ሙሾ እናውርድ!

ሙሾ ጥበብ ሙሾ እንጉርጉሮ፤ ለኛ ሲያንጎራጉርና ለውስጣዊ ስሜታችን እላይ ታች ሲል እንዳልከረመ ሁሉ አሁን ለእርሱም በትዝታ የሚያንጎራጉርለትን ሳይፈልግ አልቀረም። ምክንያቱም ከነበረበት የጥበብ ከፍታ፤ ከተሰቀለበት የማህበረሰቡ ልብ ውስጥ ወጥቶ ባይተዋርነት ከተሰማው ዋል አደር ብሏል፡፡ አሁን መሪር እንባዋን የምታፈስለት ጥበብ ናት፡፡ ሀዘኗ ተገልጦ ለአይን የሚታይ ቢሆን ምናልባትም እንባዋን ልክ እንደዚህች ብላቴና እያዘራችው ይሆናል፡፡ ድሮ ድሮማ የማህበረሰቡ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ሁሉ በሙሾ የተዋዛ፤ የት አለ ሙሾ የሚያስብል ነበር፡፡

እቤት ውስጥ አባት ከልጁ፤ ሚስት ከባሏ፤ ጎረቤት ከጎረቤቱ፤ አዙሮ ለመናገር የፈለገውን ነገር ሁሉ በቅኔ እያሾረ የሚገልጸው በሙሾ ነበር፡፡ በየስብሰባና እድሩ ሙሾ ያለምንም አጀንዳ ሁሌም ድባቡን ይዘውራል። በየሠርግና ማህበሩ ሁሉ ከጠላና ጠጁ ቀጥሎ የሚቀዳው ሙሾው ነው፡፡ በባህሪው፤ የሀዘንና የመሪሪ እንባ አቁማዳ ብቻ አይደለም፡፡ አንዳንድ ጊዜም አፈንጋጭነቱ የተለየ ነው፡፡ የማይገባበትና እየያዘ የማይጥለው ጥበባዊ የስሜት አንጓ የለም፡፡ በሙሾ ውስጥ የሞተ ሰው ብቻ ሳይሆን ከሰማይ እስከ ምድር፤ ከሰው ልጆች እስከ ፈጣሪ፤ ከነፍሳት እስከ ግኡዝ አካላት፤ ከክዋክብት እስከ ዘመንና የጊዜ መዘውሮች፤ ለሁሉም ሙሾ ይወረድላቸዋል፡፡

ሀዘን፣ ቅሬታ፣ ንዴት፣ ስላቅ፣ አሽሙር፣ ምስጋና፣ ደስታ፣ ፍትህ፤ እውነት…ሁሉም ማህበራዊ መንፈሳዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ይንጸባረቁበታል፡፡ አንዳንዴ፤ ሙሾ ምን መልክ አለው? ብሎ ከመጠየቁ የሌለውን መጠየቁ የሚቀል ነው፡፡ አንዱ ሙሾ የተሠራው፤ ከሦስት የጥበብ ልጆች ዘረመል ነው፡፡ የመጀመሪያው ግጥም ነው፡፡ ሙሾ ያለግጥም አይወርድም፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የዜማን ዘረመል እናገኛለን፡፡ ግጥሙ እንዳለ፤ ዜማው ከሙዚቃ ጋር የሚያመሳስለውን ነገር ይፈጥራል፡፡ ጥበባዊ ይዘቱ ጎልቶ እንዲታይ የሚያደርገው ሦስተኛው ነገር ቅኔው ነው፡፡ በቅኔ የተለወሰ ሙሾ ማለት በቅቤ እንደተለወሰ ‘ጭኮ‘ ማለት ነው፡፡ ከመጣፈጡም ዘመን ተሻጋሪነቱ ከፍ ያለ ነው፡፡

