«በዞናችን ያሉ አነስተኛ ከተሞች ሁሉ ከወንጪ ደንዲ ፕሮጀክት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንፈልጋለን» አቶ ቶሎሳ ተረፈ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ

በኦሮሚያ ክልል የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ዞኑ በገበታ ለሀገር መርሃ ግብር ውስጥ ከተካተቱ እና በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ተገንብተው ለምረቃ ከበቁ ፕሮጀክቶች አንዱ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትም አገልግሎት መስጠት ስለጀመረው ፕሮጀክት እና በዞኑ ስላሉ የልማት እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ስራዎች ከደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ከሆኑት ከአቶ ቶሎሳ ተረፈ ጋር ቆይታ አድርጓል፤ መልካም ንባብ፡፡

አዲስ ዘመን፡- የዞኑን ማኅበረሰብን ተጠቃሚ በማድረግ በኩል የተሰራው የልማት እንቅስቃሴ እና የጸጥታ ሁኔታ እንዴት ይገለጻል?

አቶ ቶሎሳ፡– የአስተዳደሩ ጽህፈት ቤት ከአዲስ አበባ በ114 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ነው፡፡ በዞናችን 12 ወረዳ እና 316 ቀበሌዎች ይገኛሉ፡፡ እንዲያም ሆኖ በእነዚህ ሁሉ ወረዳዎች እና ቀበሌዎች ወደ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ማኅበረሰብ ይኖራል፡፡ በዚህ ውስጥ የተለያዩ የልማት ስራዎች፣ የጸጥታ ሁኔታ እና የመሰረተ ልማት ስራዎች በመሰራት ላይ ናቸው፡፡

በዚህ ጊዜ አንዳንዴ አነስተኛ የሆኑ የጸጥታ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡ እሱን ለማስተካከል ደግሞ ከጸጥታው አካላት ጋር ሆነን የፖለቲካ አመራሩ አንድ ላይ ተቀናጅቶ የኅብረተሰቡን ሰላም እና ጸጥታ የማስከበር ስራዎች እየተሰሩ ነው፡፡ ሁሉም ወረዳዎች ላይ በአሁኑ ሰዓት የልማት ስራዎች በስፋት እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡ የተለያዩ ፕሮጀክቶችም እየተገነቡ ነው፡፡ ሌላ ቦታ እንደሚወራው የጸጥታ ችግር ሆኖብን ስራ ያቆምንበት ወረዳም ሆነ ቀበሌ በአሁኑ ወቅት የለም፡፡ ከዚህ የተነሳ የተለያዩ ስራዎች በመሰራት ላይ ይገኛሉ፡፡

በዘንድሮ ዓመት ብቻ ማኅብረሰቡ የሚጠቀምበት ወደ 235 የግንባታ ስራዎችን እየሰራን ነው፡፡ ይህንን ፕሮጀክት እየሰራን ያለነው ዘንድሮ ለመጨረስ ነው፡፡ በሌላ በኩል መንግስት የቀረጻቸው የተለያዩ ተነሳሽነቶች አሉ፤ ለምሳሌ አንዱ የበጋ ስንዴ ሲሆን፣ ይህን በስፋት እየሰራንበት ያለ ክንውን ነው፡፡

የበጋ ስንዴ በተለይ ወደ ሰበታ ሃዋስ እና ኢሉ አካባቢ የበጋ ስንዴ በስፋት በኩታ ገጠም ተዘርግቷል፡፡ እሱም በመልማት ላይ ነው። ገበታ ለአገር አካል የሆነው የወንጪ ደንዲ ፕሮጀክት የመጀመሪያው ምዕራፍ አልቆ በጠቅላይ ሚኒስትራችን ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡ ይህ ታላቅ ፕሮጀክት ተመርቆ ለስራ ክፍት መሆኑ የሰላሙንና የጸጥታውን መልካም መሆን ያመላክታል፡፡ ስራችንን አቅደን፣ ጀምረን እና ሰርተን መጨረስ ችለናል ማለት ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከወራት በፊት የተመረቀው የወንጪ ደንዲ ፕሮጀክትን ለመጎብኘት በርካቶች ወደ ዞኑ መምጣታቸው አይቀሬ ነው፤ ይህን ፕሮጀክት ለማየት ለሚመጣው ቱሪስት ከመንገድ እና ከሌሎች መሰረተ ልማት አኳያ ምን ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮለታል?

