ቃል እና ተግባር የተደጋገፉበት ዘርፈ ብዙ ስኬት

ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ በሕዝብ ብዛት፣ በቀደምት ሥልጣኔ፣ በሀገረ መንግሥት ምሥረታ እና በሌሎች ታሪካዊ ዳራዎችም ሲታይ ቀዳሚ ናት። በአጠቃላይ ኢትዮጵያ መልከ ብዙ ሀገር ናት። በዚያው መጠን በርካታ የፖለቲካ ሥርዓቶችና ባሕሪያትን አስተናግዳ ዛሬ እንደመድረሷም፤ የእነዚህ ሥርዓቶች የተግባር ውጤት የወለዳቸው ችግሮች ዛሬም ድረስ እየፈተኗት መሆኑም ሊዘነጋ አይገባም።

እነዚህ ችግሮች ደግሞ ከትናንት አልፈው ዛሬን ለመረበሻቸው በርካታ ምክንያቶች ሊነሱ ቢችሉም፤ የችግሮቹን እሳቤ ተሸካሚ የሆኑ አካላት ግን የበለጠ ችግሩን ለማስፋት አቅም እየሆኑ ናቸው። በዚህ ረገድ እነዚህን የጥፋት ሀሳብ ተሸካሚ ኃይሎች አደብ ማስያዝ የዚህ ዘመን የቤት ሥራ፤ የሁሉም ሕዝብ ኃላፊነት መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል።

ከዚህ አኳያ፣ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከበዓለ ሲመታቸው ቀን ጀምሮ በኢትዮጵያ በአራቱም ማዕዘናት የሠላም አየር እንደሚነፍስ ቃል ገብተዋል። ሠላምና ዴሞክራሲም እውን ይሆናል፤ ኢትዮጵያም ትበለፅጋለች ሲሉ ቃል ገብተዋል። የፍትሕ ሥርዓት መስፈንን በተመለከተ፡-

‹‹በዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ውስጥ የሕግ የበላይነት መስፈን ይገባዋል። የሕግ የበላይነትን ለማስፈን በምናደርገው ትግል መርሳት የሌለብን ቁም ነገር ሕዝባችን የሚፈልገው የሕግ መኖርን ብቻ ሳይሆን የፍትሕ መረጋገጥንም ጭምር ነው። የሕዝብ ፍላጎት ከፍትሕ የተፋታ ደረቅ ሕግ ሳይሆን፣ በፍትሕ የተቃኘ፣ ለፍትሕ የቆመ የሕግ ሥርዓትን ነው። የሕዝብ ፍላጎት የሕግ አስከባሪ ተቋማት ገለልተኛና ለፍትሕ ታማኝ፣ ለዜጎች መብት ቀናዒ እንዲሆኑ ነው። ሕግ ሁላችንንም እኩል የሚዳኝ መሆን አለበት። እንዲህ ሲሆን ሕግ በተፈጥሮ ያለንን ሰብዓዊ ክብራችንን ያስጠብቅልናል። ይህን እውነታ በመረዳት በሀገራችን ዲሞክራሲ እንዲያብብ፣ ነፃነትና ፍትሕ እንዲሰፍን፣ የሕግ የበላይነት እውን እንዲሆን አስፈላጊውን ማሻሻያ በማድረግ በዘርፉ ያለውን ክፍተት እንሞላለን›› ነበር ያሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ንግግራቸው በርካታ ጉዳዮችን የቃኙ መሆኑ እሙን ነው። በዚህም መሠረት በርካታ የሪፎርም ሥራዎች ሠርተዋል። ያለአሳማኝ መረጃ እና ማስረጃ ለዓመታት በማረሚያ ቤቶች ሲማቅቁ የነበሩ ዜጎች በተመለከተም ፖለቲካዊ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሠላማዊ ሕይወት እንዲኖሩ ተደርጓል።

የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በአግባቡ ለጭቁኖች ድምፅ እንዳይሆኑ በፀረ ሽብር ሕግ ሥም እጅ ተወርች ይዞ የነበረውን አካሄድ ለመቀየር ተሠርቷል። ፖሊሲም ተቀርፆለታል። ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በማሳተፍ በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች የማወያየትና የጋራ የፍትሕ ሠርዓት መዘርጋት በሚቻልባቸው አንኳር ጉዳዮች ላይ መግባባት ላይ ተደርሷል። እነዚህና ሌሎች ጉዳዮች ሲታዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ቃላቸውን ለመኖር የታተሩ መሆኑን ያሳያል።

በፍትሕ ተቋማት ላይ የተወሰደው የሪፎርም ርምጃም፣ ዘርፉ ለሕግ የበላይነት እና ለፍትሕ እውን መሆን ሚናውን በአግባቡ ይወጣ ዘንድ ያለውን ከፍ ያለ መሻት ብቻ ሳይሆን፤ ቁርጠኝነቱንም ያረጋገጠ ነበር። በዚህም የተሻለ የፍትሕ አሠራርን መዘርጋት ተችሏል። ይሁን እንጂ በዚህ ረገድ አሁንም ያልተፈቱ አሠራሮች መኖራቸው አልቀረም። ለምሳሌ፣ የፍርድ ቤቶች እና ፖሊስ ተቋማት መካከል አለመናበብ ምክንያት ፍርድ ቤት የወሰነውን ፖሊስ ያለመፈጸም አይነት ክፍተቶች ይስተዋላሉ።

ከዚህ ሌላም፣ በገንዘብና በሥልጣን መከታ አድርገው ሕዝብን የሚያማርሩ አመራሮችና ባለሙያዎች በየተቋማቱ ውስጥ አሁንም አሉ። ብሔርተኝነት፣ መንደርተኝነትና ዘውጌነትን በማጣቀስ ፍትሕን በማጣመም የራሳቸውን ኑሮ ብቻ የሚያደላድሉ ተበራክተዋል። ከመንግሥት በላይ መንግሥት መሆን የሚዳዱ አያሌ ግለሰቦችን እየተመለከትን ነው። ታዲያ እነዚህ ጉዳዮች ኢትዮጵያ ወደ ብልፅግና እጓዛለሁ ብላ እየተጋች ባለችበት ወቅት ላይ የበቀሉ አደገኛ አረሞች በመሆናቸው መነቀል ያስፈልጋቸዋል።

የምጣኔ ሃብት ዕድገትን በተመለከተም ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ዕድገቱ በቅርፅና በይዘት ተለዋዋጭ የሆነውን የወጣቱን ትውልድ ፍላጎት በሚፈለገው ደረጃ የሚያረካ አለመሆኑንና ሕዝቡን ያላረካ መሆኑን በበዓለ ሲመታቸው መጥቀሳቸው የሚታወስ ነው። ይህን ለማስተካከል ሲባልም ኢትዮጵያ ለወጣቶቿ ተስፋ የምትሰጥ ሀገር እንድትሆን የተቻላቸውን ሁሉ ለማድረግ ቃል ገብተው ነበር።

በዚህ ንግግራቸው መሠረትም የኢትዮጵያን ከፍታ ሊያረጋግጡ የሚችሉ ዘመን አሽሬ ተግባራትን ፈፅመዋል። በተለይም በኢትዮጵያውያን ሕዝብ ዘንድ ትልቅ ተስፋ የተጣለበትና የምጣኔ ሃብቱን ምንዳጌ ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሻግር ብሎም ፖለቲካዊና ማኅበራዊ አንድምታው እንደ ሀገርም ሆነ ዓለም አቀፍ ደረጃ ጥልቅ ትርጉም የሚሰጠውን የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከውድቀት አንስተው ነብስ ዘርተውበታል። በዚህ ተግባራቸውም የሚወደሱና በታሪክ የሚዘከሩ መሆኑም አያከራክርም። ከዚህም በተጨማሪ ዓመታትን የዘገዩ ፕሮከጀቶች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ አድርገዋል። በሀገሪቱ በተለያዩ ቦታዎች የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በፍጥነት ማጠናቀቅ ማለት ደግሞ በሀገሪቱም ላይ ያንዣበቡ ምጣኔ ሃብታዊ ችግሮች ፈጣን እልባት እንደመስጠት ይቆጠራል።