በአጠቃላይ ማንነቱ ከብዙ የጥበብ ትውፊቶች ለየት የሚያደርገው ነገር፤ እያንዳንዱ የሙሾ ግጥም፤ ዜማና ቅኔዎች በምክንያትና ከእውነት ወንዝ ላይ የሚቀዱ መሆናቸው ነው፡፡ ማህበረሰቡ ሙሾ በሚያወርድበት አጋጣሚ ሁሉ የተፈጠረ ክስተት ከበስተጀርባው ይኖራል፡፡ በሙሾ ቤት ውስጥ ሁለት ነገሮች አሉ። አንደኛው ነገር፤ ሙሾ አውራጁ ከማውረዱ በፊት ስለሚለው ጉዳይ ብዙ አውጥቶና አውርዶ እውነታውን አጢኖ የሚፈጥረው ነው። ለምሳሌ፤ በለቅሶ ቤት እየተከፈላቸው በሚሠሩ አስለቃሾች ዘንድ የሚታይ ነው፡፡ ግጥሞቹ የሟችን እውነተኛ ማንነት፤ ዕድሜ፤ ጾታ፤ መልክ ባህሪ፤ የኑሮ ደረጃና መሰል ጉዳዮችን ጠንቅቆ ማወቅ ይጠበቅበታል። ሁለተኛው ደግሞ፤ ስለምንና እንዴት ብዬ…በማለት ተጨንቆና ተጠቦ የሚፈጠር ሳይሆን ለአንድ ለተፈጠረ ነገር ውስጣዊ ስሜትን በውጫዊ ቃላት ለማንጸባረቅ በድንገት ጣል የሚደረግ ነው፡፡ በዚህ ወቅት ሙሾ የሚወርደው በቅኔ ዘረፋ ነው፡፡ ለማለት የፈለጉትን የሚያመለክቱት በውስጠ ወይራ ዘንግ ነው፡፡ ከስሜት የመነጨ እንደመሆኑ መልእክቱም ጠጣርና ከበድ ያለ ነው፡፡

ሙሾ ያለምክንያት አይወርድም፤ ቅኔውም ያለ ቦታው አይፈስም ብለናል፡፡ በሀገራችን ታሪክ ውስጥ ሆኑ ተከሰቱ ከተባሉት ከእያንዳንዱ ክስተቶች በስተጀርባ ሙሾ አለ፡፡ ጥቂቶቹንም እንደማሳያ እንመልከታቸው፡፡ ደርግ የንጉሡን ዘውድ ገርስሶ በመጣበት ወቅት በጎንደር አካባቢ ይኖር የነበረው መላኩ ተፈራ የተባለው ሰው ግን አብዮቱን አልታዘዝም በማለት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶችን ረሽኖ በማስረሸን ጭካኔው የታወቀ ነበር፡፡ የጎንደር እናቶችም እንዲህ ሲሉ የዜማ ሙሾ አወረዱለት፤

«መላኩ ተፈራ የእግዜር ታናሽ ወንድም

የዛሬን ማርልኝ የነገን አልወልድም»

የሙሾ ጥበብ የማይረሳውን መልኩን ያኖረበት ክስተት የአጼ ምኒልክ ሞት ነው፡፡ በጊዜው ንጉሡ የሞቱ ቢሆንም የቤተ መንግሥቱ ሰዎች ግን ነገሮች ፈር እስኪይዙ ድረስ በማለት ሀዘኑንም መርዶውንም አምቀውት ለመቆየት ሞከሩ፡፡ ጭምጭምታው ግን ከውጭ ወጥቶ ስር ስሩን ይሄድ ነበርና “እምዬ..ጌትዬ…አባቴ…” እያለ ከየቤቱ ሆኖ የሚያለቅሰውም ብዙ ነበር። ከእዚህ መሃከልም ቤተ መንግሥቱ ድረስ የዘለቀ አንድ አልቃሽ እንዲህ ሲል ሙሾውን አወረደው፤

«ፈረስ በቅሎ ስጠኝ ብዬ አለምንህም

አምና ነበር እንጂ ዘንድሮ የለህም» በማለት ሕዝቡ ስለ ንጉሡ ሞት ማወቃቸውን አፍረጠረጠው፡፡ በዚሁ ለቅሶ ወቅትም እቴጌ ጣይቱ ሌላ ታሪካዊ ሙሾ አወረዱ፡፡