አቶ ቶሎሳ፡- የወንጪ ደንዲ ገበታ ለአገር ፕሮጀክት የተሰራው በጠቅላይ ሚኒስትራችን ጠንሳሽነት ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት የመጀመሪያው ምዕራፍ ተጠናቅቋል፡፡ እዛ አካባቢ ያለው የውስጥ ለውስጥ መንገድ በሙሉ ተሰርቶ ያለቀ ነው፡፡ በዚህ በተሟሏ አሰራሩ ደግሞ ማኅበረሰቡ በጣም ደስተኛ ሆኗል፡፡

ከፕሮጀክቱ ጋር የሚገናኙ መስመሮች ለምሳሌ መብራት፣ ውሃ ሁሉ የተሰራለት ነው። ሌላው ቀርቶ ከስፍራው ለተነሱ 13 አርሶ አደሮች 150 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት መኖሪያ ቤት ተገንብቶላቸዋል፡፡ መኖሪያ ቤት ብቻ ሳይሆን ሙሉ እቃ ጭምር ተሰጥቷቸዋል፡፡ ስለዚህ እንደ ከዚህ በፊቱ ፕሮጀክት ሲሰራም ሆነ ኢንቨስትመንት ሲመጣ እና ሲሰራ የነበረው አርሶ አደሮችን እያፈናቀለ ነው፡፡ አሁን ግን በወንጪ ደንዲ ፕሮጀክት የተሰራው ቤተ መንግስት ማኅብረሰቡን አቅፎ ነው፡፡

የወንጪ ደንዲ ፕሮጀክት የሆነው ሎጅ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሆኖ የተሰራ ነው፡፡ የአካባቢውም አርሶ አደር፣ የተገነባለት ቤት ከእሱ ጋር የሚመጣጠን ነው፡፡ አርሶ አደሮቹ ራሳቸው ፕሮጀክቱን “የእኔ ነው” ብለው እንዲንከባከቡ የሚያግዝ ነው፡፡ በፕሮጀክቱ ውስጥ እንደ ዞናችን ወደ 839 ስራ አጦች ስራ እንዲያገኙ ተደርገዋል።

በተጨማሪ እንደዞን ለ36 ወጣቶች ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ አድርገን ሳይክል ገዝተን አቅርበንላቸዋል፡፡ በተሰጣቸው ሳይክል በአሁኑ ወቅት የየራሳቸውን ስራ እየሰሩበት ይገኛል፡፡ እግረ መንገዳቸውን ቱሪስቶች ሲመጡ እያከራዩ ስለሆነ ማኅበረሰቡ በጣም ደስተኛ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳም ፕሮጀክቱ የእሱ መሆኑን አውቋል፤ የፕሮጀክቱ መኖርም ተጠቃሚ እያደረገው ይገኛል፡፡

ነገር ግን ያለው ችግር የመንገድ ነው፡፡ እንዲህም ሲባል ችግሩ ከዚህ በፊት ተጀምሮ በነበረው በአምቦ ወሊሶ የአስፓልት መንገድ ነው። ከዚህ በፊት ከወሊሶ ወደ አምቦ ሲሰራ የነበረ ቢሆንም ከሁለትና ሶስት ዓመት በፊት ተቋርጦ ነበር፡፡ ፕሮጀክቱ የፌዴራል መንግስት ሲሆን፣ የሚያሰራው የፌዴራል መንግስት ነው፡፡ ይሁንና እሱ መንገድ እስካሁን አላለቀም፡፡

