ዓባይ – አንድም፣ ብዙም ግድብ!

ኢትዮጵያውያን ታላላቅ ገድሎችን በመጻፍ ይታወቃሉ። ከእነዚህ ገድሎቻቸው አንዱ የዛሬ 128 ዓመት ሀገራቸውን በቅኝ ገዥ ለመያዝ በማን አለብኝነት የመጣባቸውን የጣልያን ጦር በማሸነፍ የተጎናጸፉት የዓድዋ ድል ተጠቃሽ ነው። በዚህም ሉዓላዊነታቸውን ሊዳፈር፣ ነጻነታቸውን ሊፈታተን፣ በባርነት ቀንበር ስር ሊያሳድራቸው ዘመናዊ መሳሪያ ታጥቆ፣ በእጅጉ ሰልጥኖና ተደራጅቶ የመጣውን ይህን የጣልያን ቅኝ ገዥ ኃይል ምኞት ከንቱ ያስቀሩት ነው።

ይሄን ገድል የፈጸሙት ደግሞ የወቅቱ መሪያቸውን ጥሪ ተቀብለው እና ከዳር እስከ ዳር ተጠራርተው በአንድነት ሆነው በዓድዋ ተራሮች ላይ ባደረጉት ተጋድሎ ድል በማድረጋቸው ነው። በዚህም ሀገራቸው ኢትዮጵያን ለቅኝ ገዥዎች ያልተንበረከከች ማድረግ ችለዋል። እነርሱም በውጭ ኃይልም ሆነ ተላላኪዎቻቸው የማትደፈሩ ክንደ ብርቱዎች መሆናቸውን አሳይተዋል።

እናም በዚህ ታላቁ ድላቸው ሀገራቸውን የነጻነት ቀንዲል ማድረግ ችለዋል፤ ከራሳቸውም አልፈው ለአፍሪካም ለዓለምም ታሪክ ጽፈዋል። ይህ መላ አፍሪካንና ዓለምን ዛሬም ድረስ እያስገረመ ያለ ገድል፣ በቅኝ ግዛት ስር የነበሩ አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት ራሳቸውን እንዲያላቅቁ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ለመላ ጥቁር ሕዝቦች ከባርነት ቀንበር መላቀቅ መነሳሳትም፣ አቅምም ሆኗል። አፍሪካውያን ብቻ ሳይሆኑ መላ ጥቁር ሕዝቦች ይህን የኢትዮጵያውያን ውለታ ሁሌም ይጠቅሳሉ።

ኢትዮጵያውያን ታላቅነታቸውን ለመላው ዓለም የማሳየት ልዕልናቸው እና ገድላቸው በዓድዋ ላይ ብቻ አላቆመም። ያ ድላቸው የአንድነታቸው ተምሳሌት ሆኖ ዛሬም ድረስ ዘልቋል፤ አንድነቷን ሊፈታተኑ፣ ሉአላዊነት ሀገራቸውን ሊደፍሩ የመጡ የሀገሪቱን ጠላቶችና ተላላኪዎቻቸው በዚህ የአንድነት ኃይላቸው ሲያሳፍሩ ኖረዋል።

ለምሳሌ፣ ቀደም ሲል በዓድዋ ድል የደረሰባትን ሽንፈት ለመበቀል የጣሊያኑ ፋሽስት ኃይል ለ40 ዓመታት ዝግጅት አድርጎ ሀገራቸውን ቢወርም፣ በዱር በገደል ተዋግተው ያሰበው እንዳይሳካና ተጠራርጎ እንዲወጣ አርገውታል። በተመሳሳይ፣ “ታላቋ ሶማሊያን መገንባት” በሚል ቅዥት ውስጥ የነበረውን የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ዚያድባሬን ምኞት ከንቱ አስቀርተውታል። ሌሎች የሀገሪቱ ጠላቶች ፊት ለፊትም ሆነ የሀገር ውስጥ ባንዳዎችን በመመልመል በተለያዩ ጊዜያት የሞከሩትን ሀገርን የመበተን አደጋ ቀልብሰዋል።

