ለ270 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች በውጭ ሀገራት የሥራ ዕድል ተፈጠረ

አዲስ አበባ፡- የሥራ አጥነት ችግር ለመፍታት እየተሠራ ባለው ተግባር እስከ መጋቢት 12 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ለ270 ሺህ ለሚሆኑት ዜጎች በውጭ ሀገራት የሥራ ዕድል መፈጠሩን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ አለቃ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በሀገሪቱ የሚስተዋለውን የሥራ አጥነት ችግር ለመፍታት እየተሠሩ ባሉት ሥራዎች በበጀት ዓመቱ እስከ መጋቢት 12 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስም ለ270 ሺህ ዜጎች በውጭ ሀገራት የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል።

በ2016 በጀት ዓመት በሀገሪቱ የሚስተዋለውን የሥራ አጥ ቁጥር ለመቀነስ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፤ እየተሠራ ካለው ሥራም አንዱ ዜጎችን በሕጋዊ መንገድ ወደ ውጭ ሀገራት ሄደው መብታቸው ተጠብቆላቸው ሥራ ሠርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ መሆኑን ጠቅሰዋል። በዚህም እስካሁን ድረስ ለ270 ሺህ ለሚሆኑት ዜጎች በውጭ ሀገራት የሥራ እድል ተፈጥሮላቸዋል ብለዋል።

ወደ ውጭ ሀገራት ሄደው ለመሥራት የሚፈልጉ 900 ሺህ ዜጎች የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ የመረጃ ሥርዓት መተግበሪያ ቴክኖሎጂን እየተጠቀሙ ነው ያሉት አቶ ብርሃኑ፤ እየተጠቀሙ ካሉት 900 ሺህ ሥራ ፈላጊዎች ውስጥ ለ270 ሺህ ዜጎች በውጭ ሀገራት የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው አስታውቀዋል።

በ2016 በጀት ዓመት ለ500 ሺህ ዜጎች የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ለማድረግ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ባለው ሥራም እስካሁን 270 ሺህ ዜጎች ወደ ዩናይትድ ዓረብ ኤሜሬት፤ ኳታር፤ ሳዑዲ ዓረቢያና ጆርዳን ሀገራት ሄደው የሥራ እድል ያገኙ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከተላኩት 270 ሺህ ዜጎች ውስጥ 66 በመቶ የሚሆኑት ሳዑዲ ዓረቢያ፣ 25 በመቶ የሚሆነው ደግሞ ዩናይትድ ዓረብ ኤሜሬት ድርሻውን እንደሚይዙም ጠቁመዋል።

ዜጎችን በውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት ተጠቃሚ ማድረጉ ጥራት ያለው የሥራ እድል እንዲፈጠርላቸው ያደርጋል፤ የዘመናዊ አኗኗር ልምድና ሥልጠና እንዲያገኙ ያግዛል፤ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ዜጋ ወደ ሥራ ለማሰማራት ይጠቅማል ሲሉ ተናግረዋል።

ዜጎች ወደ ውጭ ሀገራት በሥራ ተሰማርተው ገንዘብ በሕጋዊ መንገድ በባንክ ለቤተሰቦቻቸው ሲልኩም ሀገሪቱ በዓመት አንድ ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት ትችላለች ያሉት አቶ ብርሃኑ፤ የዜጎች የውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት ለሥራ አጦች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ ሀገሪቱ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንድትሆን አስተዋፅዖ እንዳለው ጠቁመዋል።

በ2014 በጀት ዓመት 40 ሺህ፣ በ2015 በጀት ዓመት 120 ሺህ የሚሆኑ ዜጎች የውጭ ሀገር የሥራ እድል እንደተፈጠረላቸው ያስታወሱት አቶ ብርሃኑ፤ በ2016 በጀት ዓመት እስካሁን ለ270 ሺህ የሚሆኑ ዜጎች የውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት እንዲያገኙ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል፤ ይህም ተጠናክሮም ይቀጥላል ብለዋል።

ታደሠ ብናልፈው

አዲስ ዘመን መጋቢት 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You