ኢትዮጵያ በማዕድን ሀብት ባለጸጋ ናት። የወርቅ፣ የከበሩ ጌጣጌጦች፣ የታንለም፣ የሊቲየም፣ የድንጋይ ከሰል፣ የብረት፣ የተፈጥሮ ጋዝ፣ ለኢንዱስትሪና ለኮንስትራክሽን ግብአቶች የሚሆኑ ማእድናት በስፋት እንደሚገኙባት መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ሀብቱን በማልማት ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች እምብዛም አለመስራታቸውን ተከትሎ፣ ከዘርፉ የሚገባትን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማግኘት ግን አልቻለችም። የማዕድን ዘርፉ ትኩረት ተነፍጎት የቆየ መሆኑ ላለመልማቱ ከሚጠቀሱ ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የማዕድን ዘርፍ በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ሰፊ ትኩረት ከተሰጣቸው አምስት ዘርፎች መካከል አንዱ ተደርጓል፤ ይህም ለማእድን ልማቱ ትልቅ አስተዋጾኦ እያበረከተ ነው።
የዘርፉ ችግር ማእድኑን ማልማት አለመቻል ብቻ አይደለም። የሕገወጥነት መንሰራፋትም ዋንኛው ችግር ሆኖ ይታያል። ሕገወጥነቱ ከለማው ማእድን አልሚዎቹና ሀገር በተገቢው አግባብ መጠቀም እንዳይችሉ እያደረገ ይገኛል።
የሕገወጥነቱ መስፋፋት አገሪቷ ያላትን እምቅ የማዕድን ሀብት በማልማት ጥቅም ላይ ለማዋል እያደረገች ያለችውን ጥረት በማደናቀፍ እንቅፋት እየሆነ መምጣቱም በተደጋጋሚ ሲገለጽ ይሰማል። በዚህም የተነሳ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክተውና ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር እንደሚችል የታመነበት ይህ የማዕድን ዘርፍ የተፈለገውን ውጤት ማምጣት አልቻለም። የወርቅ ምርት እየተመረተ ቢሆንም፣ በሕገወጥነት የተነሳ የሚፈለገውን ያህል ለብሄራዊ ባንክ እንዲገባ እየተደረገ አይደለም።
ይህን ሕገወጥ የማዕድን ዝውውርና ግብይት ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ለውጦችና መሻሻሎች እየመጡ መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፤ ይህን ጥረት የሚያደንቁት የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች፣ ችግሩን በዘላቂነት መከላከል በትኩረት መስራት እንደሚገባ ይመክራሉ።
የዘርፉ የሕገወጥነት ችግር የማዕድን ልማት ባለባቸው በሁሉም አካባቢዎች የሚስተዋል ተግዳሮት እንደሆነም ይታወቃል። በተለይ በወርቅ ምርቱ የሚታወቀው የጋምቤላ ክልል በዚህ ሕገወጥነት እየፈተነ ስለመሆኑ የክልሉ ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ መረጃ ያመለክታል።
የክልሉ ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አኳታ አቻም እንደሚሉት፤ በክልሉ የማዕድን ዘርፉ ዋንኛ ተግዳሮት የሕገ-ወጥነት መስፋፋት ነው። በክልሉ የኮንትሮባንድ ንግድና ሕገ-ወጥነት በከፍተኛ ደረጃ መኖሩ ክልሉ የሚታወቅበትን የወርቅ ማዕድን አምርቶ የተሻለ ውጤት እንዳያመጣ እያደረገ ይገኛል። በተለይ ክልሉ ከማዕድን ዘርፍ ሊያገኝ የሚገባውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዳያገኝ እንቅፋት ሆኗል።