ኢትዮጵያውያን ይህን የአድዋ እና መሰል የጦር አውድ ገድላቸውን ሁሌም ያስቡታል፤ የሚያስቡት ለማሰብ ያህል ብቻ አይደለም፤ ድሉን በልማቱ መስክ ለመድገም በሚያሰርጉት ርብርብ ላይ አቅምም እንዲሆናቸው እንጂ። የአድዋውን ወኔ በመላበስ በድህነት ላይ ድል ለመቀዳጀት በተለያዩ ታላላቅ እቅዶቻቸው ላይ ስኬትን ለማስመዝገብ የመተባበርን ፋይዳና ጣፋጭ ፍሬም ያስገነዝቡበታል።

በዚህም የአድዋ ድል የሀገር ሉዓላዊነት ማስጠበቂያ፣ ከድህነት የመውጫ ልማት ከፍታ ልኬት አድርገውታል። እንደ ሀገር የሚታሰበውን፣ የሚታቀደውን ልማት ተሻጋሪ እንዲሆን ሲታሰብ መለኪያው የዓድዋ ድል ሆኗል። በዓድዋ ልክ አስቦ መስራትን ኢትዮጵያውያን ባህላቸው እያደረጉ መጥተዋል።

በዓድዋ ልክ አስቦ መፈጸም ደግሞ ብዙ ስራን ይጠይቃል። ሕዝብ ማነቃነቅን፣ በራስ አቅም መስራትን ይፈልጋል። ብዙ ውጣ ውረዶች እንደሚገጥሙ አውቆ ተዘጋጅቶ መስራትን ይጠይቃል። ከሀገርም አልፎ ክፍለ አህጉራዊ፣ ዓለም አቀፋዊ ልክ አንዲኖረው አርጎ ማቀድን፣ መፈጸምን እንዲሁ ይፈልጋል።

በዚሁ አግባብም ኢትዮጵያውያንና መንግስቶቻቸው ዓድዋ ላይ የተጎናጸፉትን ድል በሌላ ልማት ለመድገሞ ታግለዋል። በዚህም የአባይን ወንዝ ለልማት ለማዋል ብዙ ጥረት ተደርጓል። በወንዙ ላይ ግድብ ገንብቶ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ጥናቶች ተሰርተዋል።

ይህን ጥናት ካሰሩት መካከል የቀድሞው ንጉስ አጼ ኃይለስላሴ አንዱ ናቸው። የግድቡን ጥናት ይፋ በተደረገበት ወቅት ንጉሱ፣ ግድቡን መጪው ትውልድ እንደሚገነባው ተስፋ ነበራቸው። ጊዜው ሲደርስም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ግንባታውን አስጀምረዋል። ግንባታው ችግር ውስጥ በወደቀበት ወቅት ደግሞ የለውጡ መንግስት መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ታድገውታል።

በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ አልፎም ዛሬ ግድቡ እውን ሆኗል። ግድቡ ለኢትዮጵያውያን ትርጉሙ ብዙ ነው። በታላቁ ወንዛቸው አባይ ለዘመናት ሳይጠቀሙ መቆየታቸው በእጅጉ ሲያንገበግባቸው የኖሩት ኢትዮጵያውያን፤ ያንን ቁጭታቸውን ተወጥተውበታል። በእልህ በቁጭት ተረባርበው ግድቡን እውን አርገውታል። በዚህ ወንዛቸው እንዳያለሙ ሲያደርጓቸው የኖሩትን ጠላቶቻቸውንም ድል አድርገውበታል።

አይገነቡትም፣ አቅሙ የላቸውም፤ አይሞክሩትም፤ እንሞክር ቢሉ እንኳ ያላቸውን አቅም የሚያጡባቸውን ጥፋቶች ከጀርባ ሆነን እንፈጽምባቸዋለን ያሉ ጠላቶቻቸው እንኳን የሆነውን ማመን እስኪያቅታቸው ድረስ ግድቡን ሰርተው አሳይተዋል። ለጠላቶቻቸው፣ ለአፍሪካም ለዓለምም ሕዝብን አስተባብሮ ግዙፍ ፕሮጀክት መስራት አንደሚቻል አሳይተዋል።

