በገበያ ትስስር የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት የማሳደግ ጥረት

የኢንዱስትሪ ፓርኮች (Industrial Parks) ልማት የኢትዮጵያን መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግርን እውን ለማድረግ አስተዋፅዖ ይኖራቸዋል ተብለው ትኩረት ከተሰጣቸው ተግባራት መካከል አንዱ ነው። የኢንዱስትሪ ፓርኮች የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የመሳብ፣ የሥራ እድል ፈጠራን የማስፋት እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን እውን የማድረግ ዋና ዋና መሰረታዊ ተልዕኮዎች አሏቸው። ፓርኮቹ በሚገነቡባቸው አካባቢዎች ለሚኖረው የኅብረተሰብ ክፍል ስራ በመፍጠርና ከአካባቢ ጋር ተስማሚ የሆነ የሥራ ከባቢ እውን በማድረግ ለሀገራዊ የምጣኔ ሀብት እድገት ትልቅ አስተዋፅዖ ይኖራቸዋል፡፡

በተለይም የግብርና ውጤቶችን እሴት በመጨመር በብዛትና በጥራት ተወዳዳሪ የማድረግ አቅም እንዳላቸው የታመነባቸው የተቀናጁ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ((Integrated Agro-Industry Parks)፣ የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግርን ያሳካሉ ከተባሉ የኢንዱስትሪ ፓርክ ዘርፎች መካከል በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ የአግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለአርሶ አደሮች የግብይት ሰንሰለቱን ቀላል በማድረግ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የገበያ ትስስር ይፈጥራሉ፡፡ ባለሀብቶች የግብርና ግብዓቶችን ከአርሶ አደሮች እንዲቀበሉ በማድረግ አርሶ አደሮች የልፋታቸውን ያህል እንዲጠቀሙ አወንታዊ አስተዋፅዖ ያበረክታሉ፡፡

መንግሥት አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለመገንባት እስካሁን ድረስ ከ30 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉንና ይህ ወጪ ባለሀብቶች በፓርኮቹ ውስጥ ገብተው በምርት ስራዎች ላይ እንዲሰማሩ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ለሚያስችሉ ስራዎች የዋለ እንደሆነ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

የሲዳማ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተገነቡና የመሰረተ ልማት አገልግሎት ተሟልቶላቸው ወደ ስራ ከገቡት የተቀናጁ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል አንዱ የሆነውና በሀገሪቱ ከሚገኙ የአግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል ቀድሞ ወደ ስራ የገባው የይርጋለም የተቀናጀ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ ለአርሶ አደሮች የገበያ ትስስር እድል በመፍጠር ለአግሮ-ኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች፣ እድገት ምቹ ሁኔታ ከሚፈጥሩ እድሎችና ግብዓቶች መካከል አንዱ ሆኗል፡፡

በሲዳማ ክልል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን፣ ፈቃድና መረጃ ዳይሬክተር አቶ ታሪኩ ሮባ እንደሚገልፁት፣ በአሁኑ ወቅት ከ25 በላይ አልሚዎች ከሲዳማ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር ውል ፈፅመው ወደ ፓርኩ ገብተው ለማምረት በተለያየ የትግበራ/ስራ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡ ኩባንያዎቹ በመደበኛ ምርት፣ በሙከራ ምርት እንዲሁም በማሽን ተከላ ላይ ይገኛሉ፡፡ አምራች ድርጅቶቹ በአቮካዶ፣ በማንጎ፣ በእንጆሪ፣ በቡና፣ በማር፣ በወተት፣ በስጋ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በአኩሪ አተርና በሌሎች ምርቶች ማቀነባበር ተግባራት ላይ የተሰማሩ ናቸው፡፡

በሙሉ አቅማቸው እየሰሩ ከሚገኙት ኩባንያዎች፤ የአቮካዶ ዘይት በማቀነባበር ለውጭ ገበያ፣ ወተት እና የተለያዩ የፍራፍሬ ጭማቂዎችን በማቀነባበር ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እንዲሁም የማር ምርትን ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚያቀርቡት አምራቾች ናቸው፡፡ ምርቶቹን ለሀገር ውስጥ ገበያ ከማቅረብ በተጨማሪ ወደ ውጭ ለመላክ በተደረገ ጥረት አበረታች ውጤት ተገኝቷል፡፡