ከአምቦ እስከ ወንጪ ያለው መንገድ ግን አልቋል፡፡ ይኸኛው ስላላለቀ ኅብረተሰቡ ዘንድ ቅሬታ የፈጠረ ሲሆን፣ ቶሎ እንዲያልቅለትም ይፈልጋል፡፡ ምክንያቱም መንገዱ ከተፈጀመረ ወደ ስምንትና ዘጠነኛ ዓመት አስቆጥሯል፡፡ የወንጪ ደንዲ ፕሮጀክት በተመረቀበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ የመከላከያ ሚኒስትሩ በተለይ የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ ፕሮጀክቱን የሚመሩት እርሳቸው ስለሆኑ ባለፈው ፕሮጀክቱ የወንጪ ደንዲ ፕሮጀክት አካል ሆኖ መንገዱ ቶሎ እንዲያልቅ አቅጣጫ አስቀምጠዋል። በዚህ አግባብ ሚኒስትሩ ጉዳዩን እየተከታተሉት ሲሆን፣ እኛም የኅብረተሰቡ ቅሬታ በነበረው ጉዳይ ላይ ምላሽ ስላገኘን በዚህ ደስተኞች ነን፡፡

አዲስ ዘመን፡- 236 ፕሮጀክቶች በመሰራት ላይ እንደሆኑ ተናግረዋል፤ ምን ምን አይነት ፕሮጀክቶች ናቸው?

አቶ ቶሎሳ፡– ፕሮጀክቶቹ ባለፈው ዓመት ተጀምረው ባለመጠናቀቃቸው ምክንያት ለዘንድሮ የተላለፉ አሉ፤ ዘንድሮ ደግሞ ወደ አንድ መቶ ፕሮጀክቶች በእቅድ ተይዘው እየተተገበሩ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል መንገድ፣ ድልድይ፣ የውሃ ፕሮጀክቶችም የተካተቱበት ነው፡፡

ሌላው ቀርቶ የአስተዳደር ሕንጻም በዚህ ፕሮጀክት ውስጥ የተካተተ ነው፡፡ ይህን ፕሮጀክት ስራ ለማስጀመር ጨረታ ሁሉ ወጥቶ ወደ ስራ መግባት ችለናል፡፡ ይህ የአስተዳደር ሕንጻ ብቻ ባለ አምስት ወለል ሲሆን፣ ወደ 307 ሚሊዮን ያህል ብር ወጪ ተደርጎ የሚገነባ ፕሮጀክት ነው፡፡ ወረዳዎች ራሳቸው በማኅበረሰብ ተሳትፎ፣ በመንግስት በጀት እና መንግስታዊ ባልሆኑ ልማታዊ ድርጅቶች የሚሰሩ ፕሮጀክቶች አሏቸው፡፡ ለአብነት ያህል ትምህርት ቤቶች፣ ውሃ፣ ድልድይ፣ መንገድ እና መሰል ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡

በዚህ ዓመት እናጠናቅቃለን ብለን ያቀድነው 235ቱን ፕሮጀክቶች ሲሆን፣ አጠናቅቀንም ለኅብረተሰቡ አገልግሎት እንዲበቁ ለማድረግ እየሰራን ነው፡፡ በእስካሁኑ ሒደት 26ቱን ፕሮጀክቶች ጨርሰናል፡፡ ይሁንና ፕሮጀክቶቹ የሚመሩት በመርሃግብር እንደመሆናቸው ገና አልተመረቁም፤ ነገር ግን በቅርቡ ለምረቃ የሚበቁ ይሆናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- የወንጪ ደንዲ የአገር ፕሮጀክትም ጭምር ነው፤ ወደዚህ ስፍራ ቱሪስቶች በስፋት ይመጡ ዘንድ በእናንተ በኩል ምን አይነት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ተዘጋጃችሁ? እንደ ዞን ከፕሮጀክቱስ ምን ትጠብቃላችሁ?

