የአፍሪካ የነፃነት ዓርማ፤ የጥቁር ሕዝቦች መከታ እና የአልሸነፍ ባይነት ተምሳሌት የሆነችው ኢትዮጵያ ከጥንት እስከ ዛሬ የጋራ ተጠቃሚነት መርሕን በማንገብ ለተግባራዊነቱ ስትንቀሳቀስ ቆይታለች፡፡ በዚሁ ጥረቷም በርካቶች ከቅኝ ግዛት ተላቀው ነፃ ሀገር እንዲሆኑና ነፃ ኢኮኖሚም እንዲገነቡ የበኩሏን ድርሻ ስትወጣ ቆይታለች፡፡ ከአፍሪካ አንድነት ምሥረታ ጀምሮ አፍሪካ በኢኮኖሚ ጭምር የተዋሓዱ እንዲሆኑ አበክራ ሠርታለች፡፡ ለዚህም አንዱ ማሳያ አፍሪካውያንን በኢኮኖሚ ለማስተሳሰር በማሰብ በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን እንዲቋቋም ማድረጓ ነው፡፡
ይኸው ጥረቷ ቀጥሎ የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራትን በማዕከልነት በማስተባበር በኢኮኖሚ፤ በሠላምና ፀጥታ እንዲሁም በባሕልና ታሪክ ላይ አካባቢያዊ ጥምረት እንዲፈጠር የበኩሏን አስተዋፅዖ ማበርከት ከጀመረች ውላ አድራለች፡፡ በተለይም በአፍሪካ ግዙፍ የሆነውም የዓባይ ግድብን በመገንባት በኃይል አቅርቦት ለማስተሳሰር እያደረገች ካለችው ጥረት ጎን ለጎን ውሃና የምግብ ሰብሎችን ጭምር ወደ ጎረቤት ሀገራት በመላክ ቀጣናዊ ትስስሩ ተጨባጭ እንዲሆን አድርጋለች፡፡
ኢትዮጵያ ከ13 ዓመታት በፊት የጀመረችው ታላቁ የዓባይ ግድብ ከ95 በመቶ በላይ ተጠናቋል፡፡ ግድቡ ከወዲሁ ለጎረቤት ሀገራት ጭምር የኃይል ምንጭ በመሆን ምሥራቅ አፍሪካን በማስተሳሰር ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ግዙፍ የኃይል ማመንጫ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅም የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት አስተማማኝ የኃይል ምንጭ እንዲያገኙ ከማስቻሉም በላይ የቀጣናውን ሀገራት በኃይል በማስተሳሰር የጋራ ኢኮኖሚ እንዲገነቡ በር የሚከፍት ይሆናል፡፡
ንጹሕ የመጠጥ ውሃ ለጎረቤት ሀገራት በተለይም ለጅቡቲ በመላክ ቀጠናዊ ትስስሮሽን በማጎልበት ላይ ትገኛለች፡፡ ከ258 ኪ.ሜ በላይ የውሃ መስመር ዝርጋታ በማከናወን ኢትዮጵያ በየቀኑ ለጅቡቲ እያቀረበች ያለችውን ከ20ሺህ እስከ 30ሺህ ኪዩቢክ ሜትር የሚደርስ ውሃ ወደ 100 ሺህ ኪዩቢክ ሜትር ለማሳደግ እየሠራች ትገኛለች፡፡ ይህም ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብቶቿን ጭምር በማጋራት ቀጣናዊ ትስስሩን ለማጠናከር እየሠራች መሆኑን አመላካች ነው፡፡
በግብርናው ዘርፍም ቀጣናዊ ትስስሩን የማጠናከር ሥራ በስኬታማነት በማከናወን ላይ ትገኛለች፡፡ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ የሚሆነው ደግሞ ስንዴ ምርት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከስንዴ ተቀባይነት ወደ ስንዴ ላኪነት ራሷን በመለወጥም ታሪክ ሠርታለች፤ ለቀጣናው ሀገራትም ኩራት ሆናለች፡፡
ባለፈው የምርት ዘመን ኢትዮጵያ 129 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ የስንዴ ምርት አምርታለች፡፡ ከዚህም 97 ሚሊዮን ኩንታል የሚሆን ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚውል ሲሆን 32 ሚሊዮን የሚጠጋው ወደ ውጭ መላክ ችላለች፡፡ ይህም ጥረቷም በምግብ እጥረት ለሚሰቃየው የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ብሎም ለአፍሪካ መድኅን መሆን እንደምትችል ያስመሰከረ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ በአፍሪካ ግንባር ቀደም ስንዴ አምራች መሆን ችላለች፡፡ በዚህም ስንዴን ለመግዛት የሚፈልጉ ሀገራት ቁጥር በመጨመር ላይ ይገኛል፡፡ ባለፈው ዓመት ብቻ ሱዳንና ኬንያን ጨምሮ ስንዴ የመግዛት ፍላጎት ያላቸው ስድስት ሀገራት ጋር የ3 ሚሊዮን ኩንታል የውል ስምምነት ተፈራርማለች። ይህ ኢትዮጵያ ከኃይል አቅርቦት ባሻገር በምግብ ሰብልም የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናን በማስተሳሰር በኩል ሚናውን በሚገባ እየተወጣች መሆኑን አመላካች ነው፡፡
ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ያላትን ሚና በአግባቡ ለመወጣትም ነፃ የንግድ ቀጣና በድሬዳዋ መሥርታለች፡፡ ይህ የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ደረቅ ወደብን ከዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት፣ ከባቡርና ከመንገድ ትራንስፖርት ጋር በማቀናጀት፣ ምርቶችን በቀላሉ ወደ ጎረቤት ሀገራት ለመላክ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎንም የአፍሪካ አሕጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣናን /AfCFTA/ በማጠናከር ረገድ የማይተካ ሚና እየተጫወተች ትገኛለች፡፡ በፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ መነሻነት የተመሠረተው አሕጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት ካሉት መርሆዎች ውስጥ “የአንድን ሀገር ምርት ከሌላው ሀገር ምርት ጋር እኩል ማስተናገድ” ፣ “የሀገር ውስጥ ምርትን ከአባል ሀገራቱ ከሚገቡ ምርቶች ጋር እኩል ማስተናገድ” የሚሉት ይገኙበታል፡፡ በዚህ መሠረትም ለሀገራችን ኢንዱስትሪዎች እና የንግድ ማኅበረሰብ አካላት ምርቶቻቸውን በሀገር ውስጥም በሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም አኩል የመወዳደር ዕድል ከመስጠቱም ባሻገር ከአፍሪካ ሀገራት ጋር በጋራ የመሥራትን ዕድል የሚፈጥር ነው፡፡
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ኅብረት 2063 አጀንዳ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ የሆነውን ቀጣናዊ ትስስርን የማጠናከር ተግባር በውጤታማነት እየተወጣች የምትገኝ ሀገር ሆናለች፡፡ በተለይም በኃይል አቅርቦት፤ በግብርና ምርት ስንዴን ከራሷ አልፎ ወደ ጎረቤት ሀገራት መላክ መቻሏ ተጠቃሽ ያደርጋታል፡፡ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ቀጣናዊ እና አሕጉራዊ ትስስርን በመፍጠር የአፍሪካ ኅብረት የቆመለትን ዓላማ ለማሳካት የበኩሏን ሚና እየተወጣች ያለች ሀገር መሆኗ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል!
አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 18 ቀን 2016 ዓ.ም