የይርጋለም የተቀናጀ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርክ ለምርት የሚያገለግለውን የጥሬ እቃ አቅርቦቱን የሚያገኘው ከአካባቢው ማኅበረሰብ ነው፡፡ የአካባቢው አርሶ አደሮች የገበያ ትስስር ተፈጥሮላቸዋል፡፡ ፓርኩ ስድስት (በሲዳማ ክልል ሦስት እና በጌዴኦ ዞን ሦስት) የገጠር ሽግግር ማዕከላት አሉት፡፡ ከእነዚህም መካከል አርሶ አደሮች በበንሳ ዳዬ፣ አለታ ወንዶ እና ሞሮቾ አካባቢዎች በሚገኙት ማዕከላት እና በኅብረት ስራ ማኅበራት በኩል የአቮካዶ፣ የማር፣ የወተት፣ የቡናና ሌሎች የግብርና ምርቶችን በፓርኩ ውስጥ ለተሰማሩ አልሚዎች እያቀረቡ ነው፡፡

የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የማር እንዲሁም የወተት ምርት የሚያቀርቡ ማኅበራት ግብዓቶችን የሚሰበስቡት በገጠር የሽግግር ማዕከላቱ በኩል ነው፡፡ ፓርኩ ግብአቶችን በማቅረብ የገበያ ትስስርና የገቢ ምንጭ ከፈጠረላቸው አርሶ አደሮች በተጨማሪ በየዓመቱ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል ፈጥሯል፡፡ ይህ ተግባር የሥራ እድል የመፍጠር፣ የውጭ ምንዛሬ ወጪን የማስቀረትና ገቢ ምርችን የመተካት ድርብርብ ዓላማዎች አሉት፡፡

ከዚህ ቀደም አርሶ አደሮች አቮካዶ ለነጋዴዎች ሲሸጡ በዝቅተኛ ዋጋ ያቀርቡ እንደነበር አቶ ታሪኩ አስታውሰው፣ ግብዓቱን በቀጥታ ለፓርኩ አምራቾች ሲያቀርቡ ግን የተሻለ ገቢ ማግኘት እንደቻሉ ያስረዳሉ፡፡ ከሦስት ዓመታት በፊት ትልቅ ገበያ ያልነበረው የአቮካዶ ምርት በአሁኑ ወቅት ደረጃ ወጥቶለት አርሶ አደሩ ምርት በስፋት እያቀረበ፣ ገቢ እያገኘና አዳዲስ ዝርያዎችን እያለማ ነው፡፡ ፓርኩ አርሶ አደሩ ጥሬ እቃን በብዛትና በጥራት እንዲያቀርብ እድል እየፈጠረ ነው፡፡ ይህም የግብርና ምርታማነት እንዲጨምርና የአርሶ አደሩ ሕይወት እንዲሻሻል እያደረገ ነው፡፡

አርሶ አደሮች በፓርኩ ውስጥ ለተሰማሩ አምራቾች ግብዓት አቅርበው ተጠቃሚ ከመሆናቸው ባሻገር የአቅም ግንባታ ድጋፎችንም ያገኛሉ፡፡ በፓርኩ ውስጥ የተሰማሩ ባለሃብቶች ግብዓቶችን ከየአካባቢው ሲሰበስቡ ለአርሶ አደሮች ስልጠናዎችን ይሰጣሉ፡፡ እነዚህ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎች ግብዓቶች በጥራት እንዲቀርቡና ምርታማነት እንዲጨምር እገዛ ያደርጋሉ፡፡ ስለሆነም ፓርኩ የግብዓቶችን ጥራት በማሻሻል ምርታማነት እንዲጨምር ትልቅ አስተዋፅዖ እያበረከተ ይገኛል፡፡

በአጠቃላይ በፓርኩ ዙሪያ ያሉ አካባቢዎች ለፓርኩ ግብዓት የማቅረብ አቅም ያላቸው በመሆኑ፣ በፓርኩ ውስጥ የሚከናወኑ የኢንቨስትመንት ተግባራት ለአርሶ አደሮች የገበያ ትስስርም ሆነ የስራ እድል በመፍጠር የአካባቢውን ኅብረተሰብ ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ናቸው፡፡ ስለሆነም ባለሀብቶች ወደ ይርጋለም የተቀናጀ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርክ ገብተው እንዲያለሙ የሚከናወኑት የፕሮሞሽን፣ የአገልግሎት አሰጣጥና የክትትል ተግባራት በልዩ ትኩረት የሚከናወኑ ይሆናሉ፡፡

