ሃብት መልኩ ብዙ፣ ዓውዱም ልዩ ልዩ ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያውያን ብሂልም ሆነ በሌሎች ማኅበረሰቦች እንዳለው እይታ የየራሱ መከሰቻም፤ መገለጫም አለው፡፡ ለአንዳንዱ ሃብት ገንዘብ ነው፤ ለሌላው ደግሞ ሃብት ጤና ነው፡፡ በሌላውም ሌላ መልክ አለው፡፡ ባለሃብትነትም እንደዛው እንደየማኅበረሰቡ የእሳቤ ዓውድ የሚለያይ ነው፡፡
ይሁን እንጂ አንድ ሃገር በሃብቷ ስትገለጽ፣ ከኢኮኖሚዋ ጋር የመቆራኘቱ ጉዳይ እውነት ነው፡፡ ባለሃብትነት እንደ ሃገር፤ ባለሃብትነት እንደ ማኅበረሰብ፤ ባለሃብትነት እንደ ግለሰብ ሲገለጽም በዚሁ መልኩ ካለው የኢኮኖሚ አቅም ጋር የሚተሳሰር ይሆናል፡፡
በዚህ ረገድ ባለሃብትነት ደረጃ እና መልኩ ይለያይ እንጂ፤ ከኢኮኖሚ አቅም፣ ገንዘብ ከማንቀሳቀስና ለሀገር ብሎም ለሕዝብ የሚሆን ወረት ከመፍጠር አኳያ ያለው እውነት ከሀገር ሀገር የተለያየ ገጽታ አለው፡፡
የሀገራት እድገት ከማኅበረሰቦች የሥራ እና የባለሃብትነት ደረጃ ጋር የመተሳሰሩን ያህል፤ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በድሃ ሀገር ውስጥ ቁጥራቸው ያነሰም ቢሆን የሃብት ማማ ላይ የተሰቀሉ ግለሰቦችን ማየት የተለመደ ነው፡፡
እነዚህ የባለሃብትነት መከሰቻ ተቃርኖዎች እንደተጠበቁ ሆነው፣ ዋናው ጉዳይ ይሄ የግለሰቦች አልያም የቡድኖች ሃብት ለሀገር ብሎም ለማኅበረሰብ ጥቅምና እድገት አቅም የመሆን አለመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡
በዚህ ረገድ ባደጉት ሀገራት እነዚህ ባለሃብቶች ሃብታቸውን በማንኛውም አግባብ ከሀገር እና ሕዝብ ጥቅም ውጪ እንዲሆን አያደርጉም፡፡ ይሄን ማድረጋቸውም ለእነሱ ክብርን የሚያላብስ፤ ለሀገራቸውና ሕዝባቸውም የብልጽግና አቅምን የሚያጎናጽፍ ሆኗል፡፡
በአንጻሩ እንደ አፍሪካ ባሉ የሃብታም ደሃ ሀገራት ያሉ ባለሃብት ነን ባዮች ደግሞ፤ አንድም የሃብት ምንጫቸው በወጉ የማይታወቅ፤ ሁለተኛም ይሄንኑም ቢሆን ለሀገርና ሕዝብ ጥቅም እንዲሰጥ ከማድረግ ይልቅ፤ ከሀገር ማሸሽ እና ለራሳቸው የተቀናጣ ሕይወት ብቻ የመጠቀም አካሄዶች የተለመዱ ናቸው፡፡
በኢትዮጵያም ያለው ሁነት ከዚህ ብዙም የተለየ አልነበረም፡፡ ይሁን እንጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለይም ከለውጡ ማግስት በተሠሩ ሥራዎች፤ ባለሃብቶች ሃብታቸውን ከማሸሽ ይልቅ ለሀገርም ለሕዝብም ጥቅምና አቅም በሚሆን መልኩ እንዲሠሩበት የማድረግ ጅምሮች ታይተዋል፡፡
ይሄ ጅምር ባለሃብቱ ያለውን ገንዘብ በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ እንዲያውል፤ በዚህም የሥራ እድል እንዲፈጥር፣ የኢንዱስትሪውን ምርታማነት እንዲያሳድግ፣ የሕዝቦችን ተጠቃሚነት በሚያሳድጉ መስኮች ላይ ሠርቶ ለራሱም ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ እየተቻለ ነው፡፡