አቶ ቶሎሳ፡- በዚህ ፕሮጀክት የወሊሶ ከተማ ብቻ ሳይሆን በዞናችን ውስጥ ያሉ አነስተኛ ከተሞች ሁሉ ከወንጪ ደንዲ ፕሮጀክት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንፈልጋለን፡፡ እየሰራን የምንገኘው ለዚያም ነው፡፡ ልክ ከአዲስ አበባ ሲወጣ ከሰበታ ቀጥሎ ተፍኪ በዞናችን ውስጥ የምትገኝ ከተማ ስትሆን፣ ከዚያ እዚህ ወሊሶ ድረስ እስኪመጣ እና ከወሊሶ አልፎ ደግሞ ጪቱ እስከ ሀሮ ያሉ ከተሞች መስመር ላይ ናቸው፡፡ በዚያኛው በኩልም እስከ አምቦ ድረስ ያሉ ከተሞች መስመር ላይ ናቸው፡፡

ስለዚህ የተነሳው ጥያቄ አግባብነት ያለው ነው፤ ሆቴሎቻችን ለሚመጡ ቱሪስቶች ምቹ ይሆኑ ዘንድ እና ባለሀብቶቻችን እንዲነቃቁ ከአንዴም ሁለቴ የባለሀብቶች ፎረም ፈጥረን ከወሊሶ ከተማ አስተዳደር ጋር በመሆን ስብሰባ አካሂደናል። በተለይ በዞናችን የሚገኘው የምግብም ሆነ የባህል፣ የምግብ እና የአልባሳት በጥቅሉ ዞኑን በአግባቡ የሚገልጹ ነገሮችን እንዴት አድርገን መጠቀም እንዳለብን ወይይት አድርገናል፡፡

ከተሞች ብቻ ሳይሆኑ የትኛውም ቱሪስት ወደዞናችን ሲመጣ በየአካባቢው እና በየደረሰበት እያረፈ እየተዝናና እንዲሁም አርሶ አደሩ ዘንድም እየቆየ መሄድ የሚያስችለውን ሁኔታ ለመፍጠር ነው እየሰራን ያለነው፡፡ ስለሆነም አርሶ አደሮቻችን ባላቸው አቅም ቱሪስቶች ወደመንደራቸው ሲመጡ ሁኔታዎችን ምቹ እንዲያደርጉ በስፋት ተወያይተናል፤ የማነቃቂያ ምክክርም አድርገናል። ስለሆነም የእኛ ነው፤ እንደ አገር የተሰራ ፕሮጀክት ቢሆንም በደንብ ተጠቃሚ መሆን የሚያስችለን እኛን ነው ብለን እናምናለን፡፡

በዞኑ ውስጥ ከሚገኙ 839 ስራ አጦች የስራ እድል የፈጠረ ፕሮጀክት ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፤ ገና በዚህ ፕሮጀክት ከዚያም በላይ እንጠቀምበታለን፡፡ ፕሮጀክቱ ግዙፍ እና የአገርም የእኛም ሀብት እንደመሆኑ ለመጠቀም ዝግጁዎች ነን፡፡ ለምሳሌ የስራ እድሉን በተመለከተ እንደ ዞናችን ያቀድነው በዚህ በ2016 ዓመት 73 ሺ 964 ስራ አጦችን ወደስራ እናስገባለን ብለን ነው።