እንዲህ ያሉ መሰረተ ልማቶች ሲገነቡ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ብድርና እርዳታ እንደሚያደርጉ ቢታወቅም፣ የግድቡን እውን መሆን የማይፈልጉ እንደ ግብጽ ያሉ ሀገሮችና ወዳጆቻቸው በሚፈጥሩት ጫና ገንዘብ ማግኘት እንደማይቻል መንግስት በሚገባ ተገንዝቦ መላ ያስቀመጠለትን ግድብ ነው ሀገሪቱ የገነባችው። በዚህ ዘዴም ለግንባታው የሚያስፈልገው ሀብት የተገኘው በራሳቸው በኢትዮጵያውያንና በመንግስታቸው ብቻ ነው። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ፣ የግንባታው ፋይናንስ ምንጭ እኛው፣ የግንባታው ባለቤትም እኛው፣ የግንባታው መሃንዲሶች እኛው፣ … ያሉትም ይህንኑ ያመለክታል።

መላ ኢትዮጵያውያንም መንግስት ግንባታውን ይፋ ካደረገበት መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም አንስቶ ለግንባታው አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ የገቡትን ቃል ፈጽመዋል። በእዚህ ግድብ ግንባታ ላይ አሻራውን ያላኖረ ኢትዮጵያዊ የለም። ሕጻናት፣ የጉልት ነጋዴዎች፣ የመንግስትና የግል ድርጅት ሰራተኞች፣ ጡረተኞች፣ አርሶ እና አርብቶ አደሮች፣ የመከላከያ፣ የፖሊስ አባላት፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ ዲያስፖራዎች ቦንድ በመግዛትና በመለገስ ላለፉት 13 ዓመታት የፋይናንስ ድጋፍ አድርገዋል። በሕዳሴው ዋንጫ፣ በአጭር የጽሑፍ መልእክት፣ ወዘተ. በኩልም የፋይናንስ ድጋፎች ተደርገዋል። አሁንም እያደረጉ ይገኛል።

ኢትዮጵያውንና መንግስታቸው የዓለም አቀፍ ፋይናንስ ቢያጡም፣ ጠላቶቻቸውና የሀገር ውስጥ ተላላኪዎቻቸው ሊያሰናክሏቸው ብዙ ቢወድቁ ቢነሱም፣ ይህን በሀገርም በዓለም አቀፍም በአህጉራዊ መለኪያም ግዙፍ የሆነ ፕሮጀክት እውን አርገውታል። ግድቡም በየትኛውም መለኪያ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ፕሮጀክት አይደለም። ግብጾች የግድቡን ጥራት እንደሚጠራጠሩት ቢገልጹም፣ አጥብቀው ያልሄዱበት ምክንያትም ይሄው ነው። እናም የሙግት አቅጣጫቸውን ከግድቡ ጥራት ጉዳይ አንስተው ወደ ታሪክና የቅኝ ግዛት ዘመን ውል ወደማድረግ ገቡ።

በአባይ ወንዝ ሳይጠቀሙ ዘመናት ማለፋቸው ያንገበገባው ኢትዮጵያውያንና መንግስታቸው በቁጭት ተነሳስተው የገነቡት ይህን ግዙፍ ግድብ እውን ለመሆን ነገሮች አልጋ ባልጋ የሆኑት አልነበረም። ግብጾች ሲፈጽሙ ከቆዩት አሉታዊ ጫና በተጨማሪ በሀገር ውስጥም ቀበኛ ተፈጥሮበት ነበር። ይሁንና ኢትዮጵያውያን የፋይናንስ ድጋፋቸውን በማጠናከር፣ የግብጽንና አጋሮቿን የዲፕሎማሲ ጫና በማምከን አንድ ሆነው ልክ እንደ ዓድዋ ድል ሁሉ የአንድነታቸው መገለጫ የሆነ ተግባር አከናውነውበታል። ‹‹እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን›› በሚል መርህ ግንባታውን አጠናክረው በመቀጠል ለፍጻሜ እያበቁትም ነው።

