የቀይ ባሕር ጥቃት እና የኢትዮጵያ ቡና ንግድ ፈተና

በቀይ ባሕር በተቀሰቀሰው ጂኦፖለቲካዊ ቀውስ ሳቢያ እንደ ቡና ያሉ የውጭ ምርቶችን ወደ ውጭ ለመላክ አዳጋች በመሆኑ ላኪዎችና በብዙ ሚሊየኖች የሚቆጠሩ ቡና አምራቾች ላይ አደጋ ደቅኗል። የአዲስ ፎርቹን ጸሀፊ አክሳህ ኢታሎ በዚያ ሰሞኑን ባስነበበን መጣጥፍ ለኢኮኖሚው ከመርግ የከበደ መርዶ አርድቶናል። ወደብና ባሕር አልባ መሆናችን ሳያንስ፣ በቀይ ባሕር ኮሽ ባለ ቁጥር ሕልውናችንና ኢኮኖሚያችን ምን ያህል ለአደጋ እንደሚያጋልጥ ያመላከተ ነው።

በተለይ የሁቲ አማጽያን በቀይ ባሕር ላይ በሚፈጽሙት ተደጋጋሚ ጥቃት የተነሳ፣ የጭነት መርከቦች በዚህ መስመር መቅዘፍ ቀንሰዋል አልያም ከእነ አካቴው አቁመዋል። ምክንያቱም የሁቲዎችን ጥቃት በመሸሽ በደቡባዊ አፍሪካ ኬፕ ኦፍ ጉድ ሆፕ ዙሪያ ጥምጥም ለመጓዝ በመገደዳቸው የጭነትና የዋስትና ዋጋ እጅግ አሻቅቧል። በዚህ የተነሳ ቡና ተቀባይ ሀገራት ፊታቸውን ወደ ብራዚል በማዞራቸው ከሦስት ሚሊየን ኪሎ ግራም በላይ ቡና በጅቡቲ ወደብ ተከማችቶ ይገኛል።

የቀይ ባሕር ጉዳይ በቅርቡ መፍትሔ አግኝቶ መውጣት ካልቻለ የቡና ላኪዎችና በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ቡና አምራች ገበሬዎች ሕይወት ላይ የከፋ ችግር ያስከትላል። ከዚህ ባለፈም የውጭ ምንዛሬ ማግኛ የሆነው የቡና ኤክስፖርት ላይ የሚፈጠረው ጫና ጦርነትን ጨምሮ በሌሎች ውስጣዊ ችግሮችና የውጭ ምንዛሬ እጥረት እየተፈተነ ላለው ኢኮኖሚ ተደማሪ ፈተና መሆኑ አይቀርም።

ለምን ቢባል፣ ኢኮኖሚው በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተቀሰቀሰው ጦርነት ሀገራችን ከአግዋ ተጠቃሚነት በመውጣቷ፤ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በመቀዛቀዙ እና ቱሪዝም በብርቱ መዳከሙ ሳያንስ በአማራና ኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰው ጦርነት ደግሞ በእንቅርት ላይ ቆርቆር እንዲሉ ሆኗል። የኑሮ ውድነቱም በሰዓታት ጣራ እየነካ ዜጎችን በእጅጉ እያማረረ ባለበት ነው እንግዲህ የኤክስፖርት ንግዳችን ቅርቃር ውስጥ የገባው።

በዋጋ ግሽበቱና እሱን ተከትሎ በመጣው የኑሮ ውድነት የዜጎች የሸመታ አቅም መዳከሙና መቀዛቀዙ ኢኮኖሚውን ታማሚ አድርጎታል። በአራዶች ቋንቋ አየሩ ተመቷል፤ ገቢ ቀንሷል፤ ሀገራዊ ቁጠባው እጅ አጥሮታል። በዚህ ቀውጢ ሰዓት ነው ኤክስፖርታችን በቀይ ባሕር ችግር ምክንያት ያልተጠበቀ ፈተና ውስጥ የገባው።