እስካሁን ካቀድነው ውስጥ ወደስራ ያስገባነው ስራ አጥ 44 ሺ 535 ሲሆን፣ ይህ እስከ ታህሳስ 30 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ያለው አኃዝ ነው፡፡ በዚህም ከእቅዳችን ያሳካነው 60 ነጥብ ሁለት በመቶ ነው፡፡ ይህ ማለት የቋሚ ሰራተኞችን ብቻ የሚመለከት አኃዝ ነው፡፡ ጊዚያዊ የሆኑትን በሪፖርት መልክ አንይዝም፤ ጊዚያዊ የሆኑ ሰራተኞች በብዛት የተቀጠሩ ቢሆንም፤ የተወሰነ ጊዜ ሰርቶ ወዲያው ደግሞ ላይኖር ስለሚችል ቁጥራቸው የሚያካትተው ቋሚ ሰራተኞች ብቻ ነው፡፡ ክልልም ቢሆን የሚወስደው ሪፖርት የቋሚ ሰራተኞችን ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- መንግስት የትምህርት ቤቶች ደረጃ ማሻሻል ላይ እንዲሰራ አቅጣጫ ማስቀመጡ ይታወቃል፣ በዚህ ዞን ከትምህርት ቤት ተደራሽነትና ከደረጃ ማሻሻል ጋር ተያይዞ ምን እየተሰራ ስራ?

አቶ ቶሎሳ፡– በዞናችን ደረጃ መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ በትምህርት ቤት ላይ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ናቸው፡፡ በተለይም በዞናችን ከመዋዕለ ሕጻናት ጀምሮ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ያሉት ከ450 በላይ ትምህርት ቤቶች ናቸው፡፡ ከዚያ ውስጥ 309 ሺ እና ከዚያ በላይ የሆኑ ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ ይገኛሉ፡፡

ይህ ብቻ ሳይሆን የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ መንግስትም ትኩረት ሰጥቶት የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል ስራ እንዲሁም እንደ ኦሮሚያ ክልል ደግሞ ከታች ጀምረን በትውልድ ላይ ካልሰራን አሁን ያለው ትውልድ ትንሽ የትምህርት ጥራት ላይ ችግር እያሳየ በመሆኑ በክልላችን ፕሬዚዳንት አቅጣጫ ተቀምጦ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ነው፡፡

ከዚህ ውስጥ ለአብነት “ቡዑራ ቦሮ” የሚባለውን መርሃ ግብር መተግበር ጀምረናል። በከተሞች አካባቢ በየትምህርት ቤት ውስጥ መዋዕለ ሕጻናት አለ፡፡ የአርሶ አደሩ ልጆች ግን ይህን እድል አያገኙም፡፡ ሰባት ዓመት ሲሞላቸው ቀጥታ ምንም ማንበብ እና መጻፍ ሳይሞክሩ አንደኛ ክፍል ለመግባት ወደ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ይመጣሉ፡፡ በከተማ ውስጥ ያሉ ሕጻናት ደግሞ ገና ከሶስት ዓመታቸው ጀምሮ በመዋዕለ ሕጻናት ውስጥ ከኬጂ ጀምሮ ያለውን ይማራሉ፡፡ በዚህም ውስጥ ፊደል መቁጠሩን ጨርሰው እና ለይተው አንደኛ ክፍል ለመግባት ወደ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ይመጣሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ፈተና የሚሆነው ነገር የአርሶ አደሩን ልጆች እና የከተማን ልጆች አንደኛ ክፍል እኩል አስቀምጦ ማስተማሩ ነው፡፡

ትምህርት ቤት ገብቶ የማያውቅ እና ሶስት ዓመት ሙሉ ስለትምህርት ሁኔታ የሚያውቅ ተማሪ ጋር የአርሶ አደሩን ልጅ ማስቀመጥ ሞራል መንካት በመሆኑ በትምህርታቸውም ወደኋላ እንዲቀሩ የሚያደርግ ነው፡፡ በእርግጥ በርከት ያለው ቁጥር የሚኖረው በገጠሩ ክፍል ነው፡፡ ስለዚህም ይህንን ችግር ለመፍታት “ቡዑራ ቦሩ” የሚባል እንደ ኦሮሚያ ክልል የክልላችን ፕሬዚዳንት አቅጣጫ እንዳስቀመጡት በእያንዳንዱ ትምህርት ቤት ውስጥ መዋዕለ ሕጻናት ራሱን ችሎ ተገንብቶ እንዲከፈት እና በዞናችን ያሉ ሶስት ዓመት የሞላቸው ሕጻናት ልክ እንደከተማ ሕጻናት ሁሉ ወደመዋዕለ ሕጻናት ገብተው የመማር እድሉን እንዲያገኙ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ ናቸው፡፡