በሚያዝያ ወር 2013 ዓ.ም በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የተመረቀው በኦሮሚያ ክልል፣ ምስራቅ ሸዋ ዞን፣ አዳሚ ቱሉ ጂዶ ኮምቦልቻ ወረዳ፣ ከባቱ ከተማ በ16 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የ‹‹ቡልቡላ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ›› የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የወተት፣ የማር፣ የስጋና የእንቁላል ምርቶችን የሚያቀነባብሩ አምራቾች የሚሰማሩበት የኢንዱስትሪ ፓርክ ነው፡፡

በኦሮሚያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ጌታሁን አዱኛ እንደሚናገሩት፣ የቡልቡላ የተቀናጀ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርክ ባለሀብቶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ ባከናወናቸው ተግባራት ፈቃድ የወሰዱ 29 ኩባንያዎች ወደ ፓርኩ ገብተው በግብርና ምርቶች ማቀነባበር ስራ ላይ ለመሰማራት የሚያስችሏቸውን የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡ ባለሀብቶቹ የሚሰማሩባቸው የአግሮ-ፕሮሰሲንግ (ግብርና ማቀነባበር) ዘርፎች የማርና ሰም፣ የምግብ ዘይት፣ የአትክልትና ፍራፍሬ (ቲማቲም፣ ድንች፣ ጭማቂ… )፣ የቡና፣ የአቮካዶ ዘይት፣ የስጋ፣ የወተት፣ የእንስሳት መኖ፣ የፓስታና ማካሮኒ፣ የሕፃናት ምግቦች ማምረትና ማቀነባበር ስራዎች ናቸው፡፡

ወደ ፓርኩ ከገቡት ኩባንያዎች መካከል ‹‹ሸካ ኖርዲክ›› ኩባንያ በማርና ሰም እንዲሁም ‹‹ቲኬ ግሩፕ›› (TK Group) በምግብ ዘይት ማቀነባበርና ማምረት ላይ ተሰማርተው የሙከራ ምርት ጀምረዋል፡፡ ‹‹ቲኬ ግሩፕ›› የተባለው ኩባንያ ሰባት የምርት ዓይነቶችን ለማምረትና ለማቀነባበር ከኦሮሚያ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር ስምምነት የፈፀመ ድርጅት ነው፡፡

ሌሎቹ ድርጅቶች ደግሞ መሬት ተረክበው የባንክ ብድር ለማግኘት እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ አንዳንዶቹም የባንክ ብድር ተፈቅዶላቸው ማሽን ማስገባት ጀምረዋል፡፡ ለአብነት ያህል መንግሥት ለናሙና ወደገነባቸው ስድስት ሼዶች ውስጥ ከገቡት አምራቾች መካከል ሁለቱ የብድር ፈቃድ ሂደቶችን አጠናቅቀው ማሽኖችን እያስገቡ ይገኛሉ። ወደ ፓርኩ ገብተው ስራ ለመጀመር ፈቃድ ከወሰዱት ባለሃብቶች መካከል አብዛኞቹ የሃገር ውስጥ ባለሃብቶች መሆናቸውንም አቶ ጌታሁን ይናገራሉ፡፡

እንደ አቶ ጌታሁን ገለፃ፣ ከፓርኩ ጋር ትስስር ያላቸውና ግንባታቸው የተጠናቀቀ ስድስት የገጠር ሽግግር ማዕከላት ያሉ ሲሆን፤ የማዕከላቱ ዋና ተግባር የአርሶ አደሩን ምርት በጥራትና በብዛት ሰብስቦ ለፓርኩ አምራቾች ማቅረብ ነው። ወደ ፓርኩ የሚገቡት ባለሀብቶች ከሽግግር ማዕከላቱ ጋር በሚፈጥሩት ትስስር አርሶ አደሩን ጨምሮ የአካባቢው ኅብረተሰብ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ በሻሸመኔ፣ መቂ፣ ዶዶላ፣ ባሌ ሮቤ፣ ኢተያ እና ኦለንጪቲ የሚገኙት እነዚህ ማዕከላት ግንባታቸው ተጠናቆ መሰረተ ልማቶችን (ውሃ፣ መብራት፣ መንገድ…) የማሟላት ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ የሁሉንም ማዕከላት ግንባታና የመሰረተ ልማት አቅርቦት ስራዎች በፍጥነት ለማጠናቀቅ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል፡፡

የቡልቡላ የተቀናጀ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርክ የግብርና ውጤቶችን በማቀነባበር ላይ አተኩሮ የሚሰራ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዚህ ሂደት ለፓርኩ ምርቶች የግብርና ግብዓቶችን የሚያቀርቡ በግብርና ስራ ላይ የተሰማሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ይጠበቃል። ፓርኩ በማር፣ በስጋ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በዘይትና በጥራጥሬ ማቀነባበር የሚሰማሩ ባለሀብቶች የሚገቡበት በመሆኑ አርሶ አደሮች ለአምራቾቹ ግብዓት በማቅረብ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡

የፓርኩ ግንባታ ብዙ የሰው ኃይልና ግብዓት የሚፈልግ ስለነበር፣ በፓርኩ ግንባታ ወቅት በርካታ የአካባቢው ኅብረተሰብ ተጠቃሚ እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ ጌታሁን፣ አምራቾች ስራ ሲጀምሩ የአካባቢው አርሶ አደሮች ለፓርኩ የግብርና ግብዓቶችን በማቅረብ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ፓርኩ በጥናት ላይ ተመስርቶ ሲገነባ ያስገኛል ተብሎ የታሰበው ዋና ጥቅም የአርሶ አደሩን ምርት በጥራትን በመጠን በመጨመር እንዲሁም የገበያ እድል በመፍጠር አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረግ ነው፡፡ አሁን ባለሃብቶች ገና ወደ ፓርኩ ለመግባት በዝግጅት ላይ በመሆናቸው ስለአርሶ አደሩ ሰፊ ተጠቃሚነት ለመናገር ጊዜው ገና ነው፡፡ በምግብ ዘይት ምርት የሙከራ ምርት የጀመረው ‹‹ቲኬ ግሩፕ›› ዘይት የሚያመርተው ከአኩሪ አተር ስለሆነ ግብዓቱን (አኩሪ አተር) እየሰበሰበ ይገኛል፤ አኩሪ አተር አምራች አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እየሆኑ ነው›› ይላሉ፡፡

በተጨማሪም ‹‹የቡልቡላ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ የግብርውን ዘርፍ ለማሳደግ ታልሞ የተገነባ በመሆኑ የሚጠቀመው ግብዓት የሀገር ውስጥ የግብርና ምርቶችን ነው፡፡ በፓርኩ አካባቢ ያለው ማኅበረሰብ አርሶ አደር ነው። የፓርኩ አምራቾች የሚጠቀሙት ጥሬ እቃ የአካባቢውን የግብርና ምርት ነው፡፡ አርሶ አደሩ ግብርናውን በማዘመንና አምራችነቱን በመጨመር ለምግብና ለገበያ ከሚያውለው ምርት በተጨማሪ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆን ትርፍ ምርት እንዲያመርት እየተሰራ ነው፡፡ በቀጣይ አምራቾች በማር፣ በስጋ፣ በዶሮ፣ በወተት፣ በጥራጥሬ፣ በዘይትና በሌሎች ዘርፎች ወደ ስራ ሲገቡ አርሶ አደሩ ይበልጥ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት የአካባቢው ኅብረተሰብ የገበያ እድል እንዲያገኝም ያደርጋል›› በማለት ፓርኩ ለአካባቢው ኅብረተሰብ ተጠቃሚነት ያለውን ፋይዳ ያስረዳሉ፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ከልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አክሊሉ ታደሰ በበኩላቸው፣ በተቀናጁ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት የተከናወኑ ተግባራት ከአርሶ አደሮች ጋር ያለውን ትስስር በማሻሻል አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እንዲሆን ስለማስቻላቸው ያብራራሉ፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በተገነቡባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ በርካታ አርሶ አደሮች ምርቶቻቸውን በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ገብተው ለሚያለሙ ድርጅቶች በማቅረብ የተሻለ የገበያ ጥቅምና የአቅም ግንባታ ድጋፍ እያገኙ ነው፡፡

ለአብነት ያህል ጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ከአቮካዶ ዘይት የሚያመርተው ‹‹አክሻይ ጄይ›› ኩባንያ (Akshay Jay Oil) ከአካባቢው አርሶ አደሮች ጋር ስምምነት ፈፅሞ ምርታቸውን ይቀበላል፡፡ ቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የቢራ ብቅል የሚያመርተው ‹‹ሱፍሌ ማልት ኢትዮጵያ›› ፋብሪካ (Soufflet Malt Ethiopia) ከ70ሺ በላይ ከሚሆኑ የአርሲና የባሌ አካባቢ አርሶ አደሮች ጋር ትስስር ፈጥሮ እየሰራ ይገኛል፡፡ ወደ ደብረ ብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክ የገባው ‹‹ቡርትማልት›› ኩባንያ (BOORTMALT) ደግሞ ከ50ሺ በላይ ከሚሆኑ የአካባቢው አርሶ አደሮች ጋር የገበያ ትስስር ፈጥሯል፡፡

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን መጋቢት 19/2016 ዓ.ም

Recommended For You