ወሳኝ የሆነውና ከዓለም ንግድ እስከ 15 በመቶ ይተላለፍበት የነበረው ቀይ ባሕር፣ በሁቲ አማጽያን ተደጋጋሚ ጥቃትና እገታ የተነሳ በመስተጓጎሉ የኢትዮጵያን የውጭ ንግድ አደጋ ላይ ጥሎታል። ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን የጫኑ ተሽከርካሪዎች በወደቦች ለወራት መቆማቸው ሳያንስ ግዙፍ የጭነት መርከቦች በቀይ ባሕር መቅዘፍ ማቆማቸው በሀገራችን የውጭም ሆነ የገቢ ንግድ ላይ ከባድ ሳንካ ፈጥሯል።

ግዙፉን የጭነት መርከብ ኩባንያ ሜርስክን እንኳ በአብነት ብንወስድ፣ 600 የጭነት መርከቦቹ በቀይ ባሕር መቅዘፍ በማቆማቸው ከ30 ሺህ በላይ ኮንቴነሮች በወደቦች እንዲከማቹ አስገድዷል። ለዚህ ነው በሜርስክ የኢትዮጵያ ወኪል ዳኔል ዘሚካኤል፡-

“መርከቦቻችን ለአደጋ በመጋለጣቸው በቀይ ባሕር በኩል የምናደርገውን ጉዞ ለማቆም ተገደናል። የሀገራችን ላኪዎችና የሎጅስቲክስ ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን በሕንድ ውቅያኖስ አድርገው ወደ አውሮፓ ለመላክ የሞምባሳንና የላሙ ወደቦችን ለመጠቀም ተገደዋል። ይህ ደግሞ በቀይ ባሕር በጥቂት ሳምንታት ይጓጓዝ የነበረን ምርት ቢያንስ ወር ስለሚፈጅበት የማጓጓዣ ወጪውን ስለሚያንረው ከሌሎች ጋር ለመወዳደርም አዳጋች አድርጎታል። ወደ መካከለኛው ምስራቅ የሚላኩ ምርቶችንም በአረቢያን ወሽመጥ በኩል ማጓጓዝ ግድ ሆኗል፤ሲሉ የተደመጡት።

የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አዱኛ ደበላ፣ የተከሰተው ችግር የሀገራችንን የቡና ዘርፍ ክፉኛ ይጎዳዋል ብለው ሰግተዋል። የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ኡመር በበኩላቸው፣ የኬንያን ወደቦች በአማራጭነት ለመጠቀም የዳሰሳ ጥናት እየተካሄደ ቢሆንም፤ የወደቦቹ አቅም ውስን መሆኑና ተጨማሪ ወጭ የሚጠይቅ መሆኑ ሌላው ፈተና መሆኑን ነው ያስረዱት።

የኬንያ ወደቦች የጭነት አቅም በኮንቴነር 28 ቶን ወይም 280 ኩንታል መሆኑ ቡናን ለመጫን የሚያስፈልገው የጭነት መስፈርት የሚያሟሉ አለመሆናቸው ሌላው ፈተና ነው። ስለሆነም አዋጭነታቸው ገና አለመረጋገጡ ችግሩን አሳሳቢ አድርጎታል።

በመሆኑም የተከሰተው የሎጂስቲክስ ችግር የሀገራችንን ዋና የኤክስፖርት ምርት ቡናን ወደ አውሮፓና መካከለኛው ምስራቅ የመላክ ሂደቱን ፈትኖታል፡፡ በዚህ ምክንያት ተቀባይ ኩባንያዎች ፊታቸውን ወደ ብራዚል ካዞሩ ደግሞ ደንበኞቻችንን ልናጣ እንችላለን። ደንበኞች አንዴ ከእጅ ከወጡ ደግሞ መልሶ ማግኘት ፈተና ነው።

ቡናን ወደ ውጭ የሚልኩት አቶ ዘላለም እሸቱ ይሄን ሁነት አስመልክተው ለ”አዲስ ፎርቹን” እንደተናገሩት ደግሞ፤ ከዚህ በፊት በአማካኝ እስከ 26 ሚሊየን ዶላር የሚያወጣ ቡና ወደ መካከለኛው ምስራቅ ይልኩ ነበር፡፡ አሁን ግን የገዙትን ቡና ለመላክ ተቸግረዋል። 10ሺህ አባላት ያሉት የኢትዮጵያ ቡና ማኅበር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሰይድ ሁሴን፤ መንግስት በቡና ኤክስፖርት ላይ ላጋጠመው ችግር አፋጣኝ መፍትሔ የማይሰጥ ከሆነ ሌላ መላ ይገኝለታል ብለው ተስፋ እንደማያደርጉ ለዚሁ ጋዜጣ ገልጸዋል።