በእነዚህ እና ሌሎች የበዙ ምክንያቶችም ለእኔ ሕዳሴ ግድብ እንድ ፕሮጀክት ብቻ አይደለም፤ ዘርፈ ብዙ ፕሮጀክቴ ነው። ይህ ከአምስት ሺህ አንድ መቶ በላይ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያመነጭ የሚጠበቀው ግድብ የብዙ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድቦች ሁሉ ግምት ተደርጎ ይወሰዳል። እዚህ ላይም በየግድቦቹ የተያዘውን የውሃ መጠን፣ ግድቦቹ የሚያመነጩትን የኤሌክትሪክ ኃይል እየደመሩ መድረስ ይቻላል። በሀገሪቱ በተለያዩ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች የሚገኘውን የኤሌክትሪክ ኃይል ምርት የሚያህል የሚያመርት መሆኑ ግዝፈቱን ያመለክታል።

በመሰረቱ ግድቡ ከሀገር ውስጥ የኃይል ማመንጫ ግድቦች ጋር የሚወዳደርም አይደለም፤ ለመወዳደር የሚመጥኑትም በአፍሪካ እንዲሁም በዓለማችን የተገነቡ ግዙፍ የሚባሉቱ ግድቦች ናቸው። በሚይዘው የውሃ መጠን ከግብጹ አስዋን ይልቃል። አስዋን 44 ቢሊየን 300 ሚሊየን ሜትር ኩብ የሚይዝ ሲሆን፣ የኛው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግን 74 ቢሊየን ሜትር ኩብ ውሃ መያዝ ይችላል። በኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት በኩልም ከአምስት ሺህ አንድ መቶ በላይ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጭ ነው፤ ይህም በሀገሪቱ በተለያዩ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች ከሚመነጨውም በላይ ነው። በሚያመነጨው የኃይል መጠንም በአፍሪካም ግንባር ቀደሙ እንደሆነ ይነገርለታል።

ግድቡ የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ ፍላጎት የሚያሽር፣ ለጎረቤት ሀገሮች ለሚቀርበው ኃይልም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችል ነው። በዚህ ደግሞ የኤሌክትሪክ ብርሃን አይተው የማይውቁትን ኢትዮጵያውያን ከኤሌክትሪከ ብርሃን የሚያገናኝና ከኩራዝ ጭስ የሚታደግ ብቻ ሳይሆን፤ በኩበትና በመሳሰለው የማገዶ ጭስ የሚደርስበትን ችግር የሚያስቀርም ነው። እያደገ የሚመጣውን የከተሞችንና የኢንዱስትሪዎችን ፍላጎት የሚመልስ፣ የሕዝቡን አዳዲስ ፍላጎት የሚሞላ ነው።

ይህ ብቻ አይደለም የግድቡ ፋይዳ፤ ከዚህ ሁሉም ይሻገራል። በግድቡ የተፈጠረው የውሃ አካል ግዙፍ እንደመሆኑ ለዓሣ ሀብት ለማልማት፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመታደግ፣ በሚፈጠሩት በርካታ ደሴቶች የቱሪዝም መሰረተ ልማቶችን በመገንባት አካባቢውን ልዩ የቱረስት መስህብ ለማድረግ ትልቅ አቅም መፍጠር የሚችልም ነው። ወደ ግድቡ በሚወስዱ መንገዶች ላይ ከተሞች እንዲመሰረቱ፣ ያሉትም ይበልጥ እንዲስፋፉ በማድረግ ለከተሜነት የበለጠ መስፋፋትና መጎልበትም አስተዋጽኦ ያበረክታል።

ግድቡ እየተገነባ ያለው በጣልያኑ ሳሊኒ ኩባንያ እንደሆነ ይታወቃል። በግንባታው የበርካታ ሀገሮች ዜጎችም ተሰማርተውበታል። ይህ ሁኔታ ለልምድ፣ ለተሞክሮና ቴክኖሎጂ ልውውጥ ምቹ መሆኑ ይታመናል። የሕዳሴ ግድብ ግንባታ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግንባታ ትምህርት ቤት ሊባል የሚችል ነው። ለዚያውም ተግባር ላይ የተመሰረተ።