በሌላ በኩል ሕገ-ወጥ የማዕድን ዝውውርን ከመከላከል አንጻር ብዙ ሥራዎች መስራታቸውን የሚናገሩት ኃላፊዋ፤ በክልሉ ርዕስ መስተዳድር የሚመራ ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ በየጊዜው ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ይገልጻሉ። በኮማንድ ፖስቱ አማካይነት ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ ባሉ አደረጃጀቶች በየጊዜው፣ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚደረግ ጠቁመው፤ ክፍተቶች ሲገኙም እርምጃ በመውሰድ ቁጥጥር የማድረጉ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።
እንደ ኃላፊዋ ማብራሪያ፤ በክልሉ ወርቅ በስፋት ይመረታል። የኮንስትራክሽን፣ የኢንዱስትሪ ማዕድናት እና ሌሎች ማዕድናትም በክልሉ የሚገኙ ቢሆንም፣ እስካሁን ሌሎች ማዕድናት እምብዛም ወደ ምርት የገቡ አይደሉም። ወርቅ የሚመረትባቸው አራት ወረዳዎች (ዲማ፣ አቦቦ፣ ጋምቤላና መንገሺ) ሲሆኑ፤ የዲማ ወረዳ ግን ወርቅ በስፋት ይመረትበታል።
እነዚህ ወርቅ የሚመረትባቸው አካባቢዎች ከወረዳዎቹ በጣም ራቅ ያሉ መሆናቸው የወርቅ ምርቱን ለመቆጣጠር ስለማያመች ሕገወጥነት እንዲስፋፋ ምክንያት ሆነዋል። የቀበሌዎቹ (አካባቢዎቹ) ርቀት የክትትልና የቁጥጥር ሥራውን አዳጋች አድርጎታልም። በሌላ በኩል ቀደም ሲል ወርቅ በሚመረትባቸው ቦታዎች ላይ የወርቅ ምርቱን የሚረከብ ባንክ አለመኖር ችግር ነበር፤ አሁን ላይ ግን ወርቅ በሚመረትባቸው እያንዳንዳቸው ወረዳዎች ባንክ በመኖሩ የተመረተውን ወርቅ በማንኛውም ሰዓት ለባንክ ለማስገባት የሚቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ችግሩ በስፋት እየተፈጠረ ያለው ወርቅ ከሚመረትበት ቦታ ባንክ እስኪገባ ድረስ ባሉ ቦታዎች ላይ ሕገወጥነት በመኖሩ የተነሳ ነው።
ክልሉ በአብዛኛው የሚታወቀው በወርቅ ምርቱ መሆኑን ኃላፊዋ ጠቅሰው፣ በተያዘው በጀት ዓመት አንድ ሺ ሁለት መቶ ኪሎ ግራም ወርቅ ለማምረት ታቅዶ በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ያመላክታሉ። በግማሽ ዓመቱ 625 ኪሎ ግራም ወርቅ ለማግኘት ታቅዶ፤ አንድ መቶ ሃምሳ አራት ነጥብ ሃያ ስምንት ኪሎ ግራም ወርቅ ብቻ ለብሔራዊ ባንክ ማስገባት መቻሉን አስታውቀዋል። ይህም የሚያሳየው በእቅዱ መሠረት ወርቅ ማምረት አለመቻሉን እንደሆነም ጠቅሰው፣ ለዚህም ምክንያት የኮንትሮባንድ ንግድና ሕገወጥነት በከፍተኛ ደረጃ መስፋፋቱ መሆኑን ጠቁመዋል።
እንደ ኃላፊዋ ማብራሪያ፤ በክልሉ ወርቅ የማምረት ሥራው የሚካሄደው በባሕላዊ መንገድ ነው። በክልል ደረጃ ሁለት የወርቅ አምራች ኩባንያዎች ያሉ ሲሆን፤ እስካሁን ወደ ሥራ የገባው አንድ ኩባንያ ብቻ ነው። ሌላኛው በቀጣይ ወደ ሥራ ሊገባ ይችላል ተብሎ ይጠበቃል። አሁን ላይ ወርቅ የሚመረተው በአነስተኛ እና ባሕላዊ ወርቅ አምራቾች ነው፤ ይህም ለሕገወጥነት እየተጋለጠ መሆኑ ምርቱን የመቆጣጠሩን ስራ አስቸጋሪ አድርጎታል። በዚህም የተነሳ በትክክለኛው መንገድ የተመረተው ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ሳይገባ በሕገወጥ መንገድ የሚወጣበት መንገድ ሰፊ ነው።