ዘጠኝ እቃ ጫኝ መርከቦች እንዳሉት የሚታወቀው የኢትዮጵያ የመርከብና የሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ በሪሶ አማሎ በበኩላቸው፣ አጋር የጭነት መርከብ ኩባንያዎች በቀይ ባሕር መቅዘፍ በማቆማቸው የድርጅታቸው አገልግሎት መስተጓጎሉን እና ችግሩን ለማቃለል ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

70 ሺህ ቡና አምራች ገበሬዎችን በአባልነት ያቀፈው የሲዳማ የሕብረት ስራ ዩኒየን ዋና ስራ አስኪያጅ ጸጋዬ አኔቦ፤ “ላለፉት ሁለት ወራት ወደ ውጭ ለመላክ ጅቡቲ ወደብ ያደረስነው 3800 ኩንታል ቡና በዚያ እንደተቀመጠ ነው። በአየር እንዳናጓጉዝ የጭነት ዋጋው ከመርከብ 25 እጥፍ ይበልጣል። ይወደዳል። የምናደርገው ግራ ገብቶን ተቀምጠናል፤” ሲሉ መናገራቸውም የችግሩን መፍትሄ ፈላጊነት አመላካች ነው።

የቀድሞው የቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳኒ ረዲ በዚህ ፈታኝ ወቅት ከትርፍ ይልቅ ደንበኞችን ላለማጣት ጥረት ሊደረግ ይገባል ሲሉ ያሳስባሉ። የቡና ኤክስፖርት ስትራቴጂንም እንደነባራዊ ሁኔታው መከለስና መቃኘት ያሻል። ደንበኛ አንዴ ከእጅ ካመለጠ መልሶ ማግኘት ያዳግታል ሲሉ አስጠንቅቀዋል። በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ቡና በዓለም ገበያ የሶስት በመቶ ድርሻ ብቻ ያለው ሲሆን፤ የቬትናምና የብራዚል ድርሻ ግን እጅግ ከፍ ያለነው። ድርሻችን ከፍ እንዲል ምርታማነትን ማሳደግ ላይ ጥረቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል።

በሌላ በኩል የቡና ባለሙያዎችና የዘርፉ አንቀሳቃሾች እንደገለጹት፣ በ1980ዎቹ መጨረሻ የቡና ምርትና ግብይት ሒደት ለቀቅ ቢደረግም፤ ከፖሊሲ አንጻር ግን ይህ ነው የሚባል መሠረታዊ ለውጥ ስላልታየበት በዓለም ገበያ ለሚከሰቱ አሉታዊ ተጽዕኖዎች በተደጋጋሚ ተጋላጭ መሆኑን ይናገራሉ። በዚህ ሁሉ ተግዳሮት ውስጥ ሆኖም የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ምርታማነትን ለማሳደግና ተጨማሪ መዳረሻ ገበያን ለማግኘት እየሰራ ሲሆን፤ በዓለም ገበያ ተፈላጊ የሆነውን ቡና በምታመርተው ይርጋ ጨፌም የምርምርና የልማት ኢንስቲትዩት ተከፍቷል።

በሀገራችን ቡና ወደ ስድስት ሚሊየን ለሚጠጉ ዜጎች የስራ ዕድል ሲፈጥር፤ ወደ ውጭ ከሚላኩ ምርቶች ደግም ሲሶውን ይይዛል። ባለፈው ዓመት አንድ ነጥብ ሥስት ቢሊየን ዶላር ገቢ አስገኝቷል። ቡና በብዛት የሚመረተው በተወሰኑ አካባቢዎች ብቻ መሆኑ ምርታማነቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ፈጥሯል። ኦሮሚያ 59፣ የደቡብ ምራብ 15፣ ሲዳማ ክልል ሰባት በመቶ ቀሪው ድርሻ የተለያዩ ክልሎች ነው።

