ሁሉም እምነቶች በእኩልነትና በወንድማማችነት የሚኖሩባት ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም ወዳድ ሕዝብ ነው፡፡ ለዘመናት አብሮ ተከባብሮ በመኖርና የሠላም ተምሳሌት በመሆን በአርዓያነት ሲጠቀስ የኖረ ነው፡፡ ከኢትዮጵያውያን ዘመን ተሻጋሪ አኩሪ መገለጫዎች መካከል የብሔር፣ የእምነት፣ የቋንቋ፣ የባሕልና ሌሎች ልዩነቶችን ዕውቅና በመስጠት ተሳስቦና ተከባብሮ መኖር ትልቁ እሴት ነው፡፡

ከኢትዮጵያውያን ነባር ዕሴቶች መካከል አንዱና ዋነኛው በሃይማኖቶች መካከል ያለው የአብሮነትና የወንድማማችነት መስተጋብር ነው፡፡ ኢትዮጵያ የአይሁድ፤ የክርስትናና የእስልምና ሃይማኖቶችን ተቀብላ ያስተናገደችና የተለያዩ እምነቶችም በእኩልነት እና በወንድማማችነት እንዲኖሩ ዕድል የሰጠች ድንቅ ሀገር ነች፡፡

ኢትዮጵያ ሕዝቦቿ የአይሁድ እምነትን፤ ክርስትናን፣ ዋቄፈታንና እስልምናን የተቀበሉባት ሀገር በመሆኗ ከየትኛውም ሀገር በተለየ መልኩ የእምነት ብዝኃነት የሚንጸባረቅባት ሀገር ነች፡፡ ከዚሁ ሁሉ በላይ ግን በተለያዩ እምነቶች መካከል ያለው መቻቻልና መከባበር ለሌሎች ሀገራት በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው፡፡

በኢትዮጵያ አንዱ እምነት ሌላውን ማክበርና በተለያዩ ማኅበራዊ መስተጋብሮች ውስጥም አብሮ መሳተፍ የኖረ እሴት ነው፡፡ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ክርስቲያኑ የሙስሊሙን መስጊድ ማሠራት፤ ሙስሊሙም የክርስቲያኑን ቤተ ክርስቲያን ማሠራት የተለመደ ባሕል ነው፡፡ አንዱ የአንዱን ቤተ እምነት መጠበቅና ማክበርም የኢትዮጵያውያን አማኞች መገለጫ ነው፡፡

በኢትዮጵያ የተለያዩ እምነት ተከታዮች ሃይማኖታዊ በዓላትን በጋራ ማክበራቸውም የተለመደ ነው፡፡ የክርስትናም ሆነ የእስልምና በዓላት ሲከበሩ የተለያዩ የሃይማኖት ተከታዮች በጋራ በመሆን በዓላትን ሲያከብሩ ኖረዋል፡፡ በበዓላት ዕለት ጎረቤታሞች በመጠራራት ማዕድ በመቋደስ እና በዓላትን በድምቀት ማክበር የተለመደ ኢትዮጵያዊ ዕሴት ነው፡፡ በዚህ የደስታ ወቅትም ስለሀገራቸው ሠላምና አንድነት በጋራ መጸለይና ለሀገራቸውም መልካም ምኞት መመኘት አንዱ መገለጫቸው ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን የእምነት ልዩነት ሳይበግራቸው ደስታንም ሆነ ኃዘንን በጋራ ያሳልፋሉ፡፡ የሀገራቸውንም ዳር ድንበር ይጠብቃሉ፤ ወራሪን በጋራ ድል ይመታሉ፤ በልማት ይሳተፋሉ፤ ሀገራቸውን ጥሪ ስታደርግላቸው ያለምንም ማመንታት ከጎኗ ይቆማሉ፡፡ ይህ አንድነታቸውን አብሮነታቸውም ከበርካታ የዓለም ሕዝብ ዘንድ ትልቅ ክብርና ግርማ ሞገስ አጎናጽፏቸዋል፡፡ በአርዓያነትም እንዲወሰዱ አድርጓቸዋል፡፡

ይህ አብሮነትና አንድነት ዘንድሮ የተለየ ገጽታ ተላብሶ መጥቷል፡፡ የኦርቶዶክስ አማኞች ዓቢይ ጾምና የእስልምና እምነት ተከታዮች የረመዷን ጾም በአንድ ቀን ተይዟል፤ ይህም የአንድነታቸውና የአብሮነታቸው ተምሳሌት ተደርጎ ከመወሰዱም ባሻገር ኢትዮጵያውያን አማኞች በአንድነት ለሀገራቸው ሠላም፤ ልማትና አብሮነት እንዲጸልዩ ዕድል ሰጥቷል፡፡

ከእነዚህ እድሎች አንዱ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ደምቀው ያመሹበትና አብሮነታቸውንም ለዓለም ሕዝብ ያሳዩበት ‹‹ኢፍጣራችን ለአንድታችን›› የተሰኘውና ለአራተኛ ጊዜ የተካሄደው መርሐ ግብር ነው፡፡ በዚህ መርሐ ግብር ላይ በርካታ ኢትዮጵያውያን ከመሳተፋቸውም በላይ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፤ ታዋቂ ሰዎችና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ተሳትፈውበታል፡፡

ታላቁ የጎዳና ላይ ኢፍጧር አንድነት የተንፀባረቀበት፣ ያለው ለሌለው ያካፈለበት፤ በጦርነትና በተፈጥሮ አደጋ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉና የተቸገሩ ወገኖች የታወሱበት እና አብሮነት እና መተሳሰብ የበለጠ የጎላበት ዝግጅት ነበር፡፡

‹‹ኢፍጣራችን ለአንድነታችን›› የተሰኘው ይኸው ደማቅ ሥነሥርዓት ኢትዮጵያውያንን አንድነት፤ አብሮነትና መከባበር ያሳየ እና ኢትዮጵያ ሁሉም እምነቶች በእኩልነትና በወንድማማችነት የሚኖርባት ሀገር መሆኗን ለዓለም ያሳየ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ 98 በመቶ እምነት ያለው ሃይማኖተኛ ነው፡፡ ሃይማኖተኛ ሕዝብ ደግሞ ለሠላም ዘብ የሚቆም፤ የተቸገረን የሚረዳ፤ የተራበን የሚያበላ እና ሌሎች መልካም ዕሴቶችን የተላበሰ በመሆኑ ለብጥብጥና ሁከት እንዲሁም ለዜጎች ደም መፍሰስና ሕይወት መጥፋት ምክንያት የሚሆኑ ሃሳቦችንም ሆነ ድርጊቶችን በሙሉ አይቀበልም፡፡ በተቃራኒው በጽኑ ይታገላቸዋል፡፡

ስለዚህም የሁለቱ ታላላቅ ሃይማኖቶች የጾም በወቅት በሆኑት የዐቢይና የረመዳን አፅዋማት የግጭት፣ የጦርነት፤ ያለመግባባት ታሪካችን ተዘግቶ በጋራ ታሪኮቻችን ላይ የምንግባባ፤ ለጋራ ሀገራችን የምንተጋ፤ ለልጆቻችንም የበለጸገች ኢትዮጵያን ለማውረስ የጋራ ዕሳቤ የጨበጥን በእምነት የታነጽን ትውልዶች ልንሆን ይገባናል!

አዲስ ዘመን መጋቢት 20/2016 ዓ.ም

Recommended For You