የአፍሪካ ብርሃን

የዛሬ 13 ዓመት የዓባይ ግድብ መሠረት ድንጋይ ሲጣል ብዙዎቻችን እንዴት ሆኖ የሚል ጥርጣሬ ልባችን ውስጥ ጭሮ ነበር። ይህ ሃሳባችን ለሀገራችን ቅን ካለመመኘት ወይም ደግሞ የመበልጸግ ፍላጎት አጥተን ሳይሆን አቅማችንን አይተን ግንባታው የሚጠይቀውን ወጪ ፈርተን ነው። ያም ቢሆን ግን ኢትዮጵያውያን ወትሮም ቢሆን ከጨከኑና በአንድ ከተነሱ የሚሳናቸው ነገር አለመኖሩን ያሳዩበት ድንቅ ሥራ ነው፡፡

በጋራ ጥረታችንም አሁን የዓባይ ግድብ ወደ መጠናቀቁ ደርሷል፡፡ ዛሬ ላይ የሥራውን 98 በመቶ ለማገባደድ ችለናል። በእውነት ይህ ለእኛ ትልቅ ደስታ ኩራት የአንድነታችንንና የኅብረታችን ማሳያ የመቻላችን ውጤት በመሆኑ ሁላችንም ልንኮራ ይገባል፡፡

ዛሬ ላይ የዓባይ ግድብ 98 በመቶ ደረሰ እንበል እንጂ ባለፉት 13 ዓመታት ያየናቸው ችግሮች፤ የደረሱብን ውጣ ውረዶች እንዲህ በቀላሉ የሚታዩ አይደሉም። የመልማት ፍላጎታችን ያልተዋጠላቸው የዓረቡ ዓለም ሀገራትና ምዕራባውያኑ በቻሉት ሁሉ ከረዥሙ ጉዟችን ሊያሰናክሉን ያልቆፈሩት ጉድጓድ አልነበረም። እኛ ኢትዮጵያውያን ግን ወትሮም ቢሆን ለእነሱ በትር ዋጋ የምንሰጥ አይደለንምና መሪዎቻችን በዲፕሎማሲው እኛ ደግሞ አቅማችን የቻለውን ሁሉ ወደ ግድባችን በመወርወር ስኬታማ ለመሆን በቅተናል። እንኳን ደስ ያላችሁ! እንኳን ደስ አለን!

ኢትዮጵያ ከጥንት እስከ ዛሬ የጀግንነት፤ የአይበገር ባይነት ብሎም የደግነትና ተሳስቦ የመኖር ምሳሌ ናት። አዎ ይህንን ሁኔታ ደግሞ በተለያዩ አጋጣሚዎች አሳይተናል፤ አሳክተናልም። ዓባይ ወንዛችንን ተጠቅመን እንልማ ስንል ጎረቤቶቻችንን እናክስር ወይም ችግር ላይ እንጣል ማለት እንዳልሆነ በቃልም በተግባርም በተደጋጋሚ አረጋግጠናል፡፡

አዎ እኛ ብቻችንን የምንበላ ስግብግብ ወይም ራስ ወዳዶች አይደለንም፡፡ ጎረቤቶቻችንን እንደራሳችን የምንወድ ችግራቸውን ችግራችን፤ መልማታቸውን መልማታችን የምናደርግ ኩሩ ሕዝቦች ነን።

ይህንን የቆየ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን እኛነታችንንም በታላቁ ዓባይ ግድባችን ደግመነዋል፡፡ እናት መቀነቷን ፈታ፤ አባት ከልጆቹ ጉሮሮ ቀንሶና ነጥቆ የመንግሥት ሠራተኛው ኑሮን ተቋቁሞ ነጋዴው ትርፉን ትቶ ባለሀብቱ ካለው ቀንሶ ብቻ ሁሉም የአቅሙን አድርጎ ያሠራው ግድብ ለሌሎች ሀገሮችም በሚጠቅም መልኩ አዘጋጅተነዋል። አሁን ከሁላችንም የሚጠበቀው በፍቅርና በሠላም የሀብቱ ተቋዳሽ መሆን ብቻ ነው ብዬ አስባለሁ።

በሌላ በኩልም ይህ ግድብ ኢትዮጵያውያንን ከጨለማ አውጥቶ ብርሃን የሚያሳይ እንደ ሀገር በሁለት አግራችን ቆመን ዜጎቻችንን ከስደትና እንግልት የምናድንበት ነው። ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ ከጎረቤቶቻችን ጋር ያለንን ቀጣናዊ ትስስር በማሳመርና በማሳለጡ በኩልም የሚወጣው ሚና በትንሹ የሚታይ አይደለም።

ብዙ ጎረቤቶቻችን የእኛን ያህል የውሃ ሃብት የላቸውም። ይህ ሁኔታ ደግሞ ለእኛ ጥሩ አጋጣሚ ነው። የዓባይ ግድብ ደግሞ ለሁሉም መትረፍ፤ መትረፍረፍ የሚችል ታላቅ ፕሮጀክት ነው። በመሆኑም ፍቅር ካለ እንደሚባለው እስከ ዛሬ እንደመጣንበትም ሆነ ከዛሬ በኋላ አሻሽለን በምንቀጥልበት ሁኔታ ላይ የምንሠራው ሥራ በሙሉ ጎረቤቶቻችንን ታሳቢና ተጠቃሚ ያደረገ እንደሚሆን ሙሉ እምነት አለኝ።

