ዩኒቨርሲቲው ለግዢ ያወጣውን 163 ሚሊዮን ብር ማወራረድ እንደሚጠበቅበት ማሳሰቢያ ተሰጠው

አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ባለፉት ዓመታት ለግዢ ሠራተኞች እና ለእቃ አቅራቢዎች የከፈለውን ከ163 ሚሊዮን ብር በላይ በአስቸኳይ እንዲያወራርድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

ቋሚ ኮሚቴው የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የ2014 በጀት ዓመት የፋይናንስ ሕጋዊነት ኦዲት ሪፖርትን በትናንትናው እለት ገምግሟል።

በግምገማው ዩኒቨርስቲው ግዢ የፈጸመባቸው በርካታ ንብረቶች ቢኖሩም የግዢ ጨረታ ሰነድ አቅርቦ ሂሳብ አለማወራረዱ ተነስቷል። በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው በንብረት አያያዝና አመዘጋገብ እንዲሁም በስፖንሰርሺፕ የሚያስተምራቸው መምህራንን በገቡት ውል መሠረት መክፈል ያለባቸውን ክፍያ አለመፈጸማቸውን በኦዲት ሪፖርቱ ተመላክቷል።

በወቅቱ የቋሚ ኮሚቴው ዋና ሰብሳቢ የሺእመቤት ደምሴ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ዩኒቨርስቲው ከኦዲት ግኝቱ በኋላ በድርጊት መርሐ ግብሩ የግዢ ሰነድ ማቅረብ ችሏል። ሆኖም ሰነድ ከማቅረብ ባለፈ ለዕቃ አቅራቢዎች የተሰጠ 163 ሚሊዮን 70 ሺህ 630 ብር እንዲሁም ለግዢ ሠራተኞች የተሰጠ 882 ሺህ 886 ብር በአስቸኳይ ሊወራረድ ይገባል።

ማወራረድ የማይቻለውን ገንዘብም ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመሆን ጉዳዩ እልባት እንዲያገኝ ዩኒቨርስቲው መሥራት ይኖርበታል ያሉት ሰብሳቢዋ፤ የግዢ ጨረታ ሰነድ የተሰበሰበላቸው ጉዳዮችን ሂሳባቸውን በማወራረድ እስከ ግንቦት 30 ቀን ለዋና ኦዲተር ማቅረብ እንደሚገባው አሳስበዋል።

ሰብሳቢዋ፤ ከመምህራን ጋር በተገባ ውል መሠረት ዩኒቨርሲቲው በ2013፣ 2012 እና 2011 ዓ.ም ስምንት ሚሊዮን 359 ሺህ 744 ብር ያልሰበሰበው ገንዘብ እንዳለ በኦዲት ሪፖርቱ መመላከቱን ገልጸው፤ ዩኒቨርስቲው ይህን ገንዘብም በአስቸኳይ ሰብስቦ ወደ ካዝና ማስገባት አለበት ሲሉ አሳስበዋል።

ዩኒቨርሲቲው በንብረት አያያዝና አመዘጋገብ ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት እንዳለበት አመልክተው፤ በተለይም በወቅቱ ጥቅም ላይ መዋል የነበረባቸው 114 ቶነሮች ጊዜ ያለፈባቸው በመሆኑ ሊወገዱ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ወይዘሮ መሠረት ዳምጤ እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲው የኦዲት ግኝት አስተያየት መነሻ በማድረግ የሠራቸው ሥራዎች ለሌሎች ተቋማት አስተማሪ የሚሆኑ ናቸው። ብዙዎቹ የኦዲት ግኝቶች ላይ ዩኒቨርሰቲው የግዢ ሰነዶችን በማሟላት ማቅረብ ችሏል ብለዋል።

ዩኒቨርስቲው ከኦዲት ግኝቱ በኋላ የንብረት አያያዝና አመዘጋገብ ላይ የሠራው ሥራ ግን አናሳ ነው ያሉት ዋና ኦዲተሯ ፤ በተለይም የሚሠሩና የማይሠሩ ቶነሮች በአንድ ላይ የተቀመጡ በመሆናቸው ዩኒቨርስቲው ይህን በመለየት መወገድ ያለባቸውን ማስወገድ ይኖርበታል ሲሉ አሳስበዋል።

የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ደረጀ እንግዳ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የተፈጸሙ ግዢዎች በ2006 ዓ.ም መከናወናቸውን ገልጸው፤ ሆኖም ይህ ግዢ እንዳልተወራረደ ዩኒቨርሲቲው በተረዳ ጊዜ ኮሚቴ አዋቅሮ የግዢ ጨረታ ሰነዱን በማሟላት በአሁኑ ጊዜ ለዋና ኦዲተር ማቅረብ ተችሏል ብለዋል።

መምህራን መክፈል ያለባቸውን ክፍያ በተመለከተም እስካሁን 60 ሺህ ብር ተመላሽ ማድረግ ተችሏል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ቀሪዎቹን ለማስመለስ በሕግ ሂደት ላይ እንገኛለን ሲሉ ገልጸዋል።

ፕሬዚዳንቱ፤ በግምጃ ቤት የሚገበኙ ጊዜያቸው ያለፈባቸውን ቶነሮች አሁን ላይ እየተወገዱ እንደሚገኙ ገልጸው፤ ሌሎች የዩኒቨርስቲውን ንብረቶች ለመቆጣጠርም ሲስተም ዘርግተን እየሠራን ነው ሲሉ ለቋሚ ኮሚቴው አብራርተዋል።

ዳግማዊት አበበ

አዲስ ዘመን መጋቢት 19/2016 ዓ.ም

Recommended For You