በተጨማሪም በክልሉ በማዕድን ዘርፉ የሚደራጁት ዜጎች በሁለት መልኩ ወርቅ በማምረትና በወርቅ በግብይት ሥራ እንደሚደራጁ ይገልጻሉ። በክልሉ በማዕድን ዘርፍ የተደራጁ 47 ያህል አምራቾች እንዳሉ ጠቅሰዋል። ከእነዚህ አምራቾች መካከል በሕገ-ወጥ ሥራ ተሰማርተው የሚገኙ፤ ከወርቅ አምራቾች ወርቅ ተረክበው ለብሔራዊ ባንክ ማስገባት ሲገባቸው መሀል ላይ እንዲጠፋ ያደርጋሉ ሲሉ ያብራራሉ። በእነዚህ አካላት ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አመልክተው፣ በተለይም በወርቅ ግብይት በተደራጁ 11 ማህበራት ላይ ሕጋዊ እርምጃ መወሰዱን አስታውቀዋል። በእርምጃው ንብረታቸው በመውረስ፣ በገንዘብ እና በእስር እንዲቀጡ መደረጉን አመላክተዋል።
በ2015 በጀት ዓመት ሕገወጥነት ለመከላከል በተሰራ ሥራ በውጭ አገር ዜጎች ላይ ሳይቀር እርምጃ በመወሰዱ ከክልሉ እንዲባረሩ መደረጉን ኃላፊዋ አስታውሰዋል። የውጭ አገር ዜጎችም ቢሆኑ ሕጋዊ መንገድን ተከትለው ለመስራት ፈቃድ ወስደው የሚሰሩ የውጭ ሀገር ዜጎች እንዳሉም ጠቅሰው፣ በእነዚህም ላይ ክልሉ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እያደረገ የሚገኝ መሆኑን አስረድተዋል።
‹‹የተያዘው በጀት ዓመት የወርቅ ምርትን የስድስት ወራት አፈጻጸም ብንመለከት ወርቅ በባሕላዊ መንገድ እየተመረተ በመሆኑ የሚፈለገውን ያህል ውጤት እያስገኘ አይደለም›› ሲሉ ኃላፊዋ ጠቁመዋል። ይህም በአነስተኛ የወርቅ አምራችነት ተሰማርተው ወርቅን በባሕላዊ መንገድ የሚያመርቱ አምራቾች ውጤታማ ሥራ እንዲሰሩ ማስቻል እንደሚጠይቅ አመላክተዋል። አምራቾች በእውቀት፣ በቴክኖሎጂ እና በአቅም እንዲበቁ ቢደረግ የተሻለ በማምረት ጥሩ ውጤት ማምጣት እንደሚችሉ አመልክተዋል፤ አምራቾቹ በባለፈው በጀት ዓመት ስልጠናዎች እና የተለያዩ አይነት ድጋፎች እንዲያገኙ መደረጉን ጠቅሰው፣ በቀጣይ ይህን አጠናክሮ ለማስቀጠል ከፌዴራል ማዕድን ሚኒስቴር ጋር የተለያዩ ድጋፎች ለማድረግ የሚያስችሉ ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸውን አብራርተዋል።
በክልሉ በመጀመሪያ በጀት ዓመት በወርቅ ምርት ጥሩ ለውጦች መታየታቸውንና የተሻለ ውጤትም ማስመዝገብ እንደተቻለ የጠቀሱት ኃላፊዋ፤ በመስከረም ወር የተገኘው የወርቅ ምርት አነስተኛ ቢሆንም በጥቅምት ወር 30 ኪሎ ግራም ወርቅ ማግኘት ተችሏል ብለዋል። በሕዳር ወርም እንዲሁ አበረታች ውጤት መመዝገቡን አስታወሰዋል።
በሕገወጥነት ላይ ያለው ቁጥጥርና ክትትል ሲጠናከር ለውጦች እንደሚመጡ ጠቅሰው፣ በተቃራኒው ቁጥጥርና ክትትሉ ሲላላ ደግሞ ውጤቱ እያሽቆለቆለ እንደሚሄድ ያስረዳሉ። ‹‹በእያንዳንዱ ወር የሚገኘው የወርቅ ምርት በየጊዜው ይለያያል፤ የወርቅ ሥራ እንደ አፈሩ ሁኔታም ይወሰናል፤ አንዳንድ ወቅት ላይ በጣም ብዙ ወርቅ ይገኝና ከፍተኛ ምርት የሚመረትበት አጋጣሚ ይኖራል። አንዳንድ ወቅት ደግሞ ምርቱ ጨርሶ የማይኖርበት ሁኔታም ይከሰታል›› ሲሉ ያብራራሉ።
ከፍተኛ የወርቅ ምርት በሚመረትበት ወቅት ሕገ-ወጥነት ቢኖርም ከሚመረተው ምርት ብዛት አንጻር ብዙ የወርቅ ምርት ማግኘት ይቻላል ሲሉም ተናግረው፣ በዚያው ልክ ደግሞ የምርት እጥረት ሲያጋጥም ሕገወጥነቱ እና የምርቱ መቀነስ ተደማምረው በየወሩ የሚገኘውን የወርቅ ምርት መጠን እንዲቀንስ ሊያደርጉት ይችላሉ በማለት ተናግረዋል።
ሌላኛው ለምርት መቀነስ ምክንያት ሊሆን የሚችለው ደግሞ የተፈጥሮ ክስተት መዛባት ነው ያሉት ኃላፊዋ፣ በጥቅምት ወር 30 ኪሎ ግራም የሚደርስ ከፍተኛ መጠን ያለው የወርቅ ምርት መገኘቱን ለአብነት ይጠቅሳሉ። ይሁንና ከዚያ በኋላ ግን በክልሉ በተፈጠረው ዝናብ በመብዛት የተነሳ ማሽኖች የተወሰዱበትና ምርቱም የጠፋበት ሁኔታ ተከሰቶ የምርት መቀነስ ማጋጠሙን አመላክተዋል።