አቶ ዳዊት ባደግ፣ የዘላለም እሸቱ ቡና ላኪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ የገበያ ውድድሩ እየከበደ ዓለማቀፍ ዋጋው ደግሞ እየቀነሰ መሆኑ ሳያንስ ፍላጎቱም እየተቀዛቀዘ መሆኑ በአምራቾችና በላኪዎች ዘንድ ስጋት እየፈጠረ መሆኑን አስረድተዋል። በዚህ ላይ የአውሮፓ የመድን ኩባንያዎች በቀይ ባሕር በተፈጠረው ቀውስ የተነሳ ይሰጡት የነበረውን ዋስትና በመቀነሳቸው ቡና ላኪዎችና ተቀባዮች ግራ ተጋብተዋል።

ይሄን እና መሰል ችግሮች እንዲፈጠር የቀይ ባሕርን የስጋት ቀጠና ያደረጉት ሁቲዎች እነማን ናቸው? ሊባል ይችላል፡፡ ሁቲዎች የየመን ታጣቂ ቡድን ሲሆኑ፣ መሰረታቸውም ዛይዲስ በመባል የሚታወቅ የሃገሪቱ የሺዓ ሙስሊም ነው። በአውሮፓውያኑ 1990ዎቹ ሲቋቋሙ የወቅቱ ፕሬዚዳንት የነበሩት አሊ አብደላህ ሳሌህ አገዛዝ የተንሰራፋውን ሙስና ለመዋጋት በሚል ነበር።

ስማቸውንም የወሰዱት ከንቅናቄው መስራች ከሆኑት ሁሴን አል ሁቲ ነው። በኋላም እስራኤል፣ አሜሪካ እና ሰፊውን ምዕራባዊ ክፍል የሚቃወም እና በኢራን የሚመራው ‘አክሲስ ኦፍ ሬዚስታንስ ጥምረት’ መሆናቸውንም አስታወቁ። ከሁቲ በተጨማሪ ሐማስ እና ሂዝቦላህ የዚህ ጥምረት አካል ናቸው።

ሁቲዎች በመጀመሪያ ላይ ከፍተኛ የፖለቲካ ጥንካሬ ማግኘት የቻሉት ፕሬዚዳንት አሊ አብደላህ ሳሌህን በተኩት በፕሬዚዳንት አብድራቡህ ማንሱር ሃዲ ላይ በተነሱበት ወቅት ነው። ይህም በአውሮፓውያኑ 2014 ነው። ከቀድሞው ጠላታቸው እና ከስልጣን ከተነሱት ፕሬዚዳንት ሳሌህ ጋር ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላም እሳቸውን ወደ ስልጣን ለመመለስ አስበው ነበር። በቀጣዩ ዓመትም በየመን ሰሜናዊ ክፍል የሚገኘውን የሳዓዳ ግዛትን ተቆጣጠሩ። ይህም ዋና ከተማዋን ሰንዓን መቆጣጠር ያስቻላቸው ሲሆን፣ ፕሬዚዳንት ሃዲንም ወደ ውጭ እንዲሰደዱ አስገደዷቸው።

ሆኖም የየመን ጎረቤት የሆነችው ሳዑዲ አረቢያ ወታደራዊ ጣልቃ በመግባት ፕሬዚዳንት ሃዲን ወደ ስልጣን በመመለስ፤ የሁቲዎችን ኃይልም ለማሸነፍ ሞከረች። ሳዑዲ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች እና ባሕሬንም ትደገፍ ነበር። ሆኖም ሁቲዎች የተሰነዘረባቸውን ጥቃት በመመከት ይዞታቸውን ማስፋት ቀጠሉ። በአውሮፓውያኑ 2017 የቀድሞው ፕሬዚዳንት አሊ አብዱላህ ሳሌህ ወደ ሳዑዲ ጎራ ለመቀላቀል ሲሞክሩም በሁቲ ታጣቂዎች ተገደሉ።