ይሄ ደግሞ ቀደም ሲል በተበላሹ የቢሮክራሲ አሠራሮች ምክንያት የተማረረው እና ላልተገባ የሙስናና ሌሎችም አካሄዶች ራሱን አጋልጦ የነበረው ባለሃብት፤ ከዚህ አይነት አካሄድ ራሱን እንዲያገልል እና በታማኝነት ሃብቱን ለኢንቨስትመንት እንዲያውል፤ ከትርፉም ተገቢውን ግብር እንዲከፍል የሚያደርገውን መልካም አጋጣሚ አስገኝቶለታል፡፡
መንግሥትም ይሄን እድል ተጠቅመው ወደ ልማቱም፣ ወደ ታማኝ ግብር ከፋይነቱም የተቀላቀሉ ባለሃብቶችን፤ ስለ መልካም ተግባርና ታማኝነታችሁ አመሰግናለሁ ሲል እውቅና በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ ይሄም ባለሃብቱ የተሻለ መነሳሳት እንዲፈጠርበት አድርጓል፤ ባለው ሃብትም ለሀገርና ሕዝብ ሠርቶ አቅም የሚሆንበትን የተሻለ ምሕዳርም ፈጥሮለታል፡፡
ይሄ በታማኝነት ቅኝት የተገለጸው የባለሃብቶች መንገድ ታዲያ፤ በሂደት የተሰጣቸው ሃብት አንዱ የሀገር እና ሕዝብ ማገልገያ ስጦታ ፀጋቸው መሆኑን ወደ መገንዘብ አሸጋግሯቸዋል፡፡ ምክንያቱም የእነሱ ሕዝብን ማገልገያ፣ ሀገርን መታደጊያ፣ ለወጣቱም ተስፋ መፍጠሪያ አቅምና ፀጋቸው የተሰጣቸው ሃብት ነው፡፡
በመሆኑም ይሄን ሃብታቸውን አንደኛ፣ ከሙስናና ሌላም አሠራር በራቀ መልኩ መፍጠርን፤ ሁለተኛ፣ ካገኙት ሃብት ላይ በታማኝነት ግብር መክፈልን እና የመንግሥት አቅም መሆንን፤ ሦስተኛ፣ ለሕዝቡ ተጠቃሚነት፣ በተለይም ለወጣቱ የሥራ ዕድል ፈጠራ አቅም በሚሆን አግባብ ሃብታቸውን ለላቀ የሃብት መፍጠሪያነት ማዋልን መርሐቸው እያደረጉ መጥተዋል፡፡
በዚህ ረገድ ከሰሞኑ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እነዚህን በታማኝነት መርሕ ተጉዘው፣ በባለጸግነት የተገለጡ ባለሃብቶችን በጽሕፈት ቤታቸው አነጋግረው ነበር፡፡ በወቅቱም የባለሃብቱ ታማኝ ሆኖ ግብር መክፈሉ፤ ያለውንም ሃብት ለሀገርና ሕዝብ በሚሆን አግባብ ፈሰስ ማድረጉ፤ ለብልሹ አሠራሮችና ሙስና የሚጋለጥበትን ዕድል መቀነስ መቻሉ የሚያስመሰግነው ተግባር ስለመሆኑ ተነስቷል፡፡
በተመሳሳይ አሁንም ከዚህ በላቀ መልኩ አቅምን ለልማት ማዋል፤ የታማኝነት መርሕን መላበስ፤ ያካበቱት ሃብት የሕዝብና ሀገርን ማገልገያ እንዲሆን የተሰጣቸው ፀጋ መሆኑን ከልብ አምነው በዚሁ አግባብነት መሥራት እንደሚገባቸውም ማሳሰብ ተችሏል፡፡ በመሆኑም ባለሃብቱ፣ ሃብቱን ያገኘው ከሃገር፣ እንዲያውል የሚጠበቀውም ለሃገር መሆኑን በመገንዘብ፤ በታማኝነት ተጉዞ፣ በባለፀግነት/አገልጋይነት ተገልጦ ለሀገርም፣ ለሕዝብም የብልጽግና ጉዞ አቅም ሊሆን ያስፈልጋል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 19/2016 ዓ.ም