ባለፈው ዓመት ብቻ የአርሶ አደሩን ልጆች ተጠቃሚ የሚያደርግ ወደ 221 መዋዕለ ሕጻናት በእያንዳንዱ ቀበሌ መስራት ችለናል፡፡ ዘንድሮ የያዝነው እቅድ ደግሞ ቀሪዎቹን 94 መዋዕለ ሕጻናት እንሰራለን የሚል ነው፡፡ እስካሁን 85ቱን አጠናቅቀን ስራ አስጀምረናል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ400 በላይ በሆኑ ትምህርት ቤቶች ውስጥ መዋዕለ ሕጻናት ተሰርተው አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡

ልክ ከ”ቡዑራ ቦሮ” የሚወጡ ተማሪዎች ወደ አንደኛ ክፍል እንደሚገቡ ሁሉ፤ ከዚያ የሚወጡ የተመረጡ እና ጎበዝ የሆኑ ተማሪዎች ደግሞ ብቃታቸው ታይቶ የስምንተኛ ክፍል ትምህርታቸውን በጥሩ ሁኔታ ሲጨርሱ ከዘጠኝ እስከ 12ኛ ክፍል “ኢፋ ቦሮ” በሚባል ትምህርት ቤት እንዲማሩ በማድረግ ላይ ነን፡፡

“ኢፋ ቦሮ” በሚል በዞናችን ደረጃ የተገነቡ ሶስት ትምህርት ቤቶች አሉን፡፡ አንደኛው ሃሮ ወንጪ (የወንጪ ሐይቅ) ላይ ማለትም ፕሮጀክቱ የሚሰራበት ቦታ አንዱ ሲሆን፣ ሶዶ ዳጬ ላይም እየሰራን ነው፡፡ ምንም እንኳ የትምህርትን ጥራት በአንድ ጀምበር ማስተካከል የሚቻል ባይሆንም በዚህ አካሄድ ጥራቱን ለማስጠበቅ የበኩላችንን እየተወጣን እንገኛለን፡፡

“ኢፋ ቦሮ” በሚል የተገነቡ ሶስት ትምህርት ቤቶች ቢሆኑም ይሁንና በቂ ናቸው ብለን አንወስድም፡፡ በትምህርት ቤቱ የመማር እድል የሚደርሳቸው በትምህርታቸው ጎበዝ እንደሆኑት ሁሉ በ”ኢፋ ቦሩ” ትምህርት ቤት የሚያስተምሩ መምህራንም ራሳቸው ወደዚያ ትምህርት ቤት ገብተው ማስተማር የሚችሉት ተፈትነው ካለፉ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህም በተማሪዎች ብቻ ሳይሆን በመምህራንም በኩል የተመረጡ የሚገቡበት ትምህርት ቤት ነው ማለት ይቻላል፡፡