ሌላው ታሪክ የማይረሳው፣ ትውልድም የሚኮራበት ተግባር የስንዴ ልማት እና መሰል በግብርናው ዘርፍ የተገኙ ውጤቶች ናቸው። ከባሕር ማዶ ስንዴ ከመለመን አፈርና ውሃን በማገናኘት ብቻ ራሳችን መቻል አለብን በሚል ቆራጥ ውሳኔና አመራርም፤ ኢትዮጵያን በስንዴ ምርት ራሷን እንድትችል አድርገዋል። ይህ ለኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ እውቅና ያስገኘ ሲሆን፤ በበርካታ የአፍሪካ መሪዎችም ዘንድ ትልቅ መነሳሳትን የፈጠረ ስለመሆኑን ይነገራል።

አረንጓዴ ዐሻራን በማኖር ረገድም ኢትዮጵያ ትልቁን ሚና እየተወጣች ነው። በአንዲት ጀንበር ከስድስት መቶ ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ጭምር ዓለምን እያስጨነቀ ለሚገኘው የአየር ንብረት ለውጥ የመፍትሔ አካል ለመሆን እየተጋች ያለች ሀገር መፍጠር ችለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ለዚህ ትልቅ ትኩረት የሰጡ መሪ መሆናቸውና ለቃላቸው የተገዙ ስለመሆናቸው አስመስክረዋል።

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ተከስቶ የነበረውን ግጭትና ጦርነት በማስተካከል እና የሀገሪቱን የግዛት አንድነት በአስተማማኝ ሁኔታ በማስጠበቅ በኩልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወሰዱት የአመራር ጥበብ የሚደነቅና ታሪካዊ ጠላቶችንም ያሳፈረ ነው። ኢትዮጵያን ፈተና ውስጥ ያስገባትን የጠላት ሴራ ማክሸፍ በዲፕሎማሲ ሥራም፣ የፖለቲካ ውሳኔ በመውሰድም ትልቅ ሥራ ተሠርቷል።

ኢትዮጵያን ሕልውና ከመጠበቅ ከጀምሮ እስከ ፕሪቶሪያው የሠላም ስምምነት ድረስ የዘለቀው የዲፕሎማሲ ጉዞ፤ በታሪክ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው መሆኑንም የዘርፉ ምሑራን በተደጋጋሚ በአድናቆት ሲናገሩትም ይሰማል። ይሁንና አሁንም ቢሆን በሀገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮች ዜጎችን ለከፋ አደጋ ያጋለጡ ሆነዋል። በመሆኑም በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ሰላም ለማስፈን የተወሰደው እርምጃ በሌሎች አካባቢዎችም መተግበርና አስተማማኝ ሠላም ማስፈን ግድ ይላል። ለዚህ ደግሞ መንግሥት ቀዳሚውን ሚና መጫወት ይገባዋል። ዜጎችም እንዲሁ ከልብ ሊተባበሩ ግድ ይላል።

እንደ አጠቃላይ ሲታይ ከለውጡ ማግስት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ወደሥልጣን ከመጡ ጀምሮ መንገዱ አልጋ በአልጋ ባይሆንላቸውም፤ ቃልን በመተግበር በኩል በርካታ አኩሪ ተግባራትን መፈፀማቸው አይካድም። አሁንም ግን በርካታ ሀገራዊ ፈተናዎች ተደቅነዋል። በመሆኑም እነዚህን ችግች በጥልቅ ሳይንሳዊ ትንታኔ ላይ በመመሥረት እና ብስለት በተሞላው አካሄድ በሁሉም መስክ ተምሳሌት የሆነች ኢትዮጵያን በምሥራቅ አፍሪካ ማኖር ግድ ይላል። ለዚህም ቃል እና ተግባር ተሰናስለው የፈጠሩትን ውጤት እንደ ስንቅ መጠቀም ይገባል።

ክፍለዮሐንስ አንበርብር

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You