የዘርፉ ማነቆ የሆነውን ሕገ-ወጥነት በመከላከል ረገድ በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በተለይ የወርቅ ምርትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ቀጣይነት ያላቸው ሥራዎችን ከባለድርሻ አካላት ጋር እንደሚሰሩ ኃላፊዋ ተናግረዋል።
የማዕድን ዘርፉ በርካታ የሥራ እድል ለመፍጠር ከሚያስችሉ ዘርፎች መካከል ዋንኛው ነው ያሉት ኃላፊዋ፤ በ2016 በጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት ብቻ ዘርፉ 849 ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር የተቻለ መሆኑን ገልጸዋል።
የቢሮ ኃላፊዋ እንዳብራሩት፤ በክልሉ ያሉትን የማዕድን ሀብቶች ለማወቅ በተደረገው ጥናት የማዕድን ሀብት ያለባቸው ቦታዎች ተለይተዋል፤ በቀጣይም የተቀሩትን ቦታዎች ለማጥናት ታቅዶ እየተሰራ ነው፤ ካሉት የማዕድን ሀብቶች አንጻርም ሲታይ እስካሁን እየለሙ ያሉት የተወሰኑ ማዕድናት ሲሆኑ፣ በክልሉ ያሉ የማዕድን ሀብቶች ሥራ ላይ በማዋል እንደ ሀገር ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችሉ ሥራዎች መስራት ያስፈልጋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ በክልሉ በማዕድን ዘርፍ ያለውን ሕገ ወጥነት ለመከላከል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ይገልጻሉ። ከክልሉ ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ ማዕድን መጠን በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ መምጣቱን ያመለከቱት ርዕሰ መስተዳደሩ፤ የዘርፉን ተግዳሮቶች በመፍታት ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባውን የወርቅ መጠን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ያመላክታሉ።
በተለይ በክልሉ ያለውን የወርቅ ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል ሕገ ወጥነትን ለመከላከል ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ሕገ-ወጥ የወርቅ ዝውውርን በመቆጣጠር ሀብቱን ለሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ ለማዋል በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ሕገ-ወጥ የወርቅ ዝውውርን ለማስቆም በየደረጃው ከሚገኙ የባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት፣ የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎችን በማጠናከር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አመልክተው፤ የወርቅ ልማቱን በመቆጣጠር ረገድ የወረዳና የዞን አመራሮች በቁርጠኝነት መሥራት ይጠበቅባቸዋል ሲሉም አስገንዝበዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን መጋቢት 20/2016 ዓ.ም