የሀውቲ ታጣቂዎች በቀይ ባህር በነዳጅ ጫኝ መርከብ ላይ ጥቃት አደረሱ

የሀውቲ ታጣቂዎች በቀይ ባህር በነዳጅ ጫኝ መርከብ ላይ ጥቃት ማድረሳቸው ተገለጸ። የሀውቲ ታጣቂዎች ባስወነጨፉት የባለስቲክ ሚሳይል የፓናማ ሰንደቅ አላማ እያውለበለች በቀይ ባህር ስትጓዝ በነበረች ነዳጅ ጫኝ መርከብ ላይ አነስተኛ ጉዳት ማድረሱን ባለስልጣናት ተናግረዋል።

የሀውቲ ታጣቂዎች ከጋዛ ጦርነት ጋር በተያያዘ በቀይ ባህር በሚንቀሳቀሱ መርከቦች ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት ለአንድ ወር ያህል ጋብ ካደረጉ በኋላ ይህን ጥቃት ፈጽመዋል። ታጣቂዎቹ ካስወነጨፏቸው ሦስት ሚሳይሎች ውስጥ አንዷ በሲሸልስ በተመዘገበችው እና የፓናማ ሰንደቅ አላማ ስታውለበልብ በነበረችው ‘አንድሮሜዳ ስታር’ ላይ ጉዳት እንዳደረሰባት የአሜሪካ

ጦር ማዕከላዊ ኮማንድ ገልጿል።

የግል የጸጥታ ኩባንያው የሆነው አምብሬይ እንዳለው መርከቧ ከሩሲያ ጋር ግንኙነት ባለው ንግድ የተሰማራች ነች። ኩባንያው እንደገለጸው፤ ከሆነ መርከቧ ከሩሲያ ፕሪሞርስክ ተነስታ ወደ ቫዲናር ህንድ በማቅናት ላይ ነበረች ብሏል። የሀውቲ ታጣቂዎች ቃል አቀባይ ብርጋዴር ጀነራል ያህያ ሳሬ ባወጣው ቀድሞ ሪከርድ በተደረገ ቪዲዮ መግለጫ ለጥቃቱ ኃላፊነት ወስዷል።

ቃል አቀባዩ እንዳሉት፤ መርከቧ ኢላማውን የጠበቀ ምት አርፎባታል። ጥቃቱ በተፈጸመበት ወቅት የባርባዶስ ሰንደቅ አላማ ስታውለበልብ የነበረች ሌላ መርከብ በቅርብ ርቀት ላይ እንደነበረች አሜሪካ ገልጻለች። ይህ ጥቃት የተፈጸመው ቀይ ባህር እና የኤደን ባህረ ሰላጤ በሚገናኙበት የባብኤል ማንዴብ የባህር ወሽመጥ አቅራቢያ ነው።

የሀውቲ ታጣቂዎች ከእስራኤል ጋር እየተዋጋ ላለው የፍልስጤሙ ታጣቂ ሀማስ አጋርነት ለማሳየት ነበር ከባለፈው ህዳር ወር ጀምሮ ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ያላቸውን መርከቦች እንደሚያጠቁ ያሳወቁት። እንደ አሜሪካ ማሪን አድሚኒስትሬሽን ከሆነ የሀውቲ ታጣቂዎች ከባለፈው ህዳር ወር ጀምሮ በመርከቦች ላይ 50 ጥቃቶችን ሰንዝረዋል። ታጣቂዎቹ አንድ መርከብ የያዙ ሲሆን፤ ሌላ አንድ መርከብ ላይ ደግሞ ጉዳት በማድረስ እንድትሰጥም ማድረጋቸውን አል ዐይን ዘግቧል።

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You