የግድቡ ግንባታ በኃይል ልማት ዘርፍ ትልቅ አቅም እንደሚገኝበት ይጠበቅ እንደነበረው ሁሉ ትልቅ አቅም የተገነባበትም መሆን ችሏል። የሀገሪቱ በርካታ ኢንጂነሮች አቅም አጎልብተውበታል፤ ሌሎች በርካታ ኢትዮጵያውያንም የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ግንባታ ባለሙያ መሆን ችለዋል። በአንድ መድረክ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሲናገሩ እንደተደመጠው፣ ግድቡ ትልቅ አቅም የተፈጠረበት ነው። ይህ አቅም እንዳይበተን ማድረግ ደግሞ የሁሉም የቤት ስራ ነው።

በእርግጥም በእዚህ ስፍራ ላለፉት 13 ዓመታት የተፈጠረውን አቅም ደምሮ ለቀጣይ የኤሌክትሪክ ኃይል ልማት ሁነኛ ተቋራጮችን ለመፍጠር መስራት ያስፈልጋል። ሀገራችን በገነባቻቸው የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች ብዛት የራሴ የምትላቸው የዘርፉ ተቋራጮችን አላፈራችም። እርግጥ ነው በጥገና በማስተዳደር በኩል ትልቅ አቅም እንደ ተፈጠረ ይገለጻል። እንዳንድ ስራዎችንም በከፊል ኮንትራት የሚሰሩ ድርጅቶች ሊኖሩን ይችሉ ይሆናል። ከዚህ ውጪ ግን በራስ አቅም የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብን በመገንባት በኩል ያፈራችው ኩባንያ ስለመኖሩ እጠራጠራለሁ።

የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት የምትታወቅ ሀገር ይህን የሚገነባ ተቋራጭ አለማፍራት ደግሞ አስገራሚም፣ አነጋጋሪም ሊሆን ይችላል። በቀጣይ ግን በዓባይ ግድብ ግንባታ ወቅት ባለፉት ዓመታት የተፈጠረውን አቅም ሰብሰብ አድርጎ ይዞ አንድ ኩባንያ መመስረት ላይ መስራት ይገባል።

የኤሌክትሪክ ኃይል ልማቱ ከዚህ በኋላም የሚፈጠረውን ፍላጎት ታሳቢ ባደረገ መልኩ እንደሚቀጥል ይጠበቃል። ሊዚያ ልማት የሚሆን ኩባንያ ሁሌም ከውጪ ማማተር ያስፈልጋል ብዬ አላምንም። እናም ሀገራዊ አቅም መፍጠር ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ እስከ አሁን በሀገሪቱ በተካሄዱ ግንባታዎች የተፈጠረው አቅም አንድ ነገር ሆኖ፤ በሕዳሴ ግድብ ግንባታ የተፈጠረው አቅም ብቻውን በቂ ነው።

አሁን ላይ የዓባይ/ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እየተጠናቀቀ ነው። ሆኖም ግንባታው እየተካሄደ ባለበት ወቅት ብዙ እድሎችን ፈጥሯል። ግንባታው ባልተጠናቀቀበት ሁኔታም ባለፈው ዓመት በሁለት ተርባይኖች ከ700 ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ማምረት ጀምሯል።

ባለፉት 13 ዓመታት ለብዙ ሺህ ኢትዮጵያውያን የስራ እድል ፈጥሯል፤ ከፍ ብዬ እንደገለጽኩትም የብዙዎችን የዘርፉን ሙያ ስጋ አልብሶታል፤ አዳዲስ የኤሌክትሪክ ኃይል ባለሙያዎችን ማፍራት አስችሏል። ሌላም ሌላም ትሩፋቶችን ለግሷል። ግድቡ በቀጣይም ከዋናው ኃይል ማመንጫ ስሪቱ በተጨማሪ ሌሎች ብዙ ብዙ እድሎችን ይዞ የመጣ ታላቅ ፕሮጀክት ነው። እነዚህን እድሎችም በሚገባ መጠቀም ቀጣዩ ስራ ይሆናል።

ዘካርያስ

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You