«ነጋሪት ማስመታት፤ እምቢልታ ማስነፋት ነበረ ሥራችን

ሰው መሆን አይቀርም ደረሰ ተራችን» ሲሉ ሀዘናቸውን ገለጹ፡፡

በአጼ ምኒልክ ሞት ምክንያት ይዘንቡና ይጎርፉ የነበሩት የሙሾ ግጥምና ዜማዎች በገፍ ቢሆኑም፤ ከዚህች ግጥም ግን ጥቂት ስንኞችን ቆንጥረን እንመልከተው፡፡ የሙሾው ግጥም ተጽፎ የሚገኘው “ዐፄ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት” ከሚለው መጽሐፍ ላይ ሲሆን ባለቤትነቱ ደግሞ ቀጣዩን የንግሥና ዘውድ የጫኑት፤ የንግሥት ዘውዲቱ ነው፡፡

«እልፍ ነፍጥ በኋለው፤ እልፍ ነፍጥ በፊት፣

ባለወርቅ መጣብር አያሌው ፈረስ፣

ይመስለኝ ነበር ይኼ የማይፈርስ፡፡

ብትታመም ልጅህ እጅግ ጨነቀኝ፣

ብትሞትስ አልሞትም እኔ ብልጥ ነኝ፡፡

ቀድሞ የምናየው የለመድነው ቀርቶ፣

እንግዳ ሞት አየሁ ካባቴ ቤት ገብቶ፡፡

አሻግሬ ሳየው እንዲያ በሰው ላይ

መከራም እንደሰው ይለመዳል ወይ፡፡»

እንግዲህ እኚህና እኚህን መሰል በዘመን ርቀት ያልተገቱ የሙሾ ጥበቦች፤ በአንድ ወቅት የነበረን ታሪክ ቁልጭ አድርገው የሚናገሩና ፍንትው አድርገው የሚያሳዩ በመሆናቸው ታሪክ ነጋሪነታቸው ላቅ ያለ ነው፡፡ በጥቂት ቃላት፤ በጥቂት ስንኞች ግዙፉን ታሪክ ከነ ነብሱ ያኖሩታል፡፡ አሁን ሙሾ የሚያስወርድ ሕይወት ጠፍቶ ሳይሆን የጠፋው ሙሾ አውራጁ ነው፡፡ በአብዛኛው ሰው አረዳድም፤ ሙሾ ለሙታንና በሙታን መንደር ብቻ የሚቀርብ የሀዘን ንፍሮ መስሎ ይታያል፡፡ ዳሩ ግን ይህ አንዱ እንጂ ብቸኛው አይደለም፡፡ ከዚህ የላቀ አንደምታ አለው፡፡ በእርግጥ በአንደኛው ዘመን፤ ከማህበረሰቡ ጋር ያለው ቁርኝት እየቀነሰ ሲመጣ ግብሩ ለለቅሶና ለእንባ እየዬነት ብቻ ነበር፡፡ እንደዛሬው ከሁሉም ሳይጣላ በፊት፡፡ በጥንቱ ዘመን፤ በተለይ በ1880ዎቹ በኢትዮጵያ፤ ከሰሜን ሸዋ አካባቢ በዛወርቅና ፍትግ የተባሉ ሁለት የሙሾ ጠቢባን ስለመኖራቸው ይነገራል፡፡

ከ1880-84 በነበረው ከባድ ድርቅ፤ ሰውና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ከብቶችም ያለቁበት ነበርና በየገበያው ሁሉ እየዞሩ ይሄን ሙሾ ያወርዱት ነበር። በቅርብ ርቀት ካሉት፤ የሙሾ ግጥምን በመጠቀም ደረጃ ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህንን የሚስተካከል የለም። ቢገባን ሙሾ የኋላ ቀርነት መገለጫ ተድርጎ የሚጣል አልነበረም፡፡ ከኋላ ሆነን የፊቱን ለማየት የተሳነንስ እኛው ነን፡፡ ድሮም ሆነ ዘንድሮ ኋላ ቀርነት ነው ብለው የሚሟገቱ ሰዎች የሚያነሱት ነጥብ ቢኖር “ሀዘንን እያባባሰ፤ ለጉዳት ይዳርጋል” የሚል ነው፡፡ ምርትና ግርዱን ካለየን ስንዴም ቢሆን ለመብላት የሚሆን አይደለም፡፡ የመጀመሪያው ስህተት ሙሾ ለሀዘን ብቻ የምንጠቀመው የሀዘን መወጣጫ አድርጎ ማሰቡ ነው። ሁለተኛው ስህተት ደግሞ፤ በትልቁ ነጭ ወረቀት ላይ ያለውን ትንሽ ጥቁር ነጠብ ተመልክቶ፤ ትንሹን ስህተት ከማረም ይልቅ፤ ትልቁን የጥበብ ብራና መቅደዱ ነው፡፡