መደበኛ በምንላቸው ትምህርት ቤቶች ውስጥ የመማሪያ መጽሐፍቱ፣ ቤተ መጻሕፍቱ፣ ቤተ ሙከራውም ሆነ ሌላ ሌላውም ሲታይ “ኢፋ ቦሩ” ትምህርት ቤት የተሻለ ነው፡፡ መንግስት እነዚህ ትምህርት ቤቶች ላይ ትኩረት አድርጎ ስለሰራ ተመራጭም ነው፡፡ ይሁንና በእነዚህ በዞናችን ውስጥ በሚገኙ ሶስት ትምህርት ቤቶች መማር የሚያስችላቸው ተማሪዎች ብቁ የሆኑ እና ጉብዝናቸውን ከመጡበት ትምህርት ቤት ያረጋገጡ ናቸው፡፡ በዚህ መልኩ ነጥባቸው ታይቶ መግባት ይችላሉ፡፡ በ“ኢፋ ቦሮ” በእያንዳንዱ ትምህርት ቤት እስከ 340 የሚሆኑ ተማሪዎች በመማር ላይ ናቸው፡፡ ትምህርት ቤቱ የጀመረው ዘንድሮ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት እየተማሩ ያሉት የዘጠነኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው፡፡

የትምህርትን ጥራት ለማስጠበቅ በሚደረገው ሒደት የሚጎድሉ የትምህርት ግብዓቶች ይኖራሉ፤ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ የመማሪያ መጽሐፍት ሲሆን፣ መንግስት በቶሎ የመማሪያ መጽሐፍትን ማድረስ ይጠበቅበታል፡፡ ምክንያቱም የመማሪያ መጽሐፍት ተቀይሯል፡፡ እዚህ ግን አልደረሰም። ስለዚህም የአሁን እና የዘንድሮ እየተባለ ከሚሰራ አዳዲሱን መጽሐፍት በተቻለ መጠን ወደተማሪዎች ማድረስ ያስፈልጋል፡፡ ግብዓቱ በዚያ መንገድ ሲስተካከል እኛ ደግሞ መሰረቱን እያስተካከልን እንጓዛለን፡፡

አዲስ ዘመን፡- በዞኑ የመልካም አስተ ዳደር ችግሮችን ለመፍታት እና የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን ምን እየተሰራ ነው?

አቶ ቶሎሳ፡– የመልካም አስተዳደር ችግርን በተመለከተ እንደ መንግስትም ተለይተው የተቀመጡ አሉ፡፡ እኛም እንደዞናችን የመንግስት አቅጣጫን ተቀብለንና አቅደን ከዞን አመራሩ ጀምሮ እስከ ወረዳ ድረስ ማኅበረሰቡን የፖለቲካ አመራሩ፣ የቢሮ ኃላፊዎች በሳምንት ሶስት ቀን ማለትም ሰኞ፣ ረቡዕ እና ዓርብ ሌሎች ስብሰባዎችን ትተው በቢሯቸው ሆነው ማኅብረሰቡን እንዲያገለግሉ ማድረግ ችለናል። እንዳጋጣሚ ሆኖ አመራሩ በተለያየ ምክንያት የማይገኝ ከሆነ ሌላ ሰው በመወከል የባለጉዳዩን ቅሬታም ሆነ ጥያቄ እንዲስተናገድ ይደረጋል። ይህም ማኅበረሰቡ እንዳይጉላላ የሚያደርግ ከመሆኑም በተጨማሪ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ ነው። ወደ ወረዳም ወርደው ስለሚደግፉ የወረዳው ደግሞ ወደገጠር ድረስ ወርዶ ማኅበረሰቡን ስለሚያስተባብር በዚያን ጊዜ እንዲሁ ክፍተት እንዳይፈጠር በውክልና እንዲያሰሩ ይደረጋል፡፡ በዚህን ጊዜ ማኅበረሰቡ የሚያነሳቸውን ችግሮች በማዳመጥ በአግባቡ ምላሽ የሚሰጠው ይሆናል፡፡

በዚህ ስራችንም ቀደም ሲል ከነበረው በተሻለ ለውጥ ማምጣት ችለናል፡፡ ሰው ባገኘው እና ባቀደው መሰረት የማይሄድ ከሆነ ማኅበረሰቡ መጥቶ ስለሚንገላታ እንደዚያ እንዳይሆን ቀናትን መድበን በማስተናገድ እና ችግራቸውንም እያየን መፍታት ብሎም ምላሽ መስጠት ላይ እየሰራን ነው፡፡

