አንጋፋው ዩኒቨርሲቲና የኢትዮጵያ ስፖርት

የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሚና ከመማር ማስተማር ባለፈ በጥናትና ምርምር እንዲሁም ማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት የመስጠትም ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው። አንጋፋው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍሉ በኩል ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ተቀብሎ በእውቀት ያንጻል። ከዚህ ባሻገር በኢትዮጵያ ስፖርት ውስጥ ሊነሱ የሚችሉ ችግሮችን ለይቶ በጥናት የተደገፈ ምላሽ በመስጠት እንዲሁም ስፖርቱንና የስፖርት ማኅበረሰቡን በማገልገል ረገድ የበኩሉን አስተዋፅዖ በማበርከት ላይ ይገኛል። ከዚህም ባሻገር እንደ አንድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የወጣቶች ማዕከል እንደመሆኑም በርካታ ምርጥ ስፖርተኞችንም ለኢትዮጵያ ስፖርት አበርክቷል።

ፈር ቀዳጁ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ለረጅም ጊዜ አቋርጦት የቆየውን የተማሪዎች ስፖርታዊ ውድድር በቅርቡ በማካሄድ ለሌሎች የትምህርት ተቋማት ተምሳሌት የሚያደርገውን ሥራ ማከናወኑ የሚታወስ ነው። በመማር ማስተማሩ ሂደትም በትምህርት ደረጃቸው እንዲሁም በልምድ የላቀ ደረጃ መድረስ የቻሉ መምህራን ያሉት ይህ ዩኒቨርሲቲ ለወጣት ስፖርተኞች ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር ባለፈ በስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍሉ ስር ተማሪዎችን በከፍተኛ ደረጃ (እስከ ሦስተኛ ዲግሪ) በመቀበልም ቀዳሚው ነው።

በዩኒቨርሲቲው የተማሩ ባለሙያዎችም ወደሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በመግባት በመምህርነት ሌሎች የስፖርት ባለሙያዎችን በማፍራት እንዲሁም የስፖርት ትምህርት ክፍል በሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪ እንዲጀመር አስተዋፅዖ እያደረጉ ይገኛሉ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህርና የድህረ ምረቃ አስተባባሪ ዶክተር አስጨናቂ ታደሰ፤ በዚህ ወቅት 36 የሚሆኑ የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው ትምህርታቸውን እየተከታተሉ መሆኑን ይጠቁማሉ። በመጀመሪያ ዲግሪና ድህረ ምረቃም በተመሳሳይ በርካቶችን እያስተማረ ይገኛል።

ትምህርት ክፍሉ በስሩ ከሚቀበላቸው ተማሪዎች ባለፈ በሁሉም የዩኒቨርሲቲው ትምህርት ክፍሎች ስፖርት ሳይንስ እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት (common course) ይሰጣል። ቀድሞ በሁሉም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ይህ አካሄድ ተግባራዊ ሲደረግ ቢቆይም ከዓመታት በፊት ተቋርጧል። አብዛኛዎቹ በድጋሚ ባያስጀምሩትም አንጋፋው የትምህርት ተቋም ግን በድጋሚ ወደ ሥርዓተ ትምህርቱ በማካተት ተማሪዎች በንድፍ እና በተግባር ትምህርቱን እንዲያገኙ ይደረጋል። የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በሕይወት ዘመን ሁሉ ሊተገበር የሚገባና ጠቀሜታውም ከፍተኛ መሆኑን በመረዳትም ዩኒቨርሲቲው ትኩረት አድርጎበታል። ይህም በሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም መለመድ የሚገባው ቢሆንም፤ ከአንደኛ ደረጃ አንስቶ ሊተገበር የሚገባው መሆኑን ዶክተር አስጨናቂ ያሰምሩበታል። የስፖርት ጠቀሜታ ምርታማ፣ በአካልና በአዕምሮ ንቁ የሆነ ትውልድ እስከማፍራት የሚደርስ በመሆኑ መንግሥት ልዩ ትኩረት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ሊያስፋፋ የሚገባው መሆኑንም እንዲሁ።

የተማረ ዜጋ በምክንያት የተገፋ ሲሆን ሳይንሳዊ የሆነ አካሄድንም ይከተላል። በመሆኑም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ችግር ፈቺ የሆኑ ጥናትና ምርምር ላይ እንዲያከናውኑ ይጠበቅባቸዋል። በትምህርት ክፍሉ ከመጀመሪያ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ የተለያዩ የጥናትና ምርምር ይሠራሉ። ከእነዚህም መካከል አብዛኛዎቹ መሠረታዊ የሆኑና በኢትዮጵያ ስፖርት ውስጥ ያሉ ችግሮችን የሚያመላክቱ እንዲሁም መፈታት የሚችሉበትን መፍትሔዎችም የሚያመለክቱ ናቸው። ይሁንና እነዚህን የምርምር ሥራዎች ተቀብሎ በተግባራዊነቱ ላይ የሚሠራ አካል አለመኖሩ በበርካቶች ዘንድ ወቀሳ ይቀርባል። ዶክተር አስጨናቂም በዚህ ይስማማሉ።

በእርግጥ አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ስፖርት ችግሮች በግልጽ የሚታዩና ጥናትና ምርምር ሳያስፈልጋቸው ሊፈቱ የሚችሉ ቢሆኑም፤ ከዚህ የተሻገረውን ግን በስፖርት ማኅበራቱ አመራሮች በኩል ባለው ቁርጠኝነት ላይ የተወሰነ ይሆናል።

ማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎትን በሚመለከትም ከዩኒቨርሲቲው የሚወጡ ባለሙያዎች በሃገር አቀፍ የስፖርት ማኅበራት ውስጥ ገብተው በአማተርነት እየሠሩ መሆኑን መምህሩ ያስታውሳሉ። ከዚህ ባለፈ በተቋሙ ያሉ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ለተለያዩ የስፖርት ባለሙያዎች አገልግሎት እንዲሰጡ በማድረግም ሚናውን ይወጣል። በሌላ በኩል የስፖርት ክለቦችን በመመሥረትና በውድድሮች ላይ በመሳተፍም ለስፖርቱ እድገት የድርሻውን እያበረከተም ነው።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 18 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You