ኪነ ጥበባዊ ፋይዳውን ትተን በሀዘን ቤት ስላለው ጠቀሜታ ብንመለከት እንኳን፤ ከጉዳቱ ጥቅሙ የሚያመዝንባቸው ሁኔታዎችም አሉ፡፡ በሞት ዳፋ ወደ መሪር ሀዘን ገብቶ በእንባ ማልቀሱ ይህ የማይሻር የሰው ልጆች ባህሪ ነው፡፡ በእንደነዚህ አይነት ከባድ ሁኔታዎች ውስጥ ሆኖ በአግባቡ ማልቀሱን፤ ተፈጥሮም ሆነ ሳይንሱ የሚመክሩት ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም እንባ የታመቀውን ውስጣዊ የሀዘን ክምችት የመበተንና ቀለል እንዲለን የማድረግ ኃይል ስላለው ነው፡፡ “አልቅስና ይውጣልህ” የምንለውም ለዚሁ ነው፡፡

መሆን የሌለባቸው፤ ደረት መደለቁና ከመሬት ላይ መፍረጡ እንዳሉ ሆነው፤ የሙሾ ግጥምና ዜማዎች ልብን የሚነኩ እንደሞሆናቸው፤ ለዘለዓለሙ ባይሆንም የሀዘንተኛውን የልብ ሸክም በእንባ ታጥቦ እንዲወጣ ያደርጋሉ፡፡ የውዳሴና የምስጋና እንዲሁም ሟችን ህያው የሚያደርጉ ልዩ ልዩ ስንኞችም ይኖሩታልና። በተቃራኒው ደግሞ የመጽናናትን ኃይልና ብርታት ይሰጣሉ፡፡ ሙሾን የኋላ ቀርነት መገለጫ ካደረግነው፤ ይሄ ሁላችንንም የሚያስማማ ሳይሆን የሚያጋጭ ነው። በእርግጥ ሁላችንንም ሊያስማማን የሚችል አንድ ነገር ቢኖር፤ በሙሾ አካል ላይ ተለጣፊ ሆነው የገቡት ባዕዳን ግብሮች ናቸው፡፡

የሙሾ ጥበብ ውበትና ጥፍጥናው የሚገኘው ከውስጣዊ የስሜት ቋታችን ነው፡፡ የግጥምና ዜማ ቅኔው ሁሉ የሚሠራው ከስጋችን ጠለቅ ባለው የነብሳችን አድባር ላይ ነው፡፡ እኚህ ባዕዳን ያልናቸው እንደ ደረት መደለቅ፣ ጸጉር መቧጠጥ፣ ሰውነትን መቦጫጨር፣ ከመሬት እየተነሱ መፍረጥ…ስንመለከታቸው አካልን ከመጉዳትን ሌላ የህመም ስሜት ከመጨመር ውጭ ይሄ ነው የሚባል በማስረጃ ሊደገፍ የሚችል እውነታ የላቸውም፡፡ ልንስማማ የምንችለውም በእነዚህ ባዕዳን ግብሮች መቅረት ላይ ነው፡፡