የሁቲ አማጺያን በሊባኖስ ውስጥ የሚገኘው የሺአው ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህ ጋር ጥብቅ ቁርኝት አላቸው። ሄዝቦላህም ለሁቲ አማጽያን ከአውሮፓውያኑ 2014 ጀምሮም ሰፊ ወታደራዊ ስልጣናዎችን እየሰጣቸው መሆኑን ሽብርተኝነትን የሚዋጋው ‘ዘ ኮምባቲንግ ቴሬሬዚም ሴንተር’ የተሰኘው የአሜሪካው የምርምር ተቋም አስታውቋል። ሁቲዎች ኢራንን በአጋርነት የሚያይዋት ሲሆን ሳዑዲ አረቢያም ደግሞ የጋራ ጠላታቸው ናት። ኢራን ለሁቲ አማጺያን የጦር መሳሪያ ታቀርባለችም በሚል በተደጋጋሚ ብትከሰስም፣ ታስተባብላለች።

ለምሳሌ፣ ሁቲዎች በአውሮፓውያኑ 2017 በሳዑዲ መዲና ሪያድ ላይ ያስወነጨፉትን ባለስቲክ ሚሳኤል ያቀረበችው ኢራን ናት በማለት አሜሪካ እና ሳዑዲያ አረቢያ ይከሳሉ። በተጫማሪም በአውሮፓውያኑ 2019 ሁቲዎች የሳዑዲ ነዳጅ ማምረቻዎችን ለማጥቃት የተጠቀሙባቸውን የክሩዝ ሚሳኤሎች እና ድሮኖችን (ሰው አልባ አውሮፕላኖችን) የሰጠችው ኢራን እንደሆነች ይወሳል።

ሁቲዎች በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የአጭር ርቀት ሚሳኤሎችን ወደ ሳዑዲ አረቢያ ያስወነጨፉ ሲሆን በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ኢላማዎችም ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል። እነዚህን መሳሪያዎች ለሁቲ አማጽያን ማቅረብ የተባበሩት መንግሥታት በኢራን ላይ የጣለውን የጦር መሳሪያ እገዳን የሚጥስ ቢሆንም፣ ኢራን በጭራሽ ክሱን አትቀበለውም።

ዓለም አቀፍ ዕውቅና የተሰጠው የየመን መንግሥት የፕሬዚዳንቱ አመራር ምክር ቤት ነው። ፕሬዚዳንት አብዱራቡህ ማንሱር ሃዲ በአውሮፓውያኑ 2022 ስልጣናቸውን ለምክር ቤቱ አስተላልፈውለታል። ምክር ቤቱ መቀመጫውም በሳዑዲ መዲና ሪያድ ነው። ሆኖም አብዛኛው የየመን ሕዝብ የሚኖረው በሁቲ አማጽያን ቁጥጥር ስር ባሉ አካባቢዎች ነው። በሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል ግብር የሚሰበስቡ ሲሆን የአገሪቱንም መገበያያ ገንዘብም ያትማሉ።

የመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ሁቲዎች በአውሮፓውያኑ 2010፣ ከ100 ሺህ- 200 ሺህ የታጠቁ ወታደሮች እና ያልታጠቁ ደጋፊዎች እንዳላቸው ገልጿል። የሁቲ አማጽያን ሰፊውን የቀይ ባሕር ጠረፍ ይቆጣጠራሉ። ከነዚህም አካባቢዎች ነው ጥቃቶቹን እየፈጸሙ የሚገኙት።

እንደ ቢቢሲ ዘገባ ከሆነ ደግሞ፣ እነዚህ ጥቃቶች ከሳዑዲ አረቢያ ጋር እያደረጉት ላለው የሰላም ድርድር አግዟቸዋል።“ለሳዑዲዎች የቀይ ባሕር መተላለፊያ የሆነው ባብ አል ማንዳብ መዝጋት እንደሚችሉ በማሳየት ወደ በስምምነቱ ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳረፍ ችለዋል፡፡ ሆኖም የቀጣናው ውጥረት ለኢትዮጵያም ከፍ ያለ አደጋን የያዘ መሆኑን ለአፍታም መዘንጋት አይገባም፡፡

ሻሎም ! አሜን።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን መጋቢት 20/2016 ዓ.ም

Recommended For You