ግድቡ ከወዲሁ ብዙ ተስፋ እየተጣለበት የብርሃን አክሊልን እየተላበሰ ያለ ይመስላል፡፡ በተለይም ለጎረቤት ሀገራት የኃይል ምንጭ በመሆን የሚሰጠው ጠቀሜታ ትልቅ ከመሆኑም በላይ ምሥራቅ አፍሪካን በአንድ በማስተሳሰር በኩል የሚያበረክተው አስተዋፅዖ በቀላሉ የሚታይ አይሆንም፡፡ ይህ ግዙፍ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሥራው ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት አስተማማኝ የኃይል ምንጭ እንዲያገኙ ከማስቻሉም በላይ የቀጣናውን ሀገራት በኃይል በማስተሳሰር የጋራ ኢኮኖሚ እንዲገነቡ በር የሚከፍት ይሆናል፡፡

በተመሳሳይም እንደ ኢትዮጵያ አይነት የምድር በረከት የሌላቸውን የምሥራቅ አፍሪካ አገራት ንጹሕ የመጠጥ ውሃ እንዲያገኙ በማስቻል በኩል የሚኖረው ሚና በቀላሉ የሚታይ አይሆንም። እዚህ ላይ ደግሞ በዋናነት የንጹሕ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ትሆናለች ተብላ የምትታሰበው ጅቡቲ ናት። በዚህ መሠረት ውሃን በመላክ ቀጣናዊ ትስስሮሽን ማጎልበት እስከ አሁንም የመጣንበት ወደፊትም አጠናክረን የምንቀጥልበት የጉርብትና አካሄዳችን እንደሚሆንም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያመላክቱትም እስከ አሁን ኢትዮጵያ ከ 258 ኪሎ ሜትር በላይ የውሃ መስመር ዝርጋታ በማከናወን በየቀኑ ለጅቡቲ ውሃ እያቀረበች ሲሆን ከዚህ ቀደም ትልክ የነበረውን ከ 20 ሺህ እስከ 30 ሺህ ኪዩቢክ ሜትር የሚደርስ ውሃ ወደ 100 ሺህ ኪዩቢክ ሜትር ለማሳደግ እየሠራች ትገኛለች፡፡ ይህም ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብቶቿን ጭምር በማጋራት ቀጣናዊ ትስስሩን ለማጠናከር ምን ያህል ፍላጎት እንዳላት የሚያመላክት ነው፡፡

አሁን የዘመናት ሕልማችን የሚፈታበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። የዓባይ ግድብ ደግሞ ለእኛም ሆነ ለጎረቤቶቻችን የሚሰጠው በረከት ከላይ ከገለጽኩትም በላይ ሊሆን ይችላል። ታዲያ ሌሎች ዳር ቆመው ሥራውን ለማደናቀፍ ሲሞክሩ የነበሩ አሁንም ተስፋ አልቆርጥ ብለው በአልሞት ባይ ተጋዳይነት ብዙ ጥረት የሚያደርጉ አካላት ምን ቢያስቡ ኢትዮጵያውያን ላመኑበት የመሞት ልምድ አላቸው፡፡ ምንም ቢሉ ምን ምንም ቢያደርጉ ምን የትኛውንም በር ቢያንኳኩ ኢትዮጵያውያን የጀመሩትን ለመጨረስ ቆራጥ ናቸውና ይኸው ፍጻሜው ላይ አድርሰውታል። ታዲያ ዛሬስ እነዚህ የእኩይ ተግባር አቀንቃኞች ሚናቸውን አስተካክለው አብረን ብንለማ ምን ይላቸዋል?

ሙያ በልብ ነው እንደሚለው የሀገሬ አባባል እነሱ ምንም አሉ ምን እኛ የዘመናት ሕልማችንን አሳክተናል፤ አሁን ከፈለጉ ከጎናችን ሊሆኑ ካልፈለጉም ምርጫቸውን ልናከብርላቸው ዝግጁዎች ነን። እኛ ዛሬ እንደ ዜጋ የምንፈልገው ጥርሳችንን ነክሰን ዛሬያችንን አጉለን የነገው ይሻለናል ብለን ከገነባነው ግድብ መጠቀም፤ መበልፀግ፤ የልጆቻችንን የእህት ወንድሞቻችንን ስደት ባለበት ማቆም ነው። አዎ ከዚህ በኋላ ችግረኛ ደሃ ተሳዳጅ የሚለውን ስማችንን ማረም አለብን ። ግድባችን ደግሞ የስማችን መጠሪያ፤ የማንነታችን አሻራ፤ የትናንት ጉስቁልናችንን መርሻና ማበሻ በጠቅላላው አዲሲቷን የልጆቻችንን ኢትዮጵያ መገንቢያ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለኝም።

ይህንን ሕልማችንን እውን እንዲሆን ከመሠረት ድንጋይ መጣሉ ጀምሮ ቁርጠኝነት ያሳዩት መሪዎቻችን፤ ላለፉት 13 ዓመታት በበረሃ ተቃጥለው ራሳቸውን ለሀገራቸውና ለሕዝባቸው ሰውተው በሥራው የተሳተፉ፤ ጉልት ቸርችረው ድንጋይ ተሸክመው ካስቀመጧት ጥሪት አውጥተው ቦንድ ገዝተው የታሪኩ አካል ለመሆን የቻሉ ሁሉ ምስጋና ይገባቸዋል።

የዓባይ ግድብ ዛሬ ላይ ከእኛ አልፎ የአፍሪካ ብርሃን ነው። ኢትዮጵያ ደግሞ የዚህ ብርሃን ምነጭ ሆናለች ። ግን ደግሞ ይህንን መነሻ አድርገን ሌሎች የዓባይ ግድቦችን እንሠራ ዘንድ አቅሙ እንዳለንም አሳይተናል፡፡ ሌላም ታሪክ በሌላ የልማት ሥራ ይቀጥላል። አበቃሁ!

በእምነት

አዲስ ዘመን መጋቢት 20/2016 ዓ.ም

Recommended For You