት እንድንኖር ከመፍረድ ውጪ ከድህነት መውጫ የማርያም መንገድ ሲሰጡን የማይታዩትም በዚሁ ምክንያት ነው። ሆኖም አጋጣሚዎችን ተጠቅመን ከፍ ለማለት ስንሞክር በጫናና በአይችሉም ሊሰልቡን ብዙ ቢጥሩም፤ ዛሬ ላይ የዓባይ የድል ታሪክ መቼም እንዳይጠፋ ሆኖ በዚህ ሁሉ ጫና ውስጥ የበራ ብርሃን ሆኗል።

ኢትዮጵያውያን ዕድልና አጋጣሚ ካገኙ ጥንተ ታሪካቸውን በማደስ በአፍሪካ ገንነው፣ በዓለም ላይ ተፅዕኖ መፍጠር ይችላሉ ተብሎ የሚታሰብ ፍርሀት አለ። በዚያ ፍርሀት ነው አሁን ላይ ምንም ነገር ለማድረግ ስንነሳ አይሆንም በሚል በጫና የሚያደነቃቅፉን። የግብፅ ፍርሀትም ይሄው ሆኖ እንጂ የዓባይ ግድብ የሚጎዳት ሆኖ እንዳይደለ ጠንቅቃ ታውቃለች።

የዓባይ ዘመን የኢትዮጵያ ምርጡ ዘመን እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል። ምንም እንኳን ከሌለን ላይ ቀንሰን በችግርና በማጣት የጨረስነው ቢሆንም፤ የዚህ ታሪክ አንድ አካል መሆን ሌላ በጎ ገጽ እንዳለው የሚናገሩም ጥቂቶች አይደሉም። ከቁጭት ወደውዳሴ የተመለስንበት የስኬት ጊዜአችን ነው።

ረጅሙ ወንዝ ዓባይ እንደርዝመቱ ጎረቤታሞቹን ሀገር አላፋቀረም። ተፈጥሮ በፀጋው ቢሞሽረውም ለእኔ ለእኔ በሚሉ እንደግብፅ ያሉ ራስ ወዳዶች በጋራ መልማትን አሻፈረኝ ብለው የመቶ ዓመታትን ኢ-ፍትሐዊ ስምምነት እያስታወሱ እናቱ በሆነችው ኢትዮጵያ ላይ ቢዘምቱም፤ ኢትዮጵያውያን ግን ዓባይን ጀምረው እየቋጩ ነው። ጠላቶቻችን በወሬ እኛ በሥራ ተጠምደን እነሆ ከፍጻሜው ደርሰናል።

በብዙ መልኩ ተሳክቶለት የህዳሴ ግድባችን የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ነው። በመጪዎቹ ሰባት ወራት ሙሉ በሙሉ የሚጠናቀቅበት መልካም የምሥራች ደግሞ ሌላ ተስፋ ሆኖን የአዲስ ዓመትን የተስፋ ቀናችንን በመጠበቅ ላይ እንገኛለን። ኢትዮጵያዊነት ምን ማለት እንደሆነ ለዓለም ያሳየንበት የውሕደት ታሪካችን ሆኖ እየመጣ ነው። በማያረጅ ውበት በማያልቅ ቁንጅና ታጅቦ ሊሞሸር እየተጠበቀ ነው።

በአንድነት እንችላለን፣ በኢትዮጵያዊነት እንሻገራለን። ምክንያቱም በኅብረት ብርቱዎች ነን፣ በወንድማማችነት ኃይለኞች ነን። ጥንተወንዝ ዓባይ ከምንም ተነስቶ ለክብር ሲበቃ፣ ኅብረታችንን ታክኮ ነው። ኅብረት ብረት ነው..ማንም የማይሰብረው..በማንም የማይጎብጥ። ወደፊት ለመሄድ ያለን አንድ አማራጭ ኅብረት ብቻ ነው። ልክ እንደህዳሴ ግድባችን ደማማቅ ታሪኮቻችን በማያያዝ የደመቁ ናቸው። እናም እንያያዝ።

ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 21 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You