ከዚህ ሌላ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ይበዛባቸዋል ተብለው የተለዩት መስሪያ ቤቶችንም ለይተን በውስጡ ያሉ ችግሮች ምን እንደሆኑ እና እንዴት ነው መፈታት ያለባቸው በሚልም ከየመስሪያ ቤቶቹ ጋር አቅደን እየሰራን ነው። ለአብነት ያህል የመሬት አስተዳደርን መውሰድ ይቻላል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን በየአነስተኛ ከተማ ያሉ ማዘጋጃ ቤቶች፣ መንገድ ትራንስፖርት አካባቢ እንዲሁም ማኅብረሰቡ በስፋት የሚገለገልባቸው ጽ/ቤቶች ላይ በብዙ አቅደን ስራ እየሰራን ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት እንደ አገር የተያዘ መርሃ ግብር አገራዊ የምክክር ኮሚሽን እያስኬደው ያለ ጉዳይ ነው፤ ከዚህ አኳያ ሒደቱ የተሳለጠ ይሆን ዘንድ በዞናችሁ የሚደረገው ድጋፍ ምን ይመስላል?

አቶ ቶሎሳ፡– የአገራዊ ኮሚሽን ምክክሩ ዘንድሮ ወደስራ እየገባ መሆኑ የሚታወቅ ነው። ዞናችን የምክክር መድረኩን በተመለከተ ድጋፉ ሙሉ ነው፡፡ በዚያ ውይይት ላይ አጀንዳ ለመለየት እና ለመሳተፍ የሚችሉትን እንደ ዞናችን በተጠየቅነው መሰረት ለይተን መስጠት ችለናል፡፡

እንደ አገር ዛሬ ላይ የተፈጠረ የመሰለን ችግር ዛሬ የተፈጠረ ሳይሆን ቀደም ሲል እየተደራረበ የመጣ ችግር ነው፡፡ እነዚያ ተደራርበው ዛሬ ላይ የደረሱ ችግሮች ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ተፈትተው ሰላም ይፈጠራል ተብሎ ይታሰባል። ከኮሚሽኑም የምንጠብቀው ተስፋ ብዙ ነው። ደግሞም የነበሩ ችግሮች እንደሚፈቱም ተስፋ አለን፡፡

ስለሆነም እንደ ዞናችን ከዚህ በፊት በመጀመሪያ ጊዜ የተመረጡ ሰዎች በኮሚሽኑ ጥያቄ መሰረት ሔደው ከኮሚሽኑ ጋር ምክክር አድርገው መጥተዋል፡፡ እናም በወቅቱ በሙሉ ድጋፍ፤ ያንን ማድረግ ችለናል፡፡ እንዲሁ በተመሳሳይ ለሁለተኛ ዙር ከአንድ ወር በፊት አዳማ ላይ ተመካክረው ተመልሰዋል፡፡ ውይይቱ ሲካሄድ የነበረውም በየክላስተሩ ነው፡፡ ከዚህ በኋላም ኮሚሽኑ በሚያስቀምጠው አቅጣጫ መሰረት ሙሉ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁዎች ነን፡፡ ምክንያቱም ከዚህ የምክክር መድረክ የምናገኘው ጥቅም እንዳለ ስለምናውቅ የበኩላችንን ለማድረግ ዝግጁዎች ነን፡፡ ጉዳዩም የእኛው ነው ብለን በመከታተል ላይም እንገኛለን፡፡ ስለዚህም ሙሉ ድጋፍ እያደረግን ነው፡፡ ውጤት እንደሚመጣም ተስፋ አለኝ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ አመሰግናለሁ፡፡

አቶ ቶሎሳ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

 

አስቴር ኤልያስ

 

አዲስ ዘመን መጋቢት 19/2016 ዓ.ም

Recommended For You