የአካባቢ ጥበቃ ሕግ ራሱን የቻለ የሙያ ዘርፍ ሆኖ በዩኒቨርስቲዎች ሊሰጥ ነው

አዲስ አበባ፡– የአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመከላከልና ተጠያቂነትን ለማስፈን የአካባቢ ጥበቃ ሕግ ራሱን የቻለ የሙያ ዘርፍ ሆኖ በዩኒቨርስቲዎች እንዲሰጥ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን አስታወቀ።

የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ሕግና ደረጃዎች ዴስክ ተወካይ ኃላፊ አቶ መስፍን ታደሰ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የአካባቢ ጥበቃ ላይ የሚፈጸም ወንጀልን ለመከላከልና ተጠያቂነትን ለማስፈን የአካባቢ ጥበቃ ሕግ ራሱን የቻለ የሙያ ዘርፍ ሆኖ በዩኒቨርስቲዎች እንዲሰጥ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው።

በአየር ንብረት ለውጥና በአካባቢ ብክለት የሚያስከትሉ የአካባቢ ጥበቃ ወንጀሎች እያደጉ በመምጣታቸው ተጠያቂነትን በማስፈን ተገቢ መሆኑን ገልጸው፤ የወንጀል ምርመረውን ለማሳደግ፤ የመረጃ አሰባሰብን ለማጠናከር፤ ተጠያቂነትን ለማስፈን የአካባቢ ጥበቃ ሕግ ራሱን የቻለ ሙያ ሆኖ በዩኒቨርስቲዎች መሰጠት አለበት፤ ይህንንም ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል።

የአካባቢ ጥበቃ ላይ የሚፈጸም ወንጀል የራሱ የሆነ ልዩ ባሕሪ ስላለው ወንጀሉን ለመከላከልና ተጠያቂነትን ለማስፈን በአካባቢ ጥበቃ ላይ ግንዛቤ ያላቸው የሕግ ባለሙያዎች ያስፈልጋሉ ያሉት አቶ መስፍን፤ ይህንንም ለማድረግ የአካባቢ ጥበቃ ሕግ እንደ አንድ የሙያ መስክ በዩኒቨርስቲዎች እንዲሰጥ የማድረግ ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።በአካባቢ ላይ የሚፈጸም ወንጀልን ለመከላከልና ወንጀል የሚፈጸሙ አካላትን ተጠያቂ ለማደረግ የአካባቢ ጥበቃ ሕግ ሥርዓተ ትምህርት ተቀርፆለት በተወሰኑ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለማስጀመር የተጀመሩ ሥራዎች መኖራቸውን ገልጸዋል።

የአካባቢ ጥበቃ ላይ የሚፈጸም ወንጀልን ለመከላከል የፀጥታ አካላት ሚና ትልቅ ነው ያሉት አቶ መስፍን፤ የመረጃ አሰባሰብ አቅም ለማጎልበት በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ የአካባቢ ጥበቃ ሕግ ከፖሊስ ማሠልጠኛ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ተካቶ እንዲሰጥ ተደርጓል፤ ፖሊሶችም ትምህርቱን ወስደው ወደ ሥራ ሲሰማሩ የአካባቢ ደኅንነት የሚጠብቁ ይሆናል ብለዋል።

በተጨማሪም የአካባቢ ጥበቃ ወንጀል የትምህርት ሥርዓት በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ መሰጠቱ የፖሊሶች የምርምራና የመረጃ አያያዝ በትምህርት የተደገፈ እንዲሆን በማደረግ በአካባቢ ላይ ለሚፈፀም ማለትም ከደረጃ በላይ ድምፅ መጠቀምን፣ ኬሚካልን በአግባቡ አለማስወገድንና መሰል ወንጀሎች ለመከላከልና ተፈጸመው ሲገኙም ወደ ሕግ አቅርቦ ተገቢው ቅጣት ለማስቀጣት ትልቅ ዕገዛ ያደርጋል ሲሉ ገልጸዋል።

ዳኞች፣ ዐቃቤ ሕግና ፖሊሶች ስለአካባቢ ጥበቃ ሕግ በቂ ዕውቀት ሲኖራቸው ከመረጃ አሰባሰብ እስከ ፍትሕ አሰጣጥ ድረስ ያለውን ሂደት በትክክል እንዲረዱትና ተጠያቂነትን እንዲያሰፍኑ እንደሚያደርግም አመልክተዋል።

የአካባቢ ጥበቃ ወንጀልን ለመከላከል የአካባቢ ጥበቃ ላይ የሚፈፀም ወንጀልን ብቻ የሚያስተናግዱ ፍርድ ቤቶችን ለማቋቋም የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለማፀደቅ እየተሠራ መሆኑን በቅርቡ መዘገባችን የሚታወስ ነው።

ታደሠ ብናልፈው

አዲስ ዘመን መጋቢት 19/2016 ዓ.ም

Recommended For You