ሙሾ ጥበብ በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች እንደ ባህልና ወጉ በተለየ መንገድ የሚከወን ቢሆንም በተለየ መንገድ የሚነሱ ደግሞ አሉ፡፡ ለአብነትም እንቅስቃሴያዊ የሙሾ ስልትን ድራማዊ በሆነ መንገድ የሚጠቀሙ ሁለት አካባቢዎች የነበሩ መሆናቸው ነው፡፡ የመጀመሪያው ደቡብ ጎንደር አካባቢ ነው። ሟች ወንድ በሚሆንበት ጊዜ መጠኑ ከፍ ያለ ይሁን እንጂ በሴቶቹም አለ፡፡ ፉከራው፤ ሽለላው፤ የግጥምና ዜማው እንጉርጉሮ፤ በአጠቃላይ በአንድ መራሄ ተውኔት ተዘጋጅቶ የቀረበ እንጂ ባላገሩ እዚያው በዚያው ባህላዊውን ግብሩን እየከወነ ያለ አይመስልም። ሌላኛውና ሁለተኛው የሙሾ ድራማዊ ስልት ወደ ጉራጌ ዞን የሶዶ ክስታኔ ማህበረሰብ ይወስደናል፡፡ በማህበረሰቡ ለረዥም ዘመናት ጠንከር ያለ የባህል ልማዶች ከሚከወንባቸው ስፍራዎች አንደኛው የለቅሶ ሥርዓት ነው፡፡

እንቅስቃሴያዊውን የሀዘን መግለጫ ሥርዓታ ቸውን ስንመለከት ድራማዊ የኬሮግራፊ እንቅስቃሴን እናስተውልበታለን፡፡ የሟች ዘመድ አዝማድ በተለይም ሴቶቹ በአንድ ቦታ ላይ ሰብሰብ ብለው ይቆማሉ። በመሀላቸው ከበሮ ይዛ የምትቆመዋ ሴት ከበሮውን እየደለቀች፤ ግጥሙን እያወጣች፤ በሀዘን ቅላጼ ሙሾውን ታወርደዋለች፡፡ በዚህ ጊዜም ወንዶቹ፤ ከሴቶቹ በሌላ አቅጣጫ ወይንም በስተኋላ፤ በሦስት አሊያም በሁለት እረድፍ ተሰልፈው በመቆም በእኩል እንቅስቃሴ ወደፊትና ወደኋላ እያሉ ሀዘናቸውን ይገልጻሉ፡፡ እንደነዚህ አይነቶቹ የሙሾ ሥርዓቶች፤ በሀዘን የሚገነፍለውን ውስጣዊውን ስሜታችንን ሰከን የሚያደርጉ በመሆናቸው፤ በኃይል እራስን የመጉዳት አደጋዎችን ይቀንሳሉ፡፡ እንግዲህ በዋናነት የሚታወቁበት አካባቢዎች እንዳሉ ሆነው፤ በየትኛውም የሀገራችን ክፍል ጥበብን ያላዘለ የሙሾ ሥርዓት ነበር ለማለት ያዳግታል፡፡ ሁሉም ግን አሁን ከመኖር ወደ አለመኖር ተሸጋግረዋል፡፡ እንዴት ያለውን ጥበብ ይዘው፤ እንዴት እንደጣሉት እነርሱም ሳይገባቸው ሹልክ ብሎ ወጥቷል፡፡

ከሁሉ አስቀድሞ በመጀመሪያ፤ ይህ ታላቅ ጥበብ በቀደመው ዘመን በሁሉም እጅ የነበረ እንቁ ነበር፡፡ ማኅበረሰቡም አዘውትሮ በየዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው ሁሉ ይጠቀመው ነበር፡፡ ከኛ ቀደም ብለው በነበሩት ትውልዶች እየተቀዛቀዘ ሄደ፡፡ የቀድሞ ወጉን እያጣ መጣ፡፡ በኛ ትውልድ መጀመሪያና በእነርሱ መጨረሻ ደግሞ የሁሉም መሆኑ ቀርቶ ለጥቂቶች የተሰጠ ተሰጥኦ ተደርጎ ተቆጠረ፡፡ በእጃቸው የቀረው እነዚህ ጥቂት ባለተሰጥኦዎች ወደ ሙያነት ቀየሩት፡፡ ሙሾ አውራጅ፤ አስለቃሽ እየተባሉ በዚሁ የታወቁና ተፈላጊ የነበሩ ምርጥ አስለቃሾችም ታይተውበታል።

