ብሊንከን ሩስያ በዩክሬን ላይ እየፈጸመችው ላለው ጥቃት ቻይና ድጋፍ እንዳታቀርብ ጠየቁ

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ሩስያ በዩክሬን ላይ እየፈጸመችው ላለው ጥቃት እያቀረበች ካለችው ድጋፍ ቻይና እንድትቆጠብ አስጠነቀቁ።ቻይና ለጥቃቱ የሚሆኑ ቁሶችን እያቀረበች ነው ሲሉ የወነጀሉት ብሊንከን፣ይህንን ካላቆመች ሀገራቸው እርምጃ እንደምትወስድ አስጠንቅቀዋል።

ቻይና ከቀዝቃዛው ጦርነት ወዲህ “በአውሮፓ ደኅንነት ላይ የተጋረጠውን ስጋት እያቀጣጠለች እና እየረዳች” መሆኑን በቤጂንግ በነበራቸው ቆይታ ከባለስልጣናቱ ጋር መነጋገራቸውን ብሊንከን ገልጸዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሀገራቸው በቻይና ላይ እርምጃ እንደምትወስድ ቢናገሩም ምን እንደሆነ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ብሊንከን በቤይጂንግ ቆይታቸው በአንዳንድ ሁኔታዎች መሻሻል መታየቱን ጠቅሰው፤ ለዚህ ዋቢ ያደረጉትን ፌንታኒል የተሰኘው አደንዛዥ እፅ ወደ አሜሪካ እንዳይደርስ ለማስቆም ባለስልጣናቱ ያደረጉትን ጥረት አወድሰዋል። በመላው አሜሪካ የሕዝብ ጤና ቀውስ እየፈጠረ እንደሆነ በዋይት ሃውስ የተነገረለት ፌንታኒል አደንዛዥ እፅ ዋነኛ ምንጩም ቻይና መሆኗ ይነገራል።

ብሊንከን በተጨማሪ ቻይና ከኢራን ጋር ያላትን ግንኙነት በመጠቀም ከእስራኤል ጋር ያለው ጦርነት የበለጠ እንዳይሰፋ በማድረግ ረገድ በመካከለኛው ምሥራቅ “ገንቢ ሚና” መጫወት እንደምትችል አጽንዖት ሰጥተዋል። በአስር ወራት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ የተደረገው ይህ ጉብኝታቸው በሁለቱ ተቀናቃኝ ኃያል ሀገራት መካከል ያለውን ውጥረት በማርገብ ወደ ዲፕሎማሲ እና ውይይት ለማምጣት የሚያደርጉት ጥረት አካል ነው ተብሏል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል ዋነኛ ውጥረት መነሻ ሆኖ የቆየው ቻይና ታይዋንን እንደ አንድ ግዛቷ መመልከቷ ሲሆን፤ በቅርቡ አሜሪካ ለታይዋን ካካሄደችው የጦር መሳሪያ ሽያጭ ጋር በተያያዘ በአምስት የምዕራባውያን የመከላከያ ድርጅቶች ላይ ማዕቀብ እንደምትጥል ቻይና ማስታወቋ ይታወሳል። እንዲሁም ባለፈው

ዓመት አሜሪካ ቻይና የላከችው የስለላ ፊኛ ነው በሚል መትታ መጣሏን ተከትሎ የሀገራቱ ውጥረት ተጋግሎ ነበር።

በቅርብ ቀናት ውስጥ ደግሞ ባለቤትነቱ የቻይና የሆነው የቪዲዮ መተግበሪያ ቲክቶክ በአሜሪካ ያለው ድርሻ እንዲሸጥ ወይም እንዲታገድ የሚያስገድድ ሕግ ፓርላማው አውጥቷል። ብሊንከን ከቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ ጋር በነበራቸው ውይይት የቲክቶክ ጉዳይ እንዳልተነሳ ገልጸዋል። ፕሬዚዳንት ጂንፒንግ በበኩላቸው በኅዳር ወር ከአሜሪካ አቻቸው ጆ ባይደን ጋር ከተገናኙ በኋላ በሁለቱ ሀገራት መካከል “አንዳንድ አዎንታዊ መሻሻል አሳይተዋል” ብለዋል።

አሜሪካ ለቻይና ዕድገት አዎንታዊ አመለካከት ማሳየት ከቻለች የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት “ሊረጋጋ፣ ሊሻሻል እና ወደፊት ሊራመዱ ይችላሉ” ያሉት ፕሬዚዳንት ጂንፒንግ “ተፎካካሪዎች ሳይሆኑ አጋር መሆን አለባቸው” ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You