ሙያና ሥራዬ ብለው በዚህ ብቻ ቤተሰቦቻቸውን ሲያስተዳድሩ የነበሩ ብዙ ናቸው፡፡ በሠርጉ ጊዜ አቧራ የሚያስጨሱ፤ አሉ የተባሉ አጫፋሪዎች እንደሚፈለጉ ሁሉ፤ በሀዘኑም ወቅት አስለቃሽ ሙሾ አውራጆችን መፈለጉ ተለመደ፡፡ በተለይ ደግሞ ታላላቆቹ ሲሞቱ። ሳር ቅጠሉንም እየያዘ፤ እንደምንም ሲፍገመገም ከዚህኛው ጊዜና ትውልድ ላይ ሲደርስ ግን፤ ‘አንተ ኋላ ቀር‘ በሚል ዱላ ቋንጃውን ተመቶ በአፍጢሙ ወደቀ። የተመታው እንዳይድን እንዳይሽር ተደርጎ ቢሆንም ስለመሞቱ ግን…

ሙሾ ትልቅ ጥበብ ስለመሆኑ የሚያከራክር አይደለም፡፡ ሙሾ ግን ዛሬም በሕይወት አለ ወይ? የሚለው ጥያቄ ከማከራከሩም ለፍርድም የማያመች ነገር ነው፡፡ የለም እንዳንል መልኩን እየቀያየር በሌሎች የጥበብ ሥራዎች ውስጥ እንደማጣፈጫ ሆኖ ሲገባ እናየዋለን፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከደራሲያኑ፤ ከሙዚቀኞቹ፤ ከፊልምና ቲያትረኞቹ ቤት አልፎ አልፎም ቢሆን ጎራ ሲል ይስተዋላል፡፡ እንደ ጥለት ማሳመሪያ የሚገቡት እነዚህ ቅንጭብጭብ የሙሾ ክሮች መደወራቸው መልካም ሆኖ ሳለ፤ እራሱን ችሎ እንዲታይ አለመደረጉ ግን በደል ነው፡፡ ደግሞ እግር ጥሎን ድንገት፤ ከአንድ አካባቢ በአንድ አጋጣሚ እንመለከተዋለን።

በእንጉርጉሮ የዜማ ስልቶች ውስጥም ብቅ ጥልቅ ሲል ማየቱ የተለመደ ነው፡፡ ለዛሬው መኖሩ ዋስትና ባይሆኑም፤ በድሮው ጊዜ የነበሩና አሁንም ድረስ ተጽፈው የሚገኙ እጅግ በርካታ የሙሾ ጥበቦችም አሉ፡፡ ነገር ግን አንድ ነገር ስለመኖሩ የሚታወቀው ስለነበረ ሳይሆን ዛሬም በአደባባይ ሲከወንና ሲተገበር ስናይ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ዛሬ ላይ የለም፡፡ የእውነትም ሞቶ ከሆነ ግን ጥበብ ስለመሆኑ አምነን ተቀብለን የሚገባውንም ጥበባዊ እውቅና ሳንሰጠው በመሆኑ ሀዘኑ በእንባም የሚወጣ አይደለም፡፡ የጥበብ የልብ ስብራትም የሚጠገን አይሆንም፡፡

ለስንቱ ስታለቅስ እንዳልኖርክ አሁን ላንተ የሚያለቅስ ጠፋ? ከዚህ ሁሉ ሰው እንዴት ላንተ የሚሆን፤ ለሙሾ ሙሾ እናውርድ የሚል ሙሾ አውራጅ…ግጥሙን ከዜማው አድርጎ የሚያንጎራጉርልህንስ አጣህ? ቅኔውን እየዘረፈ የሚያበላህስ? ኸረ እንዲያው ሌላውን ሁሉ ተወውና፤ የሚያስታውስህስ ይኖር ይሆን? አይ ሙሾ ምስኪኑ!…ብኩን ጥበቡ፡፡

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን መጋቢት 19/2016 ዓ.ም

Recommended For You